ጉዳዩ አዲስ ሳይሆን የተለመደ ነው። አንድ ነገር ሲለመድ ባህርይ ይሆናል እንደሚባለው ነውና ስራቸው የባህርይ በመሆኑ የማንም ሆድ አልተረበሸም። ይልቁንም “ትዝብት ነው ትርፉ …”ን አዜመ እንጂ፤ “ጉዴ ነው” ሲል የቆዘመ አንድም የለም።
አነሳሳችን በሰሞኑ ጉድ ላይ አንዳንድ ሃሳብ ለመለዋወጥ ነው። ይህ የሰሞኑ ጉድ ደግሞ “በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል የሚል ከሕወሓት ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት “ተጠያቂ” የሚያደርገውና የተሰራጨው “ሰነድ” ሲሆን፤ ሪፖርቱን/ ክሱን እንደ ብዙዎቹ “መሰረተ ቢስ” ብሎ ከማለፍ በዘለለ አንዳንድ ጉድፎቹን ለማሳየት ነው።
ሪፖርቱ “የተለመደ ነው” ስንል ያው ምንም አዲስ ነገር የለውም፤ ባጭሩ ”Cooked data” የሚሉት የተጋገረ መረጃ ነው። ይህ የተለመደ አውሮፓዊ ምስርት የሆኑ ተቋማት መረጃ የመጋገር አባዜ፣ ልምድ፣ አላማና ርእዮተ አለም (ካስፈለገ “ኒዎሊበራል ቶውት” በሉት) አዲስ ሳይሆን፤ አሮጌ ካቲካላ በአዲስ ጠርሙስ ነው። የስካሩ ከፍታም መነሻው ይሄው ሲሆን፤ በተለይ ጋገራው አፍሪካ ላይ ማተኮሩና ተጣብቆ፣ አልላቀቅ ብሎ ያለውም እዚሁ የፈረደባት “ማዘር አፍሪካ” ላይ መሆኑ ነው።
ማንም እንደሚያውቀው፣ ገብተው እንደ ፈለጉ የመሆንና እጅ የመጠምዘዝ አካሄድ ፍልስፍና (Neoliberalism)ን በአፍሪካ ላይ ለመጫን የማይፈልግ የለም። ይህ “አፍሪካን እንደገና ለመቀራመት” (የ1884ቱን የበርሊን ኮንፈርንስን ያስታውሷል) እየተደረጉ ካሉት “ዘመናዊ” ጥረቶች አንዱ አካል የሆነው የመረጃ ጋገራ ተግባር ሰበቡ ኢትዮጵያ ትሁን እንጂ ሾተሉ ያነጣጠረው ጠቅላላ አፍሪካ ላይ ስለመሆኑ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ከውሃ ቀጂ በፈጠነ ምልልስ አፍሪካን እያጨናነቋት የመሆናቸው ጉዳይ ነው።
ከመቆጣት፣ ማስፈራራት … አልፎ፣ ዛሬ ወደ ግልፅ የውክልና ጦርነት የገባው የ“ኒዎሊበራል ቶውት” አራማጅ ኃይል ህልሙ እየከሸፈ መሆኑ እየገባው ሲሆን፣ በካፈርኩ አይመልሰኝ አቋሙ በመፅናት፣ በኢትዮጵያ መነሻነት አፍሪካን እንደገና ሊያስገብር እየተጋጋጠ ይገኛል።
ሪፖርቱን በተመለከተ አስቀድመው (ሰሞኑን) ባለ ሪፖርቱ በሚገባው ቋንቋ እስኪበቃው የነገሩት አካላት ስላሉ ይህ ጽሑፍ አንቀፅና ገጽ እየጠቀሰ ድክመትና ሀጢያቱን አይን ከሰበከት እያገላበጠ ማሳየት ላይ አያተኩርም።
የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ትኩረት የሪፖርቱ “ስለምን?” ላይ ነውና በእሱው ላይ ሀሳብ ይሰነዝራል። ከዛ በፊት ግን፣ በጥቅሉ ማለት ነው፣ ሪፖርቱ በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ተገቢውን ናሙና ከተገቢ ቦታዎች (ምንጮች) ያላካተተ፣ የይድረስ ይድረስና ለአንድ ለታቀደ አላማ ቶሎ እንዲደርስ ታስቦ ለአየር የበቃ፣ ሲበዛ አድሏዊ፣ እጅግ ሲበዛም ወገናዊ (ወጋኝ)ነው።
አብዝቶም አለም ከሚከተለው ተገቢና ትክክለኛ የጥናትና ምርምር መርህ የተጣላነው ፤… ሲሆን፣ ባጭሩ ከዚህ በፊት አንዴ ተነክሬበታለሁና ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ድንቁርና ላይ የተመሰረተና እጅጉን ስነምግባር የጎደለው መሆኑ በተለያዩ አካላት በአንድ ድምፅ መነገሩን ጠቆም አድርጎ ማለፉ ተገቢ ነውና እናድርገው።
የወዲያ ማዶ ሰዎችን፣ የ#NoMore ንቅናቄ ወደ #NoMore_Colonialism መሸጋገሩ ጭራሽ እያሳበዳቸው እንጂ እንዲሰክኑና የእስከ ዛሬውን ስህተታቸውን ገምግመው፣ አርመው … የወደፊቱን እንዲያቃኑ ሊያደርጋቸው አልቻለም። በቱርጁማን አማካኝነት፣ በአማርኛም “አፍሪካን ዳግም ለመቀራመት አይቻልም” ቢባሉም ጆሯቸው ከመስማት ውጪ ሊያዳምጥ አልቻለም፤ ወይም፣ አልፈለገም።
ከ50 በላይ የሆኑ አፍሪካዊ ያልሆኑ ሀገራት አፍሪካን (ምንም እንኳን ኢትዮጵያን ባይመለከትም) ለዘመናት በቅኝ ገዥነት ሲመሩና ሲያስተዳድሩ የነበሩበትን ዘመን ዳግም ለማስቀጠል ከመቋመጥ የዘለለ እቅድም ሆነ ራእይ የሌላቸው በመሆኑ፤ አፍሪካ ወደ ምስራቁ ጎራ ዞር ልትል ነው፤ በመሆኑም ከመዞሯ በፊት ባለ በሌለ ኃይላችን የመዞሯን ጉዳይ ከወዲሁ ልናጨልመው ይገባል በሚል ዘመኑን ያልመጠነ አስተሳሰብ እየተመሩ፤ ያንንም ለማሳካት እያጫረሱን ይገኛሉ። እኛም ደካማ ጎናችንን መድፈን አቅቶን እየተጫረስንላቸው እንገኛለን። በመሆኑም እያደረጉት ያሉት ተግባር ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ንቀትም ጭምር ነው።
በአንድ ወር ውስጥ ከ12 ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ላይ በተሰበሰቡበት ጊዜ “ይህ አይን ያወጣ የቅኝ ገዥዎች ሴራ አንድም አፍሪካዊ ሀገር በማይገኝበት፣ በሌለበት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመነጋገር የጠሩት ልዩ ስብሰባ አለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር፣ ለአፍሪካ ሕዝብ ያላቸውን ከፍተኛና ገደብ የለሽ ንቀት የሚያሳይ፣ ዛሬም የቅኝ ገዢነት ፍላጎታቸውን ለማሳካት የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለመመዝበር፣ ለመቀራመት፣ በማያገባቸው እየገቡ ለእነሱ ተላላኪና አሽከር የሆነ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት የሚያደርጉት ሴራ ስለሆነ አፍሪካውያንም፣ መላው የአለም ሕዝብም ያወግዙታል።
“የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ G7 ሀገራት፣ የአውሮፓ ሕብረት አፍሪካን አይወክሉም። የቅኝ ገዢዎችና የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ስብስብ ነው። አፍሪካ ራሷን ከእነዚህ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ማግለል ይጠበቅባታል” ተብሎ ተጽፎ ቢነገራቸውም ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ ብለው እነሆ በአንዲት ሉአላዊት አገር ላይ በሀሰት ሪፖርት ላይ የሀሰት ሪፖርት፤ በግፍ ላይ ግፍ … እየደራረቡ ይገኛሉ።
የቀድሞው መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም “ደፍረውናል፣ ንቀውናል፣ ብታምኑም ባታምኑም …” ያሉት ነገር እየተደጋገመ በብዙዎች ሲነሳላቸው ይሰማል፤ እውነት ነው። አባባሉ ዛሬም ቦታ አለውና እኛም እንደግመዋለን።
አሜሪካ የራሷ ሀገር ሕዝብ በነጮች ዘረኝነትና በዴሞክራሲ እጦት እየተሰቃየ ለሌላው አለም ዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት፣ ፕሬስ ነጻነት እቆማለሁ … የምትለን ’ስለ እኔ ምንም አያውቁም’ ከሚል ንቀት የመጣ እንጂ ሌላ አይደለም። ካናዳ ውስጥ የተፈፀመውንና የተገኘውን የጅምላ መቃብር እንዳላየ የሚያልፍ የዩኤን ሰብአዊ መብት ዘርፍ፤ ቡድኑ ማይካድራ ላይ የሰራውን ዘግናኝ ስራ ባላየ የሚያልፍ ተቋምን … ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን የሌለ ሁሉ የሚታየው ከድፍረትና ተመፅዋችነታችን (ፊታችንን ወደ ልማት እናዙር የሚባለው ከዚህ ለመውጣት ነበር) የመጣ እንጂ ከሌላ ከምንም ሊሆን አይችልም።
አፍሪካዊ ሉአላዊነታችንን በመጋፋት “አፍሪካ ከቻይናና ሩሲያ ጋር ገጠመች” በማለት ግራ ኋላ ሊያዞሩን የሚፈልጉት አፍሪካውያን አልሰለጠኑም ከሚለው የልጅነት አስተሳሰባቸው ካለመውጣት ቢሆንም፤ እኛን የጉሎ ዘይት ለማጠጣት የታቀደ አይደለም ማለት አይቻልምና ዛሬ አፍሪካ አንድ ሆና ልትቆም የግድ ይሆናል።
በተለያዩ ምድር አንቀጥቅጥ ሰልፎች፣ እዛው አሜሪካ እና አውሮፓ ምድር ላይ “አፍሪካ የአሜሪካ ሞግዚትነት አያስፈልጋትም፤ ኢትዮጵያ ነጻና ሉአላዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን የማንንም ጣልቃ ገብነት አትቀበልም፤ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ጉዳይ የጠራው ስብሰባ ሕገወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው …” ወዘተርፈ ተብሎ ቢነገርም የሚመለከታቸው ጆሮ ሊሰማ፤ አይናቸውም ሊያይ – በአጠቃላይ አምስቱም የስሜት ህዋሳቶቻቸው በድን ከመሆን ውጪ ሊሰማቸውና ወደ መሀል ሊመጡ አልቻሉም።
ይህ ደግሞ ካፈርኩ አይመልሰኝ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም፣ የአሁኑ ሕወሓትን ሆኖ፣ ለእሱም ከእሱ ከራሱ በላይ ወግኖ …፤ ሰብአዊ መብት የሚል ታግ ለጥፎ፤ ከአቀራረብ እስከ ይዘቱ ድረስ የተጋገረን ጥናት “እነሆ ሪፖርት” ማለቱ ለማንም አይበጅምና፤ ከአፍሪካ ጋር አብሮ ለማደግና እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ሳይረፍድ ወደ መስመር መግባት ያስፈልጋል። ቻው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2015