ሰሞኑን የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች ለሶስተኛ ጊዜ በለኮሱት ጦርነት ስጋት ውስጥ ገብተው ሊታይ የሚችል መረበሽ ውስጥ ገብተዋል። ነገሮች ውስብስብ ሆነውባቸዋል። ከቡድኑ በላይ በዚህ ሁኔታ እየታወከ ያለ ሌላ አካልም አለ። እሱም የትግራይ ዲያስፖራ ነው። ይህ ኃይል በዚህ ጦርነት ውስጥ ያለው ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም።
አሸባሪው ትህነግን በፋይናንስም፤ በዲፕሎማሲም፤ በሞራልም የሚደግፍ ኃይል ነው። ይህ ኃይል የቡድኑ የጀርባ አጥንቱ ስለሆነ እንዲከፋው አይፈልግም። ለዚህም ነው መሬት ላይ ምንም ቢፈጠር የቡድኑ አመራሮች በቴሌቪዥን ብቅ እያሉ ድል እየተገኘ እንደሆነ እና ዲያስፖራው ድጋፉን መቀጠል እንዳለበት ጥሪ የሚያቀርቡት።
ዲያስፖራውም በዚህ ተደስቶ አሁንም ዶላር ሰብስቦ ይልካል፤ ሰልፍ ወጥቶ ይንከባለላል ወዘተ…። ሰሞኑን እንደውም በታደሰ ወረደ የሽንፈት መግለጫ በጣም በተደናገጠበት ወቅት ጌታቸው ረዳ እሱን እንዲያስተባብል ተልኮ ነበር። በሰጠው መግለጫ ላይም ይህ መረጋጋት እና ስክነት የጠፋበት ኃይል እንዲረጋጋ ተማጽኗል።
“አሁንም እደጋግመዋለሁ፤ አገር ውስጥ ሆነ ውጭ ያላችሁ፣ አገር ውስጥ ያላችሁ ህዝባችን በደጀንነት እየሰራችሁ ነው ውጭ ያላችሁም እየሰራችሁ ነው። በተለይ ግን ውጭ የምትኖሩ ባሉሽ አሉሽ ተባራሪ ወሬዎች በቀላሉ መረበሽ ብዙ አይጠቅመንም።” ብሏል ጌታቸው። እንዲረጋጋመ የተወሰኑ የውሸት የድል ዜናዎች ለግሶታል።
አንዳንዴ እነ ጌታቸው ለዲያስፖራ ደጋፊያቸው የሚዋሹለት ውሸት በጣም አስደናቂ ቢሆንም ይህ ኃይል ግን አንዴ በጦርነት ሰክሯልና እውነቱን እና ውሸቱን ለመለየት ሲቸገር ይስተዋላል። ለምሳሌ ያህል ሰሞኑን በተደረጉ ጦርነቶች 90ሺ ወታደር ገድለናል ብሎ ጌታቸው ሲናገር ውሸትህን ነው ያለው የለም።
እንዲያውም በቃ እያሸነፍን ነው ብለው ተደስተው ነበር። ጌታቸው ይህ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ገደልን ያለው ወታደር ቁጥር ቢደመር ኢትዮጵያ ካላት ሰራዊት ቁጥር በብዙ እጥፍ የበለጠ እንደሆነ እና ይህን ያህል ሰራዊት መደምሰስ ከተቻለ ጦርነቱ ከብዙ ጊዜ በፊት ያልቅ እንደነበር ማገናዘብ ግን አልተቻላቸውም።
የሆነ ሆኖ ይህ ኃይል አሁን ወደ ቀልቡ እንዲመለስ የሚያደርግ ስራ መስራት ያስፈልጋል። ትግራይ ውስጥ ያለው ህዝብ ጦርነት እንደበቃው እና እየተዋጋ ያለው በግድ ከጀርባው መሳሪያ ተደግኖበት እንደሆነ በጦርነቱ ከተማረኩትም እዚያው ትግራይ ውስጥ ካሉትም በተደጋጋሚ ተሰምቷል።
የመዋጋት ሞራሉም አላማውም አሁን ያለው በአንዳች ተአምር ይህን ጦርነት አሸንፈው ከተጠያቂነት መዳን በሚመኙት የትህነግ መሪዎች እና እውነታቸውን አልቀበልም ብሎ ቀን ከሌሊት በሚዳክረው የትግራይ ዲያስፖራ ውስጥ ብቻ ነው።
የቡድኑን መሪዎችን ጦርነትን እንዲያቆሙ ማሳመን መተንፈስ እንዲያቆሙ የማሳመን ያህል ከባድ ነውና አይሞከርም። ጦርነት የህልውናቸው መሰረት ነው። ዲያስፖራው ግን በምን ምክንያት በዚህ እሳት ላይ ጋዝ ማርከፍከፉ እንዳስደሰተው አይታወቅም። በምንም ምክንያት ቢሆን ግን ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ይህ ጦርነት በቀጠለ ቁጥር ሟቾቹ የእሱ ዘመዶች ናቸውና ነው።
ብዙዎቹ ዲያስፖራዎች (ቴዎድሮስ አድሀኖምን ጨምሮ) ትግራይ ውስጥ ስልክ ስለማይሰራ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ፤ የባንክ ኔትወርክም ስለሌለ ገንዘብ መላክ እንዳልቻሉ እና ቤተሰቦቻቸው በዚህ እየተጎዱ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ዘወር ብለው ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ቡድኑ የሚያሞካሽ እና በርታ የሚል ቅስቀሳ ያደርጋሉ፤ ይህን ለሚያደርጉ ሚዲያዎች ገንዘብ ይለግሳሉ።
በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለሚያሳድሩ የምዕራቡ ፖለቲከኞች መደለያ ገንዘብ ይከፍላሉ። ለትህነግ እና መሰሎቹ መሳሪያ መግዣ ገንዘብ ያዋጣሉ። ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ኢትዮጵያን ሲራገሙ ይውላሉ። ሌላም ሌላም ያደርጋሉ። በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ለመሆን አይቸገሩም። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ሰላም እንደምን ሊመጣ ይችላል?
የትግራይ ዲያስፖራ በዚህ ጦርነት ላይ ጦርነቱን ከማቀጣጠል ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። አሳዛኙ ነገር ደግሞ እነሱ የሚያርከፈክፉት ነዳጅ ያቃጠለው የራሳቸውን ቤት የራሳቸውን የስጋ ዘመዶች ነው። ከመጀመሪያ ጀምሮ ይህ ባይሆን መልካም ነበር። አሁንም ግን አንድ ሌላ እድል ይኖራል። ይህ እድልም ዲያስፖራው ወገንተኝነቱን ከትህነግ አንስቶ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ማድረግ።
ለትግራይ ህዝብ ወገንተኛ ከሆኑ አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ ምን እንደሚፈልግ ያውቃሉ። ያን ካወቁም ተሳትፎቸውን በዚያው ልክ ያስተካክላሉ። የትግራይ ህዝብ ወቅታዊ ፍላጎት ሰላም ነው። ጦርነቱ እንዲቆም፤ መብራት እና ኔትወርክ አገልግሎት እንዲቀጥል፤ መንገዶች እንዲከፈቱ፤ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ፤ ገበሬው ወደ እርሻው እንዲሰማራ ነው ፍላጎቱ። ይህ ፍላጎት ከትህነግ ፍላጎት ጋር ፈጽሞ አይገናኝም።
የአሸባሪው ትህነግ ፍላጎት በማንኛውም መንገድ ከተጠያቂነት መዳን ከተቻለም ስልጣን ይዞ መቀጠል በዋነኝነት ደግሞ እንደ ንጉሳዊ ቤተሰብ እነሱ እና የእነሱ ደቀ መዛሙርት ብቻ እድሜ ልካቸውን የሚመሯት ነጻ አገር ትግራይን ገንጥሎ መመስረት ነው። ይህ የቡድኑ ህልም ከትግራይ ህዝብ ፍላጎት ጋር ፈጽሞ ሊገጥም አይችልም።
ቡድኑ ከተፈጠረበት እለት ጀምሮ የትግራይ ህዝብ ከጦርነት አርፎ አያውቅምና ነው። ያለፉትን 47 አመታት ታሪክ አገናዝበን አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ከአሁን በኋላ የትግራይ ህዝብ በትህነግ አመራር ውስጥ ሆኖ ከሌላ አዲስ ጦርነት ውጭ ሊያገኝ የሚችለው አንዳች በጎ ነገር እንደሌለ ነው።
ስለዚህም ምርጫው ግልጽ ነው። የትግራይ ህዝብ በተለይም የትግራይ ዲያስፖራ ከአሁን በኋላ አሰላለፉን ሊያስተካክል እና እየሰመጠች ካለቸው የአሸባሪው ትህነግ መርከብ ዘልሎ ሊወርድ ይገባል። አሰላለፉን ከትግራይ ህዝብ ጋር አድርጎ ወደ ጦርነት አትማግዱን፤ መሳሪያ አውርዱና ሰላም ስጡን ሊል ይገባል። አልያም ግን አሁንም በዚሁ በያዘው ጦርነቱን የማቀጣጠል እና ቡድኑን የመደገፍ መንገድ ከቀጠለ መጨረሻው የከፋ ሀዘን እንደሚሆን በቅርብ ጊዜ ያያል።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2015 ዓ.ም