የመንደርደሪያችን ማዋዣ፤
“ክረምት አልፎ በጋ፤ መስከረም ሲጠባ፣
አሮጌው ዓመት አልፎ፤ አዲሱ ሲተካ፣
በአበቦች መዓዛ፤ እረክቷል ልባችሁ፣
ሕዝቦች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ::”
እነዚህ ስንኞች በዜማ ተለውሰው የተንቆረቆሩት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በተወዳጁ ድምጻዊ በጥላሁን ገሠሠ አማካይነት ነበር:: ዜማና ግጥሙ ባለፉት ዘመናት ብቻም ሳይሆን ለሚቀጥሉት ረጂም ዓመታትም ሳይደበዝዙና ትርጉማቸው “ሳይወይብ” ከትውልድ ትውልድ እንደሚሸጋገሩ ተስፋ እናደርጋለን:: እንዴት ቢባል “የጥበብ ዕድሜ ከሰው ዕድሜ የላቀ ስለሆነ” – የሚለው መልስ ይሆናል::
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ሕዝበ አዳም በነቂስ ተዘጋጅቶና አደባባይ ወጥቶ፣ ቤቱን አድምቆና አስውቦ፣ወዳጅ ዘመዶቹን ሰብስቦና ጋብዞ የሚያከብራቸውንና ፌሽታ የሚያደርግባቸውን ታላላቅ በዓለት አስመልክቶ የሚወጡት የምሁራን ምርምሮችና የጥናት ውጤቶች የዘርፉን በሳሎች ብቻ ሳይሆን በርካታ የዓለማችንን ዜጎች ሳይቀር “አሃ! ይሄም አለ እንዴ?” እያሰኙ ማስገረማቸው አልቀረም::
ይህ ጸሐፊ ዋነኛው የሥልጠናው መስኩ በድንበር ዘለል ተግባቦት (Intercultural Communicatione) ላይ ስለሆነ በየጊዜው የሚወጡትን ጥናቶች የሚከታተለውና የሚማረው ልብ ተቀልብ ሆኖ ነው:: የአዳዲስ ግኝቶቹ ይዘት ወደ ኋላ ግድም ስለሚብራራ በዓላትን አስመልክቶ በአንዳንድ የሀገራችን ምሁራንና “በእናውቃለን ባይ ጥራዝ ነጠቆች” አማካይነት የሚሰጡትን አስተያየቶች “ገረፍ” አድርገን እናልፋለን::
“እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰህ/አደረሰሽ!” ሲባሉ “ዓመቱን ማን አዲስ አደረገው? ምንም አዲስ ነገር የለውም:: ወራቱ ዞረው የሚመጡት ያው የትናንቶቹ መስከረም፣ ጥቅምት፣ ህዳር ናቸው:: ቀናቱም ከሰኞና ከማክሰኞ ዘወትራዊ ዕለታት የተለዩ አይደሉም:: የዓመቱ ክፍለ ወራት መፀው፣ ፀደይ፣ በጋና ክረምቱም እነዚያው የምናውቃቸው ናቸው:: ከሰማይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም::” እያሉ በጎልዳፋ አመለካከት፤ “እንቃሪ አስተያየት” የሚሰጡ በርካታ ሰዎች ሳያጋጥሙን አልቀሩም::
አንዳንዶች “በቡሃ ላይ ቆረቆርን” እየተረቱ “እንኳንስ በዓላትን ለማክበር ቀርቶ ድህነታችን ራሱ እያናወዘ መኖር አስጠልቶናል ወዘተ.” በማለት ከመደበኛ ሥራ የመገለሉን ምክንያትና ለበዓል የሚወጣውን ወጭ እያሰሉ አጥብቀው ሲያማርሩና ሲተቹ መስማት አንግዳችን አይደለም:: ምክንያቶቻቸው ሁለቱ ብቻ ሳይሆኑ በርከት ሊሉ እንደሚችሉ እንገምታለን:: እውነት ሀሰቱን ለጊዜው ትተን፤ እነርሱ ሰበብ እየደረደሩ ከበዓላት አከባበር ጋር ጠብ የፈጠሩ ይምሰሉ እንጂ የትኞቹም የዓለማችን ሕዝቦችና ሀገራት “የእኔ ብቻ” የሚሉትና ከሌሎች የሰው ዘሮች ጋር የሚጋሯቸው በርካታ በዓላት እንዳሉ ይታወቃል::
