‹‹የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ለትውልድ መሠረት የሚጣልበት ነው›› -ዶክተር ከበደ ወርቁ

-ዶክተር ከበደ ወርቁ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ

ከእውነት በስተቀር ውሸት የማያውቁ፣ ስስ ልብ ያላቸው፣ አንደበታቸው ጣፋጭ፣ ስሜታቸውንም የማይደብቁ ናቸው። ንጹህ ፍቅራቸውንም ሲሰጡ አይሰስቱም። ሲጎዱም ቅስማቸው ስብር ለማለት ቅርብ ናቸው። እንዲህ ያለ ስብዕና ያላቸው የዛሬ ፍሬ፤ የነገ አበባ የሆኑ ሕፃናት ናቸው። ሕፃናት ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው የነገ ሀገር ተረካቢ ናቸው።

ፍቅር ሰጥቶና ልዩ እንክብካቤ አድርጎ ሁለንተናዊ እድገታቸው ተጠብቆ ሀገሩን የሚወድና የሚያገለግል፣ በሥነምግባር የታነፀ ተተኪ ትውልድ ማፍራት ከወላጅ፣ ከማኅበረሰብ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጭምር የሚጠበቅ ተግባር ነው።

በዚህ ረገድ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። እየሠራም ይገኛል። የሚሠሩ ሥራዎች በፖሊሲ እንዲደገፉም መመሪያና ደንቦች በማዘጋጀት በሕግ ማሕቀፍ እንዲመራ እየተደረገ ነው።

በልጆች መልካም አስተዳደግ ላይ በመንግሥት በኩል እየተከናወነ ባለው ሥራ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተቋቁሞ በሥራ ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ማዕከሉ፤ በመላው አፍሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ሕይወት ለመለወጥ የሚረዳ የትምህርትና ፈጠራ ማዕከል የመሆን ርዕይ ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው። ማዕከሉ፤ መልካም ጤንነት፣ በቂ ሥርዓተ ምግብ፣ የመማር ዕድል፣ ደህንነትና ጥበቃ፣ ምላሽ ሰጪና አነቃቂ የሚሉ ነጥቦችን በዋናነት አንግቦ ነው የሚንቀሳቀሰው።

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ማዕከልን በተመለከተ ከማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ከበደ ወርቁ ጋር ቆይታ አድርገናል። ዶ/ር ከበደ ወርቁ ከዚህ ቀደም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በጤናው ዘርፍ ሲያገለግሉ እናውቃቸዋለን።

አዲስ ዘመን፤ እስኪ በቅድሚያ የአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከልነት እንዴት ተወለደ የሚለውን እናንሳ?

ዶ/ር ከበደ፤ የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዘርፈብዙ የተቀናጀ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራሞችን በሀገር አቀፍ፣ በአፍሪካ አኅጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፈፀም የተሞክሮ ማዕከል እንዲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተቋቋመ አስፈፃሚ ተቋም ነው።

ቀዳማይ ልጅነት እንደ ፕሮግራም እንዴት ተጠናከረ የሚለውን ለማንሳት ካልሆነ በስተቀር እንደ ውልደት በ2003 ዓ.ም የሚመለከታቸው የፌዴራል አስፈፃሚ ተቋማት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በጋራ በመሆን የመጀመሪያውን ሀገራዊ ቀዳማዊ የልጅነት ልማት፣ ክብካቤና ትምህርት የሚባል ሀገራዊ የፖሊሲ ማሕቀፍ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቶ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በወቅቱም በተሠሩት ሥራዎች የልጆች ጤና ከማሻሻል፣ የሞት መጠንን ከመቀነስ አንፃር ጥሩ የሆነ አፈፃፀም ተመዝግቧል። ሆኖም ግን የልጆች በሕይወት የመኖር፣ ልጆችን ከማነቃቃትና ክብካቤ፣ እንዲሁም ቅድመ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚሰጠውን ትምህርት፣ ወላጆችን አሳትፎ ከመፈፀም አንፃር በተሟላ መልኩ አልተሠራም። ወይንም ፖሊሲው በተሟላ ሁኔታ አለመተግሩ በተለያየ መንገድ ተረጋግጧል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ምን መልክ ሊኖረው ይገባል ብሎ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት ቀደም ሲል የነበረውን ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የመነሻ ዳሰሳ ጥናት ማካሄድ አስፈላጊ በመሆኑ በ2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመነሻ ጥናት ዳሰሳ በማካሄድ ክፍተቶቹን ለይቷል።

አዲስ ዘመን፤ መነሻ ጥናቱ ምን አመላከተ ?

ዶ/ር ከበደ፤ መነሻ ዳሰሳ ጥናቱ ያመላከተው፤ በኢትዮጵያ ሕፃናት በእድሜያቸው ሊደርሱበት የሚገባ የእድገት ምጣኔ ከሚጠበቀው በታች መሆኑን ነው። በአዲስ አበባ ከተማ 12.9 በመቶ ነው የነበረው። በተለይ ደግሞ ተጋላጭ ተብለው የሚታወቁ አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ልጆች ላይ ችግሩ ከፍ ብሎ ታይቷል። 25 ከመቶ የሚሆኑ ሕፃናት ከእድሜያቸው አንፃር እድገታቸው ዝቅ ብሎ ነው የተገኘው።

ምላሽ ሰጪ እንክብካቤ በሚባለው ወላጆች ወይንም አሳዳጊዎች ከሕፃኑ ጋር መጫወት፣ አብሮ ማውራት፣ ሕፃኑ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ተገንዝቦ ምላሽ መስጠት፣ ማነቃቃት ከሚጠበቅባቸው ተግባሮች መካከል ናቸው። በዚህ ምላሽ ሰጪ እንክብካቤ የወላጆች ወይንም የአሳዳጊዎች ሚና የሚጠበቀውን ያህል ሆኖ አልተገኘም። ከጽንስ ጀምሮ በቂ የሆነ ሥርአተ ምግብ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ፖሊሲ ማዕቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ከጽንስ ጀምሮ ተወልዶ እስከ ስድስት ዓመት እድሜ ድረስ ያሉትን ሕፃናት ያካትታል።

የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አምስት ማሕቀፎች አሉት። እንክብካቤ፣መልካም ጤንነት፣ በቂ ሥርአተ ምግብ፣ ምላሽ ሰጪ አነቃቂ ክብካቤ፣ የቀዳማይ የልጅነት መማር፣ ለሕፃናት የሚደረግ ጥበቃና ከለላ ናቸው። እነዚህን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመነሻ ዳሰሳ ጥናት መሠረት አድርጎ የኢዲስ አበባ ከተማ የወደፊት ተስፋ የሚል በአዲስ አበባ ከተማ ፍኖተ ካርታ ውስጥ ፕሮግራም ተቀረፀ።

ፕሮግራሙ ዝርዝር ነገሮችን ይዟል። ቀጣይ የነበረው ፕሮግራሙ መሬት ወርዶ እንዲፈፀም እንዲሁም ለልጆች ሁለተናዊ እድገት የወላጆች እውቀትና ክህሎት እንዲያድግ ለማስቻል ምን አይነት የሰው ኃይል ስምሪት ያስፈልጋል የሚል ነበር። ይህን ሥራ ለመሥራት በአዲስ አበባ ከተማ ወደ 5ሺ የሚሆኑ የወላጆች አቅም ግንባታና ምክር ባለሙያዎች እንዲዘጋጁ ተደረገ። እነዚህ ባለሙያዎች በትምህርት ዝግጅታቸው 12ኛ እና ከዚያ በላይ ናቸው። ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊትም በሶስት ዙር ለሶስት ተከታታይ ወራት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ባለሙያዎቹ ቤት ለቤት በመሄድ ለወላጆችና አሳዳጊዎች ምክርና ሥልጠና ይሰጣሉ።

ባለሙያዎቹ የተሠማሩት በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ጣቢያዎች ሥር ነው። ሕፃናት በእንክብካቤ ማሕቀፍ ውስጥ ያሉትን አገልግሎቶች ሁሉ እንዲያገኙ ባለሙያዎቹ ነፍሰጡርና የምታጠባ እናት፣ እንዲሁም እድሜያቸው ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ያሉበት ቤት በመሄድ ወላጆች ወይንም አሳዳጊዎች ማድረግ ያለባቸውን እንዲሁም በጤና ጣቢያ የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲጠቀሙ፣ የሥርአተ ምግብ ክትትል እንዲያደርጉ፣ ለሕፃናት ምላሽ ሰጪ ክብካቤ እንዲያደርጉ፣ የልጆችን ሥነልቦና የሚጎዳ ቅጣት ከመቅጣት ይልቅ በምክር ለመመለስ ጥረት እንዲያደርጉ፣ ሕፃናት ጥበቃና ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው ይመክራሉ።

ከሕፃኑ እድሜ ጋር የማይመጣጠን አጠራጣሪ የሆነ የእድገት ሁኔታ ሲያጋጥማቸውም ወደ ጤና ጣቢያ ይልካሉ። ይሄ ሥራ በተለይ ከሶስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን መሠረት አድርጎ ነው የሚሠራው። ከሶስት ዓመት በላይ የሆኑ ሕፃናት ደግሞ በመንግሥትም በግልም ትምህርትቤቶች ቅድመአንደኛ ትምህርት እንዲገቡ ይመከራል። በመንግሥት ትምህርትቤት ትምህርት በነፃ ነው የሚሰጠው። ሕፃናቱ ትምህርትቤት ሲገቡ ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ አገልግሎት ያገኛሉ። የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በአጠቃላይ ልጆች እራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው።

ሕፃናቱ በእድሜያቸው ለትምህርት ዝግጁ ከሆኑ የትምህርት ብክነት ይቀንሳል። ልጆች አንደኛ ክፍል ሲገቡ ቁጥርና ፊደል ይለያሉ። ለትምህርት ዝግጁ የሚያደርጋቸው መሠረታዊ ነገር እያወቁ ይሄዳሉ። ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት የተደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በአዲስ አበባ ከተማ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ የሆነው 49 በመቶ ለሆኑት ልጆች ብቻ ናቸው ። ወደ ትግበራ ሥራ ከተገባ ወዲህ ግን በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥትና በግል ትምህርትቤቶች ከሶስት መቶ አስር ሺ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት ዓመት የሆኑ ልጆች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።

ከአራት እስከ ስድስት ዓመት እድሜ ክልል የሆኑ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ሕፃናት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ደግሞ በቅርብ ጊዜ በተደረገ ዳሰሳ ጥናት ምዘና 89 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሕፃናት ለአንደኛ ክፍል ዝግጁ መሆናቸው ተረጋግጧል። ቀደም ሲል የነበረው መረጃ የሚያሳየው ለአንደኛ ክፍል ዝግጁ የሆኑ ልጆች 39 በመቶ ብቻ እንደነበር ነው። በተመሳሳይ ሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ላይ በሚደረገው ምዘና ቁጥሩ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። ይሄ የሚያሳየው ፕሮግራሙ በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን ነው።

ከሶስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን በተመለከተም እድሜያቸውን የሚመጥን የእድገት ደረጃ ላይ መሆናቸውን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ቀደም ሲል ከነበረው 12.9 በመቶ ወደ 12.085 በመቶ ዝቅ ብሏል።

በዚህም መሻሻል መኖሩን ለመረዳት ተችሏል። ሆኖም ግን እንደ ትልቅ ለውጥ የሚወሰድ አይደለም። ብዙ መሥራትን ይጠይቃል።

በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት እድሜያቸው ከሶስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ከእድገታቸው ወደኋላ ይቀራሉ ተብለው የሚታሰቡት በአማካይ ወደ አምስት በመቶ ነው። ከዚህ አንፃር በሀገራችን በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው ምዘና የተገኘው ውጤት ከፍተኛ ነው። ይህም ሆኖ ግን ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጋር በንጽጽር ሲቀርብ በአዲስ አበባ ከተማ በእድገት ወደኋላ የቀሩ ሕፃናት የተሻለ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። በኦሮሚያ በእድሜያቸው ማደግ ከሚገባቸው በታች የሆኑ ሕፃናት ወደ 19.9 በመቶ፣ በድሬዳዋ ደግሞ ወደ 19.2 በመቶ ነው።

የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን ለማሳካት ባለሙያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ጤና ጣቢያዎቹም በዚያው አግባብ ዝግጁ ሆነው ይሠራሉ። ጤና ጣቢያዎቹ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን መሠረት ባደረገ የክትባት፣ የሕፃናት ሕክምና ክፍል፣ የድህረና ቅድመ ወሊድ ክትትል፣ እንዲሁም ሕፃናትን ሊያነቃቁ የሚችሉ በአጠቃላይ ለእድገታቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራቶች መፈጸም ስለሚጠበቅባቸው በዚህ አግባብ ይሠራሉ።

አዲስ ዘመን፤ ፕሮግራሙ ሕጻናትን ተጠቃሚ እንዲያደርግ እየተደረጉ ያሉ ድጋፍ እና ክትትሎች ምን ይመስላሉ ?

ዶ/ር ከበደ፤ አንድ ቤተሰብ በየሁለት ሳምንቱ መጎብኘት ስላለበት ባለሙያዎቹ ይሄን ተልዕኮ ይወጣሉ። ባለሙያዎቹ በየብሎክ ተከፋፍለው ነው ተልዕኮአቸውን የሚወጡት። ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ በጤና ቢሮ ደረጃ ቡድን አለ። በየክፍለከተሞች ደግሞ አስተባባሪዎችና ሱፐርቫይዘሮች አሉ።

አዲስ ዘመን፤ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አዲስ አበባ ከተማ ሞዴል ተደርጎ ነው የተወሰደው። አዲስ አበባ እንዴት ሊመረጥ ቻለ?

ዶ/ር ከበደ፤ አዎ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሞዴል ተደርጎ ሌሎችም ትምህርት አግኝተው ወደ ትግበራ እንዲገቡ ነው እየተሠራ ያለው። ልጆች የሚጫወቱበት ቦታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ቀዳማይ ልጅነት ሕፃናት ላይ ትኩረት ያድርግ እንጂ እስከ 18 ዓመት እድሜ ያሉትም ቢሆኑ ልጆች በመሆናቸው መጫወቻ ቦታ ያስፈልጋቸዋል። አካባቢያቸውን ማወቅ አለባቸው። የአካል ብቃት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በአጠቃላይ የሥነልቦናና ማኅበራዊ ሁኔታዎቻቸው እንዲጎለብት ማድረግ ያስፈልጋል። ለነዚህ ሁሉ የመጫወቻ ቦታዎች መመቻቸት አስተዋጽኦ አለው። በተጨማሪም ከቤት ውጭ ለሚውሉ እናቶች ለልጆቻቸው ማቆያ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። እነዚህ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ማሕቀፍ ውስጥ የተካተቱ ናቸው። ልጆች የቀዳማይ የመማር እድል እንዲያገኙም ያስችላል።

በአጠቃላይ እነዚህ ምቹ ሁኔታዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ አንፃር ከወሰድነው በጣም ጥሩ የሚባል ነው። የታለመውን ከግብ ለማድረስም ከፍተኛ የሆነ የአመራር ቁርጠኝነት አለ። የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ጭምር ነው በርብርብ እየሰራ ያለው። የአመራር ቁርጠኝነቱ አቅጣጫና አመራር ከመስጠት ባለፈ በበጀት መደገፍ፣ ለሥራው የሰው ኃይል ማሰማራት፣ የቅርብ ክትትል በማድረግ ይገለጻል። አዲስ አበባ ከተማ ሞዴል እንደመሆኗ ተሞክሮውን ወደሌሎች የማስፋት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፤ የአዲስ አበባ ከተማን ልምድና ተሞክሮ በማስፋት ረገድ ስለተሠሩ ሥራዎች ቢገልጹልን?

ዶ/ር ከበደ፤ የአዲስ አበባ ከተማን ተሞክሮ ለማካፈል በ2016 ዓ.ም ማብቂያ ላይ እንቅስቃሴ ተደርጓል። በወቅቱም ድሬደዋ አስተዳደርን ጨምሮ በአማራ፣ በሲዳማ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ነበር ልምድ የማካፈሉ ሥራ የተሠራው። ክልሎቹ ያገኙትን ልምድ መሠረት አድርገው ኦሮሚያ ክልልና ድሬደዋ አስተዳደር የመነሻ ዳሰሳ ጥናት አጠናቅቀው ይፋ አድርገዋል። አማራ፣ ሲዳማና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ መረጃ ሰብስበው መረጃ ትንተና ላይ ናቸው። የመነሻ ዳሰሳ ጥናት ሥራው ከሐዋሳ፣ ዋቸሞ፣ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ነው የተሠራው። ለንደንና አሜሪካን ሀገራት ውስጥ የሚገኘው ቢግዊን የተባለ ዓለምአቀፍ ድርጅት ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ አግዟል።

ክልሎቹ ፍኖተካርታ እንዲያዘጋጁም ተደርጓል። ፍኖተካርታው ምን ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለብን የሚለውን ለማሳየት ሲሆን፣ ይሄም ወላጆችንና አሳዳጊዎችን፣ ቅድመአንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ፣ ሥርአተ ምግብ ላይ፣ እንዲሁም መልካም የልጆች ጤና ከማጎልበት አንፃር ትኩረት ማድረግ፣ የልጆች መጫወቻ አማራጮችን ከማስፋት፣ የልጆች ክብካቤ ማዕከላት ወይንም መዋያ ከማዘጋጀትና ማደራጀት አንፃር ትኩረት አድርጎ ለመሥራት ባዘጋጁት ፍኖተካርታ ላይ አካተዋል። በዚህ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ውጤታማነት በመማሪያነት መቅረቡ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

አዲስ ዘመን፤ ፕሮግራሙ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ቤት ለቤት በመሄድ በመሥራት ብቻ ውጤታማ መሆን ይቻላል ?

ዶ/ር ከበደ፤ የወላጆችና አሳዳጊዎች አቅም ግንባታና ምክር ባለሙያዎች እገዛ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ባለሙያዎቹ አንዲት ነፍሰጡር እናት ከጽንስ ጀምሮ ማድረግ ስላለባት እንክብካቤ ክትትል ያደርጋሉ። ልጅ ከተወለደ በኋላም ክትትሉ ይቀጥላል። ሕፃኑ ምላሽ ሰጭ እንክብካቤ ማግኘቱን፣ የሕጻናቱን እድገትና ክሕሎት ሁኔታ፣ የተግባር ለውጦችን ይከታተላሉ።

ሕፃኑ አራት ዓመት ሲሞላው ደግሞ ወደ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ሲገባም ክትትሉ ይቀጥላል። ባለሙያዎቹ በዚህ ረገድ ሚናቸውን የሚወጡ ይሁን እንጂ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የአንድ ዘርፍ ሥራ ብቻ አይደለም። የትምህርት፣ የጤና፣ ማኅበራዊ ዘርፎች አልፎ ተርፎም መላው ማኅበረሰብ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ነው። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ከተማ አንፃር ካየነው ለልጆች የመጫወቻ ቦታዎችን በማስፋፋት ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና የአረንጓዴ ልማት ቢሮ ትልቅ ሚና አለው።

ቢሮው ምቹ ባደረገው ስፍራ ላይ ልጆች እንዲጠቀሙ ወላጆችና አሳዳጊዎች ወደ ስፍራው በመውሰድ እየተጫወቱ ነው።

በትምህርት ዘርፉ ደግሞ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ትልቅ ለውጥ እየመጣ ያለው፤ ትምህርት ቢሮ ሕፃናትን በጨዋታ የማስተማር ሥነ ዘዴ መከተሉ ነው። ትምህርት መምህሩን ሳይሆን ሕፃናቱን ማዕከል ባደረገ ነው መሰጠት ያለበት።ከአካል ብቃታቸው አንፃር ሕፃናቱ በምንጣፍ ላይ ተቀምጠው ነው የሚማሩት። ትምህርቱም እነርሱን መሠረት አድርጎ ነው የሚሰጠው። በዚህ እድሜ በዋናነት ሕፃናቱ አካባቢያቸውን እንዲያውቁ ነው የሚደረገው።

አዲስ ዘመን፤ ሥራው ወደኋላ እንዳይጎተት የምትከተሉት ስልት ምንድን ነው ?

ዶ/ር ከበደ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ የሚመራ የክትትል አግባብ ሥርአት ተዘርግቷል። አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኒዎች አባል የሆኑበት አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሯል። በተጨማሪ በከንቲባ ጽህፈት ቤት ሥር በሚገኘው ስትራቴጂክ ፕሮግራሞች ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሰብሳቢነት የሚመራ የቴክኒክ ኮሚቴ አለ። በእነዚህ ሁሉ አካላት ክትትል ይደረጋል።

በዚሁ የስራቴጅክ ፕሮግራሞች ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ደግሞ የልጆች መዋያ ማዕከላትንና መጫወቻዎችን ከማስፋት አንፃር፣ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሁም የወላጆችና አሳዳጊዎች አቅም ግንባታና ምክር ባለሙያዎችን የሚከታተሉና የሚደግፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች አሉ። የመረጃ ፍሰቱም በሥርአት ነው የሚመራው። የተሰሩ ሥራዎች ከየወረዳው ተደራጅተው መረጃው ለከንቲባ ጽህፈት ቤት ለስትራቴጂክ ፕሮግራም ማኔጅመንት ቢሮ ይደርሳል። በዚህ መልኩ የሚከናወኑ ሥራዎች ውሳኔ ለመስጠት የሚያግዙ በመሆናቸው የመረጃ ፍሰቱ በአግባቡ ይከናወናል። ክብርት ከንቲባ አዳነችም በአካል በመሄድ ሥራዎችን በማየት ያግዛሉ። ይደግፋሉ። ሁሉም ዘርፍ የየራሱን ተግባር እየተወጣ ነው። ሥራዎች በዚህ አግባብ እየተሠሩ ነው።

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ፕሮግራሙ የሌላ አካል አይደለም። የመንግሥት በመሆኑ ወደኋላ ይቀለበሳል ወይንም ይቀራል የሚል ጥርጣሬ አይኖርም። የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የትውልድ መሠረት የሚጣልበት ነው። እስከ 90 በመቶ የሚሆነው የሕፃናት አንጎል እድገት አማካይ አዋቂዎች ላይ የሚደርሰው እስከ ስድስት ዓመት እድሜ ነው። በተለይ ደግሞ እስከ ሶስት ዓመት 80 በመቶ የሚሆን የአንጎል እድገት ይኖራል። ቀደም ሲል ያነሳናቸው የተሟላ ሥርአተ ምግብ፣ መልካም ጤንነት፣ ምላሽ ሰጭ አነቃቂ ክብካቤ፣ የቀዳማይ የመማር እድል ለአእምሮ እድገት ወሳኝ ናቸው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ሥራዎች ካልተሠሩ የጠፋ እድል ተደርጎ ይወሰዳል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በቀዳማይ ልጅነት ጊዜ ልጆች ላይ ኢንቨስት ማድረግ፤ ለምሳሌ የአንድ ዶላር ኢንቨስትመንት ከ13 እስከ 16 ዶላር በእድሜ ዘመን ምላሽ እንዳለው ነው የተረጋገጠው። በኢትዮጵያ ውስጥም በ2001 ዓ.ም አካባቢ ኮስት ኦፍ ሀንገር (የረሃብ ዋጋ) በሚል ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር ሥርአተ ምግብ ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ወደ 16.5 በመቶ አካባቢ የሀገራዊ ጠቅላላ ምርትን ዋጋ ይቀንሳል ወይንም እናጣበታለን የሚል ነበር ጥናቱ ያመላከተው። ሥርአተ ምግብ፣ ቅድመ አንደኛ ትምህርት፣ ምላሽ ሰጪ አነቃቂ ክብካቤ ለልጆች መስጠት ለእድገት ወሳኝ ነው የሚባለው ከዚህ አንፃር ነው።

አዲስ ዘመን፤ ሥራዎች ሲሠሩ የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ይኖራቸዋልና የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም እቅድ ምን መልክ አለው?

ዶ/ር ከበደ፤ ጤና፣ ትምህርት፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በጋራ ተወያይተው ያስቀመጡት የፖሊሲ ማሕቀፍ አለ። ፖሊሲው በ2015 ዓ.ም ይፋ ሆኗል። በፖሊሲው ላይ በሂደት ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በከተማ ደረጃ በእድሜያቸው የሚመጥን ወይንም የሚጠበቅ የተሟላ የሕፃናት እድገት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማስቻል ነው የሚል በፖሊሲው ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ አንፃር ከእኛ የሚጠበቀው ድጋፍ ማድረግ ነው። ፖሊሲውን የሚያስፈጽሙት ሚኒስቴር መሥሪያቤቶችና በተዋረድ ደግሞ ተቋማት ናቸው። መልካም የልጆች አስተዳደግና አያያዝ ሥርአት የማስፍን ሥራ እየተሠራ ያለው በዚህ መልኩ ነው።

አዲስ ዘመን፤ ለነበረን ቆይታ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስም አመሠግናለሁ።

ዶ/ር ከበደ፤ እኔም ስለቀዳማይ ልጅነት የልማት ፕሮግራም ሀሳብ እንድሰጥ ስለተጋበዝኩ አመሠግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You