በየጦር ግንባሮች ሽንፈት ሲደርስበት ሰላም ፈላጊ መስሎ ሕዝቡን ለማታለል ብቅ ብሎ ይዘላብዳል፡፡ እየጠየቅኩ ያለሁት ‹‹ሰላም ብቻ ነው¡›› እያለ ይለፍፋል፡፡ በዚህ መሀል ሌላ የጦርነት ዕቅድ ለማዘናጋት ይሞክራል። ደግሞ ባዘጋጀው ስልት በተቃራኒው ጊዜ ገዝቶ በድጋሚ ወደ ጦርነት ይገባል፡፡
ሰላም ወዳድ አስመሳዩ፤ ነገር ግን የጦርነት ሱሰኛው አሸባሪው ትህነግ የትግራይ ህዝብ እልቂት አያሳስበውም። ያሸነፈ ሲመስለው ‹‹የሰላም አማራጭ ከመጀመሪያውም የማይሆንና የትግራይን ሕዝብ ጥያቄ ፈፅሞ የማይፈታ መሆኑ የታመነበት ነው ›› እያለ በአደባባይ ይናገራል፡፡ በአንድ እራስ ሁለት ምላስ የሽብር ቡድኑ መለያ ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ መያዣ መጨበጫ የሌለው ሙልጭልጭ ነው፡፡
የሽብር ቡድኑን አምኖ ለመወያየትም ሆነ ለመደራደር ዕቅድ ማዘጋጀት እና ቀጠሮ መያዝ አዳጋች ነው፡፡ ዛሬ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾ፤ ሳይውል ሳያድር ያለውን እንደገና ይክዳል፡፡ የሚገባው ቃል ሁሉ በቅጥፈት የታጀበ ነው። ቡድኑ በቅርቡ የጦርነት ማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድ ብሎ በነደፈው እና ሾልኮ የወጣው ሰነድ ፤ ‹‹በጦርነት ሂደት ውስጥ የመረጃ ልዕልና ለማግኘት እና በርካታ ሃይሎችን ከጎን ለማሰለፍ ከሚያስችሉ ሁኔታዎች አንዱ፤ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለ አስመስሎ ራስን ማቅረብ ነው›› ይላል።
ይህ በግልፅ እንደሚያሳየው የሽብር ቡድኑ የሰላም ፍላጎቱን እንደሌለው፤ ስለሰላም የሚያወራቸው ወሬዎች ሁል ከልብ ያልሆኑ ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ማዘናጊያ እንደሆኑ ነው፡፡
‹‹ሰላም እፈልጋለሁ›› የሚለው ደጋፊ ለማግኘት እንጂ የቡድኑ የሁልጊዜም ምርጫው ጦርነት መሆኑ ለማንም የተደበቀ አይደለም ማወቅ ለሚፈልግም ብዙ ሳይደክም የተወሰነ ያለፈ ታሪኩን ማየት ብቻ በቂ ነው። በቀደመው ዘመን፤ ወደ ስልጣን ከመጣና ከስልጣን ከተወገደ በኋላ የለኮሳቸው ጦርነቶችን ማየት በራሱ ስለቡድኑ ጦረኝነት የሚለው ብዙ አለ ፡፡
ቡድኑ የጦርነት ማጠቃለያ ምዕራፍ በሚል ባሰናዳው ሰነድ በግልፅ እንደተብራራው፤ ‹‹በአማራ ክልል በተወሰነ መልኩም ቢሆን ፊቱን ወደ ልማት ያዞረ ገበሬ እየታየ ነው። ይህ ወደ ልማት ፊቱን ያዞረ ሃይል የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድበት ሲገባ የተፈጠረውን ጊዜያዊ ክፍተት (ሰላም) በመጠቀም ፊቱን ወደ እርሻው መልሷል፤ ይህ ሃይል የእርሻ ውጤቱን ወደ ቤቱ እንዲያስገባ ልንፈቅድለት አይገባም ›› ሲል የትግራይ ወጣት የአማራ ክልል ገበሬን ለመውጋት እንዲነሳ እየገፋፋ እና እያበረታታ በህዝቦች መካከል ግጭቶችን መፍጠር እንደ አንድ ስትራቴጂ የሚጠቀምበት መሆኑን አሳውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም “ኢትዮጵያውያን ለጦርነት ባልተዘጋ ጁበትና መንግስት በሰላም ጥሪ በተዘናጋበት ጊዜ አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ሲል በዋናነት ምርጫው ሰላም ሳይሆን ጦርነት ብቻ መሆኑን በሰነዱ ላይ አሳይቷል፡፡