ለአጠቃላይ ግንዛቤ እንዲረዳን በዓላትን በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አቧድኖ መመልከት ይቻላል:: በመጀመሪያው ክፍል የሚመደቡት ሃይማኖታዊ (መንፈሳዊ) እና ባህላዊ የምንላቸው በዓላት ናቸው:: በዚህ ዘርፍ የተለዩት በዓላት አንድም የዓለም ሕዝቦች የጋራ “ይሁንታ” የሰጧቸውና መሠረታቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ናቸው:: ለምሳሌ፡- በክርስትና እምነት በምዕመናን ዘንድ ከፍ ባለ መንፈሳዊ ክብር (Reverence) የሚከበሩትን የመስቀል፣ የልደተ ክርስቶስ፣ የስቅለትና የትንሣኤ በዓላትን ይመለከታል:: በእስልምና እምነትም የነብዩ መሐመድ ልደትን (መውሊድ)፣ ኢድ አል ፈጥር (ኢድ)፣ ኢድ አል አድሃ (አረፋ)ን የመሳሰሉትን ማስታወስ ይቻላል:: ከአይሁድ እምነት በዓላት መካከልም የፋሲካን፣ የበዓለ ሃምሳንና የዳስ በዓላት በመባል የሚታወቁትን ለማሳያነት መጥቀስ ይቻላል::
ከባህላዊ እምነቶች መካከልም በዚህ ሰሞን ጎላና ደመቅ ብለው በየብሔረሰቡ እየተከበሩ ያሉትን የዘመን መለወጫና በተለያዩ መንፈሳዊ ምክያቶች ሳቢያ በታላቅ ድምቀትና ፌሽታ የሚዘከሩትን በዓላት ማስታወስ ይቻላል:: የጋሞዎቹ “ዮ! ማስቃላ”፣ የወላይታ ብሔረሰብ “ግፋታ”፣ የሲዳማው “ፍቼ ጨምበላላ”፣ የኦሮሞ ብሔረሰብን የ“ኢሬቻ” በዓላትን በምሳሌነት መጠቆም ይቻላል::
በሁለተኛው ክፍል የሚመደቡት በዓላት የሃይማኖት፣ የብሔርም ሆነ የቋንቋ ገደብ ሳይጫናቸው በመንግሥታዊ ወይንም በፖለቲካዊ ውሳኔ “የእኛ የጋራ በዓል” ተብለው በመሰየም “በብዙኃን ዜጎች ዘንድ በዓለም አቀፍ ወይንም በሀገር ደረጃ የሚከበሩ” የአንድን ሕዝብ ወይንም ቡድን ገናናነትና አሸናፊነትን የሚዘክሩ በዓላት ናቸው:: ለምሳሌ ዓለም አቀፍ የላባደሮች ቀን፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ወዘተ. እና በየሀገሩ የሚከበሩት ከቅኝ ገዢዎች ነፃ የወጡባቸው ቀናትና የድል በዓላት ለምሳሌነት ቅርብ ሊሆኑ ይችላሉ::
በእኛ ሀገርም በካሌንደር ተዘግተው መድፍ እየተተኮሰላቸው የሚከበሩትን እንደ የአድዋና የሚያዝያ 27 ቀን የድል በዓላት፣ ወይንም በሀዘንና በትካዜ የሚከበረውን የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀንንና ከካሌንደርም ሆነ ከሕዝብ አእምሮ ጭርሱኑ ተፍቆ ሊጠፋ አንድ ኀሙስ የቀረውን አስቀያሚውን የግንቦት ሃያ በዓላት ማስታወስ ለግልጽነት ያግዛል:: ቅድመ ደርግ ዓመታት በታላቅ ክብርና ሞገስ ይከበሩ የነበሩትን የንጉሡን የልደትና የንግሥና ዕለት መታሰቢያ በዓላትንም ወደ ኋላኛው ዘመን አፈግፍጎ ማስታወስ ይቻላል::
የበዓላቱ “የምሥጢር ፍቺ”፤
ቀደም ሲል በሁለት ቡድን ከፍለን በዝርዝር የተመለከትናቸው በዓለት ሲከበሩ በአክባሪዎቹ ሕዝቦች ወይንም በተወሰነው የማሕበረሰብ ክፍልና ቡድኖች የሚፈጠረውን ስሜትና ተጽእኖ በተመለከተ በየጥናቶቹ ተብራርቶ የተገለጸውን እውነታ እንደሚከተለው አሳጥረን እንገልጻለን::
