መንግስት ኢትዮጵያ ሰላም፣ እርቅ እና አንድነት ብቻ እንደሚያስፈልጋት በማመን ለሰላም ድርድር ያልከፈለው መስዋዕትነት የለም። ለአገራችን ሰላም፣ ለህዝቡም ደህንነት ሲል ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ለመደራደር ይሁንታ ከማሳየትም በላይ፣ ድርድሩን ያለ ቅድመ ሁኔታ የትም፤ መቼም ለማካሄድ ፈቃደኝነቱንም አስታውቋል።
ይሑንና ሽብርተኛው ቡድን ይሄን የመንግስት የሰላም ጥሪ ከመቀበል ይልቅ በትግራይ ወጣቶች ደም ከንቱ ህልሙን ለማሳካት ለሶስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍቷል። በተግባሩም ለሰላም ደንታ ቢስ ስለመሆኑ በተጨባጭ አሳይቷል። ከሰላም ሳይሆን ከነውጥ ትርፍ ለማትረፍ መነሳቱን በገሃድ አስመስክራል።
አሸባሪው ሕወሓት በደደቢት በርሀ ውስጥ ወድቆ ሲበቅል መልካም ዘር ለመሆን ሳይሆን እኩይ ለመሆን ነበር። በርሀ እኮ ዘር የለውም። በርሀ እኮ መልካም ዘርን አያበቅልም። የበርሀ ተፈጥሮ አስጨናቂነት ነው።
ዛሬም እያራመደ ያለው በደደቢት በርሀ ውስጥ በገባው አገር የማፍረስና የራስ ወዳድነት መንገድ ነው። ይሕ ባይንማ ለአምስት አስርት አመታት ከጦርነት ያልወጣውን የትግራይ ህዝብ ለጦርነት ባልማገደው ነበር።
እንጂማ ከሰላም በቀር፣ ከልማት በቀር፣ ከአንድነት በቀር ምንም የማያሻትን ድሀ አገሩን በጦርነት አረርና በእዬዬ ዋይታ ሲኦል ባላደረጋት ነበር። ቡድኑ አላማው አገር መገንባት ቢሆን ኖሮ ለሀሳቡ እንደ ሰላም የሚያስፈልገው አልነበረም።
አላማው መልካም ነገር ቢሆን ኖሮ እንደ እርቅና፣ እንደ ድርድር የሚጠቅመው አንዳች አይኖርም ነበር። ግን አላማው አገርና ህዝብን መጥቀም ሳይሆን ራሱን መጥቀም ስለሆነ የሰላም አማራጮችን አልተጠቀመባቸውም። እየተዋጋ ያለው ደደቢት በርሀ ውስጥ ለገባለት በመግደል ስልጣን የመያዝ ሱስን እውነት ለማድረግ እንጂ መልካም አላማ ኖሮት እንዳይደለ የተራመደባቸው ሀያ ሰባት አመታት አመላካች ናቸው።
ቡድኑ ከታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጋር ሳይቀር በማበር በአገርና በህዝባችን ላይ ይሄ ነው የማይባል ግፍና በደል ፈፅሟል። በይቅርታ የማይጠራ፣ በእርቅ የማይሽር ምህረት የለሽ ነውር ሰርቷል። ይሑንና መንግስት ለሰላም ዋጋ በመስጠትና ከሰላም የሚገኝን ትርፍ በማስላት ያለፈን በደል ይቅር ብሎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሰላም ድርድር እንቀመጥ ሲል ጠይቋል።
ቡድኑ ህዝባዊና አገራዊ አላማ የሌለው፤ አላማው አገር ማፍረስ፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አንድነትን መስርቶ የህዝቡን ክብር፣ የአገራችንን ሉአላዊነት መሻር በመሆኑ የሰላም ድርድሩን ለመቀበል ውስጡ አልፈቀደለትም።
ቡድኑ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ እንዳለው የአገርኛ ብሂል ገጸ ባህሪ ነው። በህይወቱ አንድም ቀን ለራሱም ሆነ ለሚታገልለት ህዝብ እውነት ሆኖ አያውቅም። “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል እንደሚባለው”አንዱን ምላሱን ለግፍ አንዱን ደግሞ ለተነካሁና ለእዬዬ ሲጠቀም የኖረ ነው። አሁንም በዚህ እውነት ውስጥ የቆመ ነው። እየገረፈ መጮህ ባህሪው ነው። ሳይዋሽ፣ ሳይሰርቅ የኖረበት ጊዜ የለም።
እየገደለ ሞትኩ እንዳለ ነው። እየጎዳ ተጎዳሁ ማለት ይችልበታል። በረጅም የፖለቲካና የስልጣን ዘመኑ እንዴትና በምን መልኩ ስልጣን ላይ እንደቆየ ቢመረመር ከውሸትና ከማስመሰል ሌላ መልስ አናገኝም። ለነገሩ የሕወሓት ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ርዕዮተ አለም ምርምር አይጠይቅም። ማንም ሊረዳው የሚችል ግልጽ የማጭበርበር ፖለቲካ ነው።
ሁሉን ትተን የዚህ ሳምንት ነውሩን ብናስታውስ እንኳን የአለም ምግብ ፕሮግራም ለሰብአዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በመቀሌ ያከማቸውን ነዳጅ ሰርቆ ‹‹አልሰረቅኩም ያበደርኩትን ነዳጅ ነው የወሰድኩት››ሲል አይኑን በጨው አጥቦ አስተባብሏል። እንዴት ነው በጦርነትና በብዙ ጉስቁልና ውስጥ ያለችው ትግራይ ለአለም የተራድኦ ድርጅት ነዳጅ የምታበድረው?
ሕወሓት አይደለም ለሌላው ለራሱም እውነት የሌለው ቡድን ነው። ከአንድ ሰፈር፣ ከአንድ ነገድ፣ በአንድ ጫካ ውስጥ ተሰብስበው የመሰረቱት ለህዝብ ሳይሆን ለራስ፣ ለአገር ሳይሆን ለቡድን፣ ለትውልድ ሳይሆን ለብሄር የተቋቋመ ቡድን ነው። ይሄ ቡድን እውነት ቢኖረው እስካሁን ድረስ በአገርና ህዝብ ላይ ለፈጸማቸው በደሎች ይቅርታ ጠይቆ ወደሰላም ይመለስ ነበር።
ግን አላማው ሰላም ስላልሆነ ሰላምን አይመርጥም‹። አልመረጠምም። የሚፈልጋቸውን እኩይ ነገሮች በድርድር ሳይሆን በውድድር፣ በምክክር ሳይሆን በክርክር የሚያገኝ መስሎት እየገደለ ነው።
አላማውን የሚያሳካው በሰላም ውስጥ ሳይሆን በጦርነት ውስጥ ስለመሰለው በንጹሀን ሞት ለማትረፍ እየሞከረ ነው። የሕወሓትን ትላንትም ሆነ አሁናዊ ማንነት ለማወቅ በአገርና ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ስቃይና ኪሳራ ማየቱ ብቻውን በቂ ነው። የሰላም አማራጮችን ገፍቶ፣ የኢትዮጵያውያንን ስቃይ ችላ ብሎ በገዛ ወገኑ ላይ ጦርነት መክፈቱ ብቻ የቡድኑን አውሬነት በቀላሉ ለመረዳት ያስችላል።
ቡድኑ ትላንትና በመግደል ውስጥ ነበር፤ ዛሬም በመግደል ውስጥ ነው። እጆቹ ከመግደል፣ ልቦናው ከማስጨነቅ አልቦዘነም። አውሮፓና አሜሪካ አስቀድሞ ኢትዮጵያን እንደሁለተኛ አገሩ የተቀበለ ቡድን ነው።
ኢትዮጵያን አገሬ፣ ህዝቡን ወገኔ ብሎ የመጥራት ወኔ የለውም። አይኖረውምም። የትኛውም አገር፣ የትኛውም ጠላት አገራችንን በሕወሓት ልክ አንገት ያስደፋት የለም። ኢትዮጵያ ብትጠፋ ግድ አይሰጠውም።
ሕወሓት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ግድ የሚሰጠው ቡድን ቢሆን ኖሮ ከአንድም ሁለት ጊዜ ለቀረበለት የሰላምና የድርድር አማራጭ ይጠቀም ነበር። ኢትዮጵያውያን ይሄን ቡድን ልንረዳው ይገባል።
ሕወሓት አላማው ጥፋት ብቻ ነው። እያጠፋ ያለውም የጋራ አገራችንን፣ የጋራ ታሪካችንን፣ የጋራ እሴታችንን ነውና በአንድ ላይ ልናወግዘው ይገባል። ትግራውያንም ቢሆኑ ይሄን ቡድን ተደግፈው የሚያተርፉት አንዳች ነገር የለም።
ያለፉት ሀያ ሰባት አመታት በሕወሓት አገዛዝ የትግራይ ህዝብ ምን ሁኔታ ላይ እንደነበር የምናውቀው ሀቅ ነው። የትግራይ ህዝብ ይሄን ቡድን ገፍቶ እስካልጣለና እስካልተቃወመ ድረስ ከሞትና ከጉስቁልና መቼም አይወጣም።
ቡድኑ ጥቂት ርህራሄ እና አዘኔታ ብሎም ሰብአዊነት የሚሰማው ቢኖረው ኖሮ ለትግራይ ህዝብ ሲል ቅድመ ሁኔታዎችን ሳይደረድር የሰላም አማራጩን ተቀብሎ እየሞተና እየተንገላታ ላለው የትግራይ ህዝብ ውለታ መዋል ይችል ነበር። ይሑንና የትግራይ ወጣት ሞትና እንግልት ግድ የማይሰጠው ስለሆነ ከጦርነት አስተሳሰብ አልወጣም።
አንድ ፖለቲከኛ፣ አንድ ቡድን፣ አንድ ጦረኛ እየሞተና እየተዋጋ ያለው በአላማና ለአላማ ከሆነ መጀመሪያ ሊያደርገው የሚገባው ነገር የሰላም አማራጮችን መፈለግና በተገኘው የሰላም አማራጭ ላይ መሳተፍ ነው።
ሕወሓት ግን አይደለም የሰላም አማራጮችን መፈለግ ቀርቶ ከፌደራል መንግስት የሚቀርብለትን የሰላም አማራጮች ጥላሸት እየቀባ መቼም በማያሸንፈው ጦርነት ውስጥ የትግራይ ወጣቶችን መማገድን ነው የተያያዘው። ሰላም የማይፈልግ፣ በሰላም አማራጮች ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ያልሆነ ቡድን ከመግደልና ከማስገደል ባለፈ ምን አላማ ይኖረዋል?
አገር በደም ጥማት ሱስ አትቆምም። አገር በመግደልና በማስገደል አትለማም። ሰላም በጠመንጃ አይመጣም። ሕወሓት ግን በዚህ ዘመኑን ባልዋጀ፣ ለዚህ ትውልድም ሆነ ለዚህ ዘመን በማይመጥን ድሮዋዊ እሳቤ ውስጥ ሆኖ በህዝብ መአበል እኩይ አላማውን እየፈጸመ ነው። የሰላም አማራጮችን እየዘጋ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን እየጣሰ፣ ኢትዮጵያ የምትዋረድበትን ጊዜ እየጠበቀ በደም ጥማት ሱስ በንጹሀን ላይ ሞትን ሲያውጅ ነበር።
ከመግደል ባለፈ ለሰላም የሚሆን ሙጣጭ አቅም በውስጡ የለም። ከዚህ አውሬአዊ ባህሪው በመነሳት ለምን አላማ እንደቆመ፣ በምን አላማ እየገደለና እያስገደለ እንዳለ መረዳት ይቻላል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ለሚሞቱና ለሚገድሉ ነፍሶች ረፍት ይሆን ዘንድ መንግስት የሚሰጠውን የሰላም አማራጭ ችላ ብሎ እንቅፋት የሚፈጥረው ከምን ተነስቶ እንደሆነ መረዳት አይከብደንም።
ሕወሓት መቼም ኢትዮጵያዊ ሆኖ አያውቅም። ለታሪካዊ ጠላቶቻችን አሽከር በመሆን ለአመታት ሰርቷል። ዛሬም እየሰራ ያለው ይሄንኑ ነው። ኢትዮጵያን ማስጎንበስ፣ ህዝቦቿን ማዋረድ ለዘመናት የተካነው የክፋት ሃሳቡ ነው። ከኢትዮጵያ ላይ በዘረፈው ገንዘብ፣ በዘረፈው ጦር መሳሪያ ኢትዮጵያን እየጎዳ ነው።
ይሄ ቡድን እስካልተወገዘ ድረስ፣ ከታሪክ እስካልተሰረዘ ድረስ እኛም ሆንን አገራችን ታማሚ ናት። የሕወሓትን አላማ ተረድተን ስለ አገራችን ስንል ይሄን ቡድን በአንድ ላይ የምንፋለምበት ጊዜ አሁን ነው።
ይሄንን በእውቀት ሳይሆን በስሜት፣ በምክንያት ሳይሆን በራስ ወዳድነት እየገደለና እያስገደለ ያለ ቡድን ለመመከት ኢትዮጵያውያን አንድ መሆን ይጠበቅብናል። የትግራይ እናቶች ወልደው እንዲስሙ፣ ዘርተው እንዲቅሙ ወጣቶችም ከመሞት ወጥተው ከፍ ላለ ቁም ነገር እንዲበቁ ይሄን ነፍሰ በላ ቡድን ከታሪካቸው መፋቅ ይኖርባቸዋል።
ሰላም ቅድመ ሁኔታ የለውም። የሰላም ቅድመ ሁኔታ ተነጋግሮ መግባባት ብቻ ነበር።አሸባሪዎች አላማቸው መግደል ስለሆነ አላማ ካላቸው ቡድኖች የሰላም አማራጮችን መስማት አይፈልጉም። በሕወሓትም የሆነው ይሄ ነው። መንግስት የሰላም አማራጮችን ሲሰጠው ሰበብ በመደርደር፣ ትንኮሳ በመፈጸም፣ ቅድመ ሁኔታዎችን በመዘርዘር የሰላም ጉዞውን ሲያደናቅፍ ነበር።
ብዙዎች ተስፋ የጣሉበት፣ የአገራችን የሰላም ጮራ የፈነጠቀበት የሰላም ድርድር እንኳን የከሸፈው በዚህ ቡድን ነው። ይሄም ቡድኑ ለሰላም ሳይሆን ለመግደልና ለማስገደል ብቻ እንደተፈጠረ የሚያሳይ ሁሉም ሊረዳው የሚችል ባህሪው ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብዙ እዳ እያለበት መንግስት ግን ሰላምን መርጧል። መንግስት ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ዝም ብሎ ሳይሆን ምን ያክል የሰላምን ዋጋና አስፈላጊነት ከማወቅ የመነጨ ነው።
የትም መቼም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰላምም መፈለግ ዝም ብሎ የሚታይ ነገር አይደለም። እውቀትና አስተውሎት የታከለበት የጠለቀ የመሻት ምስጢር ነው፤ ግን አልተጠቀመበትም። እንዲህ አይነት ልቦች፣ እንዲህ አይነት እሳቤዎች ለአገር ከመወገን፣ ለወገን ከመጨነቅ የሚመነጩ ናቸው። መንግስት በዚህ እውነት ላይ ተራምዶ ነው ከሕወሓት ጋር ለድርድር መቀመጥን የመረጠው።
የሕወሓት መራሹ ቡድን ግን መንግስት ያየውን የሰላም እድል ማየት አልቻለም። በሰላምና በመነጋገር ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ገና አልገባውም። መንግስት የጀመረውን የሰላም አማራጭ ጥላሸት መቀባቱም ከሰላም ይልቅ በጦርነት ውስጥ አላማውን ለማሳካት ስለሚመቸው ነው። እንዲሁም ደግሞ ኢትዮጵያን የማፍረስ አላማ ታጥቆ ስለተነሳ ነው። አገሩን የሚወድ ሁሉ ይሄን ቡድን ሊፋለመው ይገባል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2014