
ኢኮኖሚያዊ እድገትን በተመለከተ፣ ወጥ ነው/ አይደለም የሚለው አከራካሪ ሆኖ፤ ፍትሀዊ ነው/ አይደለም እምለውም ለጊዜው የምናልፈው ሆኖ፣ በተለይ ዓለም አቀፍ የሆኑ የፋይናንስ ተቋማት የአንድን ሀገር የኢኮኖሚም ሆነ ሌሎች እድገቶችን በመፈተሽ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱባቸው መስፈርቶች አሏቸው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለመሳሰሉና በአድገሻ(ሀ)ል/አላደግሽ(ህ)ም ሲነተረኩ ለቆዩና ላሉ ሀገራት ካልሰለቸ በስተቀር አዲስ ጉዳይ አይደለም።
አማራጭ የኢኮኖሚ ልማት ሞዴሎችን በተመለከተም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ሲሆን፤ ሀገራት እንደ እድገታቸው መሻት አመቺ ነው ያሉትን የልማት ሞዴል በመምረጥ (ካስፈለገም ሀገር በቀሉን በማዘመን) ተግባራዊ ማድረጋቸው ያልተለመደ ክስተት አይደለም።
ለዚህ ደግሞ፣ በዋናነት ኢኮኖሚ ሞዴልና የልማታዊ ኢኮኖሚ ሞዴል የሚሉት እንዳሉ ሆነው፣ በርእሳችን የጠቀስነው ሞዴል አንዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ሥራ ላይ አውላው የነበረው የ”ልማታዊ መንግሥት” የኢኮኖሚ ልማትም ተጠቃሽ ነው። ከገበያ ሥርዓት (ነፃ ገበያ፣ የዕዝ እና/ወይስ ቅይጥ ኢኮኖሚ) አኳያም ሀገራት ምርጫቸው የየራሳቸው ነው።
አይኤምኤፍ የራሱ መመሪያ፣ ደንቦችና መመዘኛ መስፈርቶች አሉት፤ የዓለም ባንክ የራሱ መመሪያ፣ ደንቦችና መመዘኛ መስፈርቶች አሉት፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ በራሱ መመሪያና ደንቦች የሚተዳደር፤ መመዘኛ መስፈርቶች ያሉት አኅጉር አቀፍ ባንክ ነው። እነ አይኤምኤፍ፣ ዓለም ባንክንና እነሱን መሰሎች የሚገዳደረው፣ አዲሱ ሥርዓት የወለደው የብሪክስ አዲሱ ልማት ባንክ (ኤንዴባ)ም የራሱ የሆነ፣ አባል ሀገራት ተኮር የሆነ መመሪያና ደንቦች አሉት።
እነዚህ ሁሉ የሀገራትን ኢኮኖሚ ሲፈትሹ የእነዛ ሀገራት (የዛ ሀገር) ዋና ምርት፣ የሀገሩ መንግሥት የትኩረቱ አቅጣጫ ወዘተ ምን እንደ ሆነ ይፈትሻሉ፤ ለይተውም ከዚህ ምርት ይህንን ያህል፤ ከዛ ምርት ይህንን ያህል • • • ዶላር ተገኘ በማለት ያሰፍራሉ፤ ደረጃም ያወጣሉ። 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ • • • ሲሉም ከላይ ወደ ታች ያሰልፋሉ። ወደ ታች በተወረደ ቁጥር • • •
አንድ ሀገር ያለውን (ማዕድንም ይሁን ዛፍ ቅጠል) ሀብት መጠን፣ የሚገኝበትን ስፍራ፣ አይነት ወዘተ ለይቶ ማወቅ ያለበት ስለመሆኑ የኢኮኖሚ “ሀሁ • • •” ስለሆነ በዚሁ ማለፍ ይቻላል። ይህ ደግሞ ጠቀሜታው ከማንም በፊት ለዛው ሀገር፣ ለባለቤቱ ነውና ተግባሩ በጥልቅ ጥናት ላይ ሊመሰረት ይገባል። ቀጥለን በምንመለከተው አጠቃላይ ኢኮኖሚም የሚታየው ይኸው ነው።
ከላይ ያልነውን ወደ መሬት አውርደን በሀገራት ማሳያነት እንመልከተው። ለዚህም በአዋጭ የሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ አተኩረው የሚሠሩትን፤ በኖርዲክ ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ “ለረዥም ዘመናት ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትብብር በማድረግ የሚታወቁ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት” (2015 ዓ•ም) ያላቸው በማለት የገለፇቸውን፤ ኢኮኖሚያዊ እድገታቸው በ”ኖርዲክ ሞዴል”ነት (ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች (ወጪ ምርት) ጥራት ላይ የተገነባ ሞዴል ነው) በዓለም የሚታወቅላቸውና በጥቅል”የኖርዲክ ሀገሮች” በሚል የሚጠሩትን እንውሰድ።
ባላቸው ጠንካራ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ምክንያት፣ ኖርዌይን ጨምሮ በኢትዮጵያ የትምህርት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የዘላቂ ልማትና ሌሎች የልማት ክንውኖችን በመደገፍ የሚታወቁት የኖርዲክ ሀገሮች (ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ኖርዌጂያን፣ ስዊድን፣ እና አይስላንድ) ፖሊሲያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ እቅድና ተግባራቸውን፤ እንዲሁም ሕዝባቸውን በኢኮኖሚ ዕድገት አሽከርካሪዎች ላይ እንዲያተኩር በማድረጋቸው ምክንያት ስኬታማ መሆን የቻሉ ሀገራት ናቸው። ይህም በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ሪፖርት ላይ ሳይቀር ከፍተኛውን ደረጃ እንዲይዙ አድርጓቸዋል።
ኢኮኖሚያዊ ብቃትን እና ዕድገትን በሠላማዊ የሥራ ገበያ፣ በተመጣጣኝ የገቢ ስርጭትና በማሕበራዊ ትስስር ውስጥ በማካተት ረገድ በጣም እንደተሳካለቸው፤ ከፍተኛ ግብሮች፣ ሰፊ የደህንነት ማሕበራዊ ዋስትና እና እኩልነት ያለው የገቢ አከፋፈል ሥርዓት እንዳላቸው የሚነገርላቸው፤ ጥቅል ጂዲፒያቸው $1.5 ትሪሊዮን የሆነው፤ በኢኮኖሚያቸው ግዝፈት ከዓለም 10ኛ፣ ከአውሮፓ 5ኛ (ጁላይ 3, 2024) የሆኑት፤ 27 ሚሊዮን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው፤ የኖርዲክ ሀገሮች ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ መረቦች እና ተወዳዳሪ የገበያ ኢኮኖሚን ለማቀላጠፍ የጋራ ዘዴን መጠቀማቸው በምሳሌነት እንዲጠቀሱ አድርጓቸዋል።
ከሚከተሉት ርእዮተ-ዓለም አኳያ በሶሺያሊዝም እና ካፒታሊዝም መካከል ያለውን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ለበርካታ ዓመታት መልካም ስም ያተረፉት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑት ሀገራቱ ከየአቅጣጫው ኢንቨስተሮችን በከፍተኛ ደረጃ መሳብ በመቻላቸውም ተጠቃሽ ሆነው ይገኛሉ።
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት “በኖርዲክ ሀገሮች ውስጥ የመዋዕለ ነዋይ መመሪያ” በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገ መረጃ እንደሚያመለክተው የሀገሮቹ ጠቅላላ የእድገት መጠን “ፈጣን” ሲሆን፣ ከጁላይ 2017 ጀምሮ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ1.5 በመቶ ወደ 4.4 በመቶ አድጓል። ይህም ከዩናይትድ ስቴትስ የ1.3 በመቶ እድገት አኳያ ሲታይ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
አትኩሮት
በማሽነሪዎች፣ በሞተር ተሽከርካሪዎች፣ በወረቀት ምርት፣ በፋርማሲ እና በወታደራዊ የጦር መሳሪያዎች ኤክስፖርት ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችውና ማንኛውንም የፋይናንስ ማዕበል ለመቋቋም ዝግጁ መሆኗ የሚነገርላት ስዊድን፤ በዋናነት ኢኮኖሚዋ በማጓጓዝ እና እንደ ነዳጅ ዘይት፣ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ዓሳ ማስገርና የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ያተኮረውና የኢኮኖሚ ጥንካሬዋን ጠብቆ ለማኖር ትኩረቷን በሰሜን የባሕር ዘይት ክምችት ላይ ያደረገችው ኖርዌይ በእነዚህ ሀብቶቻቸው ላይ አተኩረው በመሥራታቸው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ከማኑፋክቸሪንግ እና ከጥበብ ሥራዎች የሚመነጨውና በዋናነት በአገልግሎት ላይ የሚውል ኢኮኖሚ ያላት፤ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 30% ድርሻን የሚይዘውና የተፈጥሮ መዳረሻ ከመሆን እና ጠንካራ የማሕበራዊ ዋስትና ሥርዓትን በመዘርጋቷ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት ከሌሎች ሦስት የኖርዲክ ሀገራት ቀዳሚ በመሆን “ከዓለም የደስተኞች ሀገር” በመሆን 1ኛ የሆነችው ፊንላንድ (ኢትዮጵያ 132ኛ)፤ በኢንቨስትመንትና በፋብሪካ ውስጥ በሰሜናዊው የባሕር ዘመናዊ የነዳጅና የጋዝ ምርቶች ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚ ያላት ዴንማርክ አጠቃላይ ክልሉን በተሻለ የኢኮኖሚ እድገ ላይ እንዲገኝ ማድረግ የቻሉ አባል ሀገራት ናቸው።
በየዓመቱ የሚካሄው የኖርዲክ-አፍሪካ ስብሰባ የአፍሪካና የኖርዲክ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚገናኙበት መድረክ ላይ ከሚነሱት አበይት ጉዳዮች መካከልም አንዱ ይኸው ኢኮኖሚያዊ እድገትና አብሮ የመሥራት ጉዳይ መሆኑን እዚህ ጋ ማስታወስ ያስፈልጋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም