የሽግግር ፍትህና ዘላቂ ሰላም

የሽግግር ፍትህ አስከፊ ግጭቶችን፣ ጭቆናዎችን እና የመብት ጥሰቶችን ተከትሎ ተጠያቂነት እንዲኖር፤ ፍትህ እና እርቅ እንዲሰፍን በማድረግ ዘላቂ ሠላም የሚፍጥሩ ሥራዎችን የሚያጠቃልል ሂደት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይገልጻል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሀገራትና ማኅበረሰቦች ከደረሰባቸው መጠነ ሰፊ የመብቶች ጥሰት ሁኔታ በመውጣት ተጠያቂነትን፣ ፍትህን እና እርቅን ባማከለ መልኩ የሚያከናውኑት የሽግግር ፍትህ ሂደትን መደገፍ እንደሚገባው በመግለጽ በተለያዩ ሀገራት የተሞከሩ የሽግግር ፍትህ ሂደቶችን ማገዙ በ “United Nations Approach to Transitional Justice, Guidance Note of the Secretary- General, 2010.” ተገልጿል።

በአፍሪካም በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የፀደቀው የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማሕቀፍ (The AU Transitional Justice Policy 2019)፣ የሽግግር ፍትህ – ሀገራት የተለያዩ መደበኛ እና ባሕላዊ እንዲሁም መደበኛ ያልሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን እና ተቋማዊ አሠራሮችን ተጠቅመው ያለፉ ጥፋቶችን፣ ክፍፍሎችንና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድና ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚደረግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ሂደት እንደሆነ ይገልጻል።

ፍትህ ሚኒስትር “የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፤ ከእርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭት እና ጭቆና በመውጣት በፖለቲካና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም ያለው ሽግግር ለማድረግ በሞከሩ ሀገራት የሽግግር ፍትህ ሂደቶች ተግባራዊ ተደርገዋል። የሽግግር ፍትህ ሥርዓት መዘርጋቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ እና ፍትህ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዎ አበርክቷል።

ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት በሽግግር ሁኔታ ውስጥ ብታልፍም በተሟላ መልኩ የሽግግር ፍትህ አላባዎች ተተግብረው አያውቁም። በእነዚህ የሽግግር ሂደቶች ያለፉ ጉልህ የሰብአዊ መብቶች ጥስቶች፡ በደሎች እና ጭቆናዎችን መንስኤ፡ ምንነት፡ አይነት እና የጉዳት መጠን በበቂ መንገድ በማጣራት፡ እውነትን በማውጣት እና እውቅና በመስጠት – በተጠያቂነት፡ በይቅርታ እና በእርቅ ላይ የተመሰረተ የተሟላ ሂደት አልተከናወነም።

ደርግ ንጉሱን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ – በንጉሱ ሥርዓት ዘመን መጠነ ሰፊ በደል ፈፅመዋል፤ አላግባብ በልፅገዋል እና ለወሎው ረሀብ እልቂት ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን መኳንንቶች፣ መሳፍንቶች፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ባለስልጣናትን አስሯል። የነዚህን ባልስጣናት ጉዳይ እያጣራ ለፍርድ የሚያቀርብ አጣሪ አምስት ኮሚሽንም ተቋቁሞ ነበር። አጣሪ ኮሚሽኑ ምርመራውን ማካሄድ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ምርመራውን ከማጠናቀቁ በፊት ደርግ ከ50 በላይ በሚሆኑት ባለሥልጣናት ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔ በማስተላለፍ እርምጃ ወስዷል።

ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ሲመሰሠርትም በደርግ አስተዳደር ዘመን ለተፈጸሙ ጥሰቶች ምላሽ ለመስጠት የወንጀል ክስ መመስረትን እንደ ዋነኛ መንገድ ተጠቅሟል። በአዋጅ ቁጥር 22/1985 መሰረት ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ልዩ የዓቃቤ ሕግ ፅህፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን – በስሩም ከ400 በላይ ሰራተኞች ነበሩት። የፅህፈት ቤቱ ዋና ሥራም የደርግ ባለስልጣናት የፈጸሟቸውን ወንጀሎች መመርመር፡ ክስ መመስረት እና ማስቀጣት ነበር። በዚህም መሰረት በተለያዩ ሰዎች ላይ ምርመራዎችን በማጣራት፣ በመደበኛው ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት እና በመከራከር ኮሎኔል መንግሥቱ ሀይለማርያምን ጨምሮ በበርካታ ተጠርጣሪዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ አድርጓል። በሂደቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃዎችን ተደራጅተው ክስ ተመስርቷል።

በ2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ያለፉ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ቁርሾዎችን እና በደሎችን በእውነት፣ በእርቅ እና በፍትህ ላይ ተመስርቶ በመፍታት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መንገዱን ለማመቻቸት በርካታ የሽግግር ፍትህ እርምጃዎችን ወስዷል። ለደረሱ በደሎች እንደመንግሥት በይፋ ይቅርታ የመጠየቅ፤ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን የማቋቋም፤ ክስ፣ ምህረት እና ለሽግግር ፍትህ ሂደት አስተዋፅዎ የሚያደርጉ የሕግ እና የተቋማት ማሻሻያ ሥራዎችን የማሻሻል ተግባራት ተከናውነዋል። ይሁንና የሽግግር ፍትህ በተሟላ እና ወጥ በሆነ መልኩ የሚተገበርበት የፖሊሲ አቅጣጫ ባለመኖሩ እንዲሁም የተወሰዱት ርምጃዎች የየራሳቸው ጉድለቶች ስለነበሩባቸው የሽግግር ፍትህ ሂደት ዓላማን ማሳካት አልተቻለም።

በየትኛውም ሀገር ተግባራዊ የሚያደርግ የሽግግር ፍትህ የሚተገበርባቸው አማራጮች እና መንገዶች በሀገሩ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ አውድ እንዲሁም በሽግግር ሂደቱ ባህሪ ላይ ተመስርቶ ሊወሰን ይገባል። የሽግግር ፍትህ ሂደት ክስን፣ እርቅን፣ ምህረትን፣ እውነትን፣ ማካካሻን፣ ተቋማዊ ማሻሻያን እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው የሽግግር ፍትህ አላባዎችን በአንድነትና በተመጋጋቢነት ያካተተ ሁለንተናዊ አካሄድ ነው። እነዚህ ስልቶች የሀገራትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ተገቢ ተቋማዊ አደረጃጀትን በመጠቀም ሲተገበሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ ሲል የሚያትተው ሰነዱ፤ ኢትዮጵያ አሁን በሽግግር ሂደት ውስጥ ያለች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ማድረግ ይገባታል ሲል ይደመድማል።

ፍትሕ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የጥናት ሰነድ እንደገለጸው በኢትዮጵያ አሳታፊ የሆነ፤ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፤ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መርሆችንና ድንጋጌዎችን ያከበረ፤ በሌሎች ሀገራት እና በሀገራችን ከነበሩ ልምዶች ትምህርት የሚወስድ እንዲሁም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ አውድ ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባ የሽግግር ፍትህ ሂደት በመቀመር እና በግልፅ የፖሊሲ ማሕቀፍ እንዲመራ በማስቻል ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ የዲሞክራሲ ሽግግርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ማስቻሉ ነው።

የተሳካ የሽግግር ፍትህ ሂደት ሳይተገበር የዲሞክራሲ ሽግግርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የማይቻል መሆኑ ነው። በተለያዩ ሀገሮች እንደተስተዋለው ያለፉ በደሎች እና ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአግባቡ ሳይፈቱ፤ ሙሉ እውነት ሳያወጣ፤ ተጠያቂነት ሳያሰፍን እና እውቅና ሳይሰጥ በእርቅ፣ በሰላም እና በፍትህ ላይ የተመሰረተ የተሳካ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ አዳጋች ነው። ስለዚህ በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ጉልህ የመብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች አግባብነት ባለው መልኩ ተፈተው በደሎቹ እንዲሽሩ፤ ቁርሾዎች እንዲጠገኑ፤ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲሳካ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንዲቻል የተሟላ የሽግግር ፍትህ ሂደት መተግበር እጅግ ጠቃሚ ነው።

የሕግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን እንደሚናገሩት፤ የሽግግር ፍትህ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ ነው ተብሎ ከሚታሰብበት ከአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ነጻና የፖለቲካ ምህዳሩ ወደሰፋበት የፖለቲካ ሥርዓት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሚተገበር የፍትህ ሥርዓት ነው። ጦርነትና ግጭቶች አብቅተው ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በሚደረግ ሽግግር ውስጥ የሚተገበር የፍትህ አይነት ነው።

ጽንሰ ሀሳቡ ሐረጉም በግልጽ እንደሚያስቀጣው የተለየ ሀሳብ በማራመዳቸው የሚታሰሩ፣ የሚሰደዱና ብዙ ዋጋ የሚከፍሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እውነተኛ የሽግግር ፍትህ በሚተገበርበት ሁኔታ ውስጥ የተለየ አመለካከታቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ዕድል የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የተለየ ሀሳብ በማራመዳቸው ምክንያት የደረሰባቸው ጉዳት እና የተፈጸመባቸው ኢፍትሃዊ እርምጃ ካለ ያ የሚካስበት መንገድም ይፈጠራል።

የሽግግር ፍትህ ቡድኖችም በቡድን ሲያነሷቸው በነበሩ ሀሳቦች እና የማኅበራዊ ፍትህ ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉባቸውን ዕድሎች የሚፈጥር ነው የሚሉት አቶ አመሃ፤ የተሳካ የሽግግር ፍትህ ለማካሄድ ቁርጠኝነት ካለና ሂደቱንም ሕዝቡ በቀጥታ የሚሳተፍበት፣ የሚቆጣጠረው እና የሚመራው ከሆነ ዜጎች የፖለቲካም ሆነ ሌለች አስተሳሰቦቻቸውን በኃይል እንዲያራምዱ የሚገደዱበት ዕድል አይኖርም። ይልቁንም ሀሳባቸውን ወይም የፖለቲካ አመለካከታቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚያራምዱበት አውድ ይፈጠራል ባይ ናቸው።

አያይዘውም በጣም ጥንቃቄ የሚያሰፈልገው በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ሁሉም ሰው የሚያምንበት አውድ መፈጠር አለበት። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የሽግግር ፍትህን ሥልጣን ላይ ያለው ወይም ሌላ ኃይል ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን ወይም አስመስሎ ለማለፍ ተብሎ የተደረገ ነው የሚል እምነት ከተያዘ ውጤቱ ጎጂ ነው የሚሆነው። ስለዚህ በሽግግር ፍትህ ሥርዓቱ አሠራርን አወቃቀር ላይ ሙሉ የሕዝብ አመኔታ እና ተሳትፎ እንዲኖር በጣም መሠራት አለበት ይላሉ።

የሽግግር ፍትህ ለሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን የሚጠቁሙት የሕግ ባለሙያው፤ እንደ አለመታደል ሆኖ አሁንም በሀገራችን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱ ጦርነቶች መቀጠላቸውን ይጠቅሳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትጥቅ ፈትተው የሰላም አማራጭን የሚከተሉ ታጣቂዎች እኳን ሰላም ለማምጣት ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች እየተያየ ቢሆንም በአንድ ወገን እዚህም እዚያም ጦርነቶች ባሉበት ሁኔታ የተሳካ የሽግግር ፍትህ ማካሄድ አይቻልም የሚል እምነት ያለው ክፍል እንዲሁም በሌላ ወገን ሂደቱ ላይ እምነት በመጣል ውጤት ያመጣል ብለው እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች መኖራቸውን ይገልጻሉ ።

“እኔ እንደማስበው ጦርነቶች ባሉበት ሁኔታ የተሳካ የሽግግር ፍትህ ማካሄድ አይቻልም የሚለው ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ የሚጣል አይደለም፤ ግን ደግሞ ሂደቱ ዋጋ የለውም ብሎ መተውም ትክክል ነው ብዬ አላምንም” የሚሉት አቶ አመሃ፤ የተሳካ የሽግግር ፍትህ ሂደት እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነት የሁላችንም ነው ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

ለሽግግር ፍትህ ሂደቱ ትግበራ አስፈላጊ ነው የተባለው የልዩ ፍድ ቤት ማቋቋሚያ ረቀቂቅ አዋጅ ለውይይት ቀርቦ እርሳቸውም ተሳታፊ እደነበሩ ገልጸው፤ የሚቀርቡ የሕዝብ አስታያየቶች ምን ያህል ዋጋ እየተሰጣቸው ነው የሚለው የራሱ ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም የእስካሁኑ ሂደት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ፣ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ እና አጠቃላይ የሰላም ግንባታው ተናቦ መሠራት ያለበት ሥራ ነው ብዬ አምናለው። በእኔ ምልከታ መናበቡ ላይ ክፍተት አለ። ሀገራዊ ምክክሩና የሽግግር ፍትህ ሂደቱ የት ቦታ ነው መቀናጀት፣ ቅንጅቱ ምን መምሰል፣ እንዴት መመራት እና ማን ምን ኃላፊነት መውሰድ አለበት የሚለው ነገር በሥነሥርዓት ተጠንቶ በሰነድ መገለጽ ያለበት ነው። እስካሁን እስከማውቀው ድረስ ይህ ሥራ እየተሠራ አይደለም። በዚህ ረገድ ያለው ክፍተት በቶሎ መልክ መያዝ አለበት ሲሉ ይመክራሉ።

ፍትህ ሚኒስትር ባዘጋጀው ሰነድ እና የሕግ ባለሙያው አቶ አመሃ ያነሷቸው ሀሳቦች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ በደሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በማሰብ ሊተገበር የታቀደው የሽግግር ፍትህ፣ የጋራ ትርክትን በመቅረጽ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል።

በተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You