የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ለስራው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ሂደት ላይ ተጠምዶ እንደቆየ ነው። ሀገራችን ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንጻር ስራውን ለመጀመር ረጅም ጊዜ ቢወስድበት ብዙም የሚያነጋግር አይሆንም። ከትናንት ወደ ዛሬ የመጡ፣ ከዛሬ ወደ ነገ ለመሄድ የሚያኮቦኩቡ ብዙ ችግሮች አሉብን። እነሱን በአግባቡ ሳናጠራ ሌሎች አጀንዳዎችን እየፈጠርን ነው። ባሳለፍናቸው አንድና ሁለት ወራት ውስጥ ለቁጥር የሚታክቱ ነውጥ ፈጣሪ አጀንዳዎችን ተመልክተናል።
እንደ ሀገር ለሚፈጠር ሁሉ ችግር መፍትሄውም ሕዝብን ያማከለ ውይይት ነው። ሀገራችን አሁን ላለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ከውይይት ሌላ የሚበጃት የለም። ውይይት ሲባል ተጀምሮ የሚቆም ሳይሆን ተግዳሮትን እያለፈ የሚቀጥል ማለት ነው። ባሳለፍነውም ሆነ አሁን ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ሀገራችን ሕዝብ አሳሩን የሚያይበት፣ ትውልዱ ዋጋ የሚከፍልበት አጀንዳ አጥታ አታውቅም። የጠራና የነጣ ተጠያቂነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት የለንም። ጥፋተኞችን የሚቀጣ፣ ልከኞችን የሚያሞግስ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር በሚፈለገው ደረጃ አልገነባንም።
አሁን አሁን ከዚህም ባለፈ መልኩ ምን እንደሆነ በማያውቀው አሉባልታ በለው የሚል፤ መነሻና መድረሻውን ሳያውቅ የውሸት ትርክት ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የምንተጋ ፤ በበጎ እውቀት ለሀገር ከመልፋት ይልቅ ሀገር ለማፍረስ እንቅልፍ ካጡ ጋር በመተባበር የሚቀናው ትውልድም እየታየ ነው። እውቀትና መረጃን መሰረት ያላደረጉ አካሄዶች ሀገራችንን እየጎዷት ነው። ከዚህ የምንወጣበት የሎጥ መንገድ ያስፈልገናል። ሎጥ ከሰዶም ሲወጣ ኋላውን ትቶ በአዲስ መንገድ ነበር። ኋላዬን አልተውም ያለችው ሚስቱ የጨው ሀውልት ሆናለች ። እኛም መከራችንን ለመሻገር እንደ ሎጥ ያለ አዲስ መንገድ ያስፈልገናል። አዲሱ መንገዳችን ደግሞ በምክክርና በውይይት ውስጥ ነው።
ሀገር የሰከነ ሕዝብ ትሻለች። ሕዝብ ሳይሰክን የምትፈጠር ሥልጡን ሀገር የለችም። እዛም እዚህም የሚነሱ መሰረት አልባ አጀንዳዎች የሕዝቡን ሥነልቦና የተረዱ አንዳንድ ክፉዎች የፈጠሩት ከመሆን ባለፈ ሌላ አይደሉም።ረጋ ብለን ችግሮቻችንን ካጠናናቸው ከኛ አቅም በላይ አይደሉም። አጀንዳዎቻችን ምንም ይሁኑ ምንም በውይይት የሚፈቱ ናቸው። ያጣነው አጀንዳ ሳይሆን ተቀምጦ መነጋገር ነው። ያጣነው ኃይል ሳይሆን ስክነት ነው። የመነጋገርን ባህልን ሳናዳብር አጀንዳ እየፈጠርን ብንሄድ ትርፋችን ራሳችንን መጉዳት ብቻ ነው። ስክነት ያልታከለባቸው የኃይል ርምጃዎች ሀገርና ሕዝብን አደጋ ውስጥ ከመክተት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም።
ያሉና የነበሩ ወደፊትም የሚኖሩ አጀንዳዎቻችን መፍትሄ እንዲያገኙ ተቀምጦ መወያየትን መልመድ አለብን። ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደ ኮሚሽን ሲመሰረት ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እኚህንና የመሳሰሉ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ነው። ችግሮቻችን እንዴትም፣ ከየትም ይምጡ የሚበጀን ነገር ለነዛ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት ነው። እኛ በተቋጠረና ማንም በማይፈታው ጥብቅ የአብሮነት ቋጠሮ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን። ይሄ ቋጠሮ በማንም እንዳይፈታ ሆኖ የተገመደ የወንድማማችነት ውል ነው። ይሄ ውል የሚጠብቀው በፍቅርና በአብሮነት፤ የሚላላው ደግሞ በጥላቻና በመለያየት ነው። ችግሮቻችን እንዴት መጡ፣ ለምን መጡ፣ ከየት መጡ፣ መቼ መጡ የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ነው ወደቀጣዩ ምዕራፍ የሚወስደን። እንዴት መጡ የሚለው ጥያቄ የችግሮቻችንን መነሻ ምክንያት እንድናውቅ ይረዳናል። መነሻ ምክንያቱን አወቅን ማለት ለችግሩ መፍትሄ እንድናመጣ መንገድ ይከፍትልናል።
ለምን መጡ የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ ችግር ያለ ችግር ፈጣሪ ዝም ብሎ አይመጣም እና ከችግሮቻችን ኋላ ያሉ ችግር ፈጣሪዎችን እንደርስባቸዋለን ይረዳናል። ለምን ብለን ስንጠይቅ ከችግራችን እኩል የችግር ፈጣሪዎችንም ዓላማ እንደርስበታለን። ከየት መጡ የሚለው ጥያቄ ችግሮቻችንን ለማሸነፍ ወሳኝ ጥያቄ ነው። አሁን ላይ እየጎዳን ያለው ችግሮቻችን ከየት እንደተነሱ አለማወቃችን ነው። ከየት የሚለው ጥያቄ መፍትሄዎቻችን ያሉበት ብቸኛው ቦታ ነው። ከየት የሚለው ቃል ቦታን አመላካች ነው። ለጥያቄዎቹ የምንሰጣቸው ትክክለኛ ምላሾች ፖለቲካችንንና ፖለቲከኞቻችንን እንድንመረምር እና እንድናውቅ አቅጣጫ ጠቋሚ ናቸው። ኢትዮጵያንና ፣ ጠላቶች እንድናይ እድል የሚሰጡን ናቸው።
መቼ መጡ ብለን ስንጠይቅ የምንደርስበት ጊዜ አለ። ጊዜውን ስናውቅ የችግሩን መነሻ ምክንያት በዛውም እንደርስበታለን። ጊዜ እውነትን ጠቋሚ ነው። ጊዜ ፍትህን ገላጭ ነው። አሁን ላይ እየተቸገርንባቸው ያሉ አንዳንድ አጀንዳዎች ጊዜአቸው የማይታወቅ ምናልባትም መቶና ከዛ በላይ ዘመን ያስቆጠሩ አጀንዳዎች ናቸው። በነዚህ አጀንዳዎች ላይ የምንለዋወጣቸው የጥላቻ ልውውጦች ከዚህ ዘመን ትውልድ የማይጠበቅ ተግባር ነው። ሰው ከእሱ ትውልድ በብዙ በራቀ መሰረት አልባ አጀንዳ ይጋጫል? ከዚህ ባለፈ መቼ የሚለው ጥያቄ ሀሰተኞችን እንድናጋልጥበት በር ይከፍትልናል።
ችግር እስካለ ድረስ ችግር ፈጣሪዎች የማይቀሩ ናቸው። ችግር ፈጣሪዎች ከነችግራቸው እንዲታወቁ ሕዝብ የሚሳተፍበት የውይይትና የተሳትፎ መድረክ ያስፈልጋል። ችግር ፈጣሪዎች ከሕዝብ ሌላ መደበቂያ የላቸውም። ሕዝብ ላይ ችግር ፈጥረው ሕዝብ መሀል የሚደበቁ ናቸው።ሀገራችን ከአሁን በፊት ሕዝብን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ያደረገችው ያዝ ለቀቅ በሆኑ አካሂዶች ናቸው። አሁን አንዳንዶች ችግርና ችግረኞችን እየፈጠሩ በአጀንዳ የተጥለቀለቀች ሀገር ለማድረግ እየሰሩና ፋታ እየነሷት ያለው። ሕዝብ መቅደም አለበት.. የመፍትሔያችን ወንፊት በሕዝብ እጅ ነው። እነማን ምን እንደሚሰሩ፣ እነማን ምን እንደነበሩ ሙሉ መረጃው ሕዝብ እጅ ውስጥ ነው። ሕዝብ ነውረኞችን እያጣራ የሚለይ፣ ችግር ፈጣሪዎችን ከነአጀንዳቸው እየለየ የሚያንጓልል ወንፊት ነው። ወንፊቱን ትተን የምንሰበስበው ጤናማ እህል የለም። ሕዝብ ለሀገር ወንፊት ነውና..
ሀገር መሰረቷ ሕዝብ ነው። ሕዝብ ስንል የተለያዩ ባህልና ሥርዓቶችን ያጠቃልላል። አጀንዳ የሚነሳው ከሕዝብ ነው መፍትሄውም የሚመጣው ከራሱ ከሕዝብ ነው። ከሕዝብ የተደበቀ ምንም አይነት ችግር የለም። ነጻና ገለልተኛ በሆነ የምክክር ሂደት ውስጥ ነው እንደ ሀገር የሚፈለገውን ለውጥ ልናመጣ የምንችለው።ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራውን ሲጀምር ዓላማና ግብ አንግቦ ነው። ዓላማው ደግሞ መፍትሄ አዘል በሆነ ምክክር ጤነኛ ሕዝብና ጤነኛ ሀገር ማስቀጠል ነው። በሕዝብ መካከል መለያየትን የሚፈጥሩ አጀንዳዎች ሕዝብ ተሳትፎባቸው መፍትሄ እንዲያመጡ ማድረግ ነው። ለሀገራዊ ምክክሩ እንዲረዳ በተለያዩ የክልል ከተሞች ቢሮ እንደከፈተ የኮሚሽኑ መግለጫ አስታውቋል። እኚህና የመሳሰሉ አካሄዶች ምክክር ኮሚሽኑ ምን ያክል ርቀት ለመሄድ እንደተሰናዳ የሚያሳዩ ናቸው። በቀጣይ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ችግሮቿን በመነጋገር የምትፈታ፣ ጦርነትን ታሪክ ያደረገች ሀገር እንደምትፈጠር እናምናለን።
የሌለን ምንም የለም.. በብዙ ነገር ሙሉ ነን። ግን የሁሉም መሰረት የሆነው ተግባቦት የለንም። ለዛም ነው በብዙ ሙላት ውስጥ ጎድለን የቆምንው። ለዛም ነው በብዙ መትረፍረፍ ውስጥ አንዳች እንደሌላት ምስኪን እመበለት የተጎሳቆልነው። መውጫችን አንድ መንገድ ነው.. እርሱም ተነጋግሮ መግባባት ነው።መቼም የትም አጀንዳ ሊፈጠር ይችላል፣ እንዴትም፣ በማንም ችግር ሊመጣ ይችላል ከእኛ የሚጠበቀው ወደ ጦርነት ሊወስዱን የመጡትን ችግሮች በመነጋገር ማስቆም ነው። ሊያደነቃቅፉን የተፈበረኩ የውሸት ትርክቶችን በውይይትና በምክክር ወደ እውነት ማምጣት ነው። እንደ ሀገር ያጣነው ይሄን ብቻ ነው። ልባችንን ለውይይት ከከፈትን አሁንም ብዙ እድሎች አሉን። ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋራ ሃሳብ የጋራ ሀገር ሊሰራ ወዳለንበት እየመጣ ነው። የጋራ ሀገር ለመስራት ደግሞ የጋራ ሃሳብ ማዋጣት አለብን።
ከነውጥና ከጦርነት ነጻ የሆነችን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሁላችንም ሃሳብ ያስፈልጋል። መድረኩ ጥቂቶች የሚናገሩበት ሳይሆን ሁላችንም ተናግረን የመፍትሄ ሃሳብ የምናመጣበት ነው። እንዳለፈው ጊዜ ጥቂቶች ተናጋሪ ብዙሃኑ አድማጭ የሚሆንበት መድረክ አይሆንም። በሕዝብ ድምጽ ውስጥ ነው የምንፈልገው ሰላምና አንድነት ያለውና ሕዝብ መናገር አለበት። የሀገር መድኃኒት ያለው በሕዝብ ድምጽ ውስጥ ነው። ሕዝብ ሲናገር ሀገር እፎይ እያለች ነው። ሕዝብ ሲናገር ሀገር ሰንደቋን እያውለበለበች ነው። በጋራ ጉዳያችን ላይ በግልጽ የሚመከርበት የአንዱ ቁስል ለሌላው የሚሰማበት የምክክር መድረክ እንናፍቃለን። ያ ከሆነ መጪው ጊዜ የተሻለ እምርታን የምናይበት ይሆናል።
እስከዛሬ ፖለቲከኞች ሲያወሩ ሕዝብ ሲሰማ ነበር። አሁን ደግሞ ሕዝብ ይናገር መንግሥትና ፖለቲከኞች ይስሙ። ሕዝብ ያውራ ፖለቲከኞች ያድምጡ። ከሕዝብ የተደበቀ የሀገር ችግር የለም። ሕዝብ ሃሳቡን በነጻነት የሚገልጽበትን እድል ካገኘ ፖለቲከኞች የሚሰሙት ብዙ ነገር ይኖራል። እስካሁንም ዋጋ ያስከፈለን ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ያልተሳተፈበት ፖለቲካ ነው። ፖለቲከኞች አለን የሚሉትን እየተናገሩ፣ ያሳምንልናል የሚሉትን አጀንዳ እያረቀቁ ወደ ሕዝቡ ሲልኩ ኖረዋል። ሕዝብ ዝም ባለበት፣ ሕዝብ እንዳይናገር በተከለከለበት ፖለቲካ ውስጥ የሚመጣ ለውጥ የለም። ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሕዝብ እንዲናገር ፖለቲከኞች እንዲያደምጡ የቀየሰው አዲስ አካሄድ አጀንዳዎቻችንን በማርገብ የላቀ ፋይዳ እንደሚኖራቸው እናምናለን። የአጀንዳ መብዛት መፍትሄ አይሆንም.. የአጀንዳ መብዛት ለውይይት በር መከፈት ግን ይችላል። የእውቀትና የተግባቦት ምንጭም ሊሆን ይገባል። ልዕልና ያላቸው አጀንዳዎች እንዲነሱ የውይይትና የንግግር ፖለቲካ ያስፈልገናል። ከዚህ አንጻር ተስፋ የተጣለበት ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንም በርካታ የቤት ስራዎች ይጠብቁታል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም