ስንዴ ከሩዝ ቀጥሎ በዓለማችን በስፋት የሚመረት የሰብል ዓይነት ነው። በዓለማችን በድሃም ሆነ በሀብታም አገራት እጅግ ተፈላጊ የሆነ ሰብል ነው። ከምግብነት ባሻገርም ለአገራት ሰፊ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት በኩልም ሚናው ላቅ ያለ ነው። ለዚህም ይመስላል በርካታ አገራት ለስንዴ ከምግብ በላይ የሆነ ግምት የሚሠጡት።
በዓለም ላይ በስንዴ አምራችነታቸው ከሚታወቁ አገራት ውስጥ ቻይና፤ ሕንድ። ሩስያና ዩክሬን ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ቻይና የዓለማችን ቁጥር አንድ ስንዴ አምራች አገር በመሆን በአመት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ቶን የምታመርት አገር ነች። ይህም የዓለማችንን 17 በመቶ የስንዴ ምርት የሚሸፍን ነው።
ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር ግን የምታመርተውን ሁሉ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ታቀርባለች፤ በዚህም ታላቋ ስንዴ ተመጋቢ አገርም በመሆን ትታወቃለች። ስንዴ በስፋት በማምረቷ ሕዝቦቿን በቀላሉ መመገብ ችላለች። ከተረጂነት ተላቃም በምግብ እህል እራሷን በመቻል ከስንዴ ፖለቲካ እራሷን መታደግ ችላለች።
ሌላኛዋ ስንዴ አምራች አገር ራሺያ ናት። ራሺያ ስንዴ የውጭ ንግዷ መሠረት አድርጋም ትወስዳለች። 8 ነጥብ 4 በመቶ የሆነውን የዓለማችንን የስንዴ ምርት የምትሸፍን ሲሆን፣ ከዚህ ምርቷም 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች። ከምርታማነቷና ከምታገኘው ገቢ (ዶላር) ባሻገርም በምግብም እራሷን የቻለች፤ በስንዴ ፖለቲካ ነፃነቷን ማስከበር የተሳካላት አገር ለመሆን በቅታለች።
ዩክሬን ዓለምን በስንዴ እህል በመመገብ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፈች አገር ነች። ከአመት በፊት ከሩሲያ ጋር በገባችበት ጦርነት ምክንያት እንኳን 3 መቶ ሺህ ቶን ስንዴ እና በቆሎ እንደተበላሸባት መግለጿ የሚታወስ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩክሬንን ስንዴ በዋነኝነት ገዥ ሲሆን፤ የገዛውንም ስንዴ አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም በረሃብና በተለያዩ አደጋዎች ውስጥ ለሚገኙ አገራት ዜጎች ያከፋፍላል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ያህል ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ብትሆንም በምግብ ሰብል እራሷን ባለመቻሏ ነፃነቷን የተሟላ ማድረግ ተስኗት ቆይቷል። በአድዋ የተገኘው ድል በቅኝ ገዢዎች የፈረጠመ ኢኮኖሚ ሲጠመዘዝ ኖሯል። የኢትዮጵያ ኩራትና ድል በስንዴ ልመና ኮስሶ በዓለም መድረኮች ሁሉ ለምናቀርበው ጥያቄና ለምናሰማው ድምጽ መጀመሪያ ሆዳችሁን ሙሉ የሚል ምላሽን ሲነገረን ኖረናል።
ዛሬ ግን የአድዋ ድል በተገቢው ቦታው ላይ እንዲነግስ የሚያስችል አኩሪ ታሪክ መጻፍ የምንችልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስላል። ኢትዮጵያ ዳግም ነፃነቷን ልታውጅ እሷም እንደነዩክሬን በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደ ውጭ ገበያ ልትልክ፤ ከስንዴ ለማኝነት ወደ ስንዴ ላኪነት ልትሸጋገር ዳር ዳር እያለች ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ስንዴ ሸማች ከሆኑ አገራት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ ስትሆን በየአመቱም እስከ 107 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማስገባት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ታወጣለች። ይህንን እውነታ ለመቀልበስ በተደረገው ርብርብ /ባለፉት አራት አመታት መንግሥት ለስንዴ ምርት በሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆሟም ባሻገር ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች።
ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት እራሷን በመለወጥም ታሪክ እየሠራች ነው፤ ይህ ለቀጣናው አገራት ኩራትና ተስፋ፤ ሠርቶ የማሠራት ተምሳሌትም ያደርጋታል። ጥረቷ በታሰበው ልክ ከተሳካም አገሪቱ በዓለም ስንዴ በማምረት ተጠቃሽ ከሆኑ 18 አገራት ተርታ ያሰልፋታል።
በተያዘው አመት ኢትዮጵያ 129 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት ታመርታለች ተብሎ ይጠበቃል። 97 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ሲሆን 32 ሚሊዮን የሚጠጋው ወደ ውጭ ተልኮ ዶላር የሚያስገኝ ነው። ለዚህም ዘንድሮ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ስድስት አገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈርሟል።
የረድኤትና ሌሎች የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ የሚገዙትን ስንዴ ምርት በአገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት በመፈረም ላይ መሆናቸውም ተሰምቷል። በዚህም ኢትዮጵያ ከ200ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታገኝ ይገመታል።
ይህ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባሻገር የጎረቤት አገራት ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ካናዳ ደጅ ጠንተው የሚገዙትን ስንዴ ከደጃቸው በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የምሥራቅ አፍሪካን አካባቢም ከግጭትና ሁከት በማውጣት አገራቱን በልማት እንዲተሳሰሩ በር ይከፍታል።
ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን መቻል አቅቷት ቢሊዮን ዶላር አውጥታ ከውጭ ከማስገባት በዘለለ፣ ለዕርዳታ የብዙዎችን በር ስታንኳኳም ሰንብታለች። አንዳንድ ጊዜም ረጂ አገራት ስንዴን እንደመያዣ አድርገው የሚፈልጉትን ሁሉ ለመጫን ሲሞክሩ ታይተዋል። ሆኖም ይህ ታሪክ ዘንድሮ ያበቃ ይመስላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) «ስንዴ አምርተን ከራሳችን አልፈን ወደ ውጭ እንልካለን›› ብለው ሲናገሩ ብዙዎች ንግግሩን ከፖለቲካ ፍጆታነት የሚያልፍ አልመሰላቸውም ነበር። ሆኖም ንግግሩን በጥርጣሬ የተመለከቱት ሁሉ ዛሬ ምስክርነታቸውን መስጠት ጀምረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ርዕይ ግቡን መምታቱን ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ከዘርፉ ባለሙያዎችም አልፎ በአሜሪካ የውጭ ግብርና ቢሮም ‹‹በኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ትልቅ እመርታ እያሳየና ምርታማነቱ እየጨመረ ነው›› ተብሎለታል።
በአገሪቱ ዓምናና ዘንድሮ ስንዴ የተሸፈነው መሬት 2ነጥብ8 ሚሊዮን ሔክታር ነው፤ በበጋ ወቅት ይመረታል ተብሎ የታሰበውን 50 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴን ሳይጨምር ከ108 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ስንዴ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች እንዲነቃቁ የሚያስችል ሞተር ነው። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩትም፤ የስንዴ ልማቱ በአገር ውስጥ ላሉ ከ440 በላይ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትን ሙሉ በሙሉ በአገር አቅም መሸፈን የሚያስችል ነው። ከዚህም ባለፈ ስንዴን በጥሬው ብቻ ሳይሆን እሴት ጨምሮ ፓስታ፣ ማካሮኒና የመሳሰሉትን ምርቶች በማቀነባበር ወደ ውጭ ለመላክ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በትኩረት እንደሚሠራበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ስንዴን ለውጭ ገበያ አቅርባለሁ ስትል፣ ዘገባው በጣም የተጋነነና ከሁኔታዎች ጋር ያልተገናዘበ ነው በማለት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር። ከዚህም አንፃር የኢትዮጵያ የምግብ እጥረት ችግር የማይፈታ ነው ብለው የሞገቱም ነበሩ። ሆኖም ኢትዮጵያ የተናገረችውን እውን ማድረግ ችላለች። ይህንኑ አስመልክተውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ኢትዮጵያ ከስንዴ እርዳታ መላቀቅና ወደ ውጭ መላክ አትችሉም ያሉንን ችለን በማሳየታችን ኩራት ተሰምቶናል›› ብለዋል።
በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚመረት ቢሆንም በዋናነት ስንዴ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በስፋት ይመረታል። በአገሪቱ ከሚመረተው የስንዴ ምርት ውስጥ 54 ነጥብ 4 በመቶ ከኦሮሚያ የሚገኝ ሲሆን 27 በመቶ ከአማራ፤ 8ነጥብ 7 በመቶ ከደቡብ ሕዝቦች እንዲሁም 6ነጥብ 2 በመቶ ከትግራይ የሚገኝ ነው።
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትም የሶማሌ፣ የቤኒሻንጉል፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማን እና የመሳሰሉት ክልሎች ኃይላቸውን አስተባብረው ስንዴን ማምረት ጀምረዋል። የእነዚህ አካባቢዎች ምርታማነት ሲጨምርም ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ያላት ስንዴን የማምረት ታሪክ በእጅጉ የሚቀይረው ይሆናል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ስንዴ አምራች አገር ለመሆን በቅታለች። የአፍሪካ አገራት ስንዴን ከውጭ በመቀበል የሚታወቁ ናቸው። ስንዴንም ለማግኘት በርካታ ውጣውረዶችን ማለፍ ይገባቸዋል። በዩክሬንና በራሽያ ጦርነትም በግልጽ እንደታየው በዓለም ላይ በሚነሱ መስተጓጎሎች የቅድሚያ ተጠቂዎቹ የአፍሪካ አገራት ናቸው። በዩክሬንና በራሽያ ጦርነትም በተከሰተው የስንዴ እጥረት እስከ 300 ሚሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ ለርሃብ እንደሚጋለጥ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግዙፍ ሚዲያዎቻቸው ጭምር በስፋት የዘገቡት ነው።
ኢትዮጵያ ስንዴ አምራችና ላኪ አገር መሆኗ በስጋት ውስጥ ላሉት የአፍሪካ አገራት ትልቅ እፎይታን ይዞ የሚመጣ ነው። ይህንኑ ሃቅ መሠረት በማድረግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶክተር) በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ‹‹ኢትዮጵያን ኤይድ›› በሚል ስንዴ ለመለገስ ተግተን እንሠራለን ነው ያሉት። በዓለም ላይ የተፈጠረውን የስንዴ ገበያ ችግር ለማቃለልም ኢትዮጵያ የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጸዋል።
“ Index box market intelligence ” የተሰኘ የመረጃ መረብ ይፋ እንዳደረገውም፤ የአፍሪካ አገራት የስንዴ ፍላጎት እየጨመረ ነው። እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2012 ብቻ የአፍሪካውያን የስንዴ ፍላጎት በ1 ነጥብ 3 በመቶ ጨምሯል። ይህ አሃዝ በቀጣዮቹ አመታት እንደሚጨምር የመረጃ መረቡ ትንበያውን አስቀምጧል። ይህ ደግሞ እንደኢትዮጵያ ላሉ ስንዴ አምራችና ላኪ አገራት ጥሩ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው።
ወደ አፍሪካ ከሚገባው ስንዴ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን ምርት የሚወስዱት ናይጄሪያ፣ አልጄሪያና ግብጽ ናቸው። የጎረቤታችን ኬንያ ፍላጎትም በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል። ዘንድሮም ኢትዮጵያ ኬንያን ጨምሮ ወደ ስድስት አገራት የስንዴ ምርቷን ለመላክ ዝግጅቷን ጨርሳለች። አሁን በተጀመረው ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ሂደት ከኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ሌሎች አገራት ጋር ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችል ነው።
በዚህ ዓመት ከአገር ውስጥ ፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚኖር በመተንበይ፤ የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የስንዴ ኤክስፖርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የኤክስፖርት ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ግርማ ብሩ መናገራቸውም ይህንኑ እውነታ ታሳቢ በማድረግ ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም