«ሰሊጥ ምርት ላይ እሴት መጨመር ሽፋኑን በመግፈፍና በመቁላት ለምግብ የሚውለውን ክፍል ማሸግ ነው።ይሁን እንጂ አሁን በስፋት እየተላከ ያለውና በስፋት የሚሰራው ግን ምርቶቹን በጥሬ መላክ ነው» ያሉን የአምባሰል የንግድ ሥራዎች ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ መካሻ ናቸው፡፡
አቶ አዲስ እንደሚያስረዱት፤ በብዛት እየተላከ ያለው የተበጠረ ጥሬ ሰሊጥ በመሆኑ የገበያ ውድድሩ ከፍተኛ ነው፡፡ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና፣ ቅመማ ቅመም የውጭ ንግዱ ላይ ያለው ሥራ ተመሳሳይ ስለሆነ ገበያ ማስፋት ሳይሆን መቀራመቱ ላይ ትኩረት የተደረገው፡፡ የገበያ ውድድሩን ትርጉም ያለው ለማድረግ እሴት መጨመር የተሻለ ዕድል ይፈጥራል፡፡አሁን ሁሉም ላኪ በጥሬ ስለሚልክ በንግዱ ውጤታማ ለመሆን ወደ ሌላ አማራጭ መቀየር አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
«እሴት መጨመሩ ላይ ደፍሮ የሚገባ የለም» የሚሉት አቶ አዲስ፤ ከገበያ አማራጭ ማስፋትና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር እሴት መጨመሩ የተሻለ አዋጭ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እሴት መጨመር መጀመሪያ ላይ ጥቅም ባይገኝበትም በረጅም ጊዜ ግን ትርፍ ማግኘት የሚቻልበት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እሴት ጨምሮ መሸጥ ጥቅም እንዳለው አቶ አዲስ ቢያምኑም ሥራው ሲሰራ ጎን ለጎን ችግሮች መኖራቸውን ያነሳሉ። « እሴት ጨምሮ ለመላክ ምቹ ሁኔታዎች የሉም፡፡ የቅባት እህል የአገር ውስጥ ገበያ ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ በዓለም ገበያ ዋጋው ሳይጨምር የአገር ውስጥ ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ የዋጋ ውድነቱ ለዓለም ገበያ በበቂና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳያቀርቡ ያግዳል፡፡ በአገር ውስጥ ገበያ ዋጋ የተረጋጋ እንዲሆን ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው፡፡
አብዛኛው የውጭ ዜጎች ከአፍሪካውያን እሴት ተጨምሮ ለምግብነት ለገበያ የቀረበን ነገር ደፍረው ለመግዛት አያምኑም፡፡ ይህ ከረጅም ጊዜ ቆይታ ገበያ ለማላመድ ከሌሎች አገራት ድርጅቶች ጋር በገበያ ማፈላለግ ላይ በሸሪክነት በመስራት ሊቀረፍ ይቻላል»፡፡ የቅባት እህሎች እሴት መጨመሩን ድርጅታቸው በመስራት ገበያ ማፈላለጉን ደግሞ የእስራኤል ድርጅቶች እንዲሰሩ እየተነጋገሩ መሆኑን ይናገራሉ።
የዛብሎን ትሬዲንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በደዌ መንግሥት የወጪ ንግድ ከቀረጥ ነፃ ዕቃዎች እንዲገባ፣ በአነስተኛ ወለድ ከባንክ ብድር እንዲሰጥ ብሄራዊ ባንክ መፍቀዱና ያለምንም ታክስ ምርቶቹን ወደ ውጭ መላክ መቻሉ አበረታች መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የግብዓት አቅርቦት በሌለበት እሴት መጨመር ላይ መሸጋገሩ አዋጭ አለመሆኑ እንደ ስጋት ያነሳሉ፡፡ የአገር ውስጥ ምርት ከቦታ ቦታ የሚዘዋወርበት የትራስፖርት እና የጉምሩክ አሰራሮች የተወሳሰበ በሆነበት አገር እሴት ጨምሮ መላክ ላይ መሰማራት ከባድ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ እሴት ወደ መጨመር ከመሸጋገር በፊት አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን መስራቱ መቅደም አለበት ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሀይሌ በርኼ በበኩላቸው ለላኪዎችም ለአገርም ትርፍ ጠቃሚው እሴት ጨምሮ መላክ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ የኢትዮጵያን ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ መላክ ቀላል መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ህንድ የነጭ ሰሊጥ ምርቷ ከ200ሺ ቶን አይበልጥም፡፡ ነገር ግን ያላቸውንም አነስተኛ ምርት ሙሉ በሙሉ እሴት ጨምረው ነው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት›› በማለት የኢትዮጵያ ላኪዎችም እሴት ወደመጨመር መሸጋገር እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
‹‹በዓለም አንደኛና ተፈላጊ ሰሊጥ የኢትዮጵያ ነው፡፡ በምርትና በማጓጓዝ ላይ የሚታየው የጥራት መጓደልን ዕሴት በመጨመር ማስቀረት ይቻላል›› የሚሉት አቶ ኃይሌ፤ እሴት ለመጨመር በርካታ አበረታች ዕድሎች እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡ አሁን ባለው ገበያ እሴት ጨምሮ መሸጥ በአንድ ቶን እስከ 300 ዶላር ተጨማሪ ትርፍ እንደሚያስገኝ በመጠቆም፤ ላኪዎች ዕሴት ጨምሮ ወደመላክ ለመሸጋገር ማቀድ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
165 አስመጪና ላኪ ድርጅቶች በጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም የውጭ ገበያ አቅራቢነት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ሁሉም ምርቶቹን የሚልኩት በጥሬ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ሁለት ድርጅቶች ብቻ ምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር በመላክ ላደረጉት ሙከራ እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፣ አምባሰል ንግድ ሥራዎች አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር እና አንለይ ዓለሙ አስመጪና ላኪ 62 ሺ ዶላር ገቢ አስገኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ንግድ 24 በመቶ ድርሻ በመያዝ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ከቡና በመቀጠል ሁለተኛ ድርሻ ይይዛል፡፡ ምርቶቹን ከቤት ፍጆታና ከአገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ለውጭ የምታቀርበው ኢትዮጵያ የውጭ ገበያው እንዲደራላት መሰራት አለባቸው የሚባሉ የቤት ሥራዎች አሁንም ሊዘነጉ እንደማይገባ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይመክራል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2018
በሰላማዊት ንጉሴ