እንሆ የፀደዩን ወራት አሳልፈን በብዙዎች በተለይም በተማሪዎች የሚናፍቀው የክረምት ወራት ላይ እንገኛለን:: ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል::አብዛኞቹ መምህራንም ለቀጣዩ ዓመት ፊት በነበራቸው ላይ ተጨማሪ እውቀት ጨምረው መስከረም ላይ በአዲስ መንፈስ ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው ለማገዝ ብርቱ ዝግጅት የሚያደርጉበት ስልጠና እየወሰዱ ናቸው:: ከዚሁ ጎን ለጎንም እረፍታቸውን እያጣጣሙ የሚገኙም አሉ:: ለመሆኑ እረፍት ላይ የሚገኙት ተማሪዎች በእረፍታቸው ጊዜያቸው ምን እየሠሩ ይሆን? ስንል የተለያዩ ኣላትን አነጋግረናል።
ወይዘሮ ሙሉወርቅ ሞገሴ ይባላሉ። የሦስት ልጆች እናት ናቸው። ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ልክ እንደተዘጋ ለእረፍት ክፍለ ሀገር የሚኖሩት አያቶቻቸው ጋር እንደመልኳቸው ይገልጻሉ::እሳቸው እንደሚሉት፤ከዚህ ቀደም ሄደው ስለማያውቁ የወላጆቼን ቤትም ሆነ የሚኖሩበትን አካባቢ አያውቁትም ነበር:: የላኳቸው አንድም ለእረፍት ሁለትም የማያውቁትን አዲስ አካባቢ በመጎብኘት ለሀገራቸው ፍቅር እንደያድርባቸው ነው::አልፎ አልፎ አያቶቻቸውን በሥራ ያግዛሉም:: ይህ ደግሞ ክረምት ወቅት ምን ምን ተግባራት እንደሚከናወን እንደረዱ ያደርጋቸዋል::
ልጆች በትምህርት ተጨናንቆ የቆየ አዕምሯቸውን ተፈጥሮን በማየትና ሥራ በመሥራት እንደያፍታቱ ያስፈልጋል:: መረጋጋት አለባቸው:: ይሄንን ደግሞ በተለይም በአደስ ሁኔታ ውስጥ ገብተው ቢያሳልፉ አዋጭነቱ የጎላ እንደሆነ ያስረዳሉ:: አክለውም በቀጣዩ ዓመት ለሚጠብቃቸው ትምህርት በአዲስ መንፈስ ዝግጅት የሚያደርጉ መሆን አለባቸው ይላሉ::
የስምንተኛ ክፍል ፈተና በመውሰዱ ቀደም ብሎ እረፍት መውጣቱን የሚያስተውሰው ተማሪ መራዊ መዝሙር በበኩሉ ከሰባተኛ ክፍሏ ተማሪ ከታናሽ እህቱ ጋር በመሆን በቤታቸው ውስጥ ቁጭ ብለው የተለያዩ መጽሐፍቶችን በማንበብ የእረፍት ጊዚያቸውን እያሳለፉ እንደሆነ ይናገራል:: እስካሁን ባለው ጊዜም ሦስት ያላነሱ የልጆች ተረት መጽሐፍቶችን እንዳነበበ ይገልጻል:: እንደ ሰው በምድር እንደ አሳ በባሕር፤ ከአድማስ ባሻገር፤ ኦሮማይ፤ መንዱባ፤ የተሸጠው ሰይጣን ከአነበቧቸው ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፍት ውስጥ የመጠቀሱ መሆናቸውንም ነግሮናል::
መጽሐፍቱን ያነበቡት አብርሆት ሩቅ ስለሆነ እና ቤተሰብ በየቀኑ ወደዚያ ሄደው እንዲያነቡ ስለማይፈቅድላቸው በአቅራቢቸው ካለ መጽሐፍ ሻጪ በቀላል ብር እየተከራዩ ነውም:: በቀጣይ ወር የእረፍት ጊዚያቸው ደግሞ የእንግሊዝኛ ቋንቋቸውን ያሻሽሉልናል የሚሏቸውን የእንግሊዝኛ ፊልሞች የማየት ዕቅድ እንደያዙ አጫውቶናል::
“የእንግሊዝኛ ፊልም ማየት የቋንቋ ችሎታዬን ስለሚያዳብርልኝ እወዳለሁ” የምትለው እህቱ ተማሪ ሜሮን መዝሙር፤ መምህሮቿ፤ ወላጆቻቸው ታሪኩ ፍቅር ላይ ቢያጠነጥንም እንኳን እነሱ ታሪኩ ላይ ሳይሆን ቋንቋው ላይ በማትኮር መከታተል እንዳለባቸው ያስገነዘቧቸው መሆኑንም አጫውታናለች::
ፈተና ከመጀመሩ በፊት ከጊቢ ውጭ ጭምር በትምህርት ቤቱ በተካሄደ ችግኝ ተከላ በመሳተፍ የበኩሉን አሻራ እንዳሳረፈ የነገረን ደግሞ የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሚካኤል ዶጂ ነው:: እርሱ እንዳለን፤ ባለፈው ሳምንት ነው ፈተና ያጠናቀቀው:: ሆኖም ከፈተና በኋላ ያለውን የእረፍት ጊዜ እንዴት ማሳለፍ እንዳለበት ቀድሞ አቅዷል:: ዕቅዱ ደግሞ የኮዲንግ እና ፋይናንስ ላይ የሚያጠነጥን ሥልጠና መውሰድ ነው:: አሁን ፈተናውን በመጨረሱ የተነሳ ሁለቱንም ሥልጠና ጎን ለጎን እየወሰደ ይገኛል::
