ከስኬቶቻችን የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ለሰላማችን ዘብ ልንቆም ይገባል

አዲስ ዓመት ሰዎች ተስፋ የሚያደርጉበት፣ በጎ ነገር ለማድረግ የሚነሳሱበት፣ የተለያዩ እቅዶችን ለመፈጸም ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል:: በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከክረምቱ የጨለማ ወቅት ወጥተው ወደ አዲሱ ዘመን እና ወደ ብርሃን የሚሸጋገሩበት ስለሆነም በደስታ ይቀበሉታል::

የዘመን መለወጫን ፣ መስቀል ፣ የነብዩ መሐመድ ልደት (መውሊድ)በዓላትን በተከታታይ አክብረን የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ደግሞ በዝግጅት ላይ እንገኛለን:: እነዚህን በዓላት ተከትሎ ደግሞ ከመስከረም 17 ጀምሮ ደግሞ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን ይከበራል:: የዓለም ቱሪዝም ቀን ሲከበር የተለያዩ መርሀ ግብሮች ይኖሩታል:: ታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን የመጎብኘት፣ቀኑን አስመልከቶ ፓናል(ውይይቶች) ማካሄድ፣ ጥቂቶቹ ናቸው::

የጀመርነው 2016 ዓመተ ምህረት በጎ ነገሮችን ከመባቻው እንካችሁ እያለን ይመስላል:: በጎ ነገሮቹ ሐሴት የሚያጭሩ ብቻ ሳይሆን፣ ዕሴት የሚጨምሩም ናቸው:: አንደኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 4ተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ያበሰረው ዜና ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የግድብ ግንባታውን መጀመር በደስታ እንደተቀበለው ሁሉ፤የግድቡ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት የመጠናቀቁን ብሥራት ሲሰማ ደግሞ የደስታ ስሜቱ ከፍ እንደሚል መገመት አያዳግትም::

የ4ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ተከትሎ የግድቡ ተጨማሪ /አምስት/ ተርባይኖች ወደ ሥራ ይገባሉ መባሉም ደስታውን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።ለብዙ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋን የሰነቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለጎረቤት ሀገሮችም በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ፣እንደሀገርም ከኤሌክትሪክ ሽያጭ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ጥቅሙን ዘርፈብዙ ያደርገዋል::

ጎረቤት ሀገሮች ከኢትዮጵያ በሚያገኙት ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ በሀገራቱ መካከል የሚኖረው የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ የተሻለ እድል ይፈጥራል::

መስከረም 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ በተካሄደው 45ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ጉባዔ ላይ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የጌዴኦ መልክአ ምድርን በዓለም አቀፍ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)መመዝገቡ ደግሞ ሌላው የአዲስ ዓመት የብሥራት ዜና ወይንም መልካም እሴት ነው::

የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስነት በተመዘገበበት በዚህ ዓመት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክም በተመሳሳይ መመዝገቡ በደስታ ላይ ደስታን ፈጥሯል:: ከቱሪዝም ኮሚሽን ማኅበራዊ ሚዲያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የጌዴኦ መልክዐ ምድር በውስጡ በርካታ እሴቶችን አካትቷል:: የመሬት አያያዙ፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ትክል ድንጋዮች፣ (በዞኑ የተለያዩ ሥፍራዎች ከ6ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮች መኖራቸው) የዋሻ ላይ ጽሑፍ እና በባሕላዊ መንገድ ብቻ የሚተዳደሩ ደኖች ጥቂቶቹ ይጠቀሳሉ::

በ1962 ዓ.ም የተቋቋመው የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የቆዳ ሥፋቱ 2150 ካሬ ኪ.ሜትር፤ የመሬት ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ ከ1ሺህ500 እስከ 4ሺህ337 ሜትር ይደርሳል:: በፓርኩ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ትልቁ ተራራ ቱሉ ዲምቱ አንዱ ነው:: ለፓርኩ መመስረት በቀዳሚነት ምክንያት ከሆኑት መካከል ብርቅዬ የእፅዋት እና የዱር እንስሳት ዝርያዎች መገኘታቸው ነው:: በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ በጥናት ከተለዩት 1ሺህ660 የእጽዋት ዝርያዎች (40 በመቶ የሚሆኑት የመድኃኒትነት ፋይዳ ያላቸው)፤ 177 ዝርያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው::

ከዱር እንስሳት ዝርያ አንጻርም በሁሉም ምድቦች ብርቅዬ ዝርያዎች የተመዘገቡበት ፓርክ ነው:: ለአብነትም በሀገሪቱ ውስጥ ከተመዘገቡት 57 የአጥቢ ዝርያዎች፤ 22 ብርቅዬ ዝርያዎች በባሌ ተራራዎች ፓርክ ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው:: ቀይ ቀበሮ፣ የደጋ አጋዘን፣ የባሌ ጦጣ በዋቢነት እንደሚገኙበት ከቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል::

ብሔራዊ ፓርኩ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የውሃ ማማ ያሰኙት ከፍታማ ቦታዎች መካከል ትልቁን ድርሻ የያዘ ነው:: ከ40 በላይ ለሚሆኑ ወንዞች መነሻ ሲሆን፤ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑት እንደ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዱመል፣ ወልመል፣ ያዶት ወንዞች ይገኙበታል:: ከብሔራዊ ፓርኩ የሚነሱ ወንዞች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወደ 30 ሚሊዮን ለሚሆኑ የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ሱማሌ እና ሰሜን ኬንያ ሕዝቦች አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው::

በሳዑዲ አረቢያ በተካሄደው በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ጉባኤ ሁለቱ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገባቸው ለኢትዮጵያ የምስራች ነው::

የዘንድሮ የዓለም የቱሪዝም ቀን ‹‹ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት- አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ44ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው። ይህም ሀገራችን እመርታ ያሳየችበትን ከአረንጓዴ አሻራችን ጋር የሚስተካከል መሪ-ቃል መሆኑ ይበልጥ ድምቀት ይሰጠዋል። ኢትዮጵያን በቱሪዝምም ሆነ በአረንጓዴ ልማት ያላትን ተቀባይነት ይበልጥ የሚያጎላ ይሆናል::

በዘንድሮው ዓመት በዮኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመረጡት የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርም ሆነ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በደንና ተፈጥሮ ልማት በሕዝቡ በትውፊት ለረጅም ጊዜ ተጠብቀው መኖራቸውም ‹‹ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት- አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም›› የሚለው የቱሪዝም መሪ -ቃሉ በራሱ የሚገልፀው ነገር እንዳለ ያሳያል::

እርግጥ ነው ቀደም ብሎ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ቦታዎች የሚጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች በተለይ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ሲጎበኙ እንደ ነበር ይታወቃል:: በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ቅርስነት መመዝገቡ ግን ቱሪስቶችን የበለጠ እንዲስብ፣ የበለጠ ገቢ እንዲያመነጭ በር የሚከፍት እንደሚሆን ይታመናል::

ከነዚህ የአዲስ ዓመት የሀገር ብስራቶች / ስኬቶቻችን/ በአግባቡ ተጠቃሚ ለመሆን ግን ከሁሉም በላይ ለሰላማችን ዘብ ልንቆም ይገባል:: ለዚህ ደግሞ የግጭት መንገዶችን በሚቻለው አመራጭ ሁሉ መዝጋት፤ ችግሮችን ለዘለቄታው በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር ይጠበቅብናል።

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You