የንባብ ባህል ለሀገር እድገት ያለው ፋይዳ

ትውልድ ከሚገነባባቸው መልካም እሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ጠንካራ የንባብ ባህል ነው:: የእያንዳንዳችን ነገ ለመጽሀፍ በሰጠነው ክብርና ዋጋ ልክ እንደሚመዘንም አምናለሁ::

በህይወት ውስጥ አብዛኞቹ አደጋዎች ከእውቀት ማነስ የሚመጡ ናቸው:: በዛው ልክ በቁጥጥራችን ስር ያደረግናቸው ችግሮቻችን ሁሉ በእውቀታችን ታግለን የጣልናቸውም ናቸው ብል ልክ እሆናለው:: እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን ለብዙ ነገር ጊዜ ሲኖረን ለመልካም ነገር ግን ጊዜና ቦታ የሚጠበን ነን:: ዛሬ ላይ በብዙ ነገር ጎለን የምንገኘው የሚጠቅመን እያለ በማይጠቅመን ላይ ስለምንለፋ ነው:: እስኪ ልጠይቃችሁ ስልጣኔ ለእናንተ ምንድ ነው? የሀገርና የማህበረሰብ እድገትና ስልጣኔ በምን የሚለካ ይመስላችኋል?

ስልጣኔ መነሻው እውቀት ነው:: ያለእውቀት ስልጣኔን ማሰብ የማይታሰብ ነው:: የሀገርና ማህበረሰብ እድገትና ከፍታ የሚለካውም በዚህ እውቀት በሚሉት የተሀድሶ ሚዛን ነው:: ሀገር ትላንትን መሰረት አድርጎ ወደነገ የሚወስድ ተራማጅ እሳቤ ከሌላት፣ አደጋ ነው:: በዚሁ መጠንም ትውልድ ከፍ ባለ የእይታ መነጽር የእውቀትና የንባብ ልምምድ ከሌለው እንደሀገር ተሀድሶ እንደሚያስፈልግ እሙን ነው::

ተሀድሶ ከእውቀት የሚጀምር የልዕቀት ማዕከል ነው:: ሀገር በእውቀት ካልተቀየረች፣ ትውልድ በማንበብ ባህል ካልዘመነ ከመሬት የሚያነሳው ሌላ ሀይል የለውም:: ስለዚህም ንባብ የዕውቀት መሰረት፤ እውቀት ደግሞ የብልጽግና መሰረት መሆኑን መረዳት ይቻላል:: ስለዚህም የንባብ ባህላችን ለሀገራችን ያለው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ መሆን የለበትም:: በተለይም አሁን ያለንበትን ማህበራዊ ምስቅልቅል ፈር ለማስያዝና በአመክንዮ የሚያምን ማህበረሰብ ለመፍጠር ንባብ ወሳኝ ሚና ይጫወታል::

ዛሬ ያለውን ምስቅልቅል ሁኔታ ቀይረን አዲስ ገጽታ ለመላበስ አዳዲስ ማህበራዊ ልማዶች ያስፈልጉናል:: እውቀት የንቁ ማህበረሰቦች መፈጠሪያ ማህጸን ነው የሚል የጋራ እውነት አለ:: ትጋትና ንቃት መገለጫችን ሆነው ከዝቅታችን ከፍ እንድንል ትውልዱ በንባብ ባህል መታረቅ አለበት:: ዓለም ከጥንት እስከዛሬ ሰንኮፏን ጥላ ዛሬ ላይ ተውባ የቆመችው በእውቀት ተመርታ ነው:: በሌላ አገላለጽ የትኛውም ስልጣኔ እውቀትን መሰረት ያደረገ ነው እያልኩ ነው:: ራሳችንን የምንፈልግበት ፈልገንም የምናገኝበት አንድ ጥበብ እውቀት ነው:: የዕውቀት ምንጩ ደግሞ ንባብ ነው::

ብዙዎቻችን ማንበብ ትልቅ ሰው ያደርጋል፣ አንባቢዎች መሪዎቻችን ናቸው እየተባልን ያደግን ቢሆንም ወደተግባር ስንመጣ ግን ሌላ ነን:: አብዛኞቻችን እያወቅን የምንሳሳት ነን:: ለአልባሌ ነገሮች ጊዜ ሲኖረን የእውቀት ሁሉ መሰረት የሆነውን መጽሀፍ ለማንበብ ግን ጊዜ የምናጣ ብዙዎች ነን:: ሰው የህይወቱን ትልቁን ግብ እውቀት እስካላደረገ ድረስ ከስልጣኔ ደጃፍ አይደርስም:: የምንፈልገው ማንኛውም ነገር እውቀታችን ውስጥ ያለ ነው::

ሳናነብና ራሳችንን ለእውቀት ሳናዘጋጅ የምንለውጠው አንዳች ነገር የለም:: እውቀት ማለት እኮ ህይወትን ቀላል ማድረግ ማለት ነው:: እውቀት እኮ ለችግሮቻችን መፍትሄ የምንሰጥበት ነው:: እውቀት እኮ ነገን የተሻለ ማድረግ ነው:: ማንበብ እኮ ራስን ማሳደግ፣ አእምሮን ማበልጸግ ነው:: ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ህይወትን ከማክበድ ውጪ የምንፈጥረው መልካም ነገር ሊኖረን አይችልም::

ዓለምን የለወጧት የትላንትናዎቹ ጠበብቶች አንባቢዎች ነበሩ:: የዛሬዎቹ የእኔና የእናንተ ትውልድም የዓለምን አዳፋ መልክ በንባባቸው የቀየሩ ናቸው:: ፍላጎታችን ምንም ይሁን እውቀት ያስፈልገናል:: እውቀት ሀሳባችንን የምናክምበት፣ አእምሯችንን የምናንጽበት ፍቱን መድሀኒታችን ነው::

ካለእውቀት የምንሄድበት ጎዳና በእንቅፋት የተሞላ ነው:: አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ለመገንባት ያለጥርጥር የንባብ ባህሉ የዳበረ ማህበረሰብ ያስፈልገናል:: እውቀትና መልካም ልምዶች የሚገኙት ደግሞ ከማንበብና ራስን ለእውቀት ዝግጁ በማድረግ ነው:: ዛሬ ላይ ብዙ ነገሮች እየተበላሹብንና እየፈረሱብን ያሉት ካለእውቀት በዘልማድ ስለምናደርጋቸው ነው::

ያለንባብ የሚሳካ ግለሰባዊም ሆነ ሀገራዊ ህልም የለንም:: ይሄን እውነት በመረዳት ራሳችንንም ሆነ በእኛ በኩል ለሚመጣው ትውልድ የንባብ ባህልን ልናወርሰው ግድ ይላል:: ንባብን ባህሉ ያላደረገ ማህበረሰብ በብዙ ነገሩ ወደ ኋላ የቀረ ነው:: እንደ ሀገር የኋላቀርነታችንን ሰበብ ብንፈትሽ እንዲህ አይነቱ የመልካም ልማድ ጉድለቶች እንደሆነ እንደርስበታለን::

ዓለም ላይ በንባብ ባህላቸው አንቱታን ያገኙ ሀገራት ጥቂቶች አይደሉም:: እኔና እናንተ ሞባይላችን ላይ ተጥደን ስንውል ውሏቸውን ከመጽሀፍ ጋር ያደረጉ ሀገራት አሉ:: ለዚህ እንደማሳያ የብላድሚር ፑቲንን ሀገር መጥቀስ ይቻላል:: ሩሲያ ውስጥ ‹ቢብሎፎቢያ› ወይም በላኢ መጽሀፍ የሚባል ከትላንት ወደዛሬ የመጣ ማህበራዊ ልማድ አለ::

ሩሲያ ውስጥ ካሉ ከተሞች ወደአንዱ የመሄድ እድል ቢገጥማችሁ ከተለመደው ወጣ ያለ ማህበረሰብን ነው የምታገኙት:: ጎዳና ላይም ሆነ ትራንስፖርት ላይ መጽሀፍ ይዘው ሲያነቡ ማየት አዲስ ነገር አይደለም:: ልክ እኛ ሀገር ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ ሱስ እንደተጠመደ ሁሉ ሩሲያውያን በንባብ ፍቅር የተጠመዱ ናቸው::

ወደብራዚል ብትሄዱ ደግሞ አዲስ ነገር ትሰማላችሁ:: ብራዚል ውስጥ አንድ እስረኛ የእስር ጊዜው የሚቀንስለት ባነበበው መጽሀፍ መጠን ነው:: በወር አንድ መጽሀፍ አንብቦ የሚጨርስ እስረኛ ነጻ የመውጣት እድሉ የሰፋ ነው:: ወደእኛ ሀገር ስንመጣ ሌላ መልክ ነው የምናገኘው::

ለስሙ ሀገራችን የጥበብና የጥበበኞች ሀገር ትባላለች እንጂ ትውልዱ ስሙን በሚመጥን መልኩ በእውቀት መሻት ላይ ፍላጎት ሲያሳይ አይታይም:: ከተጠናወተን የድህነት ታሪክ ለመለየት አርነት የሚያወጣንን የእውቀት እሳቤ ማዳበር ግዴታችን ይሆናል:: እንደሀገር ላጣነው ሰላም፣ ላጣነው አንድነት ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው መልካም የንባብ ባህልን ያለማዳበር አባዜ ነው::

ሀገራችን ኢትዮጵያ ንባብን ሱስ ያደረገ፣ በእውቀት ጥማት ውስጥ የቆመ ማህበረሰብ ያስፈልጋታል:: አሁን ላይ የትውልዱን ውሎ ብንመለከት ለሀገር ፋይዳ በሌለው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥዶ እናገኘዋለን:: እንዴትም ብናስብ የህልሞቻችን ደጃፍ የሚከፈቱት በእውቀት ቁልፍ ነው::

የዓለም መልክ የእውቀት መልክ ነው:: ዓለምን በጥበባቸው ያሳመሩ አእምሮና ልቦች በማወቅ ውስጥ ያለፉ ናቸው:: ሁሉን ትተን ስለምድራችን ቢሊየነሮች ብናወራ እንኳን የመጽሀፍ አፍቃሪያን ሆነው እናገኛቸዋለን:: ሁሉም ባለጸጋና ስኬታማ ሰዎች ራሳቸውን ለማሳደግ በወር ሁለትና ከዚያ በላይ መጽሀፍት የሚያነቡ ናቸው::

በሀብት መጠኑ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፈው ሽማግሌው ዋሬት ቡፌት የእድሜውን ሰማንያ ፐርሰንት ያህሉን ያሳለፈው በማንበብ ነው:: በጣም የሚገርመው ደግሞ የመጨረሻው የስኬት ጥግ ላይ ደርሶ ዛሬም ድረስ ማንበቡ ነው:: ‹ሀብታም እንደምሆን ቀድሜ አውቅ ነበር፣ መቼም ቢሆን ለደቂቃ እንኳን ስኬታማ እንደምሆን ተጠራጥሬ አላውቅም የሚለው ሽማግሌው ቡፌት መጽሀፍ ማንበቤ የዛሬውን እኔን ፈጥሮኛል ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል::

የብልጌትና የቱጃሩን ቤዞስ እንዲሁም የምድራችንን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የአለን መስክን ጀርባ ብታጠኑ የስኬታቸው ምስጢር ማንበብ እንደሆነ ትደርሱበታላችሁ:: ዓለም ላይ የሁሉም ስኬታማ ሰዎች የስኬት መነሻ እውቀት ነው:: ንባብ ነው:: ለሚጠቅማቸው ነገር መልፋታቸው ነው:: አብዛኞቹ ስኬታማ ሰዎች ከማንበብ ጋር የተያያዘ ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ናቸው:: ስኬታማ ሆኖ እውቀት የሌለውና ማንበብን ባህል ያላደረገ ግለሰብ አይገኝም::

አንድ ያልገባን ነገር እንዲገባንም የምሻው ነገር አለ:: ዛሬ ላይ ሁሉ ነገራችንን ሰጥተን ምንም ያላገኘንበት ማህበራዊ ሚዲያ እንኳን እውቀት ባላቸው ሰዎች የተፈጠረ መሆኑ ነው:: አንድ ሰው ልክና ጠቢብ የሚባለው ጊዜውን ለጠቃሚና እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ሲጠቀመው ነው:: ማንበብ በየትኛውም መስፈርት ቢታይ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ነው:: በማንበብ ውስጥ፣ እውቀትን በመሻት ውስጥ የሚባክን ጊዜ የለም::

የድህነትን ያክል አስከፊ ገመና የሰው ልጅ የለውም:: ከድህነትም ሆነ ከሌሎች ነውሮች ራሳችንን ነጻ የምናወጣው ምክንያታዊነትን ሊያላብስ በሚችል እውቀት ነው:: ትውልዱ ከማይጠቅመው ከአጉል ልማድ ወጥቶ በንባብ ሱስ መያዝ አለበት:: በንባብ ሱስ የተያዘ ትውልድ ለሌላ ሱስ የሚሆን ጊዜም ሞራልም የለውም:: ያጣናቸው እንደሰላም እና አንድነት ያሉ ሀገራዊ በረከቶቻችን ከትውልዱ መመለስ በኋላ የሚመለሱ ናቸው::

ትውልዱን ወደእውቀት ለመመለስ ሁሉም ኃላፊነት አለበት:: እንደመንግስት እየተሰሩ ያሉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች አሉ:: ለዚህ አንዱ ማሳያ አብሮሆት ቤተ መጽሀፍት ነው:: አብሮሆት ቤተመጽሀፍት በምስራቅ አፍሪካ ገናና ስም ካላቸው፣ በአፍሪካ ካሉ አስር ዘመናዊ ቤተመጽሀፍቶችም ውስጥ የአንዱን ስም ያገኘ ነው::

ትውልድ በወሬ እና በምክር አይጸናም:: የትውልድ ለውጥ፣ የሀገር ተስፋ ተግባር ይፈልጋል:: እንደአብሮሆት ያለ እውቀትና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ የወጣት መዋያ የንባብ ስፍራዎች መኖራቸው ነው ትውልዱን ወደተጨባጭ ለውጥ ሊያሸጋግረው የሚችለው::

በእውቀታችን ልናሸንፋቸው እየተገባን ግን ደግሞ ባለማወቅ ተላምደናቸው እየጎዱን ያሉ ብዙ ነገሮች አሉ:: ከነጉድፋቸው በጉያችን ውስጥ የታቀፍናቸው፣ ከመጸየፍ አልፈን ያከበርናቸው፣ ከመናቅም እውቅና የሰጠናቸው ብዙ ነውሮች አሉብን:: የማንም ያልሆኑ የእኛ የኢትዮጵያውያን ብቻ የሆኑ የእልፍ ጉድፎች ሰለባዎች ነን::

ይሄ ሁሉ ነውራችን የሚስተካከለው ደግሞ በእውቀት ነው:: ይሄ ሁሉ ጉድፋችን የሚጠራው ደግሞ አንባቢ ትውልድ ስንፈጥር ነው:: ይሄ ሁሉ መደነቃቀፋችን እልባት የሚያገኘው በእኔና በእናንተ ምክንያታዊ እሳቤ ነው::

አንዳንድ ጊዜ ከተማችንን ሳያት ግርም ትለኛለች:: በየሰፈሩ..በየቤቱ በረንዳ ላይ ግሮሰሪና መቃሚያ ቤት ያልሰራ ማን አለ? በየመንገዱና በየጎዳናው ጭፈራ ቤት እና ማሳጅ ቤት ስንሰራ ለአንድ ላይብረሪ ሲሆን ቦታ የምናጣው ለምንድን ነው?:: በክልልና በዋና ከተማ ጎዳናዎች ላይ ምንም የማይሰሩ ባለቤትነታቸው የማይታወቅ ተጀምረው ሳይጠናቀቁ አስርና አስራ አምስት ዓመት የቆዩ ትላልቅ ፎቆችን ስንገነባ ለህዝብ ቤተመጽሃፍት ሲሆን አሻፈረኝ የምንል ነን:: በየቤታችን መደርደሪያ ላይ ብዙ አይነት ውስኪና ሻፓኝ ስናስቀምጥ አንድ መጽሀፍ ግን የለንም::

ሰኔ ሰላሳን ለሀገር አቀፍ የንባብ ቀን መርጠነው ከስም ባለፈ ምንም አላደረግንም:: ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ትውልድ ለመፍጠርም ሆነ ሀገር ለመገንባት የምንሮጠው ሩጫ አያዋጣንም:: ከሁሉ በፊት እውቀት ያለው ምክንያታዊ ትውልድ መፍጠር አለብን:: በእኛና ባደጉት ሀገራት መካከል የተፈጠረው የኢኮኖሚና የስልጣኔ ልዩነት በእውቀት እንጂ በሌላ በምንም የመጣ አይደለም::

አሜሪካውያን ቅድሚያ ለአሜሪካ ሲሉ እኛ ቅድሚያ ለእኔ የምንል ነን:: ቻይናዎች ቅድሚያ ለቻይና ሲሉ እኛ ግን ከሀገር ይልቅ ስለብሄራችን የምንሟገት ነን:: የአለማወቅ ትልቁ ክፋት ሰውነትን ሽሮ እኔነትን ማልመዱ ነው:: ከአፋችን ቅድሚያ ለኢትዮጵያ፣ ቅድሚያ ለትውልዱ የሚል አዲስ እውቀት ያስፈልገናል:: ይህ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው በንባብ ብቻ ነው::

በእውቀታችን ድህነታችንን ማሸነፍ ቅድሚያ የምንሰጠው አጀንዳችን ሊሆን ይገባል:: ከግሮሰሪ ይልቅ ላይብረሪ በመክፈት፣ ቤታችን መደርደሪያ ላይ ውስኪ ሳይሆን መጽሀፍ በማስቀመጥ፣ ለልጆቻችን ሽጉጥ ሳይሆን የተረት መጽሀፍ በመግዛት አጉል ልማዳችንን ማስተካከል ለነገ የማንለው የዜግነት ሀላፊነታችን ነው::

ከየትኛውም ሩጫ በላይ ለውጥ ያለው በማንበብ ውስጥ ነው:: ስልጣኔ ፎቅና መንገድ መገንባት አይደለም:: ስልጣኔ ስማርት ስልክና በስማርት ጫማና ልብስ መዘነጥ አይደለም:: ስልጣኔ በእስማርት አስተሳሰብ መዘነጥ ነው:: ስልጣኔ ነውጥ በሚፈጥር መለያየት ውስጥ ሳይሆን ሰላም በሚፈጥር ምክንያታዊ ሙግት ውስጥ ማለፍ ነው::

ብዙዎቻችን ከንባብ ይልቅ ከማይጠቅሙን ነገሮች ጋር ተዋደንና ተፋቅረን የምንኖር ነን:: ከሚጎዱንና ህይወታችንን ሊያሳጡን ከሚችሉ መጥፎ ነገሮች ጋር ተቃቅፈን ያለን ነን:: በእድሜአችን፣ በወጣትነታችን ብዙ ነገር መስራት ሲገባን ባለማወቅ ወይም ደግሞ አውቆ ባለመንቃት ጊዜአችንን በከንቱ የምናባክን ብዙ ነን::

‹‹ከአፍሪካውያን ገንዘብ መሰወር ከፈለክ መጽሃፍ ውስጥ ደብቀው›› የሚል አባባል አውቃለሁ:: ይህ እንግዲህ አፍሪካውያን ከንባብ የራቁ መሆናቸውን ለማመላከት ነው:: ይህንን ታሪክ መቀየር ደግሞ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል:: ግን ደግሞ ታሪክ ለመቀየር በከንቱ የምናሳልፈውን ጊዜ ወደ ንባብ መቀየር ይገባል:: ስለማለቁም እርግጠኛ ያልሆንለትን ጊዜአችንን በንባብ ላይ እናውለው የሚለው የማሳረጊያ መልዕክቴ ነው::

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 4/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *