መንግሥት የተማከለና በቴክኖሎጂ የታገዘ ብሔራዊ የመታወቂያ ስርዓት እንዲኖር እንቅስቃሴ የጀመረው ከ10 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን የጀመሩ ቢሆንም፣ ስራዎቹ በብዙ መሰናክሎች ምክንያት የሚፈለገውን ተጨባጭ ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል፡፡
በለውጡ ማግስት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን እውን የማድረጉ ኃላፊነት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሰጣቸው የሰላም ሚኒስቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፤ በትብብር ያከናወኗቸው የቅድመ-ዝግጅት እንዲሁም የቴክኒካዊና ሕጋዊ ማዕቀፎች ተግባራት የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ትግበራው መስመር እንዲይዝ ማስቻላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህ ተግባራት መካከል የብሔራዊ መታወቂያ ስርዓቱን ጽንሰ ሃሳቦችን ያብራሩና አቅጣጫ የጠቆሙ የስትራቴጂያዊና ሕጋዊ ሰነዶች ዝግጅት እንዲሁም የሙከራ ትግበራዎች ተጠቃሽ ነው፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተጠሪነቱን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያደረገው የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት፤ የ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ›› እቅድ እውን ይሆናል ተብሎ እስከታቀደበት እስከ 2018 ዓ.ም (Digital Ethiopia 2025) ድረስ 95 በመቶ ለሚሆነው የሀገሪቱ ጎልማሳ ሕዝብ የዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት እቅድ ይዞ እየሰራ ነው፡፡ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት የቅድመ ትግበራ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ ወደ ብሔራዊ ትግበራ መግባቱን ሰሞኑን ‹‹ዓለም አቀፍ የመታወቂያ ቀን›› (International Identity Day) ሲከበር ይፋ አድርጓል፡፡
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ መታወቂያ ማግኘት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች (UN Sustainable Development Goals) ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ መንግሥት አንድ የተማከለ የመታወቂያ ስርዓት ለመዘርጋት አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከ10 ዓመታት የበለጠ ጊዜ ያስቆጠረው ይህ ሃሳብ፤ ቀደም ሲል የነበረው ዕይታ ደህንነት ተኮር የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የመታወቂያ ስርዓት እሳቤውን አገልግሎት ተኮርም ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው የላቦራቶሪ ሙከራ ትግበራ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ከ2013 ጀምሮ ደግሞ ስራው በመስክ ትግበራ ደረጃ ይፋ ተደርጓል፡፡ እስከ አሁንም አንድ ሚሊዮን ሰዎች ለዲጂታል መታወቂያው ተመዝግበዋል፡፡ ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ››ን እውን ለማድረግ እስከታለመበት እስከ 2018 ዓ.ም (Digital Ethiopia 2025) ድረስ 70 ሚሊዮን ዜጎችን በዲጂታል መታወቂያ በመመዝገብ አስተማማኝ የመታወቂያ ስርዓት ለመገንባት እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡
‹‹ዲጂታል መታወቂያ ‹‹አንተ ማን ነህ/ማን ነሽ?›› የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችል ስርዓት (Proof of Identity) ነው፡፡ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚጸድቅ የሚጠበቀውና የብሔራዊ ዲጂታል የመታወቂያ ስርዓት ሕጋዊ መሰረት እንዲኖረው የሚያደርገው የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅም የተቀረፀው በዚህ እሳቤ ነው፡፡ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አስገዳጅ ያልሆነና በነፃ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ነው፡፡
ምዝገባው በአዋጁ አስገዳጅ ያልተደረገ ቢሆንም፣ አዋጁ ግን ለተቆጣጣሪ ተቋማት የማስገደድ መብት ይሰጣል፡፡ ተቋማቱ ‹‹ይህ መታወቂያ ለዚህ ዘርፍ አስገዳጅ ነው›› ብለው እንዲወስኑ የማስገደድ መብት ይሰጣቸዋል፡፡ መንግሥት (የሚመለከተው የመንግሥት አካል) መታወቂያ ለሚፈልግ ዜጋ መታወቂያ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበትም በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል፡፡ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት ፕሮጀክት በመሆኑ በማንኛውም የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሁሉም ዜጋ ለዲጂታል መታወቂያ መመዝገብ ይችላል፡፡ ምዝገባው በነፃ የሚከናወን ሲሆን ሌሎች የፕሮጀክቱ ደረጃዎችና ተግባራት ግን ክፍያ የሚጠየቅባቸው ይሆናሉ›› ይላሉ፡፡ ከምዝገባና ማረጋገጫ ማግኘት በኋላ ያለው በመታወቂያው አገልግሎት የማግኘት ተግባር (‹‹መታወቂውን ከያዝኩ በኋላ ምን አገኝበታለሁ?›› ብሎ መረዳት) እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ዮዳሄ ይናገራሉ፡፡
ዜጎች ለዲጂታል መታወቂያ ሲመዘገቡ የሚሰበሰቡት መረጃዎች ተገቢነት ከመታወቂያ ስርዓቱ አስተማማኝነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚኖራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ዜጎች ለዲጂታል መታወቂያ ሲመዘገቡ የሚሰበሰቡት መረጃዎች ጥንቃቄን በተላበሰ የዓለም አቀፍ ጥናት የታገዘ እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉ አሰራሮችን ከግምት ውስጥ ባስገባ አካሄድ የሚሰበሰቡ እንደሆኑ አቶ ዮዳሄ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ስም፣ ፆታ፣ አድራሻና የትውልድ ዘመን አስገዳጅ መረጃዎች (Mandatory Attributes) ናቸው፡፡ ይህም የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አሰራሩ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‹‹ሕጋዊ ማንነት››ን (Legal Identity) ከሚያብራራበት ትርጓሜ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ያደርገዋል›› ይላሉ፡፡
በ2015 ዓ.ም 12 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመዝገብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በራስ የቴክኖሎጂ አቅም ላይ በመመስረት የምዝገባ ስርዓቱ በመንግሥት ኔትወርክ በወረዳና በቀበሌ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ኤጀንሲ ኔትወርኮች አማካኝነት አገልግሎቱን በስፋት ለማቅረብ እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ኢትዮጵያ ከመታወቂያ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ከሚስተዋልባቸው ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነች ይጠቅሳሉ፡፡ የመታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን፣ መብትን ለመጠየቅና ግዴታን ለመወጣት የሚያስችል ግብዓት መሆኑን ጠቁመው፤ ከመታወቂያ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ዘመናዊ የመታወቂያ ስርዓትን መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚያብራሩት፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት፤ ዜጎች የመታወቅ መብት እንዲያገኙ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶቻቸውን የመጠቀም እድላቸውን እንዲያሰፉ፣ በአገልግሎት ሰጪነትና ተቀባይነት መካከል የሚኖር እምነት እንዲዳብር፣ ምጣኔ ሀብታዊ ሽግግር እንዲኖር፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ የሐብት ብክነት እንዲቀንስ፣ አካታችነት እንዲጎለብት፣ ፍትሃዊ ሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ በፖሊሲ ቀረፃና በልማት ስራዎች ትግበራ ላይ ድግግሞሽ እንዳይኖር፣ እንዲሁም ግልጽና የተሳለጠ የአገልግሎት ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል፡፡ አስተማማኝ፣ ተደራሽና የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት እና ተገማችነት ለማሳደግ፣ የነዋሪዎችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም አስተዳደራዊና የፍትህ ስርዓቱን ለማጠናከር ያግዛል፡፡
አቶ ተፈሪ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመታወቂያ ስርዓት አለመኖሩ ያስከተላቸውን ችግሮች ሲያብራሩ ‹‹በሀገራችን ዘመናዊ የመታወቂያ ስርዓት ባለመኖሩ ዜጎችን ከሌሎች ግለሰቦች በልዩ ሁኔታ ለመለየት እንዲሁም የዜጎችን ትክክለኛ የዲሞግራፊ መረጃ ለማወቅ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት አልተቻለም፡፡ ይህም በአግባቡ ሊዘጋጁና ሊተገበሩ የሚገባቸው የህዝብ ብዛትና ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም ወሳኝ የማኅበራዊ ልማት መለኪያዎች አግባብነት ያለውን አሰራር ተከትለው እንዳይሰበሰቡ፣ እንዳይጠናቀሩና እንዳይተነተኑ በማድረግ የዜጎች መረጃ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቀረጻና ትግበራ የአፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ለማድረግ እንዲሁም ግብረ መልስ ለመስጠት አስፈላጊ የመረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግልበት ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር አድርጓል›› ሲሉ ያብራራ፡፡
በሀገሪቱ በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የቀበሌ የነዋሪነት መታወቂያ ስርዓት ዜጎች ሕጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን ለማረጋገጥና የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚጠቀሙበት ስርዓት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ስርዓት ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ ዝቅተኛ የአስተዳደር መዋቅር በቀላሉ የሚያገኙት የመታወቂያ አቅም ቢሆንም በርካታ ጉድለቶች አሉበት ይላሉ፡፡ የቀበሌ መታወቂያ በታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ብቻ የሚመዘገብና ማዕከላዊ የምዝገባ ቋት የሌለው መሆኑን ጠቅሰው፣ አንድ ሰው ከተለያዩ ቦታዎች በርካታ መታወቂያዎችን እንዲያወጣ እንደሚያስችለውም ነው የተናገሩት፡፡ ጠንካራ መለያዎች የሌሉት በመሆኑም በቀላሉ ሊጭበረበር እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡ አንድ ሰው በተለያዩ ስሞችና ማንነት በርካታ መታወቂያዎችን በመያዝ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ሲሳተፍ መመልከት የተለመደ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያገለግል ወጥ፣ አስተማማኝና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለመዘርጋት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ግን እንዳልተቻለ ይጠቅሳሉ፤ ይህን ችግር ለመፍታት የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
‹‹የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ስትራቴጂው ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ነው፡፡ ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት በማድረግ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ እቅዱን ለማሳከት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክትን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስር በማደራጀትና አስፈላጊውን የሰው ኃይል ግብዓት በማሟላት ወደ ስራ የተገባ ሲሆን፣ ስራው በሕግ ማዕቀፍ የተደገፈ እንዲሆንም የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል›› በማለትም አሰራሩን ለመዘርጋት እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ይናገራሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ተግባራት መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የሚያመለክቱ ማሳያዎች እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ተፈሪ፤ ባለድርሻ አካላትም የዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን ከስራዎቻቸው ጋር እንዲያስተሳስሩና ግንዛቤ እንዲፈጥሩም አሳስበዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሰረት ከሆኑ ግብዓቶች መካከል አንዱ ነው፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አጠቃላይ የዲጂታል አሰራሩ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል ስራ ጀምሯል፡፡
የዲጂታል መታወቂያ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ለመጠበቅና አንድ ሰው አንድ ብቻ እንደሆነ ማረጋገጫ ለመስጠት፣ የአገልግሎት መተማመኛ መሰረት ለመዘርጋት፣ የዜጎችንና የአገልግሎት ሰጪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ያስችላል ያሉት አቶ ሰለሞን፣ በተጨማሪም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂው ዓላማ በመንግሥትም ይሁን በግሉ ዘርፍ የሚቀርቡ አገልግሎቶች ማጭበርበሮችንና የሳይበር ውንጀላዎችን በሚቀርፍ አግባብ ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የንግዱን ማኅበረሰብ በዘመናዊ መታወቂያ ለመለየት የሚደረጉ ጥረቶች በቂ እንዳልሆኑ የተናገሩት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝደንት ኢንጂኔር መላኩ እዘዘው፤ የዲጂታል መታወቂያ አሰራር ሲተገበር የብድር፣ የሎጂስቲክስ፣ የግብር አከፋፈል አሰራሮችንና መረጃዎችን ለንግዱ ማኅበረሰብ ቀልጣፋና ግልጽ በሆነ አሰራር ለማቅረብ እንደሚያግዝ እንዲሁም መንግሥት ለሚያዘጋጃቸው እቅዶችም ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አገልግሎቶች ግልጽና ቀልጣፋ የሚሆኑት አንድ ሰው አንድ መታወቂያ ብቻ ሲኖረው ነው፡፡ የዲጂታል መታወቂያ ይህን ለማሳካት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል›› ብለዋል፡፡
በቴክኖሎጂ የተደገፈ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት መዘርጋት ከአስር ዓመቱ ሀገራዊ የልማት እቅድ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (Strategic Pillars) መካከል አንዱ የሆነውን የቴክኖሎጂ አቅም እና ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ወሳኝ ግብዓት በመሆኑ ዲጂታል መታወቂያን ለዜጎች በማዳረስ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሀገራዊ እቅድን ማሳካት ይገባል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2015 ዓ.ም