የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፤ በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የፌደራል መንግስት አስፈጻሚ አካል ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያከናውናል።
የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ግብዓት፣ ምርትና አገልግሎት ብቃትን፣ ጥራት፣ ፍቱንነት፣ ጤንነት እና ደህንነት በማረጋገጥ የመንግስትን በጀትና ሌሎች ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ጊዜና ወጪ የሚቆጥቡና በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ የአካባቢ ደህንነትን ያገናዘበ፣ የዘመነ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ተገልጋዮችን ጭምር በሬጉላቶሪ አገልግሎት ማሳተፍ የሚችል የግብርና ሬጉላቶሪ የአሠራር ስርዓት በመገንባትና የግብርና ምርቶች የጥራት ጉድለት የሚያስከትሏቸው የጤና ችግሮች በማስወገድ አገራዊ ምርት ተጠቃሚነትን በማሻሻል፣ ለውጭ ንግድ የሚቀርበው፣ የግብርና ምርትና ግብዓት ጥራትና ደህንነት ሊረጋገጥ በሚችል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ግልጽና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ የገበያ መዳረሻን ማስፋትና የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅምን ማሳደግ የተቋሙ ዋነኛ ተልዕኮዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፤ በዛሬው ‹‹የተጠየቅ››አምድ ዕትማችን ባለስልጣኑ ከተቋቋመበት ዓላማና ግብ አንጻር ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ነወይ ስንል ቃለመጠይቅ አድርገንላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋነኛ ተግባራት ምን ምን ናቸው?
አምባሳደር ድሪባ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አዲስ ተቋም ነው፤ ዕድሜ በወራት የሚቆጠር ነው። ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተደራጀ ሲሆን ተልዕኮውን በስፋት ለማከናወን እየተጋ ነው። ተልዕኮው በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ የሚመረቱ ጥሬ የግብርና ምርቶችን ጥራት፤ ደህንነት እንዲሁም የምርቶችን ጤንነት ማረጋገጥ ነው። ምርቶችንም ብቻ ሳይሆን ግብዓቶችን፣ አገልግሎቶችን፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው መስፈርትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የገባንባቸው ሥምምነቶች አሉ። በተለይም አሁን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምናደርገው ጥረት ምርቶቻችን የዓለም ገበያ የሚፈልገው ጥራት፣ ደህንነትና ጤንነት ያሟሉ፣ በአገር ውስጥ ደግሞ የዜጎችን ደህንነትና ጤንነት፣ ዜጎች ገንዘብ ለሚከፍሉለት ምርት ጥራት ያለው ምርት መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ እንሰራለን። ይህን ለመሥራት አምራች ተቋሞችን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞችን፣ የግብዓት፤ የምርት፣ የቴክኖሎጂ፣ አገልግሎትም ተቋሞች በሙሉ ብቃት እናረጋግጣለን። የሰው ኃይላቸው፣ አሰራራቸው፣ የምርት ሂደታቸው ጥራትን የሚያረጋግጥ መሆኑን እናያለን። ምርቶችን ከበሽታ የሚጠብቅ ስለመሆኑም በማረጋገጥ ለተቋሞቹ ሰርተፍኬት እንሰጣለን።
በሌላ በኩል ወደ ዓለም ገበያ የሚላኩ ምርቶች የዓለም አቀፍ ገበያ የሚፈልገውን የጤንነት ደረጃ መያዛቸውን ለምሳሌ የእንስሳት ምርት ከሆነ የሳልሞኔላ፣ አንትራክስና ከመሳሰሉት ነፃ መሆናቸውን እናረጋግጣለን። እንደ ሰሊጥ፣ ቡና የመሳሰሉት ምርቶችን ደግሞ ሳይቶ ሰኒተሪ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የጤና፣ የዕፅዋት ምርት ጥበቃ ተቋም ከሚጠይቀውና ዓለም አቀፍ ደረጃ ከገባንባቸው ሥምምነቶች አንፃር መስፈርቱን ያሟሉ ናቸው ወይ የሚለውን እናረጋግጣለን።
ተቋሙ እየተጠናከረ ሲሄድ በተለይም የአገሮችን የምርት ጥራት ደረጃ እናመጣለን። የአውሮፓ ህብረትን፣ የቻይናን አብዛኛው ምርቶቻችን የሚወስዱ አገራት የሚጠይቁትንና የሚፈልጉትን የጥራት ደረጃ በማምጣት አርሶ አደሮቻችን በጥራት ደረጃ እንዲያመርቱ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንሰጣለን፤ ክትትል እናደርጋለን፣ ብቃታቸውን በየጊዜው እየተከታተልን እንቆጣጠራለን። በዋናነት እነዚህን ሥራዎች ለመስራት የተቋቋመ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቡና እና ሰሊጥ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚወስኑ እየሆኑ መጥተዋል። የእነዚህ የጥራት መገለጫ ምን ይመስላል?
