ኢንስቲትዩቱ በሰባት ዓመታት 280 የምርምር ሥራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፡ባለፉት ሰባት ዓመታት 280 የምርምር ሥራዎችን ማከናወኑን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በስድስት የምርምር ማእከላት 52 የጥናት መስኮችን ለይቶ እየሠራ ይገኛል። ባለፉት ሰባት ዓመታትም በተለያዩ ዘርፎች ላይ 280 የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ተቋሙ ማስረጃን መሠረት ያደረጉ ጥናትና ምርምሮችን ይዞ መውጣት፣ ፖሊሲ ምክረሃሳቦችን ለሚመለከታቸው ፖሊሲ አውጭዎችና ፖሊሲ አስፈጻሚዎች እንዲሰጥ፣ አቅም ግንባታ፣ የፋይዳ ዳሰሳ ማከናወን ለተቋሙ ከተሰጡት ተልእኮዎች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ነባር ፖሊሲዎችን የፈተሹ አዳዲስ የፖሊሲ ሃሳቦችን ያመላክቱ 280 ምርምሮች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው ከ35 በላይ ጥናትና ምርምሮች ተከናውነዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢንዱስትሪ ትስስር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የመካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ተግዳሮቶችና የፖሊሲ አማራጮች፣ የቤት ልማት ፋይናንስ ላይ ያሉ ማነቆዎች፣ የኢትዮጵያ እንስሳት መኖ አቅርቦት እና በንብ ርባታ ሥራ ዙሪያ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማነቆዎችና የፖሊሲ አማራጮች፣ በሀገራዊ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች፣ በሀገራዊ የመስኖ ልማት ዙሪያ፣ የግብርና እድገት ትራንስፎርሜሽንን፣ የፋይዳ ግምገማ፣ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ የትግበራ ፋይዳ ግምገማ ተሳትፎና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ላይ የተደረጉ ተሳትፎዎች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የጥናት መነሻዎች የ10 ዓመቱ የልማት እቅድ፣ የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም እና የመንግሥት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ጠቁመው፤ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገቡ ሀገራት ጠንካራ የምርምር ተቋማትን ገንብተው ጥቅም ላይ ያዋሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ያስቀመጠቻቸውን የልማት ግቦች ለማሳካትም ማስረጃን መሠረት ያደረገን ምርምር በግብዓትነት ለመጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተው፤ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ከሌሎችም ባለድርሻዎች ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከፍተኛ ሀብት፣ ጊዜና እውቀት ፈሶባቸው የተጠኑ ጥናቶችም መደርደሪያ ላይ የሚቀመጡ ሳይሆኑ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የፋይናንስና የዕውቀት አቅምን በማሳደግ ውጤታማ ተቋም እንዲሆን አጋርነትን ማሳደግ እንደ አንድ ስትራቴጂ ነድፎ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ ከ50 የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በጥናትና በአቅም ግንባታ ሥራዎች በመደጋገፍ በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን በሚል የተያዘውን የልማት ትልም ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በ2023ዓ.ም ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት ተርታ በማሰለፍ የብልፅግና ማማ ላይ ለማድረስ የተነደፈውን ሀገራዊ ዕቅድ እውን ለማድረግ የልማት ማስፈጸሚያ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በጥናትና ምርምር የተደገፉ እንዲሆኑ ለማስቻል የራሱን ተቋማዊ ስራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You