በአፍሪካ ወጣቶች ቻምፒዮና የሚሳተፈው ቡድን ዛሬ ይጓዛል

በናይጄሪያ ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ20 እና 18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ ኢትዮጵያን የሚወክለው ልዑክ ከትናንት በስቲያ ሽኝት ተደርጎለታል። ዛሬ ደግሞ ወደ ስፍራው ያቀናል። በሽኝት መርሃግብሩ ኢትዮጵያን የሚወክሉት አትሌቶች እና አሰልጣኞች ለውድድሩ ጠንካራ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ወደ ናይጄሪያ እንደሚጓዙ ተናግ ረዋል።

“ኢትዮጵያ ለዓመታት በጀግና አትሌቶቿ ያስመዘገበችው ውጤት በትልቅነቱ የሚታወስ ነው” ያሉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ፥ ይሄኛው ትውልድ ታሪክን የማስቀጠል ትልቅ ኃላፊነት አለበት ብለዋል። ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አበባ ዮሴፍ ፌደሬሽኑ ለዓመታት የነበረበትን የእድሜ ተገቢነት ችግር ለመቅረፍ፤ በርካታ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ እና በናይጄሪያ በሚደረገው መድረክም የሚሳተፉ አትሌቶች በትክክለኛው መንገድ የተመረጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፌደሬሽኑ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከእስከዛሬዎቹ የዕድሜ ዕርከን ውድድሮች በተለየ፤ በትክክለኛው ዕድሜ ላይ የሚገኙ አትሌቶች እንዲሳተፉ ከህክምና ምርመራ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ለዚህም ቀደም ብለው በተለያዩ ውድድሮች ከተመረጡት 88 አትሌቶች ውስጥ፤ በርካቶቹ ከተቀመጠው የዕድሜ ገደብ በላይ መሆናቸው በመረጋገጡ እንዲቀነሱ መደረጋቸው ማሳያ መሆኑ ተጠቅሷል። በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከሐምሌ 9 እስከ 13 በሚካሄደው ውድድር 28 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች የሚሳተፉ ይሆናል።

በናይጄሪያዋ አቡክታ ከተማ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ43 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 937 አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ይወዳደራሉ። አዘጋጇ ሀገር ናይጄሪያ 60 ወንዶችና 50 ሴቶች በድምሩ 110 አትሌቶችን በማሳተፍ ቀዳሚዋ ሆናለች። ኢትዮጵያ ደግሞ 8 ወንዶችና 20 ሴቶች በድምሩ 28 አትሌቶችን በመያዝ ተሳታፊ ትሆናለች።

የተሳታፊዎቻችን ቁጥር ዝቅ ሊል የቻለው በቅርቡ በድሬዳዋ በተካሄደው የወጣቶች ውድድር አሸንፈው ከተመረጡት በርካታ አትሌቶች መካከል አብዛኛዎቹ በተደረገላቸው ምርመራ ከዕድሜ በላይ ሆነው በመገኘታቸው ነው።

ለምሳሌ በድሬዳዋው ውድድር በ10 ሺህ ሜትር የተሳተፉት አትሌቶች በሙሉ በምርመራው የዕድሜ ማጣሪያውን መውደቃቸው ተረጋግጧል። በመሆኑም በዚህ የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና የ 10,000 ሜትር የወንዶች ውድድር ኢትዮጵያ የማትወዳደር ይሆናል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You