በጎነትን ትርጉም ላለው ዓላማ

በጎ ፈቃድ በእኛ ሀገር በይፋ በእድገት በኅብረት ዘመቻ የገጠሩን ሕዝብ ለማስተማር በትምህርት ይጀመር እንጂ ባህሉ ከድሮም ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከትምህርት ባሻገር በየትኛውም መስክ ሲተገበር የነበረ እንደሆነ ነው የሚያመለክቱት። በተለይ በጦር ግንባር መስክ ከሚያሳዩት ጀግንነት በተጨማሪ የራበውን በማብላት፤ የታረዘ በማልበስ የተጠማ በማጠጣት በአጠቃላይ ለተቸገረ ደርሶ በመረዳዳት መንፈስ ኢትዮጵያውያን ለዓለም አርዓያ የሚሆን ታሪክ አላቸው ሁሉ ነው የሚባለው።

ይሄ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የበጎ ፈቃድ ባህል በኢትዮጵያ በእድገት በኅብረት ዘመቻ በትምህርት በይፋ ከወጣ በኋላ በተለይ በክረምት ወራት በጤናው፤ በግብርናው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በኮሪዶር ልማት እና በሌሎች ዘርፎች ያለው አበርክቶ በቋሚነት ተጠናክሮ እስካሁን የቀጠለበት አለ።

በዘንድሮ ክረምት እንደ ሀገር ተግባሩ በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እየተከናወነ ይገኛል። ዜጎች አገልግሎት የሚሰጡባቸው 17 ዘርፎችም ተለይተዋል። በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ያሉ ክልሎች እነዚህኑ የተለዩ መስኮች መሠረት በማድረግ ወደ ተግባር እየገቡ ይገኛሉ።

ለማሳያ ያህል እንደ አማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ላይ ያለውን ብናነሳ የባሕር ዳር የኮሪዶር ልማት እና የጣና ዳር ልማት፤ የገጠር ኮሪዶር፤ ኢትዮ ኮደርስ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ፤ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት የቤት ግንባታ እና እድሳት፤ የማዕድ ማጋራት፤ የአካባቢ ጥበቃ፤ የጤና ሥራዎች፤ የትውልድ ግንባታ፤ የግብርና ልማት ሥራዎች፤ የመሠረተ ልማት ሥራዎች፤ ልዩ ልዩ መሠረታዊ መረጃዎችን ማሰባሰብ፤ የሀብት ማሰባሰብ ሥራዎች ወደ ተግባር ተገብቶ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰጠባቸው ካሉት መካከል ይጠቀሳሉ።

እንደ ክልል በነዚህና በሌሎች በዘንድሮው ክረምት ለማከናወን በተለያዩ መስኮች በሚከናወን የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት 222 ሺ 416 ዜጎች ለማሳተፍ ታስቧል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ273 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን ይሄም በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። በተለይ ወደ ገንዘብ ሲተመን 196 ሚሊዮን ብር እስከ መገመት የሚደርስ ነው። ይሄ የክልሉን የመንግሥት ወጪ ከማዳን አንፃር ሲቃኝ አበርክቶው እጅግ ከፍተኛ ነው።

በዚሁ የዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምቱ ወራት እንደ ሀገርም ቢሆን ለማከናወን የታቀደው ቀላል አይደለም። ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከ34 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንዲሁ እንደሀገር በተለዩ የሥራ መስኮች ይሳተፋሉ ተብሎ ነው የታቀደው። ዜጎቹ የሚሳተፉባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች በመንግሥት እና አቅሙ ባላቸው ባለሀብቶች እንዲሁም በማኅበረሰቡ ያልተሸፈኑ ናቸው። ይሄ በራሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው።

ታዲያ በዚህ እንደ ሀገር ከ34 ሚሊዮን በላይ በሚሳተፉበት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ በአጠቃላይ እንደ ሀገር ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በክረምቱ የዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው ከሚገመቱት ከነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል አቅመ ደካማ አረጋውያን፤ አካል ጉዳተኞች፤ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ እንኳን ለመሆን የተሳነው ምንም ገቢ የሌላቸው፤ በድርቅ፤ በጎርፍ፤ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ፤ ንብረታቸውን ያጡ፤ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይጠቀሳሉ።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎቹ በአጠቃላይ በተለዩ በ14 መስኮች ሲሆን የሚከናወኑት የአረንጓዴ ዐሻራ የዜጎች በጎ ፈቃድ ሥራ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ቀድሞ በመጀመር እየተከናወነ ነው የሚገኘው። የማጠናከሪያ ትምህርትም የበጎ ፈቃድ ሥራ እንዲሁ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ወደ ሥራ እየገባ ያለበት እና እየተከናወነ የሚገኝበት ሁኔታ አለ።

የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ሥራም ወደ ትግበራ የተገባበት ሲሆን በተለይ በዚህ በኩል ቀደም ብለው የስምንተኛ ክፍል ፈተና ወስደው በየቤታቸው ቁጭ ብለው የነበሩ ተማሪዎች እንዲሁም በቅርቡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች በስፋት አሳትፈዋል።

ደም ልገሳ፤ ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረግ፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ እና መገንባት፤ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን መደገፍ፤ ማዕድ ማጋራት፤ አብሮነት እና ሀገር ግንባታን ማጠናከር ዘንድሮ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጥባቸዋል ተብሎ እንደ ሀገር ከተለዩ መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ።

በአጠቃላይም በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁሉም መስኮች ላይ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይታሰባል። እንደ ሀገርም በነዚህ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እና የልማት ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሎም ታቅዷል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎቹ ከኢኮኖሚ ካላቸው አስተዋፅዖ በዘለለ በርካታ ማኅበራዊ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳዎችም አሏቸው። የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አዕምሯዊ እርካታ ይሰጣል። መስጠት ጭንቀትን፤ ድብርትን ወይም ድባቴ ተብሎ የሚታወቀውን ያስወግዳል። ቁጡነትንም ያረግባል። መተሳሰብ እና መረዳዳትን በአጠቃላይ አብሮነትን፤ አንድነትን ማኅበራዊ መስተጋብር ያጠናክራል። ወደ በጎ መንገድ ይመራና የተሳሳተ አስተሳሰብንም ያርቃል።

በአጠቃላይ በክረምትም ሆነ በበጋ የሚከናወን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትን ያጎለብታል። በችግር እና በድንገተኛ ጊዜ፣ በፈተና እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሁሉ በማንኛውም አገልግሎቱን መስጠት የሚፈልግ ዜጋ ሊተገበር የሚገባው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሃገራት ሁለንተናዊ እድገት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው። በመሆኑም ሁላችንም እንደተመቸን በየመስኩ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንስጥ፤ ድህነትንም እንቀንስ አልን!

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You