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኮዲንግ ሥልጠናን የግድ መውሰድ አለበት“ የሚለው ተማሪው፤ በፋይናንስ ላይ ያተኮረ የውጭ ሀገር ሥልጠና መከታተሉን የመረጠው ወደፊት በሥራው በሚሠማራበት ወቅት ገበያዎችን መተንበይ የሚያስችል ሰፊ ዕድል ስለሚሰጥ እንደሆነ አንስቷል:: በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ተማሪ እንደመሆኑ መጠን በውጭ የፋይናንስ ሙያ መሰልጠኑ ወደፊት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተስፋ ይሰጠኛል የሚል እምነት አለው:: ከእረፍቱ በኋላ ነጥብ ቢመጣለት ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር ማቀዱንና ምርጫዎቹ የተሻሉ እንደሆኑለት እንደሚረዳውም ያምናል:: ነጥብ ባይመጣለት ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና በመውሰዱ ወደፊት በራሱ የፈጠራ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቤተሰብ ማስተዳደር የሚችል ሰው ለመሆን እንደሚችልበትም ያስባል::
ሌላኛው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቅዱስ ዳዊት እንዳጫወተን ደግሞ የክረምቱን የእረፍት ወራትን ማሳለፍ የጀመረው የአውቶሞቢል መኪና ሹፌር ለመሆን የሚያስችለውን የመንጃ ፈቃድ ሥልጠና በመውሰድ ነው:: ሥልጠናውን የጀመረው የ12ኛ ፈተና ከማጠናቀቁ በፊት ሲሆን፤ እኛ ስናገኘው መሰልጠን ከጀመረ አንድ ሳምንት አስቆጥሯል:: መንጃ ፈቃዱን ማውጣት የፈለገው ከሌሎች ሦስት ጓዶቹ ጋር የእረፍት ጊዚያቸውን የራይድ አገልግሎት መስጠት ሥራ ላይ ተሰማርተው ለማሳለፍ በማቀዳቸው ነው::
ይሄን ሥራ ለመጀመር የሚሆናቸው መነሻ ገንዘብም ከየቤተሰቦቻቸው እንዳገኙም አጫውቶናል:: ሀሳቡም ከድሮ ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ያለሥራ መቀመጥ የለብንም፤ የራሳችንን ሥራ ፈጥረን መሥራት አለብን ብለው ከጓደኛቹ ጋር ያሰቡት ነው::
ተማሪ ቅዱስ ነጥብ ከመጣላቸው ዩኒቨርሲቲ ገብተው የመማር እቅዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አንዱን ራይድ ወደ አራት ከፍ በማድረግና ሥራውን በማስፋት እየተማሩም የሚሠሩበትን ሁኔታ ከወዲሁ የሚያመቻቹ መሆኑንም ነግሮናል:: በተለይ አሁን በፈረቃ ስለሚሠሩ በሚኖራቸው ትርፍ ጊዜ ተማሪዎችን በማስጠናት፤ አረጋውያንን የማገልገል እና ሌሎች በነፃ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆነም ይናገራል::
ሌላዋ የእረፍት ጊዜዋን እንዴት እንደምታሳልፍ የጠየቅናት የተስፋ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዋ ትህትና ፋንታሁን ነች:: ትህትና ስድስት ልጆች ላላቸው ቤተሰቦቿ ሁለተኛ ልጅ ስትሆን የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት እና ውጤት በመጠባበቅ ላይ ካሉት ተማሪዎች አንዷ ናት:: ተማሪዋ እንደምትለው፤ ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ተማሪዎች በክረምት የረፍት ጊዚያቸው በተለይም የ12ኛ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ቤተሰብ ላይ በመሆኑ ጫናውን የበለጠ ማክበድ የለባቸውም:: ቢያንስ አቅማቸው የሚመጥነውን ትንንሽ ሥራ በመሥራት ልብስና ጫማን ጨምሮ የትራንስፖርት ወጪያቸውን መሸፈን መቻል አለባቸው ብላ ታምናለች::
ቤተሰቦቿ ግን 10ኛ ክፍል ከነበረችበት ክረምት እረፍት ጀምሮ ሀሳቧን ለመተግበርና እሷን ጨምሮ በልጆቻቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ብትሞክርም ትምህርቷ ላይ ብቻ ትኩረት እንድታደርግ ስለሚፈልጉ ሳይፈቅዱላት ቆይተዋል:: በዚህም ትምህርት ቤት ከሚጠየቀው መዋጮ ውጭ እናቷን እና እህቷን ለትራንስፖርት ወይም ፀጉሯን ለመስሪያ እና ለሌሎች ጉዳዮች ስትጠይቃቸው ትሳቀቅ እንደነበር ታስታውሳለች::
በዘንድሮው የእረፍት ወራት ግን በሀሳቧ ስለተስማሙ አንበሳ ኢንሹራንስ በተላላኪነት ተቀጥራ በመሥራት የእረፍት ጊዜዋን እያሳለፈች ትገኛለች:: የገባችው ሞዴል ፈተና እንደወሰዱ በመሆኑም የመጀመሪያ ደሞዟን 3ሺ 700 ብር በቅርቡ ተቀብላለች:: በደሞዟ ከራሷ አልፋ ተርፋም ቤተሰቦቿን ማገዝ ችላለች::
”በዚህ ሥራ ተወስኜ መቀመጥ አልፈልግም” የምትለው ተማሪ ትህትና፤ አሁንም እጇን አጣጥፋ ቁጭ አላለችም:: በግሏ ራሷን የሚያስችል፤ በተሻለ ሁኔታም ቤተሰቧን የበለጠ የምትደገፍበት የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ሌላ ሥራ እያፈላለገች ነው:: ከውጤት በኋላም በቱሪዝም መስክ ትምህርቷን የመከታተል ሀሳብ የወጠነች መሆኗን እና ራሷን የሚያስችላትን እና ቤተሰቧ የበለጠ ለመደግፍ ከሚያመቻትን ሥራ ጎን ለጎንም ትምህርቷን የመከታተል እቅድ ያላት መሆኑን አጋርታናለች::
እንደ ተማሪ ትህትና ሁሉ የእረፍት ጊዜዋን በሥራ እያሳለፈች ያለችው ሌላዋ ተማሪ ጽናት ግርማ ነች:: እሷን ጨምሮ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች ላላቸው ቤተሰቦቿ ሦስተኛ ልጅ ስትሆን ጽናት ከ10 እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን በአብዛኛው በግሮሰሪ ውስጥ በአነስተኛ ክፍያ ዕቃ በማጠብ እየሠራች ስለመማሯ ታነሳለች:: እንዲህ ዓይነቱን የሥራ ተሞክሮ በየክረምቱ ያለውን የእረፍት ጊዜ በሥራ ከምታሳልፈው ተማሪ ጎረቤቷ መቅሰሟንም አልሸሸገችንም:: ተማሪዋ በምታገኘው አንድ ሺ 500 ብር ዝቅተኛ ደሞዝም ኑሮ ውድ በመሆኑ ከራስዋ ትራንስፖርት መሸፈኛነት ከማዋል አልፋ ቤተሰቦቿን ስትደጉም መቆየቷንም ገልፃለች:: ተማሪዋ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷንም ግማሽ ዓመት ድረስ በዚሁ መንገድ እየተከታተለች መቆየቷን ነግራናለች::
እርሷ እንደምትለው፤ ከግማሽ ዓመት በኋላ ፈተናው ላይ በቂ ዝግጅት ለማድረግ ስለማያመቻት ሥራውን አቋርጣው ነበር:: ይሄም ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንድታደርግ አስችሏታል:: እኛ ስናገኛትም ቀድሞ ትሰራው የነበረውን ሥራ ለፈተና ዝግጅት ብላ ባቋረጠችበት ወቅት ነው::
”ፈተናውን አጠናቅቄ ጨርሻለሁ:: የክረምቱን ወራት የእረፍት ጊዜዬን ከቀድሞው የተሻለ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ ማሳለፍ እፈልጋለሁ:: መሥራት ቤት ውስጥ ተቀምጦ ከመጨነቅ ይሻላል:: በተጨማሪም ለኔም ለቤተሰቦቼም ወጭያችንን የምንደጉምበት ገቢ ያስገኝልናል:: በመሆኑም ሥራ እየፈለግኩ ያለሁት የክረምቱን የእረፍት ወራት በሥራ ለማሳለፍ ነው” ብላናለች ጽናት::
”ጥሩ ነጥብ ቢመጣልኝ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ቶሎ ሥራ በሚገኝበት በማርኬቲንግ የትምህርት መስክ ትምህርቴን መከታተል ነው የምፈልገው ” የምትለው ተማሪዋ፤ የኮዲንግ ስልጠና ወስዳ የነበረ መሆኑን እና ተማሪዎች የክረምት የእረፍት ጊዚያቸውን ቤታቸው ቁጭ ብለው ከመዋል ይልቅ የተለያዩ አቅማቸውን የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች በመውሰድ እና ሥራዎችን በመሥራት ቢያሳልፉ መልካም እንደሆነ ምክሯ ነው::
ከዚሁ ተማሪዎች እና መምህራኖች የክረምቱን የእረፍት ጊዜ ከሚያሳልፉበት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ወደ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎራ ብለን በወቅቱ ያገኘናቸውን የትምህርት ቤቱን ምክትል ርዕሰ መምህር አንተናእኔ አንለይ ያላቸውን ሀሳብ እንዲያካፍሉንም ጠይቀን ነበር::
ምክትል ርዕሰ መምህሩ አንተእናእኔ እንደነገሩን፤ በዘንድሮ ትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቱ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል 1 ሺ 14 ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር ቆይቷል:: ከነዚህ ውስጥ 228ቱ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ናቸው:: በተለይ የ12ኛ ክፍል ፈተናውን የወሰዱት ከሌሎች ተማሪዎች አንፃር 18 ዓመት የሞላቸው እና በእድሜም ከፍ ያሉ ናቸው:: ለሥራ ደርሰዋል ማለትም ይቻላል:: እንደዚህም ሆኖ ጥሩ ውጤት አምጥተው ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚፈልጉ ተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ ከ12ኛ ክፍል በኋላ በሥራ መሰማራት የሚፈልጉ አሉ::
ከዚሁ ጎን ለጎን ተማሪዎች ለቀጣይ ትምህርት ዘመን የሚያግዛቸው የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት መማር ወይም የተለያዩ ተጓዳኝ ሙያዎች ሥልጠና መውሰድ ይፈልጋሉ:: ትምህርት ቤቱ በተለይ ማጠናከሪያ ትምህርት መማር የሚፈልጉ ተማሪዎችን አስመልክቶ ከወላጆቻቸው ጋር ግንኙነት ባደረገበት ወቅት እንደተረዳው 90 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች ልጆቻቸው በእረፍት ጊዜ በሚያዝናኑ በተለያዩ ነገሮች በትምህርት ተጨናንቆ የነበረውን አእምሯቸውን ዘና እያደረጉ እንዲያሳልፉ እንጂ ትምህርት እንዲማሩ እንደማይፈልግ ተገንዝቧል::
ወላጆች በተለይ 12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ልጆቻቸውን ነጥብ ባያመጡና ዩኒቨርሲቲ ባይገቡ ምን ሊሆኑ ነው በሚል ስጋት በመኪና መንጃ ፈቃድ፤ በሞባይል፤ በኤሌክትሮኒክስ እቃ ጥገና እና በሌሎች ሙያዎች እያሰለጠኑ ነው ያሉት ብለውናል:: ምክትል ርዕሰ መምህሩ በእረፍት ወራት ተማሪዎች በሚፈልጉት አካባቢ ሄደው ፍላጎታቸውን ያማከለ ስልጠና ቢወስዱና ሙያ ነክ ትምህርት ቢማሩ መልካም የመሆኑን ምክራቸውን ለግሰዋል:: በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቱ ያሉት 36 መምህራን በበኩላቸው በትምህርተ ቤቱ ባይሆንም መንግሥት ባወጣው የሥልጠና መርሐ ግብር መሰረት በራሳቸው እየሰለጠኑ ያሉበት ስለመኖሩም አውግተውናል::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም