አሸባሪው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሰላም አማራጮችን ባለመቀበል ሦስተኛ ዙር ወረራ ፈጽሟል። በወረራ በያዛቸው አካባቢዎችም መገለጫው የሆነውንና የለመደውን ግድያ፣ ዝርፊያና ውድመት እየፈጸመ ይገኛል። መንግሥትም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አሁንም ቁርጠኛ እንደሆነና የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገርን አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመግለፅ የሰላም እጆቹን ሳያጥፍ ወረራውን የመቀልበስ ስራ እየሰራ ይገኛል።
ታዲያ የቡድኑን ወረራ ለመቀልበስና ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታም ይሆኑ ዘንድ በጥምረት ሆኖ ወረራውን በጀግንነት እየመከተና እየቀለበሰ የሚገኘውን የጸጥታ ኃይል መደገፍና ማጠናከር ወሳኝ ግብዓት ነው። በዚህ ረገድ ትኩረት የሚሹ ጥቂት ጉዳዮችን በዝርዝር መመልከት ያስፈልጋል። ሕዝቡና መንግሥት ለጸጥታ ኃይሉ የሚያደርገው ድጋፍ በተለያዩ መልኮች ሊገለገጽ የሚችል የደጀንነት ተግባር ነው። ምግብና መጠጥ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ ደም መለገስ፣ በሞራል ማበረታታት … ድጋፉ ከሚገለጽባቸው መንገዶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሕዝቡ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት የሕግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻዎች ለጸጥታ ኃይሉ ያደገው ድጋፍ እጅግ የሚደነቅ እንደነበር ታይቷል። ምግብና አልባሳትን አቅርቧል፤ ቁስለኞችን ተንከባክቧል፤ የጸጥታ ኃይሉን በሞራል አበረታትቷል፤ ከሠራዊቱ ጋር ተሰልፎም ተዋግቷል፤ በአጠቃላይ ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሳይሰስት ሰጥቷል። የጸጥታ ኃይሉ ስለሕዝቡ ደጀንነት የሰጠው ምስክርነት የሚዘነጋ አይደለም። ይህ የሕዝቡ ደጀንነትም የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻዎቹ በድል እንዲጠናቀቁ አስችሏል።
ታዲያ አሁንም ጥምር ጦሩ ሕወሓት የከፈተውን ወረራ በመቀልበስ አስተማማኝ ድል እንዲያስመዘግብ ሕዝባዊ ደጀንነቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ሕዝቡ በአሉባልታዎች ተደናግጦ አካባቢውን መልቀቅ የለበትም። ከዚህ ቀደም ለጸጥታ ኃይሉ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አሁንም አጠንክሮ ማስቀጠል አለበት። በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ከሚገኘው ሕዝብ በተጨማሪ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኘውም ሕዝብ ለጸጥታ ኃይሉ ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን ማረጋገጥ ይገባዋል። በእርግጥ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያለው ሕብረተሰብ አሁንም ለጸጥታ ኃይሉ ደጀንነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው። ይህ ደጀንነት ሀገር አቀፍ ሆኖ አሁን ካለው የበለጠ መጠናከር አለበት።
የመረጃ ፍሰት አመራርና አስተዳደርም ሌላው በጥብቅ ሊታሰብበትና ችላ መባል የሌለበት ጉዳይ ነው። ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የመረጃዎች ተደራሽነት ጥንቃቄ ይፈልጋል። መንግሥት፤ ሕወሓት የከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ ምላሽ መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ‹‹አክቲቪስት›› ተብዬዎች ዘንድ የሚታየው መረን የለቀቀ የመረጃ አያያዝና አሰጣጥ ጉዳይ የሚያስደነግጥና የሚያሳፍር ነው።
‹‹የመረጃ ባለቤት ነን›› ብለው መረጃ የሚያቀርቡ እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ከመረጃ አያያዝና አቀራረብ ሥርዓት ጋር የማይተዋወቁ፣ የውሸት መረጃ በማሰራጨት የተካኑ እንዲሁም የመረጃን ትርጉምና አስፈላጊነት የማያውቁ ናቸው። የእነዚህ ‹‹አክቲቪስቶች›› መረጃዎች በውሸት የታጨቁ፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ወቅታዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ እና ማሕበረሰባዊ እሴቶችን የጣሱ የጥራዝ ነጠቆች ፕሮፖጋንዳዎች ሆነው ታዝበናል።
ሕወሓት የከፈተውን ወረራ ለማስቆም የሚደረገውን ዘመቻ በተመለከተ በአንዳንድ አክቲቪስቶች በኩል የሚቀርቡት መረጃዎች ለሕወሓት ወታደራዊ ዘመቻ አጋዥ የሆኑና የሕዝብንም ሆነ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ሆነው ይስተዋላሉ። የአክቲቪስቶቹ መረጃዎች አብዛኞቹ በሀሰተኛ ዜናዎች የተሞሉ ናቸው። የጥምር ጦሩን እንቅስቃሴና ብዛት ይፋ የሚያደርጉ ብዙ ‹‹አክቲቪስት›› ነን ባዮችም አሉ። ሕዝቡ ተደናግጦ አካባቢውን እንዲለቅ ምክንያት ሲሆኑ ተስተውሏል። ሠራዊቱ የሚጓዝበትን አካባቢ በፎቶ ጭምር እያስደገፉ በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚያሰራጩ አካላት በዋጋ የማይተመን ውድ መረጃ ለሕወሓት አሳልፈው እየሰጡ እንደሆነ አያውቁም ማለት ሞኝነት ነው፤የሕወሓት ተባባሪዎች ናቸው ብሎ ማሰብም ሞኝ አያስብልም።
ይህ የባንዳነት ተግባር የሚታይበት የ ‹‹አክቲቪስቶች›› የመረጃ ስርጭት ተግባር፤ ለሕወሓት ዓለም አቀፋዊ ወዳጆች የሐሰት ዘመቻ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል። በኢትዮጵያ ላይ የሐሰት ዘመቻ የከፈቱ የሕወሓት ወዳጆች የእነዚህን ‹‹አክቲቪስቶች›› መረጃ በመያዝ መንግሥት ፀብ ጫሪ እንደሆነ አድርገው ስም ማጥፋታቸውን ተያይዘውታል። ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለሕግ ማስከበሩም ሆነ ስለሕልውና ዘመቻው የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ፀረ- ኢትዮጵያ ዘመቻ እንደነበር ይታወሳል።
ይህም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) ከማድረጉ ባሻገር የኢትዮጵያ ጠላቶች ‹‹ኢትዮጵያን ለመበታተን ከዚህ የተሻለ ጊዜ/እድል አናገኝም›› ብለው ታጥቀው እንዲነሱና በረጅም ጊዜ ታሪኳ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፤ ከኃይል ይልቅ ንግግርን ለማስቀደም እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ትብብርንና ወንድማማችነትን የሚያሰፍኑ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲመሰረቱና እንዲጠነክሩ ባላት ቁርጠኛ አቋም የምትታወቀው ኢትዮጵያ ስሟ እንዲጠለሽ በር ከፍቶ እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም።
በሌላ በኩል ሕ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ባሉ አጋሮቹ በኩል አገሪቱ ልትበታን እንደሆነና የፌዴራሉ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ አስመስሎ በርካታ የውሸት መረጃዎች እንዲሰራጩ አድርጓል። እነዚህን መረጃዎች ያዳመጡና የተመለከቱ ብዙ የውጭ አገራት ሰዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ መረጃዎቹን እንደወረዱ በመቀበል ከእውነት የራቀ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ተስተውለዋል። አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፣ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተማራማሪ ሆነው የሚንቀሳቀሱት እነዚህ የሕወሓት ወዳጆች፤ ወረራውን የመቀልበስ ስራውን አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ‹‹አክቲቪስቶች››ን መረጃ በመያዝ የለመዱትን ቅጥፈታቸውን ቀጥለውበታል።
መንግሥት የመረጃ ፍሰቱ ጉዳዩን በሚመለከተው አካል ብቻ ይከናወናል ብሎ ቢያሳውቅም፤ እንዲህ ዓይነት አደገኛ መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ ቁጥጥር እያደረገ ግን አይመስልም። ወረራውን ለመቀልበስ የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች በግልጽ እየታወቁ ሳለ፤ እንዲህ ዓይነት ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ‹‹እንዲያው ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱ ይቅርና ኮስተር ባለ ዓይን የሚያያቸው አንድም የመንግሥት አካል የለም እንዴ?›› ያስብላል።
መላው ኢትዮጵያዊ ለቡድኑ የጥፋት ተልእኮ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። በዚህ በኩል ምንም አይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም ። በአሁኑ ወቅት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ያለው የሀገሪቱ ሕዝብ ለጥፋት ሃይሉ የሰጠው ትኩረት እኩል ነው ለማለት አያስደፍርም። ብዙ ሰው ሀገሪቱ እጅግ ዘግናኝ ወንጀሎችን ከሚፈጽም እንዲሁም የግዛት አንድነቷን ለማሳጣት ቆርጦ ከተነሳ ሀገር አፍራሽ ቡድን ጋር እየተፋለመች እንደምትገኝ በአግባቡ የተረዳ ፤አንዳንዱም እውነታውን ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተል አይመስልም።
አሸባሪው ቡድኑ የአማራና የአፋር ክልሎች ብቻ አደጋ ተደርጎ መቆጠር የለበትም። በእርግጥ የክልል መንሥታት ሕወሓት የፈጸመውን ወረራ ማውገዛቸውና ወረራውን ለመቀልበስ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፤ሕዝብን አስተባብሮ ይህን የአጋርነት መልእክት ወደ ተግባር መለወጥም ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ችግር የሚወገደው በመላው ኢትዮጵያዊ ትብብር መሆኑ መዘንጋ የለበትም። በአጠቃላይ ሕወሓት የከፈተውን ወረራ ለመቀልበስና ድል ለማስመዝገብ ሁሉም ሕብረተሰብ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ ሕዝባዊ ደጀንነትን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ነው!
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2014