ሃይማኖታዊ ወይንም “መንፈሳዊ” በዓላትን የሚያከብሩ ሕዝቦችና የማሕበረሰብ ክፍሎች በዓላቱን ለማክበር በዋዜማው ቀናትና በበዓላቱ ዕለታት የሚያደርጉትን ዝግጅትና ሽር ጉድ ወይንም ፌሽታውን የሚያደምቁትና የሚንበሸበሹት በተፍታታ ስሜት፣ ተስፋ በሰነቀ እምነትና በተረጋጋ ቀልብ ሰክው ነው::
ወቅታዊው የድህነታቸው፣ የችግራቸው፣ የእጦታቸውም ሆነ የሀዘናቸው ጉዳት እጅግም እንዳዘቦቱ ቀናት ተጫጭኖ አይደብታቸውም:: እነዚህ በዓላት ሲከበሩ ልግስና፣ አብሮነት፣ መረዳዳትና መደጋገፍ ጎልተው ይስተዋላሉ:: አብሮ መብላቱና መጠጣቱ፣ የወትሮ ዓይነት ስሜት ሳይሆን የሚፈጥረው ሰንባች ትዝታን ነው::
ሕዝብን እዬዬ የሚያሰኘው የኑሮና የኢኮኖሚ ጣጣ፣ ፖለቲካው የሚረጨው ፕሮፓጋንዳና ጫና፣ በሀገር ላይ የደረሱ ለየት ያሉ ወቅት ወለድ ችግሮችና መከራዎች ለጊዜውም ቢሆን በበዓላቱ አከባበር ወቅት ስለሚደበዝዙ በሕዝቡና በማኅበረሰቡ የሚስተዋለው እፎይታ፣ የተረጋጋና የሰከነ ስሜት ነው::
ስለዚህም ይላሉ አጥኚዎቹ፡- ሁካታና ግርግር፣ ጦርና የጦር ወሬ፣ ድህነትና የተፈጥሮ አደጋ ወዘተ. እየናጣት አሳር በልታ አሳሯን ባሸከመችን ዓለማችን ላይ እንደነዚህ ዓይነት ሃይማኖታዊና “መንፈሳዊ” ዓላማና ተልእኮ ያላቸው በዓላት መከበራቸው ፋይዳቸው ከፍ ያለ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊነት ክብርም ደመቅ ብሎ የሚገለጽበትና መንፈሳዊ ስክነትና መነቃቃት የሚስተዋልበት ጭምር ነው:: እነዚህን በዓላት ማክበሩ ሊበረታታ እንጂ “ለቁሳዊ ጉዳዮች ብቻ ትኩረት ሰጥቶና የኢኮኖሚ ‹ብክነትን› እንደ ምክንያት እያጎሉ የበዓላቱ አከባበር እንዳይኮነን ምሁራኑ ማጠቃለያቸው ላይ አስፍረዋል::
በአንጻሩም፡- በመንግሥታዊ ትዕዛዝና አዋጅም ይሁን በፖለቲካ ትግል አሸናፊነት ወይንም የድል አድራጊነትንና የአሸናፊነትን ታሪኮች ለመዘከርና ለማስታወስ ታስበው የሚከበሩት ሕዝባዊ በዓላት ልክ እንደ ሃይማኖታዊያኑና ባህላዊ በዓላት ስሜትን ከማረጋጋት ይልቅ ቂምን፣ ያለፈ በደልን፣ መጠቃትን፣ በግፍ መወረርንና መደፈርን አጉልተው ስለሚዘክሩ አከባበራቸው የቀዘቀዘ፣ ስሜትን ከማስከን ጋር ያላቸው ቁርኝትም እጅግም ስለሆነ የሚወደስና የሚናፈቅ አይደለም::
በጥናቶቹ እንደተረጋገጠው ለምሳሌ፡- የዓለም አቀፍ የላብ አደሮች (ሜዴይ)፣ ወይንም የሴቶች በዓል (ማርች ስምንት) የመሳሰሉት በዓላት ሲዘከሩ አክባሪው ማኅበረሰብ ቁጣውን፣ መጠቃቱን ወይንም ግፉን የሚገልጽበት ስሜት እየተብከነከነና በሞቅታ ስሜት እንጂ እንደ ሃይማኖታዊና “መንፈሳዊ” በዓላት ተረጋግቶና ሰክኖ የሚያከብራቸው አይደሉም::
እኛም ብንሆን የድል በዓላቶቻችንን ስናከብር ወራሪዎቹን እየኮነንና ያደረሱብንን የግፍ ወረራ እያስታወስን ስሜታችንን በማስቆጣት እንጂ በተረጋጋና በሰከነ ስሜት እንዳልሆነ የምንረዳው ይመስለናል:: በጥሩ ማሳያነቱ የሚገለጸው ቀደም ሲል የጠቀስነው አይረቤው የግንቦት 20 “በዓል” ነው:: ይህ ዕለት የሚከበረው ጥቂት የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ቄጤማ ጎዝጉዘውና “ዋንጫ ኖር!” እያሉ በፈንጠዝያ ያከብሩት ካልሆነ በስተቀር ብዙ ዜጎች ዕለቱን የሚያስታውሱት ሀዘናቸውን እየገለጹ፣ መከራቸውን እየዘከሩና የሥርዓቱን ጨቋኝነት አፍ ለአፍ እየተቀባበሉና በተጎዳ ስሜት እየተከዙ ጭምር ነው::
በተለይም ለእንደኛ ዓይነቱ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን “ለአፍ ማበሻ ዳቦ ሳይቀር ብርቅ ለሆነብን” ኢኮኖሚው ለሚያንገላታን ዜጎች፣ በፖለቲካው ምክንያት ናላችን እየዞረ መረጋጋት ለራቀንና የጦርነት ዜና ጆሯችንን ጭው አድርጎ ድብርት ውስጥ ለከተተን ሕዝቦች ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላቶቻችን ስሜታችንን ለጊዜውም ቢሆን ለመፈወስ ትልቅ አቅም እንዳላቸው የምንረዳ ይመስለናል::
ማሕበራዊ ሕይወታችንን ለማነቃቃትና ጫናው በጠነከረበት መንፈሳችን ላይም ሰላምን ለማርበብ ድርሻቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ስለዚህም እነዚህን መሰል በዓላቶቻችንን እየተጋገዝን፣ እየተረዳዳንና እየተደጋገፍን ማክበሩ መልካም ነው:: ይሄም ሲባል ግን በትንሽ በትልቁ፣ በውስን ቡድኖችና አካባቢዎች የበዓላት ቁጥርን በሰበብ አስባቡ እያበራከቱ ከእርሻ፣ ከምርት ተግባራትና ከተግባር ውሎ መዘናጋቱ ይወገዝ ካልሆነ በስተቀር ሊበረታታ አይገባም::
በተመቻቸ ኑሮና ሕይወት ወይንም እጅግም ችግር ባልተጫነው ሁኔታ ውስጥ በመሆን በዓላትን በፌሽታና በደስታ ለማክበር ዕድልና ጊዜ ፊቷን ያላጠቆረችብን ዜጎች ለሌሎች ወገኖቻችን የደስታ ምንጭ መሆንን ፈጣሪም ሆነ ሰብዓዊነታችን ግድ ይለናል:: በተለይም እኩይ የሚለው ቃል ከሚገልጣቸው በላይ “ልጆቻችን” በሚሏቸው ወበከንቱዎች መከራ የወደቀባቸውን የትግራይ ወገኖቻችንን፣ ጦርነቱ የሚያመረቅዝ ደዌ የሆነባቸውን የአፋርና የአማራና አካባቢ ሕዝቦችን፣ የውዶቻቸው ነፍስ በወራሪዎች የተነጠቁ መከረኞችን፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው “በደም ሱሰኞች” የተፈናቀሉትንና የሀዘን ወስከንባይ የተደፋባቸውን ዜጎቻችንን ቅድሚያ ሰጥተን ልናስባቸው ውዴታችን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው::
ቤት ንብረታቸው ወድሞ አውላላ ሜዳ ላይ የወደቁትንና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ላብና ደማቸውን እየገበሩልን ላሉት ጀግኖቻችንና ቤተሰቦቻቸው የደስታና የመጽናናት ምክንያት ሆነን ከስሜት እረፍታችን፣ ከገበታችን ማእድ ልናጋራቸውና ለተወሰኑ ጊዜያችም ሆነ በዘላቂነት ካሉበት ስሜት ወጥተው “እፎይ” እንዲሉ ልናግዛቸውና አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል:: ሰላም ይሁን
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2015 ዓ.ም