ሉዓላዊነቷንና ነጻነቷን ጠብቃ ሳታስደፍር የኖረች ጥንታዊት ኢትዮጵያ ፤ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ፤ እስከ አፍንጫው የታጠቀን ቅኝ ገዢን ከአንድም ሁለት ጊዜ ድል ያደረገች። በጸረ ቅኝ ግዛት ትግሉ ቀንዲል የሆነች። የፓን አፍሪካኒዝምና የብላክ ኮንሽየስ ዋልታና ማገር፤ የራሷ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያላት፤ የሚሉ እውነቶች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በተነሱ ቁጥር አብረው የሚወሱ ቢሆንም ድህነቷ፣ ኋላቀርነቷና በምግብ እህል ራሷን አለመቻሏና ተመጽዋችነቷ ጋርዶባት፤ ጥላውንና አዚሙን ጥሎባት፤ አንጸባራቂ ገጽታዋን አጠልሽቶባት ይገኛል። ድርቅና ረሀብ በተነሳ ቁጥር ስሟ አብሮ ይነሳል።
በመዝገበ ቃላት ላይም ሆነ በሌላ መጽሐፍ ላይ የረሀብ ምሳሌ ሆና ስትጠቅስ ማንበብ ምን ያህል ቅስም ሰባሪና አንገት አስደፊ እንደሆነ ለኢትዮጵያውያን መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው። ተረጅነትና ተመጽዋችነት አገር ፊት ላይ ያለ አሸማቃቂ ለምጽ ነው። አይደብቁት አይሸግጉት ነገር ፊት ላይ ያለ የአገር ለምጽ ነው። ቢያንስ ላለፉት 50 አመታት ይህ ማንነቷ ኢትዮጵያንም ሆነ ዜጎቿን በሄዱበት እንደ ጥላ ሲከተል ኖሯል። ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና ለመንግስታቸው ምስጋና ይግባውና በዓለም አደባባይ በኩራት ደረታችንን ነፍተን፣ አንገታችንን ቀና አድርገን እንዳንራመድ ቀይዶ ይዞን የነበረው የተመጽዋችነት ሰንሰለት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመበጣጠስ ከጫፍ ደርሰናል።
ባለፉት ጥቂት አመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ፣ የኩታ ገጠም ግብርና፣ የበጋ ስንዴ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፤ የሜካናይዜሽን ግብርና፤ የህዳሴው 3ኛ የውሃ ሙሊትና 2ኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመር፣ ወዘተረፈ. የአገራችንን ተስፋ ከወዲሁ እያለመለመ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የዱግዳና ቦራ ወረዳዎችን የስንዴ ኩታ ገጠም እርሻን በጎበኙበት ወቅት፤ በያዝነው አዲሱ ዓመት ስንዴን ለውጭ አገር ገበያ ለማቅረብ የተያዘው ግብ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ትልቅ አገራዊ ብስራት ነው።
እንደ አለመታደል ሚዲያዎቻችን በነጠላ ዜና አለፉት እንጂ በሰበር ሊዘገብ፤ አንድምታውና ትርጉሙ በስፋት ሊተነተንና ሊበየን ይገባ ነበር። ለዛውም አገር በታሪካዊ ጠላቶቻችንና እንደ ሽብርተኛው ሕወሓት ባሉ ከሀዲና ባንዳዎች እንደ ሌጦ በየቅጣቸው በተወጠረችበት የተበሰረ ብስራት መሆኑ ደግሞ ልዩ ትኩረትንና ዕይታን ይሻ ነበር። ሆኖም ዛሬም አልረፈደምና ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን ሊያገኝና እንደ አገር ሊከበር/ሴሌብሬት/ሊደረግ ይገባል።
ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ስመለስ፤ ኢትዮጵያውያን በዚህ ልክ መስራታችን ብሔራዊ ክብራችን እና የአገር ሉዓላዊነታችንን ከማስከበር ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን፤ የመንግስትም ዋነኛ ትኩረት ከዚህ በፊት የነበረውን ረሀብ የተፈጥሮ ሀብታችንና ያለንን ጉልበት በአግባቡ በመጠቀም ስንዴን ከአገር ቤት ፍጆታ አልፈን ወደ ውጭ ወደ መላክ መቀየር እንደሆነ፤ መሰደድን በአገር ወደ መስራት መቀየር፤ የመሬት መራቆትን ወደማልበስ ለማሸጋገር የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የምስራች ብለዋል። ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ 600ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 26 ሚሊዮን ኩንታል መመረቱን፤ በአጠቃላይ የበልግን ሳይጨምር በክረምትና በበጋ 90 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገልጿል።
ይህ ታሪካዊ እመርታ የአገራችንን ገጽታ፣ ግብርናዊ ስሪትና የስነ ልቡና ውቅር የሚቀይር ወሳኝ መታጠፊያ/ክሪቲካል ጃንክቸር/ ነው። ለሌሎችም ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና መስፈንጠሪያ ሆኖ ስለሚያገለግል በቀላሉ የሚታይ ስኬት አይደለም። በአጠቃላይ አገራችን ግብርናና አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሰጠችው ትኩረት፤ በአለማችን ላይ ከተከሰተው የአየር ጠባይ ለውጥ፤ የዓለም ሕዝብ ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ በመምጣቱ የግብርና ምርት ውጤቶች በእጅጉ እየተፈለጉ ባለበት ወቅት ጋር መገጣጠሙ ዓለም አቀፍ አንድምታ እንዲኖረው አድርጓል።
ያለንበት ዘመንም ሆነ መጪው ጊዜ ለግብርና ምቹ ነው። ለዚህ የሚበጅ የግብርና መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ፤ ይሄን የሚመጥን የግብይት ስርዓት፣ ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነት በንግዱ ዘርፍ ተግባራዊ ካልተደረገ ምርትና ምርታማነት የቱንም ያህል ቢጨምር ገበያውን ማረጋጋትና ሸማቹንም አምራቹንም ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ አበክሮ ጎን ለጎን ሊሰራ ይገባል።
በተደጋጋሚ እንደምለው መጪው ዘመን ለግብርና ኢኮኖሚው ብሩህ እንደሆን እየተለፈፈ ይገኛል። አፍሪካም ሆነች አገራችን የሰፋፊ የእርሻ መሬቶች፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰፊ ገበያ፣ በመልማት ያለ የሰው ኃይል፣ …፤ እምቅ አቅም potential ያላቸው መሆናቸው አይን ማረፊያ አድርጓቸዋል። እ.አ.አ በ2050 የዓለም ሕዝብ ቁጥር 10 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ተተንብዮአል። የቻይናና የሕንድ ኢኮኖሚ እድገትን ተከትሎ የመሸመት አቅም መጎልበት ጋር ተያይዞ የሚያሻቅበው የምግብ ሸቀጦችን ፍላጎትን ለማርካት፤ በአመት ከ100 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚያገላብጠው ግብርና የዓለም ኢኮኖሚ መሪነትን በቅርብ ከኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ይረከባል ተብሎ ስለሚጠበቅ፤ ትኩረቱ ባልታረሰው የአፍሪካ ድንግል መሬት ላይ መሆኑ ዘመኑን ይዋጃል። አገራችን ለግብርናውና ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠችው ትኩረት ትክክለኛና ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ነው።
የዓለም ሕዝብ ቁጥር እድገት አሁን ከሚገኝበት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን፤ በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ 11 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ መተንበዩ፤ በዓለም በተለይ በቻይና፣ በሕንድና በሌሎች ታዳጊ አገራት እየተመዘገበ ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር የምግብ ፍላጎት እጅግ ጨምሯል። እድገቱን ተከትሎ የመግዛት አቅም ከፍ በማለቱ እና የመጣው የአመጋገብ ለውጥ ፍላጎቱን አንሮታል። ባለፉት 20 እና 30 አመታት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያን፣ ሕንዳውያን፣ ብራዚላውያን ፣ ኢንዶኔዣውያን፣ ማሌዣውያን፣ ወዘተረፈ ከድህነት ወደ መካከለኛ ገቢ ማደጋቸው በግብርና ውጤቶች ፍላጎት ላይ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል።
በተቃራኒው የሚታረስ መሬትና የውሃ እጥረት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በአናቱ ተጨምሮ ከአመት አመት ፍላጎቱን ማሟላት አዳጋች እያደረገው መጥቷል። የዓለም ሙቀት መጨመርና የደኖች መጨፍጨፍ፤ የአፈር መሸርሸርንና የመሬት መራቆት፣ በረሃማነት፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት፣ ጎርፍ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚውን እያሽመደመደው ነው። በዚህ የተነሳ ፍላጎቱንና አቅርቦቱን ማጣጣም ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጋች እየሆነ መጥቷል። እንደ ኮቪድ 19 ያለ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ደግሞ ችግሩ ክፉኛ ይባባሳል።
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ቀደም ባለ ጊዜ ይፋ እንዳደረገው ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ 265 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ የምግብ እህል እጥረት ተዳርጓል። ከባድ ውሽንፍር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ድርቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ዓይነት የተፈጥሮ አደጋዎች በተከሰቱ ቁጥር የምግብ እህል እጥረት ከፍ ሲልም ረሀብ ይከሰታል። በመላው ዓለም አንድ ቢሊዮን ሕዝብ በምግብ እጥረት ሳቢያ ለተለያዩ የጤና እክሎች ተዳርጓል። ወደ አገራችን ስንመጣ 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የከፋ የምግብ እጥረት እንዳለበት መረጃዎች ያትታሉ። ከወረርሽኙና ከድርቅ ጋር ተያይዞ ባለፈው ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ወገናችን ለምግብ እህል እጥረት መጋለጡን መንግሥት ይፋ አድርጓል። ግብርና ለአገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ ቢሆንም እድገቱ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም።
አገራችን የወጣት፣ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በገጠር የሚኖር፣ አመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች፣ የሁለት ጊዜ የዝናብ ወቅት፣ የሚታረስ ሰፊ መሬት፣ ታታሪ ሕዝብ ያላት እና ቀደምት ከስድስት ሺህ አመታት የሚሻገር የእርሻና የግብርና ታሪክ ያላት ምድር ብትሆንም ራሷን እንኳ በቅጡ መመገብ አልቻለችም። በስንዴውና በዘይቱ ሲገርመን ሽንኩርትና ምስር ከውጭ እያስገባን ነው። በእኛው አባይ የለማ የግብጽ ብርቱካን በአለፍ ገደም ብቅ እያለ ነው። ካለፉት ሦስት አመታት ወዲህ ግን ከዚህ አዙሪት ለመውጣት በመንግሥት በኩል ፍላጎትና ቁርጠኝነትን እየተመለከትን ነው። ዛሬም ተረጂ፣ ዛሬም ስንዴና ዘይት ከውጭ አስመጪ መሆናችን ቁጭት የፈጠረ ለለውጥ ያነሳሳ ይመስላል።
ቀድሞውኑም በኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና በጥናት ባልተመሠረተ አግባብ ግብርናው የሚገባውን ያህል ድጋፍ ሳያገኝ ከፈረሱ ጋሪው እንዲሉ በግዕብታዊና በፖለቲካዊ ውሳኔ የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ፓርክ መዓት አግተልትለን ለምሩቃኑ ሥራ ለፋብሪካው ጥሬ ዕቃ ማቅረብ አልቻልንም። ለዚች አገር ነፍስ መዝሪያዋም መሞቻዋም ግብርና ነው። ግብርና ላይ ከተሳካልን ሌሎችን ዘርፎች ይዞ መውጣት ይቻላል። ለቀደሙት 27 አመታት ከፕሮፓጋንዳ ባለፍ የአገራችንን ስነ ምህዳር ታሳቢ ያላደረገ የዘመቻ ሥራ መሠራቱ ዛሬ ላይ ጥሎናል። ቆም ብለን ትንፋሽ ስበን የመጣንበትን መንገድ ገምግመን በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሚስተዋለውን መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር ቀርፈን ትኩረታችን ግብርናው ላይ ሊሆን ይገባል።
ይህ እስኪሆን የለውጥ ኃይሉ እጁን አጣጥፎ አለመቀመጡና የህልውናችን መሠረት የሆነውን አየር ንብረታችን እንዲያገግም በአምስት አመታት ውስጥ ወደ 25 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ግብ ጥሎ ካለፉት አራት አመታት ጀምሮ ወደ ተግባር መገባቱ የኑሮአችንና የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ለሆነው ግብርና መልካም ዜና ነው። በሚቀጥሉት አምስትና አስር አመታትም የአገራችንን አየር ንብረትና ሥነ ምህዳር / ኢኮሎጂ / ፍጹም ይቀይረዋል። ይህ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መስፈንጠሪያ ነው። ይህ በሒደት እውን እስኪሆን የለውጥ ኃይሉ ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ለማስቀረት፣ ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግ፣ መሬት ጦም እንዳያድር፣ የኩታ ገጠም አሠራርን ለማስፋፋት የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ወጥ በሆነና ስፋት ባለው አግባብ እንደየሥነ ምህዳሩ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ግን ይበልጥ ሊሠራ ይገባል።
እንደ አገር ያለን ሀብት የሚታረስ መሬት፣ ውሃና የሰው ኃይል ነውና ለግብርናው ቅድሚያ ሰጥተን ልንረባረብ ይገባል። ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ሽግግር ያለ ግብርናው ጽኑ መሠረት እውን ሊሆን አይችልምና። ስለሆነም ያለንን ሀብት ሁሉ አቀናጅተን ግብርናው ላይ ልንረባረብ ይገባል። የአረንጓዴ አብዮት በማቀጣጠል አንገታችንን ሲያስደፋን ሲያሸማቅቀን ከኖረው ረሀብ፣ ቸነፈርና ድህነት ይህን ተከትሎ ከማይለየን ተረጂነት መላቀቅ አለብን። ከ600ሺህ ሔክታር መሬት በላይ መሬት ላይ የበጋ ስንዴ ማምረት መቻሉ ዘርፉ ከድህነትና ከተረጂነት ማምለጫችን መሆኑን ያረጋግጣል።
አብዮትም ብርቃችን አይደለም። አንድ ሁለት ጊዜ አብዮት ሁሉን ነገራችን ነቅሎ መቀመቅ አውርዶናልና። ለዚህ ነው ቃሉን ስንሰማ እንደ ኮሶ መድኃኒት የሚያንገሸግሸን። አረንጓዴ አብዮት ግን ረሀብን፣ ችጋርን፣ ቸነፈርን፣ ተመፅዋችነትን ከስሩ መንግሎ የሚጥል ዶዘር ነው። ከቀደሙት ሁለት የደም፣ የጥፋት ወይም የቀይ አብዮቶች አንዱ አረንጓዴ አብዮት ቢሆን ኑሮ የአገራችን መለያ ከሆነው ረሀብ እስከ ወዲያኛው በተለያየን። ዛሬ ለምንገኝበት የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ባልተዳረግን። አሁንም በሕዝብና በአገር ኢኮኖሚ እንዲሁም ገፅታ ላይ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣውን የአረንጓዴ አብዮት ለማካሄድ አልረፈደም። እንግዲህ የ«አረንጓዴው አብዮት» ስርወ – ሀረግ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት / ዩኤስኤአይዲ/ አስተዳዳሪ የነበሩት ዊሊያም ጋውድ እኤአ በ1968 የአብዮቱን አረንጓዴ ችቦ በለኮሱበት ሥነ ሥርዓት፤ «… ይህ አዲስ አብዮት ነው። የሶቪየት ሕብረቱ ቀይ አብዮት አልያም የኢራን የሻህ ነጭ አብዮት አይደለም። አረንጓዴ አብዮት ብየዋለሁ። …»
የአረንጓዴ አብዮት የ2ኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የተከሰተውን የምግብ እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓት እጥረት ለማሟላት በ1950ዎቹና 60ዎቹ ተለኩሶ የተቀጣጠለ አብዮት ነው። ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያን፣ ጸረ ተባይ ኬሚካልን፣ አስተማማኝ የውሃ አቅርቦትን በማረጋገጥ በተለይ የስንዴንና የሩዝ ሰብልን ምርትን በእጅጉ ማሳደግ ያስቻለ አረንጓዴ አብዮት ነው። አረንጓዴ አብዮት በብራዚል፣ በሕንድ፣ በፊሊፒንስ፣ ወዘተረፈ ፈንድቶ ጎተራውን ሙሉ አድርጎታል። እኛም የአገራችንን ሥነ ምህዳርና ብዝሀ ሕይወት ከግምት ያስገባ አረንጓዴ አብዮት ያስፈልገናል። ረሀብን፣ ቸነፈርንና ችጋርን በቃ ! ልንለው ይገባል። ሁላችንም ከፖለቲካ ተንታኝነትና ከሴራ ፖለቲካ አራጋቢነት ወጥተን፤ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተን ፤ አረንጓዴ አብዮትን እንቀላቀል። እናቀጣጥል። ግብርናውን እናግዝ፤ በጓሮአችን አትክልት እናልማ፤ የተከልናቸውን ችግኞች እንንከባከብ። ችግኝ እንትከል። የተገኘውን ውጤት ወደኋላ እንዳይመልሰውና የኑሮ ውድነቱን እንዳያባብሰው፤ እየተስተዋለ ያለው የማዳበሪያ ዕጥረትና አልቀመስ ያለው ዋጋ አፋጣኝ ምላሽ ይጠይቃል ።
አገራችን ኢትዮጵያ ከተረጅነትና ከተመጽዋችነት ተላቃ በምግብ እህል ራሷን ችላ ስንዴ ለውጭ ገበያ ታቀርባለች !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2015 ዓ.ም