
– አቶ ኢዘዲን ሙስባህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ተግባሩ በከተማ አስተዳደሩ ያሉ ትምህርት ቤቶች ብቁ ዜጋ ለማፍራት እንዲችሉ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ ማስቻል ነው። ይህን ለማከናወን የሚያስችሉ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ዘርፍና የምዘና ዘርፎች በውስጡ አሉት። የዝግጅት ከፍላችን ባለስልጣኑ ትምህርት ቤቶችን በምን መልኩ እየተቆጣጠረ እንደሆነ፤ የ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ ገደብ ምን ያህል ወቅቱን የዋጀ ነው? ከትምህርት አሠራር ውጭ ሆነው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ምን ያህል አስተማሪ ነው? በሚሉና መሰል ጥያቄዎች ዙሪያ ከባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪጅ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ተቋሙ እያከናወነ ያለው ሥራ ምንድን ነው?
አቶ ኢዘዲን፡- የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ተቋሙ የኢንስፔክሽን፣ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ይሠራሉ። በመደበኛ የኢንስፔክሽን ሥራ እንደየትምህርት ቤቶቹ ደረጃ ይሠራል። የተሻለ ትምህርት ቤት የሚባለው ደረጃ አራት ላይ የሚገኝ ነው። በትህምህርት የጥራት ደረጃ የሚሠራው ከትምህርት ሚኒስቴር በሚወርድ ስታንዳርድ መሰረት ነው። ይህም የራሱ የሆነ የማረጋገጫ ዝርዝር (ቼክ ሊስት) ያለው ሲሆን፣ መነሻ የሚያደርገው ግብዓት፣ አሠራርና ውጤት ነው።
የኢንስፔክሽን ሥራዎች ደረጃ አንድ ላይ ከወደቀ ትምህርት ቤቱ ከደረጃ በታች ነው። ይህ ማለት ደረጃ አንድ 50 በመቶ፣ ደረጃ ሁለት ከ50 እስከ 69 ነጥብ 99፣ ደረጃ ሶስት ከ70 እስከ 89 ነጥብ 99፣ ደረጃ አራት ከ90 እስከ መቶ ድረስ ባለው ነው።
የትምህርት ቤቶች የጥራት ደረጃ ማለት ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ አደረጃቶች፣ የተሟሉለት ነው የሚለውን የሚያመላክት ነው። ደረጃ አንድ ከደረጃ በታች ስለሆነ ትምህርት አይሰጥም። ስለዚህ እውቅና ዕድሳት በየሁለት ዓመቱ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ መመዘኛ ‘ቼክሊስት’ የተለየ ነው። በመመዘኛው አደረጃትና ግብዓት ብቻ ይታያል። በዚህም እስከ 75 በመቶ ያመጡ ብቻ መስፈርቱን አሟልተዋል ተብለው የዕድሳት ፈቃዱ ይሰጣቸዋል። ከዚህ ውጭ ግን ሌሎች ነገሮች አይታዩም። መዛኝ ባለሙያዎች የሚመጡት ከኢንዱስትሪ ቢሮ ነው። በባለስልጣኑ በኩል የሚሠራው ሂደቱን ማመቻቸት፣ መከታተልና የማስፈጸም ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ቤት አገልግሎት ክፍያ ማሻሻያው ዋና ዓላማው ምንድን ነው?
አቶ ኢዘዲን፡- በበጀት ዓመቱ ትልቁ አጀንዳ የትምህርት ቤት አገልግሎት ክፍያን ሕጋዊ ማድረግ ነው። ከዚህ ቀደም የነበረው ትምህር ቤቶች በየሁለት ዓመቱ የክፍያ ማሻሻያ የሚያደርጉበት በማዋል ነበር። አሁን ላይ አንድ ሺህ 227 መንግሥታዊ ያልሆኑ የግል የትምህርት ቤቶች የክፍያ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ አለብን ብለው ያቀረቡ ሲሆን፣ ተገቢነትም አለው። ነገር ግን በፍላጎቱ ኢኮኖሚያዊና ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ምክንያቶች ለጭማሪው ምክንያት ተደርገዋል።
ስለዚህ የጭማሪ አቅርቦቱ እጅግ የተጋነነ ምክንያት የሆኑት ከትምህርት ቤቶች መካከል ከቀረበው 10 በመቶ ብቻ ነው። ትምህርት ሀገር የሚገነባበት ዋና መሠረታዊ ጉዳይ ስለሆነ ፖሊሲ ተቀርጾለት ወርዶ ሥትራቴጂ ወጥቶለት የሚሠራ ነው። ስለሆነም የግል ትምህርት ቤቶች በጥራትም በተደራሽም ትልቅ ሚና አላቸው። ይህን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል የራሳቸው አሠራር አላቸው። በደረጃቸው ልከ ሚናቸውን እንዲጫወቱ መንግሥት ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል።
ትምህርት ቤቶች በብዙ መልኩ ይደገፋሉ። ይሁን እንጂ ቀላል የማይባሉ ትምህርት ቤቶች ከዋናው ዓላማ ብቻ ባፈነገጠ መልኩ ቀጥታ ትርፍን ብቻ ያማከለ አድርገው የትርፍ መጠናቸው ሕዳግ በጣም ከፍተኛ ያደረጉ ነበሩ። ለመምህራን ቤት ኪራይ ስላለባቸው ተመጣጣኝ የክፍያ ሕዳግ እንደሚያስፈልጋቸው ትክክለኛ ትምህርት ለማስተማር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በመጠቀም ረገድ የዘጠኝ ዓመት የአሠራር ሂደት ምን እንደሚመስል ጥናት ተደርጓል። ጥናቱም ከማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት በተወሰደ መረጃ የፕላን ልማት ቢሮ ባወጣው መረጃ መሰረት የተሠራ ነው።
ጥናቱ የከተማ አስተዳደሩ ፕላንና ልማት ቢሮ፣ ትምህርት ቢሮ፣ ባለስልጣኑ፣ ፍትህ ቢሮና ንግድ ቢሮ እንዲሁም ሕብረት ሥራ ኮሚሽን በጋራ በመሆን ከትምህርት ቤት ባለቤቶቸ፣ ከወላጆች፣ ከወ.ተ.መ.ሕ ከተውጣጡ አካላት ሀሳብ ተወስዶ ጥናት አድርጓል። በጥናቱ የተገኘው ከፍተኛ ጭማሪ ቢጨመር ተብሎ ደረጃ አራት ትምህር ቤት በከተማ ደረጃ አንድ ትምህርት ቤት ብቻ ተገኝቷል። ስለዚህ እስከ 65 በመቶ ድረስ መጨመር ያስችላል የሚል እውነታነት ያለው ሀሳብ መጥቷል። ከዚህ ባሻገር በትምህርት ርከንና የትምህርት ጥራት ደረጃ አማካይ አድርገን የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኖ ደረጃ ሁለት ከሆነ እስከ 45 በመቶ ድረስ እንዲጨምር፤ ይህም ማለት ከዜሮ ጀምሮ፤ ደረጃ ሶስት ከሆነ እስከ 50 በመቶ፤ ደረጃ አራት እስከ 55 በመቶ ድረስ ነው።
አንደኛ ደረጃ፣ መካከለኛ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእርከንና በትምህርት ጥራት ደረጃ ጥናቱ በዛ ልክ አድጎ ወደ ተግባር እንዲገባ ከባለድርሻ አካት ጋር ውውይት ከተደረገበት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት አገልግሎት ክፍያ አሠራር ሥርዓት ደንብ ቁጥር 194/2017 ለካቢኔ ቀርቦ ጸድቆ ወደ ተግባር ገብቷል።
አዲስ ዘመን፡- ደንቡ በፊት ከነበረው ምን ማስተካከያ አድርጓል? በወላጆችና በትምህርት ቤቱ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር በምን መልኩ ትፈታላችሁ?
አቶ ኢዘዲን፡– ደንቡ ተገቢነት የሌለው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ያልሆነ ጭማሪን ከልክሏል። ይህም ጭማሪው የግድ የሚያስብላቸው ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች አሉ። ይህን መቀበል ደግሞ ሀቅ ነው። ስንቀበል ፍትሃዊ የሆነ መሆን አለበት። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ልቅ የሆነና አላስፈላጊ የሆነ ማለትም እስከ 213 በመቶ የጭማሪ ትምህርት ቤቱን ቀድመው ለማቋቋም ካወጡት ዋጋ በላይ በጭማሪ ለማግኘት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡን በጣም ያሸበረና ያስደነገጠ ነበር። ስለዚህ ይህ ልጓም ሊበጅለት ይገባል ተብሎ በባለድርሻ አካላት ጥናት ተጠንቶ ቀርቦ ጸድቆ ከሁሉም የግል ትምህርት ቤቶችና የወላጅ ተወካዮች ባሉበት ተወያይቶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
አሁን ባለው ደረጃ በዋጋ የጭማሪ ሕዳጉ ላይ አንድ ሺህ 195 ትምህርት ቤቶች ላይ ወላጆች ተወያይተውበታል። ከዜሮ እስከ የትምህርት ጥራት ደረጃና ጣሪያ ድረስ ተፈቅዷል ማለትም ተገድቧል። ይህ ማለት ጭማሪ ካለም እስከዚህ ድረስ ብቻ መሆኑን ለማመላከት ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ከአጠቃላይ የትምህርት አዋጅ ቁጥር 13768/2017 መሰረት በትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን የሕግ ሂደት በመከተል ሕጋዊ ለማድረግ ውክልና በመውሰድ ሕጉን አውጥቶ ወደ ተግባር አስገብቷል። የዋጋ ጭማሪው ላይ ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆች ጋር ውይይትና ክርክር አድርገው ከተማመኑ ትምህርት ቤቱ ያቀረበው እውነትነት ስላለው ተቀባይነት አለው ሊሉ ይችላሉ።
በሌላ መልኩ ለምሳሌ ቅድመ መደበኛ ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች መነሻ ዋጋ እስከ 45 በመቶ ቢሆን 45 በመቶው ይገባኛል ብሎ ሊያቀርብ ይችላል። ወላጆች ‘አይደለም ጭማሪውን 20 በመቶ ማድረግ እንጂ ከዚያ በላይ መጨመርም የለብህም’ በማለት ይከራከሩና እስከ መተማን ድረስ ይደርሳሉ። ከተቻለ ድምጽ በመስጠት በአብላጫው ድምጽ የጸደቀው ወደ ተግባር ይገባል። ስለዚህ በዋጋ ጭማሪው የወላጅ መብትም አለው። በዚህ የውይይት ደረጃ 948 ትምህርት ቤቶች ከወላጅ ጋር የተስማሙ ሲሆን፣ ይህም 79 በመቶ ነው።
247 ወይም 21 በመቶ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ውይይት ቢያደርጉም ትምህርት ቤቱ ባቀረበው የጭማሪ መነሻ ፕሮፖዛልና ወላጆች ባቀረቡት ላይ መግባባት አልቻሉም። ይህ ደግሞ በደንቡ የተሰጠው ሥልጣን ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ነው። ባለሥልጣኑ ሁለቱንም ዝርዝር አይቶ ውሳኔ ያሳለፈበት ወደ ተግባር ይገባል።
በወላጅና በትምህርት ቤቱ መካከል አለመግባት ተፈጥሮ ወደ ባለሥልጣኑ ከመጡ የወላጅ ችግሩ ምንድን ነው የሚለውን እናያለን። በዚህ ውስጥ የምናየው ግን አግባብነት ያልሆነ የወላጆችንም ጥያቄም ጭምር ነው። የኑሮ ወድነት አለ፤ ግን መጨመር የለበትም የሚሉ ወላጆች አሉ። ይህ አባባል ግን ተገቢ አይደለም።
እኛ ማድረግ የምንችለው ለመጨመር ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አለ? የለም? ካለ ምን ያህል ነው? የሚለውን ነገር እናስመርጣለን። ይህን አማራጭ ለወላጆች ያለው ሁኔታ ይህ ነው፤ የትምህርት ቤት አገልግሎት ክፍያ እኛ ለትምህርት ቤት ከፍ ብሎ እንዳይጨምር ነው የገደብነው እንጂ ከፍ ብሎ እንዲጨምር የሰጠነው ፈቃድ የለም።
በትምህርት ጥራት ተደራሽነት ላይ ሚና አላቸው። እነዚህ ተቋማት ከገበያው እንዲወጡ አይፈለግም። እንዲህ ሲባል ደግሞ አለአግባብ የሆነ ጥያቄ እንዳይፈቀድ ተከልክሏል ማለት ነው። የዚህን ሚዛን ማስጠበቅ የመንግሥት ሥራ ነው። የመክፈል አቅማቸውን ገምግመው የመረጠበት ትምህርት ቤት ማስተማር የወላጆቹ ድርሻ ነው።
አንድ ትምህርት የሚዘጋ ከሆነ ደግሞ የትምህርት ዘመኑ ከማለቁ ከሶስት ወር በፊት ማመልከት አለበት፤ ምክንያቱም እዚያ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማረው ተማሪ ትምህርት ቤት ማግኘት አለበት። ከዚህ የተነሳ እኛም መልሰናቸው ለአንድ ዓመት ይቀጥል በሚል አድርገናል፡። ከዚያ በ2018 ዓ.ም ሳይገባደድ አመልክቶ ወደፈለገው ዘርፍ መቀየር ይችላል፡ ያለው አሠራር ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ጭማሪው በትምህርት ቤቶች ደረጃ የተቀመጠ ነው። ነገር ግን ምን ያህሉ ወላጅ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ያውቃል? በወላጅና በትምህርት ቤቱ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ችግሩን ባስልጣኑ እንዴት ይፈታዋል?