አምባሳደር ድሪባ፡- ባለስልጣኑ ሁሉንም የግብርና ጥሬ ምርቶችን ማለትም የቅባት እህሎችን፣ የሆርቲካልቸር ምርቶችን፣ ፍራፍሬዎችን በሙሉ ከበሽታ ነፃ መሆናቸውንና ጥራታቸውን ይቆጣጠራል። ከዚህ አኳያ ስናይ አምራች ተቋሞች ምን ላይ ናቸው የሚለውን ማየት ነው። ቀድሞ የተወሰነ ልምድ አለ። የተበታተነ ቢሆንም በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ሲሠራ ቆይቷል፤ ዲፓርትመንቶች አሉ። ተቋሞቻችን ስናይ በከፊል አቅም አላቸው፤ በከፊል ደግሞ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ።
አንዱ ይህን የሚወስነው የሰው ኃይል ብቁ መሆን ነው። የምርት ሂደቶቹ ጥራትን የሚያረጋግጡ ሆነው መደራጀት አለባቸው። ሌላው ጥራት ያላቸው ግብዓቶች ናቸው። በየደረጃው ክፍተቶች ቢኖሩም በተለይም ወደ ውጭ ምርት የሚልኩ ፣ የቅባት እህሎችን፣ ቄራዎች ሆርቲካልቸርና ጥራጥሬዎች የሚልኩት በከፊል ጥሩ ቢሆኑም የምንፈልገው ጥራት ደረጃ ለመድረስ መስተካከል ያለበት ነገርም አለ። ተከታታይ ስልጠና አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ በማስቀመጥ ወደዚህ ማምጣት ይቻላል።
የዓለም የንግድ ድርጅት የሚጠይቃቸው መስፈርቶች አሉ። ያንን ሳናሟላ ተወዳዳሪ ሆነን መሸጥ አንችልም። እኛም የገበያ መዳረሻዎች ምን ያያሉ የሚለውን እንገመግማለን፤ አማራቾች ላይ ያለውን ክፍተትም እንገመግማለን፤ እናስተካክላለን። ቀደም ሲል ምርቶች ሲላኩ ስለነበር ክፍተቶችን ለይተን መፍትሄ ላይ እንሰራለን። የምርት ጥራት አሰገዳጅ ሁኔታዎችን በተመለከተ ደንብ አለን፤ ረቂቅ ደንቦችም እየተዘጋጁ ነው፤ ምክረ ሐሳብም እንሰጣለን። ደንብ ማስፈጸሚያ መመሪያዎችም እየወጡ ነው። የአምራቾችና አርሶ አደሮች፤ ኤክስቴንሽን አሰራራችንም፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና አጠቃቀምን እንገመግማለን አመቺ ሥርዓቶችንም እንተገብራለን። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የምትጠቀምባቸውን ህጋዊ አሰራሮችን ተግባራዊ እናደርጋለን። በፊት የነበሩ አዋጆች ላይ የኬሚካል እና የዘር ጥራትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አቅሞችን የበለጠ ለመገንባት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን ፣ ጥራትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ላብራቶሪ በበቂ ሁኔታ አለ?
አምባሳደር ድሪባ፣ የዘር ጥራት ለመቆጣጠር ላብራቶሪ አለን። ኬሚካል ላይ ላብራቶሪ የለንም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገቡ ኬሚካሎች ጥራት ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ያለው የቁጥጥር ሥርዓት በጣም የድሮ ነው። ነገር ግን አሁን ኬሚካልን የሚቆጣጠር ላብራቶሪ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ጠንከር አድርገን ቁጥጥር እናደርጋለን። በተጨማሪም የእንስሳት ምርትና የእንስሳት ግብዓት ቁጥጥር ላብራቶሪ አለን፤ ይሄ እየተደራጀ ነው። ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹አክሪዴትድ›› አይደለም። ስለዚህ የዘሩን ላብራቶሪ ጨምሮ አክሬዴትድ ለማስደረግ አማካሪ ቀጥረን እየሰራን ነው። ስለዚሀ በአንድ በኩል መሰረተ ልማት ማደራጀትና የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት በሌላ በኩል ደግሞ አምራቾችንም ማገዝ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኬሚካሎች፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶች በተመለከተ ክፍተት ስለመኖሩ በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ሲገልጹ ይሰማል፤ ይሄ እውነት ነው?
አምባሳደር ድሪባ፡- ትክክል ነው ክፍተቶች አሉ። ነገር ግን የክፍተቶቹ ደረጃ ምን ያክል ነው የሚለው በመረጃ ለማስደገፍ ያስቸግራል። መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የነበረው ለምርት ነበር። ቁጥጥር ላይ ሲደረግ የነበረው ደካማ ነው። በአደጉት አገራትም ሆነ በአንዳንድ አፍሪካ አገራት ያለው ሁኔታ ሲታይ ትኩረታቸው ጥራት ቁጥጥር ላይ ያተኩራል። ማምረቱን አርሶ አደር ወይንም ባለሃብቱ ያመርተዋል። ስለዚህ እኛም አምራች መተካት ሳይሆን ጥራትና ጤንነት ላይ ማተኮር አለብን። በተለይ ኬሚካል ላይ የጥራት ቁጥጥር ክፍተት አለ። በሌላ በኩል ለአብነት የአፈር ማዳበሪያን 99 ከመቶ የሚያስመጣው መንግስት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ድርጅቶች ነው የሚገዛው። ለዚህም ቁጥጥር ይደረጋል። ነገር ግን በሁሉም ዘርፍ ቁጥጥሩ ያልተደራጀና በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ በመሆኑ የሚፈለገው ብቃት ያለው ውጤት አልመጣም። ሆኖም ይህ ተቋም ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ክልሎችም የየራሳቸው ድርሻ ስለሚወስዱ ትልቅ ውጤት ይመጣል። ላብራቶሪና የቁጥጥር መሰረተ ልማቶችንም እንገነባለን።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 45 የቁጥጥር ጣቢያዎችን በማደራጀት ላይ ነን። ሁለት ላብራቶሪዎች አሉን። ላብራቶሪዎቹ ቄራዎች እና ዘር ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። እነዚህ የሥጋ ምርቶችና የሥጋ ተረፈ ምርቶችን ጥራትና ከበሽታ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህ በድምሩ በምናይበት ጊዜ የቁጥጥር ጥረቶች አሉ፤ ግን በቂ ትኩረት አልተሰጠም ነበር። ትኩረቱ ምርት ማሳደግ ላይ ነበር። በቀጣይ ግን መንግስት ቁጥጥሩ ላይ እየተጠናከረ ይሄዳል።
አዲስ ዘመን፡- ሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርቶች አኳያ ሲታይ በእንስሳት ኢትዮጵያ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ብትሆንም በተጠቃሚነት ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ የምትገኘው ለምንድን ነው?
አምባሳደር ድሪባ፡- ትክክል ነው። ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካም ትልቅ ሃብት አላት። ከዓለምም ከቀዳሚዎቹ 10 ውስጥ ናት። ግን ካለን ሃብት መጠቀም አልቻልንም። ችግሮቹ በጣም ‹‹ስትራክቸራል›› ናቸው። አንደኛው ከእንስሳት እርባታ የሚነሳ ሲሆን፤ የእርባታ ሥርዓታችን ምን ያክል ስጋ እና ወተት የሚያስገኙ እንስሳትን ይዘናል የሚለው ጥያቄ ይቀድማል። ሁለተኛው ግብይቱ እና ሎጂስቲክሱ ላይ ያነጣጥራል። የግብይት ስርዓቱና ሎጂስቲክሱ የተሳለጠና የተሳሰረ አይደለም። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የቁጥጥር ሥርዓቱን ይመለከታል። የቁጥጥር ሥርዓቱ አሁን የተሻለ ነገር ያለው ቄራ ላይ ነው። ዘንድሮ ቄራ 120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል። ይህ በቄራ ኤክስፖርት ታሪክ የመጀመሪያው ነው። ይህም የተገኘው በቁጥጥር ሥርዓቱና ያሉን ላብራቶሪዎች የተደራጁና የተሰናሰሉ ስለሆኑ ነው።
የቁም እንስሳትን ግብይት ስንመለከት፤ ከግብይት እስከ ኤከስፖርት ያለው ሂደት በጣም የተወሳሰበ ነው። እንስሳት ላኪዎችን ለማናገር ሞክረናል። የእኛ ሥራ እንስሳቱ ከበሽታ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። ከዚህ ቁጥር አኳያ በቂ መሰረተ ልማት የለንም። ከዚህ በፊት የእኛ እንስሳት ጅቡቲ ኳራንቲን ሄደው ነው ከበሽታ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ውጭ ይላክ የነበረው።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሁለት ዘመናዊ ኳራንቲን ገንብተናል። አንደኛው አፋር ሚሌ ላይ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ጅግጅጋ ላይ ነው። ስለዚህ እንስሳቶቻችን ከበሽታ ነፃ መሆናቸውን እዚሁ ኢትዮጵያ ተረጋግጦ ወደ ውጭ ይላካል። ስለዚህ መሰል ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን
ማስፋፋት ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር በተቀናጀ አኳሃን ማካሄድ ተገቢ ነው። የእኛ እንስሳት ድንበር አቋርጠው እንዳይወጡ ማድረግ ይገባል። ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ስልጣን የተሰጣቸው አካላት አሉ። የሚመለከታቸው አካላትና ክልሎች ተናበው መስራት አለባቸው።
ኮንትሮባንድ የሚቆመው በሰዶ ማሳደድ ሳይሆን፤ ኮንትሮባንዲስቶቹን ለህግ በማቅረብ ነው። እንስሳትን በየጫካው በማባረር አይቆምም። መጥፎ ተግባርና ዝርፊያ የሚሠራውን በተቀናጀ አኳሃን ለህግ ማቅረብ ይገባል። ክልሎችና የፌደራል መንግስታት መተባበር አለባቸው። በዚህ ዓመት ጥሩ ውጤት አምጥተናል። በቀጣይ እየተጠናከረ ይሄዳል የሚል ዕምነት አለኝ። ስለዚህ ከእንስሳት ሃብታችን አልተጠቀምንም። ከእንስሳት ሃብት ቁጥጥር እና ጤና አያያዝ አለመጠናከር፣ ኮንትሮባንድ፣ መሰረተ ልማት አለመሟላትና ሌሎች ጉዳዮች ደግሞ የዘርፉ ችግሮች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት በብዛት የሚገኘው ከሌሎች አገራት ጋር በሚዋሰኑ ክልሎች ነው። በዚህ ሁኔታ ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት ንግዱን ለማቆም አስቸጋሪ አያደርገውም?
አምባሳደር ድሪባ፡- የችግር ዋነኛ ምንጭ ላይ ማተኮር ይገባል። አርብቶ አደሩ እና አርሶ አደሩ ለምን የቁም እንስሳትን ወደ ሌላ አገር አሳልፎ በኮንትሮባንድ ይሸጣል የሚለውን ከሥሩ ማወቅ ይጠበቅብናል። ቀላል ስለሆነ፣ ኮንትሮባንዲስቶች ስለሚያታልሉ ወይስ የተሻለ ገቢ ስለሚያገኙ ነው የሚለውን በሚገባ ማወቅና መመለስ ይገባል። ይህ ከታወቀ መፍትሄ ሊበጅለት ይችላል ።
ይህን መሰል ንግድ ድንበር ዘለል ስለሆነ ከጎረቤት አገራት ጋር የተቀናጀ ፀረ-ኮንትሮባንድ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ከጅቡቲ ጋር ድሮም አብረን እንሠራለን፤ ልምዱም አለ። ከጎረቤት አገራት ጋር ተናበን መስራት አለብን። ቴክኖሎጂን ተግባር ላይ በማዋልም ህገ ወጥ የእንስሳት ዝውውርን መቆጣጠር ይቻላል። አርብቶ አደሩ በኮንትሮባንድ ከሚሸጥ በህጋዊ መንገድ ሲሸጥ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓትን መዘረጋት ይገባል። ከአገር ውስጥም ሆነ ከጎረቤት አገር ያሉትን ኮንትሮናንዲስቶች ከሚመለከታቸው አገራት እና የአገር ውስጥ አካላት ጋር በመሆን ሥርዓት ማስያዝም ይጠበቅብናል። በየጫካው የሚካሄድ ንግድ ማስቆም ይገባል። ማህበረሰቡንም ማንቃትም ተገቢ ነው። ዘመናዊ ኳራንቲን ማስፋፋትና መገንባትም ያስፈልጋል።
በዚህ ህገ ወጥ የእንስሳት ንግድ ላይ በርካታ አካላት ተሳታፊ ናቸው። በዚህ ውስጥ ብዙ ፍላጎት ያላቸው አካላት አሉ። ኮንትሮባንድ ሲቆም እንጎዳለን የሚሉ አካላት አይጠፉም። ሆኖም ተደራጅተን ከሠራን ለውጥ ማምጣት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- የቁም እንስሳት ንግድ ህጋዊ ቢሆን እንኳን ለዘረ-መል ሥርቆት ስለሚያጋልጥ ቢቀር የሚሉ ምሁራን አሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
አምባሳደር ድሪባ፡- እኔም በትክክል እስማማለሁ። ወደፊት መሆን ያለበት እንስሳት እዚሁ ታርደው ሥጋው ነው ወደ ውጭ መሄድ ያለበት። ግን የቄራ ልማት በደንብ አልተገባበትም፣፡ ትልልቅ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ኢንቨስትመንቱ ላይ አልገቡም። ይህ ቢሆን አገሪቱም ትጠቀማለች። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ሥራ ይቀረናል። እስከዚያ ድረስ ግን ያለንን ሃብት ለመጠቀም በህጋዊና ዘመናዊ አሰራርና መንገድ የቁም እንስሳት ንግድ ማካሄድ አለብን። ኢትዮጵያ ከ70 ሚለዮን ያላነሰ የቀንድ ከብት ያላት አገር ናት። ይህን ሃብት ደግሞ መጠቀም ይገባል።
ጥቅሙ ትልቅ የሚሆነው እዚሁ ታርዶ ሥጋ እና ተረፈ ስጋው ወደ ውጪ ቢላክ ነው። ለጊዜው ግን የእርድና ቄራ ስርዓቱ፤ ኢንቨስትመንቱ ዝቅተኛ በመሆኑና የዘረመል ስርቆት የሚያስከትለውን ችግር መከላከል የሚቻልበት ሥርዓትም መዘርጋት ይቻላል። የእንስሳት ሃብቶቻችን ዘረመል ‹‹ኦርጂን‹‹ ማስመዝገብ እንችላለን። በእርግጥ ከዚህ በፊት ያመለጠን ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ያለንን የእንስሳት ሃብት ዘረ-መል በማስመዝገብ ንግዱን ብንጠቀም ጥሩ ነው። ሆኖም ምሁራን ያላቸውን ስጋት እኔም በተወሰነ ደረጃ እጋራለሁ። አሁን 20 የሚደርሱ ቄራዎች አሉን። ይህን ማስፋት አለብን። በርካታ ባለሃብቶች በቄራ ልማት ለመግባት እየጠየቁን ነው። እነዚህ ወደ ሥራ ሲገቡ የቁም እንስሳት ግብይት በጣም እየቀነሰ ይሄዳል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት፤ ኮፊ አረቢካ ‹‹ኦርጂኑ›› እኛ ነን። ባለሃብቶች ግን ከኢትዮጵያ በሃብት እጅግ ያነሱ አገራት ላይ ያተኩራሉ። ምክንያቱ ምንድን ነው?
አምባሳደር ድሪባ፡- እኔ የሚመስለኝ በበርካታ አፍሪካ አገራት የእንስሳት ልማት የሚካሄደው በ‹‹ራንች›› ነው። የዝርያ ማሻሻያ ሥራዎችም አሉ። ግብይት ሥርዓቱም መልክ የያዘ ነው። እኛ አገር ስንመጣ ኢንቨስትመንቱ ይመጣል። ኢንቨስተሮቹ በዋናነት የሚያተኩሩት በአነስተኛ አቅም ነው። በመሆኑም ትልቅ አቅም ያላቸው ቄራዎች እና ራንቾች ላይ መሥራት አለብን። ባለሃብቶችን ቶሎ መሳብና ማስተዋወቅ እና አጠቃላይ ሰንሰለቱ ላይ መሥራት ይገባል። ምርጥ ዝርያ ላይ መሥራት፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ ሰፋፊ ልማት ላይ ማተኮር አለብን። ይህ ከሆነ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ኢንቨስተሮችን መሳብ እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ከባልስጣኑ ተግባራት አንዱ ዕፅዋት ኳራንቲን ተባይና በሽታ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታ ቅኝት፣ አሰሳ እና የሥጋት ትንተና ማከናወን ነው። በዚህ ረገድ ከተሠሩ ሥራዎች ምን ውጤት ተገኘ?
አምባሳደር ድሪባ፡- የበሽታ ቁጥጥር ከባድ ሥራ ነው፤ መሰረተ ልማት ይጠይቃል። አንዳንድ ጊዜ በሽታዎች ሲከሰቱ የበሽታውን ምንጭ ለማወቅ እና እንዴት ወደ አገር እንደገባ ጭምር ለማወቅ ላብራቶሪዎች በደንብ ስላልተደራጁ ወደ ውጭ ልከን ነው የምናውቀው። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በሆርቲካልቸር ላይ ሰፊ አሰሳ እያደረግን ነው። የአውሮፓ ህብረት የጠየቁን ጥያቄዎች አሉ። አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ከስጋት ነፃ መሆናቸውን አረጋግጡልን ብለዋል። በመሆኑም በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ ሆርቲካልቸሮች ላይ አሰሳ እያደረግን ነው። ይህ ሪፖርት እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ምናልባት ደግሞ እስከ ታህሳስ 2015 ዓ.ም ድረስ ሪፖርት ካልላክን በቀጣይ ወደዚያ የአበባ እና ፍራፍሬ ምርቶችን መላክ አንችልም።
እንስሳት ላይም በተመሳሳይ እንጠይቃለን። ዳሰሳ እናደርጋለን፤ ሪፖርትም እናደርጋለን። ለአብነት ክረምት ላይ የዶሮ በሽታ ተከስቶ ነበር። በሽታው የመጣው በበራሪ ወፎች ወይስ ከውጭ ከሚገቡ ጫጩቶች ነው ወይስ በክትባት ነው ብለን እስካሁን እየመረመርንና ጥናት እያደረግን ነው። ባለሙያዎች መነሻ ሃሳቦችንና አመላካች ነገሮችን ያቀረቡ ቢሆንም ግልጽ የሆነ መረጃ ላይ አልደረሰንም። በአጠቃላይ ግን አቅም በፈቀደ መጠን የዕፅዋት ኳራንቲን፣ ተባይና በሽታ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታ ቅኝት እናደርጋለን። ተቋማችን አዲስ ቢሆንም ቀደም ሲል በግብርና ሚኒስቴር ሥር ይሰራ ስለነበር ልምድ አለን። እንደአገር ግን አቅማችን ማሳደግ በሁሉም መስክ መሥራት ይጠበቅብናል። መሰረተ ልማቶችን መገንባትና የሰው ኃይል ልማትንም ማሳደግ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ባለስልጣኑ በውጭ አገር ተመርተው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና የግብርና ግብዓትና ምርት በተመለከተ ጤንነትና ደህንነት መስፈርቶችን ማሟላታቸውን ያረጋግጣል፤ ፈቃድ ይሰጣል። ይሁንና በርካታ የግብርና ግብዓቶች አርሶ አደሩ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ይሰማል። ፈቃድ ከመስጠት በዘለለ መሰል ጥያቄዎችን የሚመለስበት አሰራር አለ? ከተለያዩ አገራት የሚመጣን ግብዓት በትክክል መቆጣጠር አያስቸግርም?
አምባሳደር ድሪባ፡- ትክክል ነው። ከባድና ውስብስብ ሥራ ነው። ለምሳሌ ዘንድሮ የእንስሳት መድሃኒቶች ላብራቶሪ ገብተው ከጥራት በታች የሆኑትን በሙሉ አስወግደናል። አራት አስመጪዎች ያመጡት ወደአመጡበት አገር እንዲመለስ አድርገናል። ሂደቱ ይታያል። በተቀመጠው ደረጃ በታች የሆነ ወደመጣበት ይመለሳል ወይም ይወገዳል።
ማዳበሪያ፣ ኬሚካል እና እንስሳት መኖ ያሉ ግብዓቶችን ፋብሪካዎቹ ዘንድ ሄደን እናያለን፤ ጥናት እናደርጋለን። በቀጣይ ኬሚካል ላይ በስፋት እንሰራለን። በመላ አገሪቱ ያለጥቅም የተቀመጡ ኬሚካሎች በህጋዊ መንገድ እናስወግዳለን። ይህን መሰል ሥራ ግን አገራዊ ቅንጅት የሚጠይቅ ነው። አንዳንዴ ጊዜም ድንበር ዘለል ናቸው። ከእኛ ደረጃውን ያልጠበቀ ወደ ሌላ ሊሻገር ይችላል፤ ከሌላ አገራትም ወደ እኛ ጥራቱን ያልጠበቀ ሊመጣ ይችላል። ልክ እንደ በሽታ መድሃኒትም ደንበር ዘለል ነው። በዚህ ላይ በሂደት የተጠናከረ ሥራ እየሰራን እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ በቄራ፤ ሆርቲካልቸርና ሌሎች ዘርፎች ላይ በመሠራቱ ምን ገቢ ተገኘ?
አምባሳደር ድሪባ፡- በእርግጥ በዋናነት የዚህን ገቢ የሚቆጣጠረው ንግድ ሚኒስቴር ቢሆንም፤ ከቄራ 120 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቡና 1ነጥብ4 ቢሊዮን ዶላር፣ በሆርቲካልቸር 520 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። በአጠቃላይ ግን ጥራጥሬ እና ግብርና ውጤቶችን አስመልክቶ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ነው የተገኘው። ይህ በሚቀጥለው በጀት ዓመት የበለጠ ተጠናክሮ ይሄዳል። በ2015 የምርት ጥራት ቁጥጥር ላይ በስፋት እንሠራለን። የእኛ ተቋም ዋና ዓላማ ባዮ- ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ግን እንደ አገር ትልቅ ለውጥ እናመጣለን ብለን እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- የባለስልጣኑ ስትራቴጂክ ትልሞች ምንድ ናቸው፤ ስጋቶቹና ተስፋዎቹስ?
አምባሳደር ድሪባ፡- ከስጋቱ ልነሳ። በአሁኑ ወቅት አየር ንብረት ለውጥ አለ። ይህ ደግሞ አዳዲስ የእንስሳት፣ የዕፅዋት፣ የሰው በሽታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። በዚህ የተነሳ የበሽታዎች መስፋፋት ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ ረገድ ተቋማችን ባዮ-ደህንነት ተቋም ነው። በሽታ ድንበር አቋርጦ ወደ እኛ እንዳይመጣ፤ እኛ ዘንድ የተከሰተ በሽታ ወደ ሌላ ዓለም ሄዶ እንዳያውክ፣ ምርቶቻችን ከዓለም የገበያ ሥርዓት እንዳይወጡ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለብን። በአንድ ምርት ላይ በሽታ ቢገኝበት በዓለም ገበያ ዳግም መሸጥ አንችልም። ስለዚህ የባዮ ደህንነት ሲባል የኤክስፖርት ገቢ የማጣት ዕድል እንዳይኖር የማድረግ ሥራ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጥራትን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ምርቶች ከበሽታ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በሽታ ከሌላ አገር መጥቶ ዜጎቻችንና ምርቶቻችን እንዳይጠቁ ዘብ መቆም ይኖርብናል። ምርቶቻችንና ዜጎቻችን ከበሽታ ለመከላከል ልክ እንደወታደር መሥራት አለብን። ስለዚህ አደጋውን የሚያባብሰው የአየር ንብረት ለውጥ ስለሆነ እንደ ሥጋት እንወስዳለን። የአቅም ክፍተት፣ ዓለም ተለዋዋጭ የንግድ ሥርዓትንና ሌሎች ፈተና ነው። በዜጎች ዘንድ የእንስሳትና እፅዋት ጤንነት ላይ ያላቸው ግንዛቤም በቂ አለመሆን፣ ህገወጥነት መስፋፋት እንደስጋት የሚታዩ ናቸው። እነዚህን ለማስተካከል ስትራቴጂክ እቅዶችን አዘጋጅተናል። የቁጥጥር ሥርዓታችንም ዲጂታል ማድረግ ላይ እየሠራን ነው። እኛም ስጋቶችን ለማሸነፍም እየሠራን ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን የምናልፍ ቢሆንም እጅግ ብዙ ተስፋዎች አሉን።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለመጠይቁ በዝግጅት ክፍላችን ሥም እያመሰገንኩ፤ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ተጨማሪ ዕድል ልስጦት?
አምባሳደር ድሪባ፡- 2014 ዓ.ም አጠናቀናል። በስኬትም በድክመትም ያለፍናቸው በሙሉ ትምህርት ሰጪ ናቸው። የሰው ልጅ ስኬቶች ሁሌም የእኛ ስለሆኑ አናስተውልም። ድክመቶች ግን ትምህርት ቤቶች ናቸው፤ የሚያሙ ስለሆኑ። ከድክመቶች ሁሌም መማር ያስፈልጋል።
2015 ዓ.ም ስኬታችን እንደስንቅ ይዘን ድክመታችንን አሻሽለን ትልቅ ለውጥ እናመጣለን ብዬ አስባለሁ። በተረፈ ለመላው ኢትዮጵውያን ለመስሪያ ቤቴ እና የግብርና ሚኒስቴር የሥራ ባልደረቦች የስኬት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ።
ክፍለዩሀንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም