በኮሚናል ግንባታ እና በቆሻሻ አወጋገድ ችግር ከአስተዳደር አካላት ጋር መፍትሔ በአጣ ውዝግብ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች

የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ገነት መናፈሻ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) የተፈጠረ ውዝግብን የሚዳስስ ነው።

ውዝግቡ በገነት መናፈሻ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ከህንጻ ቁጥር አንድ እስከ ህንጻ ቁጥር አራት፤ ከህንጻ ቁጥር 28 እስከ ህንጻ ቁጥር 32 ድረስ በሚገኙ ቤቶች የሚኖሩ ነዋሪዎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መካከል ነው።

የገነት መናፈሻ የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ከወጣ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ቤቶቹ ነዋሪዎች በእጣ ሲተላለፉ ባለእድሎች ለጋራ ሥራ ማከናወኛ ኮሚናሎች ጭምር ክፍያ እንዲከፍሉ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ እስከዛሬ ድረስ ኮሚናል ሊገነባላቸው እንዳልቻለ ነዋሪዎቹ ያነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም ‹‹አካባቢው ከፍተኛ የነዋሪዎች ቁጥር ያለበት መሆኑ እየታወቀ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ መካከል ቆሻሻ እንዲከማች በማድረግ ለከፋ የጤና ችግር ዳርጎናል ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን አቤት ብለዋል።

እኛም አንባቢ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ የመልካም አስተዳደር እና የምርመራ ቡድኑ ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች እንደሚከተለው አጠናክሯል።

ከአቤቱታ አቅራቢዎች አንደበት

የገነት መናፈሻ ኮንዶሚኒየም “የፍቅር ይቅደም ፓርስል” ነዋሪ የሆኑት አቶ አበበ ተክሌ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ) በኮንዶሚኒየሙ ውስጥ መኖር ከጀመሩ ስምንት ዓመታት መቆጠሩን ይናገራሉ። በአካባቢው በተለይም በጋራ መኖሪያ ላይ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚከተለው አቅርበዋል።

በገነት መናፈሻ (ጨፌ) ሳይት የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ከህንጻ ቁጥር አንድ እስከ ህንጻ ቁጥር አራት፤ ከህንጻ ቁጥር 28 እስከ ህንጻ ቁጥር 32 ድረስ ያሉ ቤቶች ነዋሪዎች ቤቱን ከተረከቡት ከስምንት ዓመታት በላይ ጊዜ ቢያስቆጥሩም እስካሁን ድረስ ለደስታ ሆነ ለሃዘን መሰባሰቢያ የሚሆን የጋራ መገልገያ ሼድ (የኮሚናል ቤቶች) ግንባታ አልተካሄደላቸውም።

በእያንዳንዱ ህንጻም 120 እና ከዚያ በላይ አባወራ መኖሩን የሚናገሩት አቶ አበበ፤ ችግር በተፈጠረባቸው ህንጻዎች ከ960 በላይ አባወራ እና እማወራዎች መኖራቸውን ይናገራሉ። ይሄንንም ቅሬታ በተደጋጋሚ ለአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር አሳውቀዋል። ነገር ግን የተሰጣቸው ምላሽ አግባብነት ያለው እና ሕግን የተከተለ አለመሆኑን ያስረዳሉ።

ኮሚናሎቹ ሳይት ፕላኑ ላይ ያሉ ናቸው። ይሄንንም ጥያቄ ለማቅረብ በገነት ጨፌ ኮንዶሚኒየም ላይ ያሉ ነዋሪዎች በጠቅላላ ስብስባ አብይ ኮሚቴ መርጠው ነበር። በመሠረቱት አብይ ኮሚቴ አማካኝነት ጥያቄውን ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ተሞክሮም ነበር። ነገር ግን የነዋሪዎችን ጥያቄ ለማደባበሰ እና ጥያቄው ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር በማሰብ በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠው ኮሚቴ እንዲፈርስ መደረጉን ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ በሚገኙ በተለያዩ የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶች ኮሚቴ የሚመረጠው በጠቅላላ ጉባኤ ነው። ኮሚቴው የተለያዩ ኃላፊነቶች ያለው ነው። ይሁን እንጂ አቤቱታ በተነሳበት የመኖሪያ ቤት ሳይት የነዋሪዎችን ጥያቄ ለማዳፈን እና ለመደፍጠጥ በማሰብ ለአራት ህንጻዎች ወይም ለአንድ ‹‹ፓርስል›› አንድ ኮሚቴ እንዲመረጥ ተደርጓል። ይህም አብይ ኮሚቴው አቅም እንዳይኖረው እና እንዲፈርስ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

ሌላው ቅሬታ አቅራቢ ደግሞ አቶ ፈለቀ ውቤ ናቸው። አቶ ፈለቀ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ ነው። እንደ አቶ ፈለቀ ገለጻ፤ እያንዳንዱ የቤት ባለቤት ቤቱን ሲረከብ ለኮሚናል በሚል ገንዘብ ከፍሏል። ክፍያውም ለነዋሪዎቹ የተሰጠውን የመኝታ ቤት ብዛት መሠረት ያደረገ ነው። በዚህም በአካባቢው የሚኖሩ የኮንዶሚኒየም ባለንብረቶች ከስምንት ሺ ብር ጀምሮ ለኮሚናሉ ክፍያ ከፍለዋል።

በጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠው ኮሚቴ ከሳይቱ ባለፈ በወረዳው ለሚከናወኑ ማህበራዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ትልቅ ሚና ሲጫወት የነበረ ነው። ነገር ግን በወረዳው እና በጥቂት ግለሰቦች ምክንያት ኮሚቴው እንዲፈርስ ተደረገ።

ከአምስት ዓመታት ጀምሮ ቅሬታቸውንን ለአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ሲያሳውቁ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ፈለቀ፤ ኤጀንሲውም ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ ለመወሰን ኮሚቴ አዋቅሮ እንደሚልክ ቢነግራቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ጉዳያቸውን የሚመለከት አካል ማጣታቸውን ያስረዳሉ።

በወቅቱ እንደ መፍትሔ ሃሳብ የተያዙ ሶስት አማራጮች ነበሩ የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ ከእነዚህም አማራጮች መካከል በኮሚቴዎቹ ታይቶ ግንባታ እንዲፈቀድ ማድረግ የሚለው አንደኛ ነው። ከሌሎች ብሎኮች ጋር በማጣመር ነዋሪው አገልግሎቱን እንዲያገኝ ማድረግ የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ሲሆን፤ ይህ ካልሆነ ለኮሚናል ግንባታ ነዋሪዎች ያወጡትን ገንዘብ መመለስ የሚለው ሶስተኛ አማራጭ ነበር። ነገር ግን ሁሉም አማራጮች መተግበር አለመቻላቸውን ይናገራሉ።

በአንድ የመኖሪያ ቤት ሳይት ላይ የሚገኝ ነዋሪ ሁሉም የሚጠበቅበትን ከፍሎ እያለ ለግማሹ ኮሚናል ተሰርቶ መስጠት ለግማሹ ደግሞ አለመገንባት ተገቢ አለመሆኑን የሚያስረዱት አቶ ፈለቀ፤ መብታቸው እንዲከበር በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ኮሚናል የሙስና መፈጸሚያ ሆኗል የሚል ምላሽ ከቤቶች አስተዳደር እንደተሰጣቸው ይናገራሉ። ይህም ተገቢ ምላሽ አለመሆኑን እና ኮሚናሉ ተሰርቶ ተገንብቶ ተሰጥቷቸው ማስተዳደር እና በአግባቡ መጠቀም የነዋሪው ድርሻ መሆኑን ይገልጻሉ።

በመኖሪያ ሳይቱ ሳይገነባ የቀረው እና የጎደለው ሁለት ኮሚናል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሁለት ብሎኮችም (ህንጻዎች) ጭምር ናቸው። አሁን ደግሞ ነዋሪዎቹ ኮሚናል የለንም፤ ይገንባልን ብለው ጥያቄ ሲያነሱ ‹‹ቦታው የሌላ ባለይዞታ ነው›› የሚል ምላሽ መሰጠታቸውን ይናገራሉ። እንዴት የአንድ ሳይት መኖሪያ ቤት ይዞታ የሌላ አካል ይዞታ ነው ይባላል የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ ይዞታው የሌላ ነው ከተባለም እንኳን ግቢው ሰፊ ስለሆነ ሌላ ፕላን አውጥተው ወደ ውስጥ ጠጋ ብለው ኮሚናል መገንባት ይችሉ እንደነበር ያስረዳሉ።

ገንዘብ ይመለስ የሚለውም አካሄድ የገንዘቡ ዋጋ በወቅቱ ያለው እና በአሁኑ ሰዓት ያለው አንድ አይደለም። ስለሆነም ‹‹የሚመለከተው አካል ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ብሎ የከፈልንበትን ኮሚናል ይገንባልን›› ሲሉ ጠይቀዋል።

ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች

በዚሁ ሳይት ሌላኛው አብይ ችግር ከቆሻሻ ጋር የተያያዘ ነው። በኮንዶሚኒየሙ ነዋሪ እና የአካባቢው ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ደብሬ ሃብታሙ (ስማቸው የተቀየረ) እንደገለጹት፤ በገነት የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይት ከቆሻሻ ጋር የተገናኘው ችግር ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ማህበራዊ ችግር ዳርጓል።

ቆሻሻው ከኮንዶሚኒየሙ ነዋሪ የሚወጣ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አካባቢዎች ጭምር በከባድ መኪናዎች እየመጣ የሚራገፍ ነው። በጋራ መኖሪያ ቦታው በሚገኝ ቦታ ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ በየቀኑ ይራገፋል። በተለምዶ ‹‹ቆሼ›› እንደሚባለው ቦታ በመኖሪያ ሳይቱ ላይ በተሽከርካሪ ቆሻሻ እየመጣ ይደፋል።

ቀደም ብሎ ይህ ቦታ የሳይቱ ነዋሪዎች ጊዜያዊ የቆሻሻ ማቆያ ብቻ ነበር። አሁን ግን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጣ ቆሻሻ ማራገፊያ ከመሆኑ ባሻገር ቆሻሻው የሚፈጨው እና ‹‹ፕሮሰስ›› የሚደረገው በዚሁ ቦታ ነው። ቆሻሻው በሚፈጭበት ወቅት ሽታው በየአንዳንዱ ቤት እንደሚገባ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ከቆሻሻው የሚወጣውን ሽታ መቋቋም በጣም ከባድ መሆኑንም ያስረዳሉ። ለዚህም ህጻናት ልጆቻቸው በየጊዜው እንደሚታመሙ ይናገራሉ። ችግሩ በጣም የከፋ መሆኑን በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ቢያሳውቁም ተጨባጭ መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ።

ሌላው አቤቱታ አቅራቢ ደግሞ አቶ ጫኔ በላይ ናቸው፤ ስማቸው ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ተቀይሯል። በአካባቢው ስለተቀመጠው የቆሻሻ መጣያ የሚከተለውን ብለዋል። ቆሻሻ መጣያ ቦታው ከፍተኛ የነዋሪ ቁጥር ባለበት የጋራ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ መደረጉ ተገቢ አይደለም ብለው በተደጋጋሚ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አሳውቀዋል።

ክፍለ ከተማውም ለቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሚሆን ተቀያሪ ቦታ እያዘጋጀን ነው በቅርቡ ይነሳል የሚል ምላሽ ቢሰጥም ችግሩ ሳይፈታ ለዓመታት መጠበቃቸውን ያስረዳሉ። እንደ ዜጋ ጤናማ ኑሮ መኖር እንፈልጋለን የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ በዚህ ቆሻሻ መጠያ እና ማጠራቀሚያ ምክንያት ነዋሪው ለተለያዩ የመተንፈሻ ላይ ችግሮች እና በሽታዎች እየተዳረገ መሆኑን አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ምላሽ

የአዲስ ዘመን የምርመራና መልካም አስተዳደር ቡድን የገነት መናፈሻ የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይት ነዋሪዎች ‹‹ገንዘባችንን ከፍለን የኮሚናል ግንባታው አልተፈጸመልንም›› ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ነዋሪዎቹ ለኮሚናል ገንዘብ እንዲከፍሉ ከተደረገ በኋላ ያልተገነባው ለምንድን ነው? በሳይቱ ላይ የሚታየውን ኮሚናል ባለመገንባቱ ኃላፊነት የሚወስደው ማነው? የሚሉትን እና መሰል ጥያቄዎችን ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን

አቅርበን የኮርፖሬሽኑ የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ዓለሙ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ዓለሙ እንደገለጹት፤ ከኮሚናል ጋር በተገናኘ በገነት መናፈሻ ስለተፈጠረው ነገር አያውቁም። ነገር ግን ከኮሚናል ጋር በተያያዘ በገነት መናፈሻ ብቻ ሳይሆን በገላን የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይትም መገንባት የነበረባቸው ነገር ግን የተወሰኑ ኮሚናሎች ተገንብተው የተወሰኑ ደግሞ ያልተገነቡ አሉ።

ስለጉዳዩ እውቅና የለኝም ያሉት አሁን ላይ ጉዳዩ የት ደረሰ የሚለውን እንጂ ስለችግሩ እንደሚያውቁ ይገልጻሉ።

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ በገነት መናፈሻ የጋራ መኖሪያ ቤት የግንባታ ሳይት ቅሬታ የተነሳባቸው ሁለት ኮሚናሎች ሳይገነቡ የቀሩት በሁለት ምክንያቶች ሲሆን አንደኛው እና ዋነኛው በወቅቱ ቦታው ላይ የወሰን ማስከበር ችግር ስለነበረ ነው። ይህ ጉዳይ በሂደት ላይ እያለ እንደ ከተማ አስተዳደር የኮሚናል ግንባታ ይቅር ተባለ፤ በዚያው ኮሚናሎቹ ሳይገነቡ ቀሩ።

ከዚህ ቀደም ጥያቄው ሲቀርብ በአካል ቦታው ላይ ባለሙያዎችን በመላክ በተቋሙ የኮሚናል ግንባታው እንዳልተካሄደ ማረጋገጥ መቻላቸውን እና ለቤት ማስተላለፍ ዘርፍ በካሬ የከፈሉት ገንዘባቸው ተመላሽ እንዲደረግ መመራቱን ተናግረዋል። ነገር ግን የነዋሪዎቹ ጥያቄ ገንዘቡ ይመለስልን የሚል አይደለም። ነዋሪዎቹ የሚያነሱት ጥያቄ ኮሚናል ይገንባልን ወይም እንድንገነባ ፍቃድ ይሰጠን የሚል ነው።

ነገር ግን እንደ ከተማ አስተዳደር የኮሚናል አስፈላጊነትን የቤቶች አስተዳደር ቢሮ በጥናት ለመመለስ እየሠራ በመሆኑ የነዋሪዎች ጥያቄ በይደር መያዙን ‹‹ሆልድ›› መደረጉን አመላክተዋል። አሁን በሚጠናው ጥናት መሠረት ገንዘብ ለከፈሉት ሳይቶች ተቋሙ እንዲገነባላቸው ያልከፈሉ ነዋሪዎች ደግሞ በራሳቸው እንዲገነቡ ፈቃድ ይሰጣቸው የሚል ውሳኔ ሊኖር ይችላል። በመሆኑም ውሳኔውን መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ጥናቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ ግን እንደማያውቁ ገልጸዋል።

ከክፍለ ከተማው ጋር ያላቸው መናበብ ምን እንደሚመስል ለማወቅ ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ በክፍለ ከተሞች ደረጃ መዋቅር እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻቸው አማካኝነት እንደሚገኙ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ኃላፊነት ቤቶቹን ገንብቶ እስከማዋዋል ድረስ ያለው ሂደት ብቻ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ከዚያ በኋላ ያለው የማስተዳደር ኃላፊነት ለቤቶች አስተዳደር የሚተው እና የቤቶች አስተዳደርም በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹም አማካኝነት ቤቶቹ እንደሚያስተዳደር አመላክተዋል።

ነዋሪዎቹ ሳይት ፕላኑ ላይ ሁለት ብሎኮች እና ሁለት ኮሚናሎች መኖራቸውን፤ ነገር ግን ግንባታቸው አለመፈጸሙን ቅሬታ ያነሳሉ። የምርመራ ቡድኑም በቦታው ተገኝቶ የተባሉት ህንጻዎች እና ኮሚናሎች አለመኖራቸውን እንዲሁም ቦታው በሪል ስቴት አልሚዎች መታጠሩን ማረጋገጥ መቻሉን ስንነግራቸው የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል።

እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በገነት መናፈሻ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሳይቶችም አጋጥሟል። በሌሎች ሳይቶችም ሊገነቡ ከታሰቡ የህንጻ ብዛቶች ተቀንሰው የተገነቡ መኖራቸውን ያስረዳሉ። ከገነት መናፈሻ የጋራ መኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ ያልተገነቡት ህንጻች ዋና ምክንያት ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ባጋጠመ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ።

አንድ ፕሮጀክት ሊሠራ ሲታሰብ በጀት ይያዛል። ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ተከፍሎበታል ወይ? የሚለው ነው። በተደጋጋሚ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ስለሚነሱ የአዲስ አበባ ኦዲት ቢሮ ኦዲት አድርጓል። ይሄ የረጅም ጊዜ ታሪክ ነው። ህንጻዎች ሊገነቡበት በነበረው ቦታ ለሪል ስቴት አልሚዎች ተሰጥቷል ስለሚባለው ነገር ግን መረጃው የሌላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

‹‹በወቅቱ ቦታው የኛ ነበር። በወሰን ማስከበር ችግርም ሳይገነባበት ቀርቷል። መንግሥትም ያልተገነቡባቸውን ቦታዎች ለአልሚዎች አስተላልፎት ሊሆን ይችላል። ኮሚናሎቹም በዚሁ ችግር ሳይገነቡ ቀርተዋል›› ብለዋል

ቦታው የእናንተ ከነበረ ቦታችሁን ለማስከበር የምትሄዱበት አግባብ የለም ወይ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ ‹‹ቦታውን የመሬት ልማት አስተላለፈውም እኛ ተጠቀምንበትም ቦታው የመንግሥት ነው። ሁለታችንም የግል ተቋማት አይደለንም። ይሄ ብቻ ሳይሆን ቱሉ ዲምቱ ላይ በቅርቡም ጀሞ ላይ እኛ ልንገነባበት የነበረውን ቦታ ተሸንሽኖ ለጨረታ እንዲወጣ ተደርጓል። የግል ቤት ለነበራቸው የልማት ተነሺዎችም ተሰጥቷል። እኛ የምንጠብቀው የምትክ ቦታ ነው። እኛ እናልማ እንጂ የመሬት ችግርም የለም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከቆሻሻው ጋር በተያያዘ የሰጠው ምላሽ

በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩበት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምድረ ግቢ ውስጥ ቆሻሻ እንዲጠራቀም ፈቃድ እንዴት ተሰጠ? አሠራሩስ ይፈቅዳል ወይ የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሃመድ አህመድ፣ የወረዳው አስተዳደር ከማህበረሰቡ የሚወጣውን ቆሻሻን ለማስወገድ አመች የሆነና ሰፊ ቦታ ይመርጣል። የወረዳው የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት መሬቱን መርጦ ጥያቄ በመያዝ አሠራሩ በሚፈቅደው መንገድ ከክፍለ ከተማው ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ያቀርባል። የአስተዳደሩ መሬት ቢሮ ጥያቄውን አይቶ ተገቢ መሆኑን ሲያምን ምላሽ ይሰጣል። ይህ የአሠራር ሂደቱ ነው።

በክፍለ ከተማው ውስጥ 17 መሰል የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታዎች አሉ። እነዚህ ቦታዎች የሚሰጡት ግን በዘላቂነት ሳይሆን በጊዜያዊነት ነው። ይህ የሚሆነው በተለይ ደረቅ ቆሻሻ በየቦታው እንዳይጣል እና ሥርዓቱን ጠብቆ ወደ ማስወገጃ ቦታ እንዲጓጓዝ ለማስቻል ነው። የሚመረጠው ቦታ ቆሻሻውን ለማንሳት የሚያስችል ሰፊ ሥፍራ እና ምቹ መንገድ ያለበት መሆኑን ታሳቢ ይደረጋል። ይህ ሲሆን የቦታው ስፋት፣ ከመንገድ ጋር ያለው ቅርበት ይታያል።

ቆሻሻ ማስቀመጫ ቦታ ሲፈቀድ ሽታም ስለሚኖር የህብረተሰቡ ጤና ግምት ውስጥ አይገባም ወይ ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፣ ማጠራቀሚያው ሕዝብ ከሚኖርበት አካባቢ ሊሆን ይችላል። ለጤና እክል የሚሆነው እና እንደ ትልቅ ክፍተት የሚታየው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገዳችን ችግር ሲኖርበት ነው።

በገነት መናፈሻ የኮንዶሚኒየም ሳይት ያለው ሥፍራ በትክክል ችግር ያለበት ነው። ቆሻሻው ሽታ እንዳለው፣ የተበታትነ እንደሆነ ታይቷል። በሕጉ መሠረት በሰፈር ውስጥ የሚጠራቀም ቆሻሻ በ24 ሰዓት ውስጥ መነሳት አለበት። ነገር ግን ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ይለያሉ ወይ? ተብሎ ሲታይ ሰፊ ችግር አለ። ደረቅ ቆሻሻ ተብሎ የሚቀመጠው ቆሻሻ ፍሳሽ ያለበት ከሆነ ሽታ መፍጠሩ አይቀርም። ክፍተቱን በተመለከተ አመራሮችን በመጥራት ገምግመናል። በሌላ አካባቢ ላይ እንዲሁ ከቆሻሻ ጋር የተያያዘ ቅሬታ ቀርቧል።

የተሠራው መጋዝን መኪና ስለማያስገባ ቆሻሻ ውጭ ላይ ይደፋል። መኪናም በአግባቡ ስለማይገባ እንዲሁም የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቤቱ መስኮቶች በተገቢው ሁኔታ ስላልተገጠሙ ሽታ አለው። ይህ በተገቢው ሁኔታ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ችግሩን ለማቃለል ቆሻሻውን የሚያነሱትና ወደሚመለከተው የቆሻሻ ቦታ የሚወስዱት ማህበራት በአግባቡ እንዲያነሱ ደብዳቤ እንዲጻፍና እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጊዜ የሚወስድ ነው። ችግሩ እስከሚፈታ ቆሻሻው እዛው ቦታ ውሎ ማደር የለበትም በሚል በጥብቅ ዲስፕሊን ሊመራ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠናል። በተጨማሪም ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖር አሠራሩን ጠብቆ መፍትሔ እንዲበጅለት ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ነዋሪው ቅሬታ ካቀረበ ሁለት ዓመት ሆኖታል፣ ቆሻሻው በሚፈጭበት ጊዜ ሽታው እንደሚያስቸግራቸው እና ለህመምም እየተጋለጡ ነው። በተደጋጋሚ ለቀረበላችሁ ጥያቄ ለምን ምላሽ መስጠት አልቻላችሁም? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ መሃመድ በምላሻቸው፣ ቦታውን በኃላፊነት ከያዝኩ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፣ አንድም ሰው መጥቶ ቅሬታውን አቅርቦልኝ አያውቅም። ቅሬታ መቅረቡን ዛሬ እየሰማሁ ነው።

ችግሩን ለማቃለል በተገቢው መንገድ መሥራት ያስፈልጋል። ዘላቂ መፍትሔ እስከሚሰጠው ድረስ በጊዜያዊነት ቦታውን ማጠርና ቆሻሻው በፍጥነት እንዲነሳ ለማድረግ እንሠራለን። ነገር ግን ነገ ወይም ከነገ ወዲያ እናነሳለን ብለን ቃል አንገባም። ችግሩን እንደ ችግር ይዘን በአሠራር ለመፍታት አስተዳደራዊ ሥራ እየሠራን ነው። ተለዋጭ ቦታዎችን እየፈለግን ነው። ቦታው በአሠራር ጸድቆ ሲመጣ ችግሩ ይፈታል ብለን እናስባለን ብለዋል።

የምርመራና መልካም አስተዳደር ቡድኑ ትዝብት

የገነት መናፈሻ ነዋሪዎች ለቡድናችን አቤቱታውን ሲያቀርቡ የአቤቱታውን እውነታነት ለማረጋገጥ በተደጋጋሚ ወደ ሥፍራው ተጉዘናል። በቦታውም ያየነው ነገር የተባሉት ሁለት ኮሚናሎች እንደሌሉ ለማረጋገጥ ችለናል። በተጨማሪም ሁለት የሳይቱ አካል የሆኑ ህንጻዎች ይገነቡበታል የተባለው ቦታ በሪልስቴት አልሚ መታጠሩን አይተናል። ነዋሪዎቹም ለኮሚናል ግንባታው ገንዘብ ስለመክፈላቸው በሰነዶች ሊያረጋግጡልን ችለዋል።

ከቆሻሻ ጋርም ተያይዞ የቀረበው አቤቱታ ትክክል መሆኑን አረጋግጠናል። በቦታው ከፍተኛ የቆሻሻ ክምችት ከመኖሩም በላይ በከባድ መኪናዎች ጭምር እየተጫነ እየመጣ በቦታው ይጣላል። የቆሻሻ አቀማመጡ እና ክምችቱም ከፍተኛ ሽታ ያለው መሆኑን አረጋግጠናል።

መክሊት ወንድወሰን እና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You