የሽብር ቡድኑ ‹‹የእርሻ ዘርፉ እንዲደናቀፍ በየአካባቢው ግጭት በመቀስቀስ እና ግጭት ለመቀስቀስ የሚያስችሉ ሃይሎችን በማገዝ እረፍት በመንሳት፣ መንግስት የልማት ስራዎችን ትቶ እሳት ማጥፋት ላይ እንዲጠመድ ማድረግ አለብን ›› በማለት አገርን ለማዳከም ሕዝቡ የሚበላውን ለማሳጣት ልማትን ማደናቀፍ እና ለውጭ ጠላቶች መሳሪያ መሆን እንደዋነኛ ውጊያ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለው በግልፅ አሳይቷል፡፡
የሽብር ቡድኑ ጦርነቱን በመሳሪያ በዓውደ ውጊያ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መዋጋት ሥራው እንደሚሆንም አስቀምጧል፡፡ ጠላት ይቀባል ጥላሸት እንደሚባለው አገሩን የሚጠብቀውን፤ በተለያዩ አገራት ሰላም ለማስከበር ወጥቶ በድል የሚመለሰውን፤ የአገር ኩራት የሆነውን መከላከያን፤ እንዲሁም አገር በተሻለ መንገድ እንድትሔድ እየሠራ ያለውን መንግስት የሁለቱንም ስም በተለያዩ መንገዶች ማጥፋት የየዕለት ተግባሩ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ እርሱ እንዳረጋገጠው ይህ ተግባሩም አንዱ የጦርነት ሱሱን የማስታገሻ መንገዱ ነው።
‹‹መንግስት እና መከላከያ የትግራይን ሕዝብ ሊፈጁ አቅደዋል፡፡ መከላከያ ከጎረቤት ክልሎች ጋር ሆኖ የትግራይን መሬት በሃይል እየወረረ ነው፡፡ መከላከያ ሰብል እያቃጠለ፣ ንብረት እየዘረፈ፣ ሴቶችን እየደፈረ ነው፡›› ከሚለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ጀምሮ የተለያዩ ወሬዎችን በመንዛት በተግባር በውሸት መንግስት እና አገርን በመውጋት የሽብር ቡድኑ የጦርነት ሱሱን በማስታገስ ላይ ይገኛል።
ቡድኑ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በተለያዩ አካባቢዎች ምክንያት የሌለው ግጭቶች በመፍጠር በአገሪቱ በዘላቂነት ሰላም እንዳይሰፍን የማድረግ ሥራን በመስራት በኩልም ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡ አገሪቱን ወደ የማያቋርጥ ጦርነትና መከራ ለማስገባት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች አድርጓል።
በአደባባይ ጦርነት ከማወጅ በተጨማሪ ባይሳካለትም ተልዕኮውን ያነገቡ ሰዎችን በማሰማራት አገሪቱ በጦርነት እንድትታመስ ብዙ ሰርቷል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ሸኔ ጋር በመሆን በኦሮሚያ የጥፋት ተልዕኮ ለመፈፀም ሲሰራ መቆየቱን በመረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በስትራቴጂው ላይ ይህንን
እየሠራ ስለመሆኑም በዝርዝር አብራርቷል፡፡
በተጨማሪ ጦርነቱን ሲያካሂድ የኢትዮጵያን ዕድገት ከማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች እና ከአጎራባች ሃገሮች ጋር በሚስጢር ግንኙነት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶችም የሽብር ቡድኑን ሰራዊት ከማሰልጠን በተጨማሪ በአገሪቱ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለመፍጠር መሞከራቸው አልቀረም፡፡
የሽብር ቡድኑ በዚህ በኩልም አገሪቱን ወደማያባራ ጦርነት ብቻ ሳይሆን፤ መቋጫ ወደሌለው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ሊያስገቡ የሚያስችሉ ስራዎች በመስራት በተለያዩ መንገዶች አገሪቱን የከፋ ችግር ውስጥ ለመክተት እየታተረ መሆኑን በሾለከው ሰነድ ታይቷል።
ይህ ሁሉ ሲታይ ቡድኑ የተገነባበት ማንነት ሙሉ ለሙሉ በግጭት /በጦርነት/ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለማወቅ አያዳግትም፡፡ በተጨማሪ ጦርነት በዘላቂነት እንደ ዋነኛ ሱስ የተጠናወተው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ከመነሻ እስከ ዛሬ ጊዜውን በጦርነት ለማሳለፍ ቆርጦ የተነሳው ይህ ቡድን የአንድ መንግስት ጠላት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ጠላት ሆኖ ለመቀጠል የወደደ መሆኑን እያንዳንዱ ዜጋ ማወቅ አለበት፡፡
ምንም እንኳን አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች በቅጡ ባይገባቸውም፤ የሽብር ቡድኑ በዋናነት የትግራይ ሕዝብ ጠላት መሆኑን በተደጋጋሚ ለዓለም አሳይቷል። ያለውን የማታለል ስልት ሁሉ በመጠቀም በክልሉ ሕዝባዊ ተቀባይነቱን ለማስቀጠል ቢሞክርም ሕዝቡን ከመጥቀም ይልቅ አሁንም ድረስ እየሠራ ያለው ሕዝቡን መሳሪያ አድርጎ እየተዋጋበት ነው፡፡ ህዝቡን እንደሰው ሳይሆን እንደመገልገያ ዕቃ እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡
‹‹የትግራይ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ መወሰን የሚያስችለውን መብት ለማግኘት ረጅምና መራራ ትግል የሚጠይቀው መሆኑን ባለፉት አመታት በተካሄደ ትግል ተምሯል ›› የሚለው የሻለከው ሰነዱ፣ ይህ ቡድን በምንም መልኩ ፍላጎቱ ዕድሜ ልኩን የትግራይ ህዝብን መጠቀሚያ በማድረግ የማያባራ ጦርነትን ማስጀመር ብቻ ሳይሆን ማስቀጠልንም ታሳቢ ያደረገ ነው።
የዚህ ቡድን አገርን ወደማያባራ ጦርነት የመክተት ቅዠቱ ፍፁም እውን ሊሆን አይገባም፡፡ እርሱ የሚሠራውን ሴራ ለማክሸፍ ከዚህ በላይ እንዳያደክም እና ሌላ ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍል የጦርነት ሱሱን እንዲያቆም በዋናነት የትግራይ ሕዝብ ለቡድኑ እምቢተኝነቱን በመግለጽ እራሱን ነጻ የማውጣት ትግል መጀመር ይኖርበታል፡፡
የትግራይ ህዝብ ነቅቶ የጦርነት ሱስ የተጠናወተውንና መቼም የማይለቀውን ይሄንን ቡድን ‹‹አንቅሮ ሊተፋው እና መጠቀሚያ አታደርገኝም፡›› ሊለው ይገባል፡፡ ይህንን ለማለት ሽርፍራፊ ደቂቃዎችን ማባከን አይጠበቅበትም። ለሁሉም ጊዜው አሁን ነው!።
ፌኔት ከብርጭቆ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2015 ዓም