አቶ ኢዘዲን፡- የትምህርት ጥራት ደረጃ ባለስልጣኑ በሚሠራው የቁጥጥር ሥራ ነው። ቀድሞ የነበረው ክፍያ እንደተጠበቀ ሆኖ የአገልግሎት ክፍያ ጣሪያው ተግባራዊ ተደርጓል። ይህ ሲባል የሁሉንም ትምህርት ቤት ወጥ ለማድረግ አይደለም። እንዲህ አይነት አሠራር ሊኖር አይችልም። ባለሥልጣኑ የሚያስቀምጠው ጣሪያውን ነው። እስከ ክፍያ ጣሪያው ድረስ ያለው ጭማሪ በወላጅና በትምህርት ቤቶቹ መግባባት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ወደ ትግበራ የሚገባ ነው።
በትምህርት ጥራት ደረጃ መሰረት ከ40 እስከ 65 ድረስ የተባለው ደረጃ ሊጨምሩ የሚችሉት ስንት ናቸው? የሚለውን ጉዳይ ከእጃችን አውጥተናል። ወላጆች እንዲያውቋቸው የትምህርት ቤቱ ለዋጋ መነሻ ውይይት ከመቅረቡ በፊት የትምህርት ቤት ደረጃ ሰርተፊኬት ያሳያሉ። ይህን ሳያሳዩ ወደ ውይይት አይገቡም። ምክንያቱም ቅድመ መደበኛ የሆነ ትምህርት ቤት ደረጃ ሁለት ከሆነ ማቅረብ የሚችለው እስከ 45 በመቶ በሚለው ነው። ደረጃ ሶስት ከሆነ እስከ 50 በመቶ ነው። ስለዚህ ደረጃ ሁለት እያለ ደረጃ ሶስት ነኝ ብሎ እስከ 50 ቢያቀርብ ትክክል አይደለም።
ወላጅ እንዴት ያውቀዋል? ለሚለው ጉዳይ በመጀመሪያ ለዕይታ (ዲስፕሌይ) እንዲቀርብ ይደረጋል። የባለሥልጣኑ አስፈጻሚ ባለሙያዎች በየውይይት መድረኩ ተገኝተው ቃለ ጉባኤና አቴንዳንስ ይዘው የተሟላ ወላጅ ስለመገኘቱ ተረጋግጦ የተነሱ ሀሳቦች ሳይቀሩ ተመዝግበው የትምህርት ቤት የጥራት ደረጃው ለወላጁ ይፋ ተደርጎ ወደ ተግባር ይገባል። ከዚህ ባሻገር ሁሉም ሕብረተሰብ እንዲያውቀው በድረ ገጽና በባለሥልጣኑ የፌስቡክ ገጽ የትምህርት ቤቶች የጥራት ደረጃ የት? ምን? የሚባል ትምህርት ቤት ምን አይነት የጥራት ደረጃ እንዳለው አሳውቀናል።
በዚህ ደረጃ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ፈጥረናል። ስለዚህ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሰረት ስምምነት ላይ የደረሱም፤ ያልደረሱም አሉ። ነገር ግን ደግሞ አላግባብ እየተነሳ ያለው ወደ ውይይት ለምን እገባለው፤ የወሰነውን መክፈል ነው ብለው የተቀመጡ ወላጆች ነበሩ። ይህ ትክክል አልነበረም። ተቋሙ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች በመጠቀም መጥተው እንዲወያዩ ጥሪ ተደርጓል። ባይወያዩ 247 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ወደ ክርክር ባይገቡ ተስማምተው መንግሥት ያቀረበውን ሀሳብ በመውሰድ ወደ ተግባር ይገባ ነበር። እውነታው ይህ ሳይሆን ደንቡ ላይ ለወላጁ የሰጠው ሥልጣን ተጠቅሞ ትክክል አይደለም ብሎ በልዩነት ሀሳብ ወጥተዋል። አተገባበሩንም የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሌላቸውን ግብዓት ከሌሎች በመዋስ ፈቃድ ለማግኘት ይሠራሉ ይባላልና እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ የትምህርት ጥራትን የሚጎዳ በመሆኑ ተቋሙ በስያሜው ልክ እየሠራ ነው?
አቶ ኢዘዲን፡- ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲሠራ አንዳንድ ጉድለቶች እዚያም እዚህም ሊኖሩ ይችላሉ። አላስፈላጊ አሠራር ውስጥ የሚገቡ ትምህርት ቤቶችን ተከታትሎ በጥሰት ሲገኙ ርምጃ ይወሰዳል። በተደረሰበት ልክ ርምጃ እየተወሰደ ነው። ለአብነት መደበኛ ኢንስፔክሽን ተሠርቶ ደረጃ ከተሰጠ በኋላ በሚቀጥለው ጊዜም በሌሎች ባለሙያዎች ድንገተኛ ኢንስፔክሽን ማለትም የናሙና ኢንስፔክሽን ይሠራል።
እውቅና ዕድሳት ከተሰጠ በኋላ ወይም ደግሞ አዲስ እውቅናም ሲሰጥ በሚሰጡ ስታንዳርዶች ላይ የኢንስፔክሽን ሥራ ይሠራል። ለምሳሌ አንድ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ካለው ተማሪ ቁጥር አንጻር 500 ካሬ ሜትር ያስፈልገዋል ብለን ብንወስድ በሚቀጥለው የናሙና ኢንስፔክሽን ትምህርት ቤቱ ሥራ ሲሠራ ቀድሞ የነበረው ካሬ ሜትሩ አይጠብም አይቀንስም። ከቀነሰ የመጀመሪያ ኢንስፔክሽን የሠራው ባለሙያ ላይ ርምጃ እንወስዳለን።
ባለፈው ዓመት ዕውቅና ዕድሳት ለማድረግ ከተሠራላቸው 128 ትምህርት ቤቶች ዝቅተኛ መሥፈርቱን ሳያሟሉ ቀርተዋል። በዚህ ዓመት ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በመደረጉ ምክንያት በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ሥራ ሲሠራ ግን 66 ትምህርት ቤቶች መሥፈርቱን ሳያሟሉ ቀርተዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ወደ ሚፈለገው ደረጃ እየመጡ ነው። ትምህርት ቤቶቹ በአጭር ጊዜ አስተካክለው ወደ ሥራ እንዲገቡና ይቅርታም ለመሥሪያ ቤቱ አስገብተው የጊዜ ገደብ እስከ ሕዳር 30 ቀን ድረስ ተሰጥቷቸው በወቅቱ 90 ገደማ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ዝቅተኛውን መሥፈርት አሟልተዋል።
የኢንስፔክሽን ዋና ዓላማው ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ሳይሆን ማስተካከልና መደገፍ ነው። መጨረሻ ላይ ግን ዝቅተኛ መሥፈርቱን ካላሟሉ ደረጃውን ባልጠበቀ ትምህርት ቤት ጥራት ያለው ትምህርት ሊሰጥ አይችልም። ትውልድም መገንባት ስለማይቻል የመጨረሻ ርምጃ ይወሰዳል።
አዲስ ዘመን፡- የጥራት መመዘኛን ጥሰው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ምን ያህል አስተማሪና ወቅቱን የዋጀ ነው?
አቶ ኢዘዲን፡- ርምጃ የሚወሰደው የትምህርት ዘመኑ ከማለቁ በፊት ከሶስት ወር በፊት በደብዳቤ እንዲያውቁ ይደረጋል። ለአብነት 28 ትምህርት ቤቶች ለ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪ መመዝገብ እንደማይችሉ በደብዳቤ እንዲያውቁ ተደርጓል። በእርግጥ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በጥልቀት ስናይ በተገቢው መንገድ በደንብ አልታየልንም ሶስትና አራት ጊዜ ቢመዘንም አምስት ጊዜ ድረስ መታየት አለብኝ የሚል ቅሬታ አላቸው። መንግሥት ቅሬታቸውን ለማዳመጥ ዝግጁ ነው። ነገር ግን የሚጨምሩትና የሚቀንሱት እስከሌለ ድረስ የሚሻለው ነገር እውቅናቸውን ማንሳት እና ለሕብረተሰቡ ማሳወቅ ነው። ስለዚህ ደረጃቸውን ባልጠበቁ ትምህርት ቤቶች ትውልድ ማስተማር ማባከን ይሆናል።
ትምህርት ቤቶቹ ያላቸው አማራጭ በአዲስ መልክ አደራጅተው ብቁ ግብዓት ፈጥረው የሚፈለገው መስፈርት አሟልተው ከጠየቁ ፈቃድ ሊያሰጣቸው የሚያስችል እድል አለ። ለአብነት ሶስት ትምህርት ቤቶች በዚህ መንገድ ሂደት ላይ ናቸው። ስሙን፣ አደረጃጀቱን፣ ግብዓት አሟልተው የሚቀርቡ ናቸው።
ድንገተኛ ኢንስፔክሽን በማድረግ የሥርዓተ ትምህርት ጥሰት ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ተገኝተዋል። 585 ትምህር ቤቶች ላይ ጥቃቅን ጉዳዮች፤ ነገር ግን ቀላል ግምት የማይሰጣቸው እንደ ጊዜ ማዛባት፤ ያልተፈቀዱ የትምህርት መርጃ መሳሪዎችን ማለትም በትምህርት ካሪኩለሙ ያልገቡ መጽሐፍትን ተጨማሪ አድርጎ መጠቀም የትምህርት ጥራትን የሚያጓድሉ ጉዳዮች ናቸው። ስለዚህ ድንገተኛ ኢንስፔክሽን በማድረግ በተገኙት ላይ ወዲያውኑ እንዲታረሙ አድርገናል።
ከከፍያ ጋር ተያይዞ ወደ 133 ትምህርት ቤቶች ታይተው የ2017 በጀት ዓመት የትምህርት የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓቱ ምንድን ነው? የሚለውን በተባለው መልኩ መሆኑን በጸደቀው አሠራር መሰረት እየሠሩ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ለመፈተሽ ሲሠራ 55 ትምህርት ቤቶች ከተባለው በላይ ጭማሪ እስያስከፈሉ መሆኑን ደርሰናል። በዚህም የተጨመረውን ገንዘብ እንዲመልሱ አደርገናል። አዲሱ ደንብ ግን ይህን ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ያስከፈሉትን መልሰው ተጨማሪ 50 ሺህ ብር ለመንግሥት ገቢ ያደርጋሉ።
አንድ ትምህርት ቤት አስቀድሞ እውቅና ሲወስድ የተመዘነበት ‘ቼክሊስት’ ትናንት አንዱ ባለሙያ፤ ዛሬ ደግሞ ሌላው ባለሙያ ቢሔድም የሚጨምር ወይም የሚቀንስ መስፈርት የለም። እንዲህ ሲባል ተንቀሳቃሽ የሆኑ ግብዓት ሊፈጠሩ ይችላሉ። በዚህ ዓመት በባለስልጣኑ 22 ባለሙያዎች ላይ የእርምት ርምጃ ወስደናል።
ከደረጃ በታች ሆነው የዘጋናቸውን እኛ እናስከፍታለን ብለውን ሲደራደሩ የነበሩትን ባለሙያዎች በዲሲፕሊን ቀጥተናል። ለምሳሌ ሁለት ባለሙያዎችን ደግሞ እስከማሰናበት ደርሰናል። አሁንም ጉዳያቸው እየታዩ ያሉ ባለሙያዎች አሉ። ስለዚህ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትል እያደረገ፣ ኢንስፔክሽን ሱፐርቪዥን እያደረገ ባገኛቸው መረጃዎች ላይ ደግሞ በእራሱም በተቋማቱም ላይ ርምጃ እየወሰደ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ትምህርት ቤቶች በሥርዓት ትምህርት ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ አንዳንዴ ደግሞ ከሥርዓት ትምህርት ውጭ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ይነገራል፤ ለአብነት በመዋዕለ ሕጻናት ደረጃ የሚሰጠው ትምህርት አንደኛ ደረጃ ላይ የሚማሩት አይነት እንደሆነም ከወላጆች ጭምር ይሰማል፤ ይህ ደግሞ ሕጻናቱን የሚያጨናንቅ ነው። ስለሆነም የትምህርት ሥርዓቱን የምትቆጣጠሩት እንዴት ነው?
አቶ ኢዘዲን፡- በ585 ትምህርት ቤቶች ላይ የእርምርት ርምጃ ወስደናል ስንል ቅድመ አንደኛ የተባሉት 216 ናቸው። እነዚህ ላይ የታየው አንዱ ቅድመ አንደኛ ላይ በጭብጡ መሰረት አለማስተማር ነው። እንዲሁም ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ከጭብጦቹ ጋርም አዋሕዶ አለማዘጋጀት፣ የክፍለ ጊዜ ድልድል መቀነስና መጨመር፣ ከሥርዓተ ትምህርት ውጭ ቋንቋን ማስተማር፣ ያልጸደቁ አጋዥ መጽሐፍትን ማስተማር እንዲሁም የትምህርት አይነት መጨመርና መቀነስ የመሳሰሉ ጉዳዮች ታይተዋል። ለዚህም ነው ከ585 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 216 ቅድመ አንደኛ፣ 126ቱ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ 233ቱ ደግሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ፣ ቴክኒክና ሙያዎቹ ላይ ደግሞ 210 በጥቅሉ 585 ትምህርት ቤቶች ላይ የተጠቀሱት ግኝቶች ተገኝተው አስተዳደራዊ የእርምት ርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አልፎ አልፎ በወላጆች በኩል ኢንተርናሽናል ስኩል ተብሎ ስያሜ ይዞ ነገር ግን የኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለስልጣን በሚያደርው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ለኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት አይመጥንም ብሎ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲቀይር አማራጭ ሲሰጠው በመሃል በራሱ ስያሜውን ይዞ እንዳይቀጥል ከእነሱ ጋር በምን መልኩ ተናብባችሁ እየሠራችሁ ነው?
