ሰብአዊ መብቶች ሰዎች ሁሉ ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ ያገኟቸው መብቶች ናቸው።የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ ያገኛቸው መሰረታዊ መብቶች አሉት።ከእነዚህ ውስጥ ለምሳሌ በህይወት የመኖር መብት፣ ማሰብና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የመዘዋወር መብት፣ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ሰብአዊ መብቶች ከሌሎች መብቶች የሚለያቸው አራት ዋና ባህሪያት አላቸው።የማይገፈፉ ወይም የማይገረሰሱ (inalienable)፣ተፈጥሮአዊ (Inherent)፣ የማይነጣጠሉ (indivisible) እንዲሁም አለም አቀፋዊነት (universality)መሆናቸውም ልዩ የሚያደርጋቸው ባህሪያት ናቸው።
ለዛሬ ርእሰ ጉዳያችን ሰብአዊ መብቶችን ከሌሎች መብቶች ከሚለያቸው ባህሪያት መካከል አንዱ የሆነው አለም አቀፋዊነት (universality) እንመልከት።ሰብአዊ መብቶች አለም አቀፋዊ ናቸው ማለት ለመላው ሰብአዊ ፍጡር መሰረታዊ ተመሳሳይ ክብርና እውቅና የሚሰጡ ናቸው ማለት ነው።
እነዚህ መብቶች ለሁሉም የዓለም ህዝቦች በሙሉ የተከበሩና እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በማንኛውም መሰረት ልዩነት ሊደረግባቸው የማይችል የሰው ልጆች በሙሉ ሰው በመሆናቸው ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ መብቶች ናቸው።ስለሆነም ሰብአዊ መብቶች በዘር፣ በቀለም፣ በሀሃይማኖት፣በፆታ፣በሀብት ደረጃ ወይም በሌላ ልዩነት ሳያደርግ መከበር አለባቸው።
የዓለም የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠበቃና አርአያ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን በግንባር ቀደምትነት የሚያስቀምጡ ምእራባውያንና አለም አቀፍ ተቃማት ይህ እሳቤና መርህ እወቁና ተግብሩ ሲሉ አጀንዳ አርቅቀው በሰነድ አስደግፈው አቅርበዋል።በየመድረኩ ይህን መርህ ሲደሰኩሩት ይሰማሉ እንጂ ተግባር ላይ ግን የሉበትም።ለዚህ ደግሞ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ በቂ ምስክር ይሰጣል።
እንደሚታወቀው፣ አሻባሪው የሕወሓት ቡድን በህዝብ የጋራ ትግል ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም የኢፌዲሬ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኢትዮጵያ ላይ በገሃድ ጦርነት አውጆ መጠነ ሰፊ ጥፋትን አድርሷል።ጦርነቱን ወደ አፋርና ወደ አማራው ክልል በመግፋት በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው በሲቪል ሰዎች ላይ በተለይም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን እንዲሁም በሲቪል ተቋማት ላይ የመለየት መርህን ባልተከተለ መልኩ ዘግናኝ ኢ ሰብአዊ ጥፋቶችን ፈፅሟል።
ወጣት፣ሴቶች፣ ህጻናትና አዛውንቶችን ጨፍጭፋል።በርካቶችን ለአካል እና ለሥነልቦና ጉዳት ዳርጓል።የቡድኑ ታጣቂዎች በሴቶች ላይ የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃት ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።ከ60 እስከ 80 አመት ያስቆጠሩ አረጋዊ ሳይቀር ደፍረዋል።በመፈራረቅ አስገድደው የደፈሯቸው ሴቶች ቁጥር ብዙ ነው።ህፃን ልጆቻቸው ፊት ለፊት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባቸው ጥቃቱ በተፈጸመበት ማግስት ታንቀው የሞቱም እንዳሉም የአካባቢው የአይን እማኞች የመሰከሩት ሃቅ ነው።
በንብረት ላይ የተፈጸመ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና ውድመት ስፍር ቁጥር የለውም።በተደራጀ መልኩ በድሃ ህዝብ መዋጮ የተሰሩ በመንግሥት አስተዳደር ተቋማት፣ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት(በተለይ የጤና ተቋማትና የትምህርት ተቋማት) ፣ በግል ንብረቶች እና በንግድ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና የንብረት ውድመት ፈፅመዋል።የእምነት ተቋማትን አቃጥለዋል።አወድመዋል።
በመግቢያችን ሰብአዊ መብቶች ከሌሎች መብቶች ከሚለያቸው አራት ዋና ባህሪያት መካከል አለም አቀፋዊነት (universality)መሆኑን አንስተናል።እነዚህ መብቶች ለሁሉም የዓለም ህዝቦች በሙሉ የተከበሩና እውቅና የተሰጣቸው፣ማንኛውም መሰረት ልዩነት ሊደረግባቸው የማይችል፣ በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በሀብት ደረጃ ወይም በሌላ ልዩነት ሳያደርግ መከበር እንዳለባቸው አንስተናል።ይህ መርህ አለም አቀፋዊ እንደመሆኑም የትም ሊተገበር የግድ ይላል።ጥሶ የተገኘ ግለሰብ፣ቡድንም ሆነ አገር ሲገኝም ተጠያቂ ይሆናል።
ይህ ከሆነም ታዲያ ከላይ የጠቀስናቸውን የሰብአዊ መብትና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሕወሓታዊያን ለተፈጸሙት ጥፋትና ጥሰት ኃላፊነት በመውሰድ፣ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ማለት ነው።
ይህ አለም አቀፍ አራተኛ መርህ ግን ሕወሓት ላይ አይሰራም።የአለም የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠበቃና አርአያ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን የሚቆጥሩት አገራትና ተቋማትም የሽብር ቡድኑ የእብደት ተግባርና ጥፋት አይታያቸውም።
ጦርነቱ መቆም አለበት በሚል በየትዊተሩ እና ዓለምአቀፍ መድረክ ላይ እርግማን የሚያዘንቡ ተቋማትና ባለስልጣናትም፣በሽብር ቡድኑ ጥፋት የሚሞተው ወገን፤የሚባክነው ሀብት፤የሚወድመውን መሰረተ ልማት መመለክት ፈፅሞ አይፈልጉም።
ቡድኑ የሚፈፅማቸውን በደሎች ሰምተው እንዳልሰማ፣አይተው እንዳለየ፣ገብቷቸው እንዳልገባቸው ሆነዋል።በተጠናና በተቀነባበረ መልኩ የሽብር ቡድኑን የጭካኔ ጥግ የሚያስመሰክሩ ጭፍጨፋዎችን ከማጋለጥ ተቆጥበዋል።ስለሕወሓት ጥፋት ሲነሳ እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች አይነቶቹ ተቋማት የበላቸው ጅብ አይጮህም።
ሌላው ቀርቶ በአለም አቀፍ ደረጃ ህፃናትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጦርነት መመልመል፣ ማስታጠቅም፣ሰላይነት መጠቀምና ተሳታፊ ማድረግ በአለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ተመላክቷል።አሸባሪው ቡድን ህፃናትን ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑ በግልፅ አደባባይ እያስተዋሉ እንኳን አይኔን ግንባር ያድርገው ከማለት ውጪ ምንም አልተነፈሱም።
ራሳቸው ካስቀመጡት መርህ በተቃርኖ በአድሎአዊነት እይታ በትግራይ ክልል በርካቶችም አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሚነግሩን ሰዎች፣ በሚያሳዝን በሚያሳፍርና በሚያስቆጣ መልኩ የሽብር ቡድኑ በአፋርና በአማራ ክልል ስለፈጸመው ኢ ሰብአዊ ድርጊትና ለረሃብ ስላጋለጣቸው ዜጎች ትንፍሽ አይሉም።አደባባይ ወጥተው መኮነን ቀርቶ በማህበራዊ ገፃቸው ላይ አንድ መስመር አያሰፍሩም።
ይልቁንም የአሸባሪው ቡድን የጭካኔ ድርጊት ከማውገዝ ይልቅም በሰብዓዊነት ስም ለአሸባሪው ቡድን መተላለፊያ ኮሪደር ስለሚከፈትበት መንገድ ብዙ ሲጨነቁና ሲደክሙ እያየናቸው ነው።ለፖለቲካ ሸሪኮቻቸው ሲሉ ኢሰብዓዊነትን እንደሚያበረታቱ እያሳዩን ይገኛሉ።
በእርግጥ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ተከስተዋል የተባሉ የሰብዓዊ ጥሰቶች መኖራቸው አይካድም።የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቋቋሙት ኮሚቴ ጥሰት ስለመፈፀም አለመፈፀሙ ምርመራ አካሂደዋል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ተከስተዋል የተባሉ የሰብዓዊ ጥሰቶችን በጥልቀት በቦታው ተገኝተው በማጥናት ሪፖርት አቅርበዋል።ምክረ ሃሳብም ሰጥቷል።የኢትዮጵያ መንግስትም ከነጉድለቱም ቢሆን ሪፖርቱን ተቀብሎ በምክረ ሃሳቡ መሰረት ችግሮችን ለይቶ ለማረም ወደተግባር ገብቷል።
ይሁን እንጂ ሪፖርቱ የአሸባሪውን ትህነግ ጩኸት ባዶ ያደረገና ለቀለብ ሰፋሪዎቹ ምቾት የሰጠ አልነበረም።ይህን ተከትሎም በጥናት ጭምብል የአሸባሪው ትህነግን ጩኸት የሚያስተጋባና የፈለጉትን ኢትዮጵያ ላይ ጫና የመፍጠር ፍላጎት ለማሳካት ‹‹ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አለብን በሚል››ሌላ መንገድ ተራምደዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽንም የተልእኮው አስፈፃሚ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በር ከመዝጋት ይልቅ ኮሚሽኑ ምርመራውን እንዲያከናውን አመቺ ከባቢን ፈጥራለች።የኮሚሽኑ ባለሙያዎች የመስክ ምልከታ እንዲያደርጉ ጭምር ሁኔታዎች አመቻችታለች።
ኮሚሽኑ ግን ይህንን ጥሪ ወደ ጎን በመተው እውነተኛ ያልሆነ ጦርነቱ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች ቁንፅል ስዕል የያዘና ገለልተኝነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባና፣ከእውነት በራቀና በተፈበረከ ውሸት የታጨቀ ብቻም ሳይሆን ሚዛናዊነት የጎደለው ሪፖርት ይዞ ብቅ ብሏል።
አድሎአዊ ባልሆነና የአለምአቀፋዊነት (universality)መርህን በጠበቀ መልኩ ሳይሆን እንደተለመደው በፍላጎታቸው በሚያደራጁት የካንጋሮ ፍርድ በመፍረድ፣የሽብር ቡድኑን ኢ ሰብአዊ ድርጊትና ሰብአዊ መብት ጥሰት ሸፈንፈን በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ በትራቸውን ማሳረፍንም ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል።
ይህ ሁሉ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እንዳትቀጥል የማድረግ ሴራ ነው። እውነት እና ንጋት እንዲሉ ሁሉም ቀኑን ጠብቆ መጋለጡ አይቀርም።በመሰል የተንሸዋረር እይታ፣ ከመርህና ያፈነገጠ ተፅእኖና በተሳከረ የካንጋሮ ፍርድ ኢትዮጵያና ዜጎቿን ማንበርከክ አንገት ማስደፋትም ፈፅሞ አይቻልም።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015