‹‹የቴክኖሎጂ ዘመን›› የሚባለው የአሁኑ ጊዜ፤ የረቀቀውን ሰው ሠራሽ የልኅቀት ቴክኖሎጂ (Artificial Intelligence) በመጠቀም የሰውን ኑሮ ቀላል ያደረጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኝበት ወቅት ነው። አገራትም መጭውን ጊዜ በማሰብ ቴክኖሎጂን እንደዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በመያዝ ምጣኔ ሀብታቸውን በቴክኖሎጂ የሚታገዝ እንዲሆን ጥረት እያደረጉ ናቸው።
ከአስር ዓመቱ የኢትዮጵያ አገራዊ የልማት እቅድ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (Strategic Pillars) መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ አቅምን በማሳደግ ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል። በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ማድረግ ለሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የላቀ ትኩረት መስጠት አገራዊ የልማት እቅዱን ለማሳካት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ ማበልፀግ ላይ የተሰማሩ በርካታ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ተቋማት (Startup Technology Companies) እየተቋቋሙና ማኅብረሰብ ተኮር የሆኑ የፈጠራ ውጤቶችን ለገበያ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ተቋማት መካከል ግብርናን በማዘመን ላይ አተኩረው የሚሰሩት ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። የተቋማቱ የፈጠራ ውጤቶች ለማኅበረሰባዊ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት ያለሙ ሲሆኑ፣ በረጅም ጊዜ ተግባሮቻቸው አጠቃላይ አገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውን ወደ ዲጂታል አሰራር ያሻግራሉ ተብሎ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው።
እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (Artificial Intelligence)፣ ኔትወርኪንግ (Net working) እና የመረጃ ትንተና (Data Analysis) ያሉ ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን ለማኅበረሰባዊ ችግሮች መፍቻ በማዋል ላይ አተኩሮ የሚሰራው ‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› የተሰኘው የቴክኖሎጂ ድርጅት ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ተቋማት መካከል ይጠቀሳል።
የ‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› ተባባሪ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ጃርሚያ ባይሳ እንደሚናገረው፣ ‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለዓለም እየተዋወቁና ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን (Emerging Technologies) ተጠቅሞ የኅብረተሰቡን ኑሮ ቀላል ለማድረግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያበለጽግና የሚያቀርብ ተቋም ነው። በ2010 ዓ.ም የተመሰተረው ተቋሙ፣ በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ የሚገኙና ወደፊትም ወደ ገበያ ገብተውና ቆይተው ለኅብረተሰብ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ፤ በግብርና፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች አገልግሎት የሚሰጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ አተኩሮ ይሰራል። ቴክኖሎጂዎቹ አንዳንዶቹ ከሌሎች ጋር ተጣምረው የሚሰሩ ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለየብቻቸው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሚደረጉ ናቸው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ የኅብረተሰቡን ችግሮች በእጅጉ የሚያቃልሉና የሚፈቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይፋ አድርጓል። ለአብነት ያህል በግብርናው ዘርፍ ካበለፀጋቸው ፈጠራዎች መካከል የእፅዋትን በሽታ የሚለይ የቴክኖሎጂ ውጤት አንዱ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ የእፅዋት በሽታዎችን ከመለየት በተጨማሪ የተለየውን በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምን መደረግ እንዳለበትም የሚጠቁም ነው። ቴክኖሎጂው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም ማሸነፍ ችሏል።
የእንስሳትን በሽታ መለየት የሚችልና ጤንነታቸውን የሚከታተለው ‹‹ጃርሱማ›› የተሰኘው የፈጠራ ውጤትም የቴክኖሎጂ ተቋሙ የሥራ ውጤት ነው።
የሲቲ ስካን (CT Scan) ምስሎችን ተቀብሎ የኮሮና ቫይረስን መለየት የሚችለው የፈጠራ ውጤት ደግሞ ‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› በጤናው ዘርፍ ካበለፀጋቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ከምስሎቹ ወስዶ በመተንተን አንድ ሰው በኮሮና ቫይረስ መያዙንና አለመያዙን ያሳውቃል። ከዚህ በተጨማሪም የወባ በሽታ አምጭ ትንኝ ዝርያን ለመለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂም ሰርቷል።
‹‹ከ45 በላይ የወባ ትንኝ ዝርያዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል በሽታውን የሚሸከሙት አምስቱ ብቻ ናቸው። ይህን ለመለየት ወደ መስክ በመውጣት ትንኞችን ከመያዝ ጀምሮ በትልልቅ ማሽኖች የተደገፈ የሥራ ሂደትን ማለፍ ይጠይቅ ነበር። የደቦ ቴክኖሎጂ ግን የትልልቅ ማሽኖችን እገዛ ሳይፈልግ በፎቶ ወይም በቪዲዮ ብቻ የትንኞቹን ዝርያ ለመለየት ያስችላል›› በማለት ጃርሚያ ያስረዳል።
ቡና ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸውና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከምታገኝባቸው ምርቶች መካከል ቀዳሚው እንደሆነ ይታወቃል። ለአብነት ያህል በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ካቀረበችው ቡና አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። ኢትዮጵያ በዘርፉ ካላት አቅም አንፃር ከዚህም በላይ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባት ይገለፃል። ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በሚደረገው ጥረት ሊከናወኑ ከሚገባቸው ተግባሮች መካከል የቡና ምርት እንዲቀንስ የሚያደርጉ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር አንዱ ነው።
‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› ለዚህ አይነቱ ችግር መፍትሄ የሚሆን የቴክኖሎጂ ውጤት በማስተዋወቅ የቡናን ምርታማነት ለመጨመር ጥረት እያደረገ ነው። ቴክኖሎጂው በሽታው ስር ሰዶ የቡናውን ምርታማነት ከመጉዳቱ በፊት ለመለየትና ለመቆጣጠር ጥቆማ የሚሰጥ ከመሆኑ በተጨማሪ በሽታውን ለማስቆም የሚያስችሉ ምክሮችንም ይጠቁማል። ይህ ቴክኖሎጂ ከፎቶና ቪዲዮ በሚወሰዱ መረጃዎች በሽታዎቹን የሚጠቁም ሲሆን፤ ሰፋፊ እርሻዎችን በቀላሉ ለመከታተልና ለመቆጣጠርም ያስችላል።
በሌላ በኩል ፈጣንና ውጤታማ በሆነ መልኩ ቡናን እንደየደረጃው በመለየትና በመመደብ ለገበያ የማቅረብ ጉዳይም ለአብዛኛው አርሶ አደር ቀላል የሚባል ስራ አይደለም። ‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› የቴክኖሎጂ ተቋምም ይህን ችግር ታሳቢ ያደረጉ የፈጠራ ውጤቶችን ይፋ አድርጓል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የቡና ደረጃዎችን የሚመድብ ቴክኖሎጂ ነው። ‹‹ቡና ቀዩ /የደረሰ/ና በጣም የደረሰ ፣ ያልደረሰ የሚባሉ ደረጃዎች አሉት። ወደ መፈልፈያ ማሽን የሚሄደው ቀዩ ቡና ብቻ ነው። የቡና ደረጃዎችን በመመደብ በየዓይነታቸው የሚለየው ቴክኖሎጂ ግን ቡናውን ወደ ኮንቴይር በማስገባት የደረሰውን ወደ ማጠቢያ ማሽኑ ይወስዳል፤ ሌሎቹን ደግሞ የደረቁ/የበሰሉ መሆንና አለመሆናቸውን ለይቶ ወደ ሌላ ቦታ ይወስዳቸዋል›› ሲል ያብራራል።
አብዛኞቹ የቡና ገበሬዎች ማሽን እንደሌላቸው የሚናገረው ጃርሚያ፤ ‹‹ገበሬዎቹ ማሽን ስለሌላቸው ቀዩን ቡና በዝቅተኛ ዋጋ ስለሚሸጡት ተጠቃሚ አይሆኑም። ስለሆነም ደቦ ኢንጂነሪንግ ይህን የገበሬዎቹን ችግር ለማቃለል በአነስተኛ ዋጋ የምትገዛ፣ ገበሬዎቹ በቀላሉ መጠቀም የሚችሏትና በፀሐይ ኃይል የምትሰራ ቀላል ማሽን እየሰራ ይገኛል›› በማለት ተቋሙ ለአርሶ አደሮች ችግር መፍትሄ እየፈለገ እንደሆነ ይገልፃል።
ከዚህ በተጨማሪም አትክልቶችን እንደጥራት ደረጃቸው የሚመድብ ማሽንም አስፈላጊ በመሆኑ፣ ‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› አቮካዶ እና ቲማቲም ምርቶችን ጥራት እየለካ የሚመድብና ለቀጣይ አገልግሎት ዝግጁ የሚያደርግ ማሽን ናሙናውን ሰርቶ አጠናቋል።
የአፈር መመርመሪያ መሳሪያ
‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› ያስተዋወቀው ሌላው የፈጠራ ስራ የአፈር መመርመሪያ መሳሪያ ነው። ተቋሙ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች ለሚያመጧቸው የፈጠራ ፕሮጀክቶች ምክረ ሃሳቦችን በመስጠት በአጋርነት ይሰራል። ‹‹ኦሚሽቱ ጆይ›› ከተባለው ተቋም ጋር በትብብር የሰሩት የአፈር መመርመሪያ መሳሪያም የዚሁ አካል ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ከመሬት የአፈር ናሙና በመውሰድ አፈሩ ምን ዓይነት ንጥረ ነገሮችን እንደያዘ፣ ለየትኞቹ ሰብሎችና ተክሎች ተስማሚ እንደሆነና ተጨማሪ ምክረ ሃሳቦችን የያዘ ሲሆን ምርታማነትን በመጨመር ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።
እንደ ጃርሚያ ማብራሪያ፣ የአፈር መመርመሪያ መሳሪያዋ በቀላሉ መንቀሳቀስ የምትችልና በመጠንም ትንሽ ናት። ናሙናውን መለየት የሚያስችሉ ሴንሰሮች (Sensors) አሏት። መሳሪያዋን አፈር ውስጥ በማስገባት የአፈሩን ናሙና በመውሰድ የአፈሩ መረጃ (የአፈሩ ንጥረ ነገር ይዘት፣ የሙቀት መጠን፣ እርጥባማነት …) ወደ ሞባይል መተግበሪያ (Applications) እንዲተላለፍ ይደረጋል። የአፈሩ ዝርዝር መረጃም ይታወቅና ለየትኛው ሰብልና እፅዋት ተስማሚ እንደሆነ ይታወቃል።
በ2013 ዓ.ም የተሰራው ይህ የአፈር መመርመሪያ ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ሽልማትን ያሸነፈ ሲሆን ተጨማሪ ማሻሻያዎች ተደርገውበት በቅርቡ ለገበያ የሚቀርብ ሆኖ እንደሚወጣ ይጠበቃል። መሳሪያው በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በካፊቾ፣ በወላይትኛ እንዲሁም በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ የተሰራ ሲሆን በሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎችም አገልግሎት እንዲሰጥም ተደርጎ እየተሰራ ነው።
የአፈር ምርመራ የሚከናወንባቸው ማዕከላት ውድ የሆኑና በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉ ግዙፍ መሳሪዎች የሚገኙባቸው በመሆናቸው ምርመራውን እጅግ ፈጣን በሆነ ጊዜና በየትኛውም ቦታ ለማከናወን አዳጋች ይሆናል። የ‹‹ደቦ ኢንጂነሪንግ›› እና የ‹‹ኦሚሽቱ ጆይ›› የትብብር ውጤት የሆነው የአፈር መመርመሪያ መሳሪያ በመጠን አነስተኛ እንዲሁም በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል መሆኑ የአፈር ምርመራ ስራውን ቀላልና ቀልጣፋ ያደርገዋል። የአፈር መመርመሪያ መሳሪያው በአንድ አካባቢ ዘር ከመዘራቱ በፊት አፈሩ ለየትኛው የዘር ዓይነት ምቹ እንደሆነ በመለየት የምርት ውጤትን ከፍ ለማድረግ ያግዛል።
የአፈር መመርመሪያ መሳሪያውን ለመስራት የሚያገለግሉ ሴንሰሮችን በቀላሉ ማግኘት አለመቻል የስራው ዋነኛ ፈተና መሆኑን ጃርሚያ ይናገራል። ‹‹ሴንሰሮቹን እንደልብ ማግኘት አይቻልም። ሴንሰሮቹ በውድ ዋጋ የሚገዙ በመሆናቸው መሳሪያው ተሰርቶ ለገበያ ሲቀርብ ዋጋው ውድ ይሆናል። ግብዓቶቹን በቀላሉ ማግኘት ከተቻለ መሳሪያውን በብዛት ለማምረትና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል›› ይላል። ከዚህ በተጨማሪም የፈጠራው ባለቤቶች ውድድሮችን እያካሄዱ ከሚያገኙት ገንዘብ በስተቀር ድጋፍ የሚያደርግላቸው ሁነኛ አካል እንደሌለም ጃርሚያ ይገልፃል።
እንዲህ አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች መንግስት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ለያዛቸው ስራዎች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፤ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር መሰል ስራዎችን የሚደግፉበት አግባብ ስለመኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ አኳያም በቅርቡ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የእውቅናና ሽልማት መርሀ ግብር ተካሂዷል። ሚኒስቴሩ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ለስራ እድል ፈጠራ ወሳኝ መሆናቸውን ያምናል።
ደቦ ኢንጂነሪግም ሆነ በሌሎች ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ የሚሰሩ አካላትም ከሚኒስቴሩና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ለመስራት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሆነ ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚሰሩ መንግስታዊም ሆኑ ያልሆኑ ተቋማት በፈጠራ ስራ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችን ፈልገው በመደገፍ የፈጠራ ስራዎች ዜጎችንም አገርንም ተጠቃሚ ማድረግ፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን የመገንባቱን ጥረትም ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2015 ዓ.ም