እርግጥ ነው በችግር ተተብትበናል። «ሳይቸግር የጤፍ ብድር» እንዲሉ ራሳችን በራሳችን፤ እርስ በእርሳችን እየተበላላን ነው። አስታራቂው ጠፍቶ፣ የእብድ ገላጋዩ በዝቶ «እነሆ …» እንደ ተባለው እነሆ ከጦርነት ወደ ጦርነት እየተሸጋገርን፤ ዙር እየቆጠርን … በለው … በለው … እየተባባልን እንገኛለን። «ወንድም በወንድሙ ላይ …» የተባለውን ቀድመን ተግባራዊ ለማድረግ ሸብ ረብ ላይ ነን። ይሁን እንጂ … በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ብርሃን አለ።
«የዘሬን ብተው ይዘርዝረኝ »… እንዳለችው ሴትዮ ልክ ነው ብለን የተነሳንበትን ያረጀም ይሁን ያፈጀ ሀሳብ አውርዶ መጣል እንደ’ኛ የሚከብደው የዓለም ክፍል ያለ አይመስለኝም። ትናንትም፣ ዛሬም …. እዛው … ከትናንትና ወዲያ የነበርንበት ቦታ ነው ያለነው። እሚያስፈራው እሱ አይደለም፤
እሚያስፈራው ነገም እዛው ከትናንት በስቲያ እነበርንበት ቦታ ላይ እንዳንሆን ነው። እሚያስፈራው ተነገ ወዲያም ከትናንት ወዲያን አልፈን እዛኛው «ወዲያ» ላይ ሆነን በብሔር እንዳንደራጅ ነው። ተደራጅተንም እንደ ገና «በለው …»፣ «በለው …» እንዳንባባል ነው። ያኔ ዓለም ጭራሹን ጥሎን እብስ ይላልና – ግልግል ነው።
የዚህ ጽሑፍ አላማ ባለንበት ጭለማ ውስጥ ብርሃንም መኖሩን መግለፅ ነው። መግለጽ ብቻም ሳይሆን ከተቻለ ማሳየትም ይሆናል። የዚህ መነሻው ደግሞ ያለንበት ጭለማ ብርሃኑን እንዳናይ፤ አይተንም እንዳናጣጥም እያደረገን መሆኑ እየታየ ስለሆነ ነው። በመሆኑም ነው (ተስፋ ያለን መሆናችንን ለመጠቆም ያህል) ርዕሳችንን «የተጋረዱብን ሰሞነኛ ስኬቶች» በማለት ሰይመን ወደ «ሥራ» የገባነው። ከቡና እንጀምር።
ሰሞኑን ዓለም «ኢትዮጵያ …»፣ «ኢትዮጵያ …» እንዲል ካስገደዱት አንዱ ሁሉ ነገሩ ኢትዮጵያዊ የሆነው ቡናችን ነው። በዓለም ገበያ ላይ ምርጥ (single origin premium coffee beans ይሉታል) በሚል የሚታወቀው ቡናችን ሰሞኑን ከርዕሰ ዜና፣ ርዕሰ አንቀፅ … ጀምሮ የሚዲያዎቹን ሙሉ ቀልብ ተቆጣጥሯል። እኛ አስቀድመን የኢኮኖሚ ዋልታችን ቡና መሆኑን አምነን እንደዘመርነው፤ እነሱም በራሳቸው መንገድ ንጉሥነቱን አምነው በመዘመር ላይ ናቸው።
እያልን ያለነው፣ «የኢትዮጵያ ቡና» (ኢትዮጵያን ኮፊ) ነገር የፊት ገፅ ቦታን እንደያዘ እዛው ሲሆን፤ እስካሁን ወደ ውስጥ ገፆች ስለመግባቱ ምንም ፍንጭ የለም። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ሰሞኑን የብራዚል ቡና በውርጭ በመመታቱ ምክንያት ከጥቅም ውጪ ሆነ። በመሆኑም የዓለም ገበያ በቡና ድርቅ ተመታ። ለዚህ ድርቅ መፍትሄ ሆኖ የተገኘው ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና ነው። በመሆኑም፤ በፍፁም ለማመን በሚያስቸግር ደረጃ አንድ ኪሎ የኢትዮጵያ ቡና 881.10 (ዶላር) ላይ ሄዶ ቁብ አለ።
መች ይሄ ብቻ፣ አፍታም ሳይቆይ 884.50 (ዶላር) ከኢትዮጵያ ቡና አድናቂዎችና ሱሰኞች (አሜሪካ ከሁሉም በላይ ተጠቃሚ ነች)፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ እና አውስትራሊያ – እነዚህ በከፍተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ቡና ተጠቃሚዎች ናቸው) እጅ እየተቀበለ ነው። በዚህ ምክንያት የሰሞኑ የዓለም ሕዝብ የጋራ መዝሙር «የኢትዮጵያ ቡና …» ሆኗል። ይህ እንግዲህ አንዱና ያለንበት የእርስ በርስ ጦርነት እንዳናየው የጋረደን እውነታ ነው።
ሌላው የስንዴ ምርታችንን የተመለከተው ጉዳይ ነው፤ ዜናውም ”Despite an ongoing civil war and a record drought, Ethiopia’s wheat production is expected to jump 70% this year as it seeks to reduce reliance on food imports.” ይለናል – በዚህ ሁሉ የእርስ በርስ ጦርነት መሀል በዘንድሮው አመት የስንዴ ምርታችን ተስፈንጥሮ ከ70 በመቶ በላይ እድገትን እንደሚያመጣ ሲነግረን። ዜናው ይህ የስንዴ ምርት ኢትዮጵያን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተረጂነት እንደሚያላቅቃትም ያትታል።
www.icarda.org ድረ-ገጽ ዜናም “ The TAAT [Technologies for African Agricultural Transformation] project sets the country firmly on the path to achieving wheat production self-sufficiency by 2025” በማለት በ2025 ኢትዮጵያ ስንዴ ተረጂነትን ቻው እንደምትል ብቻ ሳይሆን ለሌላውም እንደምትተርፍ ከወዲሁ ተናግሯል። ሌላስ?
ሌላው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛው የውሃ ሙሌት መጠናቀቅና ኃይል ማምረት መጀመሩ ነው፤ ይህም የኢትዮጵያን የወደፊት ተጠቃሚነት፤ እንዲሁም፣ የአፍሪካ የኃይል ምንጭ በመሆን አህጉሩን እንደምታስተሳስር እየተሰራጨ ያለው ዜና ዘገባ ነው።
ሁሉም በሚባል ደረጃ ህዳሴውን በተመለከተ እያስተጋቡ ያሉት ድምፅ ተመሳሳይ ነው፤ እሱም የኢትዮጵያ ግድቡን የመገንባት ውሳኔ ትክክል መሆኑንና የወደፊት ተጠቃሚነቷን ከወዲሁ የሚያረጋግጥ ነው የሚል ነው።
ሌላው የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ቤት ገብተው እንዲሠሩ የመፍቀዷ ጉዳይ ነው፤ ይህ በሁለት መልኩ እየታየ የሚገኝ ይሁን እንጂ አብዛኛው የአስተያየት ሰጪዎች አስተያየት የመንግሥት ውሳኔ (መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ እንዳለ ሆኖ) ትክክለኛ መሆኑ ላይ ያሰመረ ነው።
ሌላው በቴሌኮሚዩኒኬሽኑ ዘርፍ ያለው ሁኔታ ሲሆን፤ የሳፋሪና ህዋዌ ኩባንያዎች፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ያለው ዓለም አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉባኤ የኢትዮጵያ ጉዳይ የበርካታ ዓለም አቀፍ (በተለይም የቢዝነስ) ሚዲያዎች ሰሞንኛ ርዕሰ ጉዳይ በመሆን እየሄደ ያለ «ስቶሪ» ነው።
በውጭ ግንኙነት በኩልም እንዲሁ የስኬት ዜናዎች በብዛት እየሄዱ ያሉበት ሁኔታ ያለ ሲሆን፤ አንዱና ብዙዎችን ያነጋገረው የኢትዮ-ፈረንሳይ ግንኙነትና የፈረንሳይ የሀይድሮ ኃይል መቆጣጠሪያ ተቋም (ደብረ ዘይት አካባቢ) መገንባት የሚያስችል የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ነው።
ፈረንሳይ እስከ ዛሬ ከአፍሪካ ጋር የነበራትን ግንኙነት በማደስ፤ ሙሉ ለሙሉም ወደ «አብሮ በመሥራት አብሮ ማደግ» መለወጧ ነው። ሩሲያ ለኢትዮጵያ 162 ሚሊዮን ዶላር ብድር መሰረዟም እዚሁ ጋ ሊጠቀስ የሚችል ነው።
ሌሎችም በርካታ ዓለምንም እያነጋገሩ ያሉ ስኬቶች አሉ። ባለንበት የጨለማው ዘመን ተግባርና ወቅታዊ ሁኔታ የራሳችንን ስኬቶች ራሳችን እንኳን መገንዘብ አልቻልንም። 2015 ዓ.ም ከዚህ ያወጣናል የሚል የብዙዎች እምነት አለና ኃላፊነትን ከመወጣት ጋር «ወደ ላይ …» በሚለው መሠረት ለዛሬ እዚህ ላይ እናቆማለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2015 ዓ.ም