እግር ኳስ እግር ኳስ ነው !

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃው እየወረደ ቢመጣም አሁንም በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ስፖርት መሆኑ አያጠራጥርም። ያምሆኖ እንደ ሀገር ለስፖርቱ ያለንን ፍቅር የሚመጥን እግር ኳስ ዛሬም ድረስ እውን ማድረግ አልተቻለም። እግር ኳሱ ከሚለወጥበት ጉዳይ ይልቅ በየጊዜው በሚለኮሱ የውዝግብና ንትርክ አጀንዳዎች ስፖርቱ ሥራ ሲበዛበት ማየት መገለጫው ሆኗል።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሪሚየርሊግ ክለቦችና በኢትዮጵያ ዋንጫ ዙሪያ ያሳለፋቸው የተለያዩ ውሳኔዎች ብዙ ውዝግብ አስነስተዋል። የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተከትሎ ጉዳዩን ከስፖርት ይልቅ ወደ ፖለቲካ ለመጎተት የሚጥሩ ወገኖችም በርክተዋል። የፌዴሬሽኑ ውሳኔዎች ትክክል ይሁኑም ስህተት በተዳከመው እግር ኳስ ነገሩን ለማጦዝና ሌላ አቅጣጫ ለማስያዝ የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉንም አካላት ትዝብት ላይ የሚጥሉ ናቸው።

እግር ኳሱ መሬት ላይ ከሚታየው እውነታ ስፖርትና የስፖርት ባህሪ ያልሆነ ፖለቲካው ጉልቶ እየወጣ የንትርክ መድረክ መሆን የለበትም። የፖለቲካ፣ የብሔርና የማንነት ጉዳይ ወደ ስፖርቱ እንዲገባ የሚጥሩ አካላትም እጃቸውን ሊሰበስቡ ይገባል።

እግር ኳስ ፌዴሬሽኑም ቢሆን ስፖርቱን በበላይነት የሚመራ የበላይ አካል እንደመሆኑ እያንዳንዱ ውሳኔዎቹ ግልፅ፣ ከውዝግብ የፀዱና ፍትሀዊ እንዲሆኑ በማድረግ በስፖርቱ ዙሪያ ሰላማዊ ከባቢ መፍጠር አለበት። ፌዴሬሽኑ ልክ እንደ ውጪው ዓለም አሰራሮችን በመዘርጋት ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት የሚወስድ አካል ሊሆን ይገባል። የሀገሪቷን የእግር ኳስ ችግር ለማስተካከል ስፖርቱ በዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ሊመራ ይገባል።

የስፖርት ሰላም፣ ፍቅርና ጤነኛ ማኅበረሰብ መገንባት መርህ ሊተገበር ይገባል። ስፖርቱ ከመርህ ውጭ ግለሰቦች/ ቡድኖች የሚጣሉበትና ልዩነቶች ጎልቶ የሚታይበት መሆን አይገባውም። የእግር ኳስ መርህ ባለመጠበቁ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲቀጥሉና ዳግም እንዲፈጠሩ መፍቀድም አይገባም።

እግር ኳስ ልዩነት መፍጠርያ ከመሆኑ ይልቅ፤ አንድነት መፍጠሪያና ትብብርን ማጠናከሪያ ነው። ስፖርቱ የተጣሉን ወገኖችን፣ የተቃቃሩ ግለሰቦችን ከዚያም አልፎ ሀገራትን ማስታረቅ የሚችል ትልቅ አቅም አለው። ለእኛም እግር ኳስ አንድነታችንና ሕብረታችንን ማጠናከር የሚችል መሆኑን ኢትዮጵያ ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችበት ታሪክ በተጨባጭ አሳይቶናል። ታዲያ ካለፈው ተምረን በቀጣይ ለተሻለ ውጤት መረባረብ ሲኖርብን ለምን የመለያያ፣ የጠብ ሜዳ እናደርገዋለን?፣ ።

ስፖርቱን ከውዝግብ ለማዳንና በተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ የፌዴሬሽኑ ወይም የክለቦች ኃላፊነት ብቻ አይደለም። የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎን የሚፈልግ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ እግር ኳስ ክለቦችና ሌሎች በስፖርቱ ዙሪያ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ከዘመኑ ጋር እኩል እየተራመዱ ሥርዓት መገንባት ካላወቁበት ልፋታቸው ከንቱ መሆኑን መረዳት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ታሪክ ማውራት እንጂ አዲስ ታሪክ መሥራት አንችልም።

እግር ኳሱ በጥብቅ ሥነምግባርና ዘመኑን በዋጀ ሥርዓት እስካልተመራ ድረስ የመጪው ዘመን እጣ ፋንታችን በሌሎች ድል ከመቆዘም የተሻገረ አይሆንም። ብዙዎች የሚቀኑበት የኢትዮጵያ አግር ኳስ አፍቃሪዎች ስሜትም በእጅጉ የሚጎዳ ይሆናል፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በዚህ ዘመን የሚያስፈልገው ውዝግብ ሳይሆን ቅንነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ስክነትና ብልሀት የተላበሰ አመራርና ሰላማዊ ከባቢ ነው። እንዲህ አይነቱ አመራር ሀገርና ሕዝብ የሚያከብር ታሪክን አስጠብቆ አዲስ ታሪክ የሚሠራ ይሆናል። ከዚህ በፊት የተሠሩ ስህተቶችን ላለመድገም እየተጠነቀቀ ለመፍትሄ የሚበጁ ሀሳቦች ላይ ያተኩራል። ለእግር ኳሱ መለወጥ ሁነኛ ሥርዓት ፈጥሮም ያልፋል።

ሰሞኑን በእግር ኳሱ ዙሪያ ከስፖርት ይልቅ ፖለቲካ የሚሸቱ ነገሮች በመከሰታቸውና ጨዋታዎች በውዝግብ ማለፋቸው “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የሀገራችን እግር ኳስ ውጤት አልባ መሆኑ ሳያንሰን ፖለቲካ ማራመጃ መድረክ መሆን የለበትም። እግር ኳሱ በጊዜ ሂደት ከመሻሻል ይልቅ ውድቀቱ እየተፋጠነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት መድረኩ የውዝግብና የንትርክ አውድማ እየሆነ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች መንስዔ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

በተለይም የ2029ን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ ባለበት በዚህ ወቅት በዚህ ስፖርት ዙሪያ የማይመጥኑ ነገሮች መታየት በፍጹም ሊፈቀድ አይገባውም፡፡ እግር ኳሳችን እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ወይም ላሊጋ ይሁን አላልንም፤ ግን ሰላማዊ መድረክ እንዲሆን እንፈልጋለን። የተለያዩ ውዝግቦች ስፖርቱን ከማቀቀጨጭ በስተቀር ለማንም እንደማይጠቅሙ ደጋግመን አይተናልና ከታሪካችን እንማር።

ፌዴሬሽኑ፣ ክለቦች፣ እግር ኳስ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች ደጋፊዎች እንዲሁም የፖለቲካ አመራሮችም ለስፖርቱ ሰላማዊነት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። በሀገሪቱ ከውዝግብ የፀዳ ሰላማዊ የእግር ኳስ እንዲኖር ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት ሲችል ነውና ሁላችንም ለውጤታማነቱ ልንረባረብ ይገባል !

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You