አቶ ኢዘዲን፡- ኢንተርናሽናል ስኩል ተብሎ እውቅና የሚሰጠው በፌዴራል ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን በኩል ነው። ስለዚህ ራሱን የቻለ የአሠራር ሕግ አለው። የግል ትምህርት ቤቶች ላይ የአሠራር ማሕቀፍ ውሥጥ አለ። በሥራዎች ላይ ከባለስልጠኑ ጋር በተገቢው መንገድ በጋራ በሚያገናኙን ጉዳዮች ላይ ተነጋግረን እንሠራለን።
ኢንተርናሽናል ስኩል የተባሉት መስፈርት እንዴት ማሟላት እንዳለባቸው፣ መቼ እንደሚመዘኑ ምን አይነት ክትትል ይደረጋል የሚለው በኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ደረጃ የሚካሄድ ነው። ስለዚህ እነሱን በሚመለከት የክፍያ ሥርዓታቸው፣ የካሪኩለም ጉዳያቸው፣ ሁሉ ነገራቸው በፌዴራል ደረጃ የሚታይ ነው።
በምናደርገው ቁጥጥርና ክትትል አንዳንድ ወጣ ያሉ ትምህርት ቤቶች ወደ ኢንተርናሽናል ስኩልነት ስማቸውን ለማዞር እንቅስቃሴ ላይ ያሉ አሉ።
ድርጊቱ ተገቢ አለመሆኑንና ኢንተርናሽናል ስኩል ማለት ትርጉሙ፣ አስፈላጊነቱና ፋይዳው ሲከፈት በማን ነው? ለማን ነው? መከፈት ያለበት በሚሉት ጉዳዮች በተገቢው መንገድ እንዲያውቁ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመገናኘት እየተነጋገርን ነው። ወደዚያ ለመቀየር የሚያደርጉት እንደ ሽሽት የሚቆጠር ነው። ይህን አይነት እንቅስቃሴ መኖሩን ትምህርት ቢሮ ወስዶ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ጉዳዩ መልክ እንዲይዝ ተደርጓል። ባለሥልጣኑ ግን እየሠራ ያለው እውቅና በሰጣቸው የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አገልግሎቱን ከንክኪ ነጻ የሆነና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን እየተሠራ እንደሆነና በአሁኑ ወቅት ከ99 በመቶ በላይ ሥራው ማለቁን ጠቅሰዋል፤ ይህ ቴክኖሎጂ ወደሥራ የሚገባው መቼ ነው?
አቶ ኢዘዲን፡- በቀጣዩ አዲስ ዓመት ወደሥራ ይገባል። የሰው ኃይሉም ቢሆን ፈተና ተፈትኖ በአዲሰ መልክ ይደራጃል። ተቋሙ ወደሪፎርም ውስጥ እየገባ ነው። የአደረጃጀት ጥናት አልቆ አሁን ጸድቋል። ስለዚህ ሁሉም ባለሙያ በአዲስ መልክ ከላይ እስከ ታች ድረስ እንደገና ተፈትኖ ብቃት ያለው ባለሙያ ወደዚህ ይገባል። በብልሹ አሠራር የገመገምናቸው ባለሙያዎች አሉ፤ እነዚህን ባለሙያዎች ለይተናል። በፈተናው ላይ የማይቀመጡ ይሆናሉ። ይህን አጽድቶ መጓዝ የግድ ይሆናል። የሕግ ማሕቀፉ ተስተካክሏል። ቴክኖሎጂ በሲስተም ውስጥ ገብቷል። በቀጣዩ ዓመት የተሻለ ሥራ እንሠራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በየደረጃው የሙያ ብቃት ምዘና ’ሲኦሲ’ ይመዝናሉ፤ እዚህ ላይ ግን ብዙ ክፍተት አለ ተብሎ ይነገራልና በዚህ ጉዳይ ላይ አሠራራችሁ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ኢዘዲን፡- ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሥራና ክህሎት ቢሮን የሚመለከት ነው። እነርሱ በራሳቸው በኩል ይሠራሉ። ሞጁሎችን መሰረት በማድረግ ሥልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የደረጃ (level) ሰልጣኞችን፣ የአጫጭር ሰልጣኞችን ወይም ሆሲ (Questional standard) የሚባለውን የሚያሟሉ የመወዳደሪያ አቅማቸውን (unity of cpompitency) የሚያረጋግጡት ለብቃት ማረጋገጫው ሁሉም የሚመጡት እኛ ዘንድ ነው።
እንደተባለው የሙያ ብቃት ምዘና ’ሲኦሲ’ አሰጣጡ ከብልሹ አሠራርና ከሌብነት ሙሉ በሙሉ የጸዳ ነው ብሎ በድፍረት መናገር ያስቸግራል። በዚያ ረገድ ለምሳሌ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአጠቃላይ ወደ 38 የሚጠጉ ሱፕርቫይዘሮች፣ መዛኝና ተመዛኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሥርዓት ውጭ ሲሠሩ አግኝተን ርምጃ ወስደንባቸዋል፤ አሰናብተናቸዋልም። ይህ በቂ አይደለም። በጣም ከባዱ ሌብነት ያለበትና አታካች የሆነው ሥራ ይኼኛው ዘርፍ ነው።
ለአብነት እውቅና ያላገኙ በምግብ ሆነ በጸጉር ሙያ አጫጭር ስልጠና የሚሰጡ አሉ። እነርሱንም ተከታትለን 85 የሚሆኑትን አግኝተናል። 25 የሚሆኑትን ወደእውቅና እንዲገቡ አድርገናል። 35ቱ ደግሞ በሒደት ላይ ናቸው። ሌሎቹን ዘግተናል። እነርሱ ዘንድ የሚሰለጥኑ ዜጎች ብራቸውን አውጥተው እየከሰሩ ነው። ነገ እነርሱ ዘንድ ሰልጥነው ወደእኛ ዘንድ ለብቃት ማረጋገጫ ቢመጡ አንቀበልም። እነዚህ ሰዎች ተገድደው “ፎርጂድ” የብቃት ማረጋገጫ (ሲኦሲ) ለማሠራት ይሄዳሉ። ፎርጂድ ሲሠሩ ከዚህ ቀደም ያገኘናቸወና ለሕግም ያቀረብናቸው አሉ።
ኮሌጆች “ፎርጂድ” የብቃት ማረጋገጫ ምዘና (ሲኦሲ) ይሰጣሉ። አንድ ሰው እዚህ ኮሌጅ ተምሬያለሁ ብሎ የትምህርት ማስረጃ እውቅና የሚሰጠው እኛ ዘንድ ስለሆነ ሲመጡ እና ስንፈትሽ “ፎርጂድ” ሆኖ እናገኘዋለን። እሱን መረጃ ተከትለን ስንሔድ እናገኘዋለን፤ “ፎርጅድ” ነውና ለፖሊስም አስተላልፈን እንሰጣለን።
ምዘና በራሱ ከንኪኪ ነጻ ሆኖ እንዲቀጥል የፌዴራልንም እገዛ የሚጠይቅ ነው። ጉዳዩ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል የሚለውን ለማስቀመጥ ነው። በእኛ በኩል በተቻለ መጠን የተሻለ ለማድረግ እየሠራን ነው። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ችግር የለበትም ብለን ምላሽ አንሰጥም።
ማኅበረሰቡ ደግሞ ገንዘብ ካልሰጠን አናልፍም የሚለውን አመለካከት መተው አለበት። እኛ መጠቆሚያ መንገዱን አመቻችተናል። ያንን ተከትሎ ችግር ካለ መጠቆም ይቻላል። እንደዚያ ካልሆነ ሀገራችን ብቃት በሌላቸው አካላት ተጥለቅልቃ በመጨረሻ ሁሉም ተያይዞ ሊወድቅ ይችላል። ስለዚህ ሁሉም የየራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዓመት ምን ያህሉን የትምህርት ማስረጃዎች አረጋገጣችሁ? ከእነዚያ ውስጥ ምን ያህሉ ሐሰተኛ “ፎርጂድ” ተገኘ? ያለፈቃድ ሲያስተምሩ በተደረሰባቸው ኮሌጆች ላይ የተወሰደ ርምጃም ካለ ቢጠቅሱልን?
አቶ ኢዘዲን፡- አስቀድሜ ኮሌጆችን በተመለከተ እውቅና ሳያገኙ የሚያስተምሩ 85 አግኝተናል። ማስረጃ አጣሩልን ብለው የላኩ የ182 ግለሰቦች የትምህርት መረጃ ተጣርቶ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ የሁለት ግለሰበች መረጃ ሐሰተኛ “ፎርጅድ” ሆኖ ተገኝቷል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ኢዘዲን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
በሞገስ ተስፋና አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም