የኢትዮጵያ ጀግንነት ከጥንታውያኑ የግሪክ አፈታሪኮች እስከ ዓድዋው ዘመን የአውሮፓ ጋዜጦች የደረሰ እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል። ከዚያም አልፎ በተፈጥሮ ይረጋገጣል። የዘመን አቆጣጠራችንና የአዲስ ዘመን አቀባበላችን ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፣ አሮጌ ምዕራፍ ተዘግቶ አዲሱ ሲገለጥ ሁሉም ሰው መጪውን ዘመን የሚያይበት አዲስ ዓይን ይታደለዋል። እንዴት ከተባለ በተፈጥሮ ላይ ተመርኩዞ የሚያየው፤ የሚመኘውና የሚያቅደው ነገር ይሰጠዋል።
ገበሬው ክረምት ላይ አርሶና ቆፍሮ ያፈራውን ከጎተራው ይከታል። ግን መጀመሪያ ያለውን አሟጦ በእምነት ይዘራል፤ የመስከረምን ልምላሜ በተስፋው መነፅር እያየ ያነጋል። ከዚያም እምነትና ተስፋው እንዲሁም ልፋቱ ተባብረው ንጋቱ ላይ ያደርሱታል። ይህም ወደጎተራው የሚከተው ፍሬው ነው። ከዚህ አኳያ እንደ አገር የምናያቸው ብዙ ጭለማ ነገሮች በተስፋና በምንመርጠው ሕሊናዊ ምልከታችን የሚወሰኑ እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልገናል።
ምርጡን ነገር ከእነ ሥራው ይዘን ከዘለቅን ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም ይነጋል። ነገር ግን ያሳለፍነውን ዓመት የምንቆዝምበት ብቻ ካደረግነው ሁሉም ጭለማ ይሆናል። ስለሆነም ተስፋችንን ከመልካምነታችን ጋር ማስተሳሰር የሁልጊዜ ልምዳችን ማድረግ ይኖርብናል። ምክንያቱም ተስፋ ዛሬ ላይ በርትተን እንድንሰራ የሚያደርገን ነው። ተስፋ የመልካም ፍጻሜውን መድረሻ የምናይበት ነው። ተስፋ መልካም ነገሮችን በደስታ የምንጠቀምበት ነው። ተስፋ በአጠቃላይ እንደ አዲስ ዓመት ሁሉ አዲስ የሚያደርገን ነው። አሮጌነታችን ይብቃ የምንልበትና ልምላሜና ድልን የምናስብበትም ነው።
ስላለፈው ዓመት ስናስብ መልካምና እኩይ አጋጣሚዎችን እናስታውሳለን። እንደ አገር ብናነሳ ጠላቶች ተደራጅተው ጥቃታቸውን ያጠነከሩበት ጊዜ ነበር። የማናውቀውን የሞት አይነት የሰማንበት፤ የንጹሐን ደም የዘነበት፣ አልፎ ተርፎ መቼም ደፍሮን የማያውቀው አልሸባብ ጭምር ሊወጋን የቋመጠበትና ጥፋት ያደረሰበት፣ የውጪው ጫና አፉን የበረታበት ወቅት ነበር። ኢትዮጵያን ለመጣል በየመድረኮችና ሚዲያዎች ጭምር የተዶለተበትም ጊዜ ነበር። ለዚህም አንድ ማሳያ ላንሳ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ያደረገውን።
በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ሰሞኑን እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ስብሰባ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የመጥራት ህጋዊ ስልጣን የለውም። አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር የውስጥ ጉዳይ ነው። አገራት ደግሞ ውስጥ ጉዳዮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት ሉኣላዊነት አላቸው። ሆኖም ጉዳዩ ዓለም አቀፍ የጸጥታና ደኅንነት ስጋት እንዲመስል እየተደረገ ነው። የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ደግሞ ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ ስብሰባ እየጠራ ነው።
የኢትዮጵያን ጉዳይ ዓለም አቀፍ የጸጥታና ደኅንነት ስጋት ይሆናል በሚል አንዳንድ አገራት ጉዳዩን ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር በማየት የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድንን ጉዳይ ይዘው ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ ሥራቸው አድርገውታል ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ሳይጨምር በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ብቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምክር ቤቱ ለ12ኛ ጊዜ ስብሰባ መጥራቱን አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ በሰሜኑ አገራችን ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ ሁለት ጊዜም መግለጫ ሰጥቷል። በአንድ አፍሪካዊ አገር ውስጥ ችግር አለ ተብሎ ከታሰበ ጉዳዩ መታየት ያለበት በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንጂ በዓለም አቀፉ የጸጥታው ምክርቤት እንዳልሆነም አስገንዝበዋል።
ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ለመንግሥታቱ ድርጅት የላካቸው ደብዳቤዎችን በተመለከተ፣ የሽብር ቡድኑ ከመርህ ባፈነገጠ መልኩ ለስድስተኛ ጊዜ ለድርጅቱ ደብዳቤ መላኩን የተናገሩት ቋሚ መልዕክተኛው፤ ደብዳቤዎቹ እርስ በእርስ የሚጣረሱና የሃሳብ ጽኑነት የሌላቸው መሆናቸውንም አስረድተዋልም። ሆኖም ኢትዮጵያውያን ለማንም የማይበገሩና እውነት ይዘው የሚሟገቱ በመሆኑ ሁልጊዜም አሸናፊዎች ናቸው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ አገራችን ለማንም የማትበገር መሆኗን ነው። የተሸነፈችበት መድረክም ሆነ ጦርነት እንዳልነበረ የሚያረጋግጥ ነው።
ኢትዮጵያ በተስፋዋ ጀግንነቷን ታሳያለች፤ በተስፋዋ የማትረታና የማትንበረከክ መሆኗን ታረጋግጣለች። በተስፋዋ ጨለማውን ትገፋለች። በተስፋዋ ትወድቃለች ያሏትን ከፍ ብላ ታሳያለችም። አሁንም ወደ ማሳያው ልግባ በአሸባሪው ሕወሓትና በመንግስት መካከል የነበረውን ፍልሚያ በማሳየት። ሁልጊዜ ጭለማ አመለካከት ያለው ሕወሓት ማንም አያደራድረኝም፤ ማንም ሊያሸንፈኝ አይችልም፤ ማንም ጦር ከመስበቅ ሊያቆመኝ አይችልም፤ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ስላለሁ ማንም አይገዳደረኝም ሲል ነበር። ይህ እብሪተኝነቱ አልፎ ተርፎ ጦርነት አስነስቶ ሕዝቡን ሁሉ ሲማግድ ቆይቷል፤ አሁንም እየማገደ ነው። ከሰሞኑ ግን ሽንፈቱን በራሱ አንደበት ማወጅ ጀምሯል።
ራሱ ሳያቆም ጦርነቱ ይቁም ስብከቱንም ጀምሯል። የአፍሪካ ሕብረት ገለልተኛ አይደለም ሲልና ሲወነጅል ቆይቶ አሁን ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ማለት ጀምሯል። ይህ ደግሞ የመሸነፍ ምልክት፤ የተስፋ መቁረጥ ማሳያ እንደሆነ ነጋሪ አያሻውም።
በድርጊቱ ከእርሱ ጎን የሚሰለፍ ማንም እንደሌለ የተረዳ ይመስላል። አይዞህ የሚሉትም የውጪ ጠላቶች በዲፕሎማሲው ስለተበለጡ ሳይክዱት የቀሩ አይመስልም። ስለዚህም እጅ ወደመስጠቱ እንደገባ ያሳየናል። በእርግጥ ሰላምን የሚጠላ አለ ለማት ያስቸግራል። ግን ሕወሓት መቼም ቢሆን ይህንን ጠላትነቱን ይተዋል የሚል እምነት የለም። አሁን ግን ወዶ ሳይሆን ተገዶ ሰላም ወደማለቱ ገብቷል። ይህ ደግሞ የሚያሳየው እንደ አገር ተደራጅተው የዘመቱብንን ተደራጅተን የመከትንበት፤ አሁንም እየመከትን ያሳፈርንበት መሆኑን ነው።
የማዕቀብ ውርጅብኞች ሲያደርጉብንም ችለን በማበብ አሳይተናቸዋል። ወደፊት ደግሞ በሕብረታችን እንደ አዝመራው ውጥናችንን ለፍሬ እናበቃለን። ይህ ግን በተስፋ ብቻ የሚሆን አይደለም። ከዘመኑ መለወጥ ጋር ራሳችንን መለወጥን ይጠይቀናል። እንደ አዲሱ ተስፋችን እኛም አዲስ መሆን ይጠበቅብናል። አሮጌውን አስተሳሰባችንን ሳናወልቀው አሮጌው ዓመት ሄዶ ሌላኛው አዲስ ዓመት ሊመጣ አይችልምና ህልማችን እንዲሳካ ከዘመኑ ጋር የተወዳጀ ሥራ መስራትም ይኖርብናል።
ዓመቱን ለማደስ የጊዜን ዋጋ መረዳትና መጠቀምም የግድ ነው። ዓመት ሁልጊዜ በቀናት፣ በሳምንታትና በወራት ተለክቶ የሚያልፍ ነው። ተጠቀምንበትም አልተጠቀምንበትምም ሂደቱን አያስተጓጉልም። ሕይወታችንን በተጠቀምነው ልክ ያስኬደዋል እንጂ። ስለሆነም ጊዜው ሳይቆጥረን ጊዜውን ቆጥረን መጠቀም ይኖርብናል። በማይቀየረው ጊዜ ውስጥ አትራፊ ሆነን ማለፍ አለብን። የማይቀበር ታሪክ መሥራትም ያስፈልገናል። ያን ጊዜ ቀዳሚ ብቻ ሳይሆን አስቀዳሚም እንሆናለን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት፤ ‹‹ በጊዜ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች አዲስ ዐሻራ በየዘመኑ ያሳርፋሉ። ታሪክን ይቀይራሉ፤ አዲስና መልካም አስተሳሰብን ለሌላ ያጋባሉ፤ የአኗኗር ዘይቤን ጭምር ይቀይሩታል። በዚህም ምክንያት ትናንትን ከትናንት ወዲያ፣ ዛሬን ከትናንት፣ ነገን ከዛሬ ይለዩታል። አዲስ ነገር በማድረግ፣ ዘመኑ ብቻ ሳይሆን ቀኑም አዲስ እንዲሆን ያደርጉታል›› ነው። እናም አሁንም በጊዜ አገራችን ብዙ ነገር ትፈልጋለችና ያንን ልንሰጣት ይገባል።
ምን ትፈልጋለች ካላችሁ አሁንም የጠቅላይ ምኒስትሩን ሀሳብ ላንሳ ‹‹ አገራችን ጊዜን የሚያሸንፉ ሕያዋን ዜጎች ትፈልጋለች። ዘመኑ እንደ ቁጥሩ አዲስ እንዲሆንላት አዲስ ሥራ በአዲሱ ዘመን የሚሠሩ ዜጎች ትፈልጋለች። ነባር ችግሮቿን በአዳዲስ መፍትሔዎች የሚተኩ፤ ነባር ፈተናዎቿን በአዳዲስ መድኃኒቶች የሚፈውሱ፤ ነባር ዕንቅፋቶቿን አንሥተው አዳዲስ መንገዶች የሚገነቡ፤ የተለመዱ የታሪክ አንጓዎቿን በአዳዲስ የታሪክ ምዕራፎች የሚቀይሩ፤ የርሃብ ታሪኳን በብልጽግና፤ የጦርነት ታሪኳን በዘላቂ ሰላም፤ የመከፋፈል ታሪኳን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት፤ የግጭት ታሪኳን በወንድምና እኅታማችነት፤ የኋላቀርነት ታሪኳን በዘመናዊነት፤ የሚቀይሩ ሕያዋን ጀግኖች ትፈልጋለች። አዲሱ ዓመት በርግጥም አዲስ እንዲሆንላት አዲስ ታሪክ የሚጽፉላትን ትፈልጋለች።›› ይህ የአዲስ ዓመት መልእክታቸው ያለምክንያት የተነገረ አይደለም። አዲስ ዓመት እነዚህን ተስፋዎች ይዞ ሌላ አዲስ ዓመት ስለሚያመጣልን ነው። በዚህ ጎዳና ስንጓዝ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ስኬት ይመጣል። በውጤታማነት እንበሸበሻለን። የእጃችን መዳፍ ብልጽግናን፣ እድገትን ይጨብጣል። ያን ጊዜ የፈለግነው ብቻ ሳይሆን የሚፈልጉንንም እናበዛለን። መጠላላታችን ያከትምለታል።
ዘመንን የመቀየር ተግባር ፍላጎትን ብቻ ሳይሆን ውጤቶችን ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሰሪ፣ ተመራማሪ፣ ቆራጥና አገር ወዳድ መሆን ግዴታ ነው። በተለይም ከዘረኝነት የወጣ አስተሳሰብን ማጉላት ከምንም በላይ ያስፈልጉናል። እርስ በእርሳችን ተበላልተን መቼም ዘመንን መቀየር አንችልም። አገራችንንም ልናሳድጋት አይቻለንም። ስለሆነም ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር፣ ግጭቶችን በማስወገድ እርስ በእርሳችን ይቅር በመባባል፤ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ያለንን የተፈጥሮ ጸጋ በሚገባ በጋራ በመጠቀም ተስፋችንን ማለምለም አለብን። ለዚህ ደግሞ እከሌ ሳይሆን እኛ በማለት እንትጋ። ሰላም!!
ክብረ ነገስት
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2015 ዓ.ም