ዓለም በቴክኖሎጂው ዘርፍ እጅግ የረቀቀና የዘመነ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሉአላዊነት የፈጠረው ትስስር ቴክኖሎጂ በፍጥነት እንዲያድግና ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች የደጃፋችን ያህል እንደቀረቡን እንዲሰማን እያደረገ ይገኛል። ምድራችንን ይፈትኑ የነበሩ ውስብስብ ችግሮች አሁን በቴክኖሎጂ አስደናቂ የፈጠራ ውጤቶች መፍትሄ እያገኙ ነው።
አገራት የንግድ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎች መሰል ትስስሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ (በይነ መረብ) ያደርጋሉ። ይህም ጊዜና ጉልበት ብክነትን፣ ከፍተኛ ወጪንና የተዛባ አሰራርን ከማስቀረቱም በላይ ደህንነትንና አስተማማኝነትን እያረጋገጠም ነው።
ከዚሁ የቴክኖሎጂ ትስስርና ፈጠራ ጋር ተያይዞ የአብዛኛውን ሰው ትኩረት የሳበው በበይነ መረብና መሰል ቴክኖሎጂ ውጤት የሚተገበረው “የዲጂታል ኢኮኖሚ” አገራት እርስ በእርስ በዘርፉ እየፈጠሩት ያለው ትስስር ነው።
አሁን የዓለማችን ግዙፉ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው በዲጂታል ኢኮኖሚ መርህ ነው። የአውሮፓ ኮሚሽን ያዋቀረው ቡድን “TAXATION OF THE DIGITAL ECONOMY” በሚል ርእስ ባሰፈረው ፅሁፍ ላይ ዲጂታል ኢኮኖሚ በበይነ መረብ ላይ ለሚፈጸሙ ሁሉም ኢኮኖሚያዊ ግብይቶች አንድ የጋራ ቃል መሆኑን ይገልፃል። ዲጂታል ኢኮኖሚ የድር ኢኮኖሚ ወይም የኢንተርኔት ኢኮኖሚ በመባል እንደሚታወቅውም ያስረዳል። በቴክኖሎጂ መምጣት እና በሉላዊነት ሂደት ቀደምት / ተለምዷዊ ወይም ባህላዊ/ የኢኮኖሚ ስርዓቶች ወደ ዲጂታል መጥተው በአንድ እየተዋሃዱ መሆናቸውን ያመለክታል። በዚህ ምክንያት ዓለም በዚህ ስርዓት ውስጥ በመግባት የኢኮኖሚ ጽንሰ-ሀሳብን የበለጠ መማር እንደሚኖርበት ነው ምክረ ሃሳቡን የሚሰጠው።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ
በአሁኑ ሰዓት በአገራችን የሚገኙ ባንኮች የቀደመውን የአሰራር ስርአት/ ባህል/ በመቀየር በስፋት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ። በተለይ የበይነ መረብ “ኢንተርኔት” ዘመናዊ ስልኮች “ስማትር ፎን” በበርካታ ሚሊዮን የአገራችን ዜጎች ዘንድ ተደራሽ መሆናቸው ለዲጂታል ኢኮኖሚ ዝርጋታው ምቹ አጋጣሚዎች እየተፈጠረ ይገኛል። ከዚህ ውጪ መንግስት የቴሌኮምና የባንክ ሲስተሙን በማቀናጀት እንዲሁም የግል የፋይናንስ ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው ስራቸውን እንዲያቀላጥፉ አመቺ ህጎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ለማስፈን ቁርጠኛነት ማሳየቱ አሁን እየመጣ ላለው “የሳይንስና ቴክኖሎጂ” እድገትና ለውጥ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።
በቅርቡ ደግሞ መንግስት አንድ መረጃ ይፋ አድርጓል። በዚህም በአገር ውስጥ ያለውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እድገት ከማፋጠን ጎን ለጎን ከጎረቤት አገራት ጋር “በዲጂታል ኢኮኖሚ ትስስር” ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ቅንጅት ፕሮጀክትን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችላቸውን ውይይት ማካሄዳቸውን ሰምተናል። ውይይቱ ሶስቱ ሀገራት ወደ ቀጣይ ሂደት ለመግባት ያሉበትን ደረጃ ለመለየት፣ ፍላጎታቸውን ለማወቅ እና ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባ ከሀገራቱ ምን ይጠበቃል በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ቀጠናዊ ፕሮጀክት የአፍሪካ ቀንድ ትስስር ተነሳሽነት እና የመጀመሪያ ምሶሶ የሆነው ቀጣናዊ የመሠረተ ልማት ማሻሻያ አካል ነው።
የፕሮጀክቱ ዋና አላማ በቀጣናው ያለውን የብሮድባንድ መሠረተ ልማት ክፍተትን በመሙላት እና የዲጂታል አገልግሎቶችን ነጻ እንቅስቃሴን በማሳደግ የቀጣናውን ልማት መደገፍ እና የአካባቢውን የዲጂታል ገበያ ትስስር እውን ማድረግ ነው።
ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ ድጋፍ ይደረግለታል፤ በየደረጃው እንደ አገር እና ቀጣናው ደረጃ የሚተገበር ነው። በኢትዮጵያም የሀገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም አካል ሆኖ እንዲተገበር የታቀደ ነው፤ በአገሪቷ ያለውን የብሮድ ባንድ ተደራሽነት እና አገራችን ለአለም አቀፉ የኢንተርኔት መስመር አገናኝ ለሆነው ባህር ጠለቅ የፋይበር ኔትወርክ ያላትን ተደራሽነት አማራጭ ያሰፋዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባ በሀገራቱ መካከል የዲጂታል ገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ የኢትዮጵያን የኢንተርኔት ተደራሽነት ለማስፋት በጅቡቲ በኩል ካለው የኢንተርኔት መውጫ መስመር ተጨማሪ መስመር እንድታገኝ እንደሚያግዛት ይናገራሉ።
“በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ውስጥ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ማዳረስ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው” የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባ ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠን እንደሚያግዝ ይጠቁማሉ።
”ዲጂታል ኢኮኖሚ‘ ምን ማለት ነው?
ዲጂታል ኢኮኖሚ በዋናነት በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እገዛ የሚገነባ ኢኮኖሚ ማለት ነው። ይህም በግለሰቦች፣ በኩባንያዎች፣ በኮምፒተሮችና በበይነ መረብ ግንኙነት ወዘተ መካከል በኢንፎርሜሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ሲ.ቲ.) የታገዙ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን፣ ስርዓቶችን፣ ግብይቶችን እና ግንኙነቶችን ያጠቃልላል። የደመና ማስላት (cloud computing)፣ በይነመረብ ቁሶች (Internet of Things) እና የመረጃ መረብ ደህንነት (Cyber Security) በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑና የዲጂታል ቴክኖሎጂውን የሚደግፉ ናቸው።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ጥቅሞች
ዛሬ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው፣ ከመደበኛ ቢሮዎች፣ ከቤታቸው ወይም አልፎ አልፎ በተለያየ ቦታ ቡና እየጠጡ በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው የሚሰሩበትን ሁኔታ ይፈጥራል። የሚሰሩበት ቦታ ቢቀያየርም በአካል ተገኝተው ከሚሰሩበት ልምድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የበይነ መረብ ግንኙነት ማግኘትን ግን ይጠይቃል። በአለም አቀፍ ደረጃ እያደገ በመጣው ተለዋዋጭና ምናባዊ የበይነ-መረብ ግንኙነት ቀልጣፋ አስተዳደርን ይጠይቃል። ሌላው ቀርቶ በተለያየ ቦታና የጊዜ ልዩነት ለዜጎች መዳረስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን ይፈልጋል።
ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጥቅሞች ውስጥ፡-
የንግድ ሥራ ዕድሎችን ያስፋፋል፡- የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ዲጂታላዜሽን አዳዲስ፣ ትናንሽ ንግዶች እና ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ እድል ይሰጣል። የእነዚህ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎቶች ግዥና ስርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታ እንዲሳተፍ ያበረታታል።
አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል፡- የዲጂታል ኢኮኖሚው ለሥራ አጦች የስራ እድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በበይነ-መረብ ላይ የተመሰረተ ዲጂታል ንግድን ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታ በመፍጠር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል።
ቀልጣፋ አገልግሎት ለህዝብ ለመስጠት ያስችላል። ዓለም አቀፍ የበይነመረብ ሽፋንን ማሳደግና እና ጠንካራ የመረጃ እና የግንኙነት መሠረተ ልማት አውታሮችን መዘርጋት በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ለህዝብ የሚሰጡ አገልግሎቶች ጥራታቸውን ለማሻሻልና ለማቀላጠፍ ይረዳል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ማሳያዎች በኢትዮጵያ
ከዚሁ ከዲጂታል ስርዓት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ አንዳንድ ተቋማት የክፍያ ስርአትን በኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ (ኢ-ኢንቮይስ) ለማድረግ የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው። ይህ ፕሮጀክት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ተቋማት በቅንጅት የሚመሩት ነው። ከሰሞኑም የገቢዎች ሚኒስቴር ባዘጋጀው የኤሌክትሮኒክስ ግብር ክፍያ ስርዓትን ለማስፋፋትና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል።
ከዚህ ውስጥ ዋንኛ ትግበራ ለማከናወን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እና ሶስት ባንኮች በጋራ አገልግሎት ለመስጠት የሶስትዮሽ የስምምነት ፊርማ አካሂደዋል።
በስምምነቱ ላይ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር /ኢመደአ/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ “በኤሌክትሮኒክስ የግብር ክፍያ ስርዓት ደህንነቱ የተጠበቀና ከሳይበር ወንጀል ስጋት የፀዳ እንዲሆን ኢመደአ በትኩረት ሚናውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ ደግሞ ስምምነቱ ሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አካል የሆነውን የዲጂታል ገቢ አስተዳደር ስርዓትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ግልፅ፣ ቀላልና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት፣ የህግ ተገዥነትን ለማሳደግ ብሎም አስተዳደራዊ ወጪን ለመቀነስ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ማስፈለጉን ተናግረዋል። ይህም ስምምነት ሚኒስቴሩ የተፈራረማቸውን ባንኮች ቁጥር ወደ 15 ከፍ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።
ባንኮች በበኩላቸው ግብር ከፋዮች በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የፈፀሙትን ግብር ወደ ሚኒስቴሩ አካውንት በፍጥነት በማስተላለፍ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱ የተቀላጠፈ እንዲሆን ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በስምምነቱ ወቅት በተደረገ ውይይት ላይ አረጋግጠዋል።
ኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት (የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የጀርባ አጥንት)
በኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፉን ለማዘመን በየጊዜው የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታዎች በመንግስትና በግል ተቋማት ጭምር በመልማት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ አማራጮች ቀደም ሲል ይወስድ የነበረውን ጊዜ፣ ገንዘብ፣ እንዲሁም ድካምን እየቀነሱ ተገልጋዩን ከእንግልት እየታደጉት ይገኛሉ። ከሁሉም በላይ በዲጂታል አማራጭ የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶች ጥራትን እንዲሁም የቁጥጥር ስርዓቱን ማቀላጠፍ የቻሉ ናቸው። ዜጎችም ዘመናዊ ኑሮን ለመምራት የሚያስችል ንቃተ ህሊና እንዲኖራቸውና ወደ እነዚህ ስርዓቶች መግባት እንዲችሉ መንገድ ጠራጊ እንደሆኑ ይታሰባል።
ለምሳሌ ያህል በፋይናንስ ቴክኖሎጂው (ፋይንቴክ) ረገድ በባንኮች የተጀመሩ ዲጅታል የክፍያ አማራጮችን ጥሩ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በሞባይል ባንኪንግ በመተግበሪያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በግል ባንኮችና በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት የሚቀርቡ የፋይናንስ መተግበሪያዎች ረጅም ሰልፎችን ከማስቀረታቸውም በላይ ጊዜንና ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚደርስ ብክነትን ማስቀረታቸው ይታመናል። የአገልግሎት ዘርፉን በቴክኖሎጂ የሚደግፉ ሌሎች ዲጂታል አማራጮችም እንዲሁ የዚሁ አካል ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ዲጂታል ሽግግር የሚደግፍ ቀዳሚ ዲጂታል መሰረተ ልማት ስለመሆናቸው የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ይመሰክሩላቸዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ ገንዘብ ሰብሳቢ ተቋማት አሁንም በእጅ አሠራር /ማንዋል/ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ደንበኞቻቸውንም ሒሳብ ለመክፈል በአካል እንዲቀርቡ ይጠይቃሉ። ይህ በሁለቱም በኩል ብዙ ችግሮችን አስከትሏል። ምክንያቱም ሰዎች እስከ አገልግሎት ሰጪዎች ቢሮ ድረስ መሄድ አለባቸው። በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ለፍጆታ፣ ለግብር እና ለሌሎች አገልግሎቶች ሂሳባቸውን ለመክፈል ረጅም ወረፋ ይጠብቃሉ። አንዳንድ ጊዜ የኢንተርኔት ግንኙነት፣ የመብራት መቆራረጥ ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ባሉ ሌሎች ምክንያቶች አገልግሎቱን በብቃት ማግኘት አይችሉም። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) አማካኝነት የሚደረጉ ሙከራዎች አበረታች ውጤቶች እያሳዩ ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2015 ዓ.ም