ሰሞኑን በየማህበራዊ ሚዲያው እየተንከራተተ ያለውን፣ ‘‘የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” (ነሐሴ 8፣ 2014 ዓ.ም መቐለ)ን አነበብኩት። ለምን እንደሆነ አላውቅም፣ ምንም አልተሰማኝም። ምናልባት ይህ አይነቱ አገርና ህዝብን ማእከል ያላደረገ ፖለቲካና እንቅስቃሴውን ስለለመድኩት ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ምናልባትም “ተጨፈጨፉ”፣ “በጅምላ ተቀበሩ”፣ “ኢትዮጵያን ማፍረስ …” እና ሌሎችንም በሰማሁበት ጆሮዬ ይህችን፣ “የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” ላይ የሰፈረችውን ከምንም ስላልቆጠርኳት ይሆን … ግን አሁንም ምንም አልተሰማኝም። ያ ማለት ግን፣ ቢሰማኝም ባይሰማኝም …. መባል ያለበት መባል የለበትም ማለት አይደለም። በመሆኑም ይህንን ሰነድ ተብዬ ሰነድ አስመልክተን መባል ያለበትን ብለን ታሪካዊ ሀላፊነታችንን እንወጣለን።
ሰነዱ ባለ 12 ገፅ ነው። እኔ የተመለከትኩት በፒዲኤፍ የታሰረውን ነው። በመሆኑም በመክፈቻው ከፍቼ ተመለከትኩት። እውነትም ያው ነው። ድሮም የነበረ ድብቅ አመለካከትና ስሜት የታጨቀበት፤ ድሮም የነበረ ምኞት የተንፀባረቀበት፤ ድሮም የነበረ ህልም የተፈታበት (ከተፈታ) … እንጂ ሌላ ሆኖ አላገኝሁትም። አንድም ቦታ 120 ሚሊዮን ቁጥር ያለውን ህዝብ እንደ አንድ ህዝብ ያላየ ሰነድ ነው።
አንድም ቦታ እንደ አገር አስቦ ለህዝብ ጥቅም ሲንቀሳቀስ ያልታየ ሰነድ ነው። አንድም ቦታ ኢትዮጵያን እንደ አገርና ምድር ቆጥሮ ስሟን ሊጠራ ያልደፈረ ሰነድ ነው። ቅርድብ አዳሪ እንጂ አንድም ቦታ ስትራቲጂክ ሆኖ ሊገኝ ያልቻለ ሰነድ ነው። አንድም ቦታ …..። ባጭሩ፣ ስሜት ሰጪ አሃዶች የጎደሉት ብቻ ሳይሆን ጭራሽም የሌሉት ሰነድ ነው። በመሆኑም “ስትራቴጂ” የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ አይመጥነውም።
ሰነዱ ገና ከርእሱ ጀምሮ፣ “የማጠቃለያ …” ማለቱን ተከትሎ እራሱ በራሱ የራሱን ውድቀት ያወጀ ሰነድ ነው። ሰነዱ የህዝብን ልብ ያገናዘበ ሳይሆን የጠመንጃን አፈሙዝ የተማመነ በመሆኑ ወደ ማንም ልብ ውስጥ ሊዘልቅ የቻለ ሰነድ ሆኖ አይደለም። የማንንም ቀልብ ስቦ የማንንም ልብ ሊያሸፍት የሚችል ሰነድ ሆኖ ሊገኝ አልቻለም። ባጭሩ፣ እዛው፣ ለዛው፣ በዛው … የተዘጋጀ ሰነድ ሆኖ ከማለፍ ሊያመልጥ አልቻለም። የተወሰኑትን ከሰነዱ እየቆነጠርን እንያቸው።
“በጦርነት ሂደት ውስጥ የመረጃ ልዕልና ለማግኘት እና በርካታ ሃይሎችን ከጎንህ ለማሰለፍ ከሚያስችሉ ሁኔታዎች አንዱ፣ ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለህ አስመስለህ እራስህን ማቅረብ መሆኑ ሊረሳ አይገባም” ከሚለው መረዳት የሚቻለው አንድ አቢይ ጉዳይ ነው፤ በተለይ የዛሬ አመት አካባቢ ኢትዮጵያ በተለይ በምእራቡ ዓለምና አሜሪካ ሚዲያዎች (ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን … እኔ ሌሎች በርካቶችም) ምን ያህል በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ስትናጥ የነበረ መሆኑን ትንሽ ወደኋላ መለስ ብሎ ማስታወስ ተገቢ መሆኑን ለማየት ይረዳል። ነገሩ እውነትና ንጋት … እንዲሉ ሆኖ እንጂ፤ ምን ያህል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ አጥለቅልቋት፤ ጭራሹንም ጠራርጎ ሊወስዳት እንደ ነበረ ለሁላችንም የተሰወረ አይደለም።
“የሕዝባችን ዘላቂ የሰላም ዋስትና የሚረጋገጠው በይምሰል በቀረበው የዐቢይ የሰላም አማራጭ ሳይሆን፣ በክንዳችን ብቻ መሆኑን በፅኑ እናምናለን” የሚለውና አገርና ህዝብን ወደ ድንጋይ ዘመን (ስቶን ኤጅ) የሚመልሰውን ዓረፍተ ነገር ጠቅሱ ከማለፍ ሌላ ስለ እሱ ምንም ማለት አይቻልም እና እንዝለለው።
ሌላው የሰነዱ አስኳል እና የስትራቴጂው ማእከል/ ኦርቢት “ለትግራይ ሕዝብ ያለው ጭፍን ጥላቻ …፣ ጫፍ የወጣ ጥላቻ …፣ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ….” የሚለው ሲሆን፤ ይህም ምናልባት እንደ አንድ የትግል ስልት (መሳሪያ) ቢያገለግል ከሚል የተሰደረ እንጂ መሬት ላይ ያለ እውነታ አይደለም።
ይህ ፀሐፊ እስከሚያውቀው ድረስ ማንም ወገን፣ ክልልም እንበለው ብሔረሰብ በትግራይ ህዝብ ላይ “ጭፍን ጥላቻ …” ቀርቶ ቅያሜ እንኳን የለውም። “ጭፍን ጥላቻ …” ቢኖር ኖሮ እውነት እስካሁን አለን? እንኖርስ ነበር? በእውነት ገና ለገና ወንዝ ለማያሻግር ፖለቲካ ተብሎ የብሽሽቅ ፖለቲካን ህዝባዊ መልክ ለመስጠት መጣር … በእውነት ያስተዛዝናል።
አገርና ህዝብ ይቀጥላል ሲባል እኮ የቃላት ጨዋታ አይደለም። አለመሆኑን ደግሞ የእነ ሩዋንዳ በዛው አለመቅረት፣ የኤርትራና ኢትዮጵያ እዚህና እዚያ መመላለስ …. ወዘተ በሚገባ ያስተምራልና። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስህተት ውስጥ መግባቱ ተገቢ አይደለም። እንደ ጥሩ “ስትራቴጂ” ተወስዶም ሊፎከርበት አይገባም።
ሌላው ሰነዱ እንደ ስትራተጂክ ሰነድ ሊወሰድ የማይችልበትና ሊወቀስ የሚገባው ከህፃናት መብቶች አኳያ ሲሆን፤ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ በየግንባሩ የሚታዩት፣ ከእነሱ ቁመትና ክብደት የተሸከሙት ክላሽ የሚበልጣቸው ህፃነት መታየታቸው ነው። ከዚህ ሰነድ መረዳት እንደሚቻለው ደግሞ “የትግራይ ወጣቶችን አሁን የሚደረገው ትግል ወደ አዲስ አበባ የመጨረሻ ምዕራፍ ትግላችን እንደሆነ በማሳመን …” የህፃናትና ወጣቶች ወደ ጦር ሜዳ የመሄዱ ጉዳይ የሚቀጥል ይሆናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሌላውና ትልቁ ስህተት ነውና ለ“የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” መውደቅ አቢይ ምክንያት ነው።
ምናልባት ከዚህ “ስትራቴጂክ” የሚባለው ሰነድ ውስጥ ለግንዛቤ ይረዳል ተብሎ ሊታሰብ የሚችለው “በጠላት ላይ ሽብር፣ ፍርሃትና የስነ ልቦና ጫና መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ሽብር የሚያስፋፉ እና በመሀል አገር ያለው ሕዝብ ሳይቀር በመንግሥት አቅም ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር የሚያደርጉ መረጃዎች በአገር ውስጥና በውጭ ሚዲያዎች በሙሉ ማዳረስ ያስፈልጋል። […] ይሄም በፓርቲያችን የፕሮፖጋንዳ ክፍል በሚቀረፁ መልዕክቶችና ይዘቶች የሚመራና በላይኛው አመራሮች ክትትል የሚደረግበት ይሆናል” የሚለው ሲሆን፣ እዚህ ያለነው ምን ያህል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ጠራርጎ ሊወስደን እየተዘጋጀ መሆኑን እንረዳ ዘንድ ማስቻሉ ነው።
ይህንን እድል በመጠቀም መረጃዎችን “ፍሬውን ከገለባው” እንደሚባለው በሚገባ መለየት ይገባናል። “ፋሽስት ዐቢይን ለመበተን፣ ፖለቲካዊ ማህበራዊ ችግሮች ማስቀጠል” የሚለው ንኡስ ርእስም (ርእሱ ብቻ) የሚለው አለና ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን እንደ አንድ የተደገሰለት ድግስ ወስዶ የውስጥ ሰላሙን መጠበቅ ይኖርበታል።
ሌላውና አሳሳቢው ጉዳይ፣ በሰነዱም ላይ በአፅንኦት እንደ ሰፈረው፣ “የሚጠብቀን ረጅምና መራር ትግል …” ነው የሚለው ነው። ይህ በህዝብና አገር ላይ ረጅም የስቃይና የጦርነት ዘመን ዜና ከማወጅ የተለየ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ መስማት የሚፈልገው የጦርነቱን ፍፃሜና የሰላም መስፈንን ዜና ነው። ይህም ሰነዱ እንደ አንድ ስትራቴጂክ ሰነድ ለመውሰድ የሚያስቸግር ሁኔታን የሚፈጥር ነው ።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ሰላም ነው። ፖለቲካዊ ልፊያም ሆነ ብሽሽቅ፤ ንትርክም ሆነ ያልተገራ ስሜት ለህዝቡ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። ከእስካሁኑም ህፃናትና ወጣቶችን አረገፈ እንጂ ጦርነቱ አንዳችም ያስገኘው ፋይዳ የለም። ስለዚህ ጦርነቱ ቆሞ፣ ሁሉም ፊቱን ወደ ልማት አዙሮ “መጣሁ …”፣ “መጣሁ …” እያለ ከሚያስፈራራን ድርቅ የምናመልጥበት እንዲፈጠርልን እንፈልጋለን።
በዚህ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነትም ሆነ “… በክንዳችን ብቻ መሆኑን በፅኑ እናምናለን።” የሚለው በአራዶቹ ቋንቋ “የፋራ …” ነውና ወደ ህሊና መመለስ ያስፈልጋል። ከዚህ በመነሳትም “የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” (ነሃሴ 8፣ 2014 ዓ.ም መቐለ) ሰነድ በዚሁ መልክ ሊከለስ እና ሊቃኝ ይገባል ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2014