በየመን ጦርነት ውስጥ የአብዱራቡ መንሱር ሃዲን ‹‹መንግሥት›› በመደገፍ እየተሳተፈ የሚገኘው የሳዑዲ-ኤምሬቶች ጥምር ኃይል ሕፃናትን ለውትድርና መልምሎ እያዋጋ እንደሚገኝ አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ይፋ ባደረገው መረጃ አመልክቷል። ጣቢያው ከጥምር ኃይሉ የምልመላ ጣቢያ አገኘሁት ያለው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ለውጊያ የተመለመሉት ሕፃናት ሳዑዲ አረቢያ ከየመን ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች ከሀውቲ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ውጊያ የተሳተፉ ናቸው።
የሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጥምር ኃይል በየመን ጦርነት መሳተፍ ከጀመረ ወዲህ ለረሃብ የተዳረጉ ሕፃናት በሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ለውጊያ እንዲመለመሉ ተገድደዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ለውጊያ ተመልምለው በጦርነቱ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ የመናውያን ህፃናት መካከል ሁለት ሦስተኛው ለሀውቲ አማጺያን የሚዋጉ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ለሳዑዲ- ኤምሬቶች ጥምር ኃይል የሚዋጉ ናቸው።
ምንም እንኳን ሳዑዲ አረቢያና የመን ህፃናት በጦርነት ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክለውን ዓለም አቀፍ ስምምነት የፈረሙ አገራት ቢሆኑም፤ ሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ዓመት ከሱዳን የዳርፉርን ህፃናት እየመለመለች ለውጊያ አሰልፋለች የሚል ክስ ቀርቦባት ነበር።
አልጀዚራ በውጊያ ላይ የተሳተፉ ሕፃናትንና ቤተሰቦቻቸውን ጠይቄ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት፤ ጥምር ኃይሉ ሕፃናቱን ከሚመለምልባቸው መንገዶች አንዱ ለሕፃናቱና ለቤተሰቦቻቸው ክፍያ እንደሚፈፅምላቸው ቃል በመግባት ነው።
ልጃቸው በጥምር ኃይሉ ጦር ከተመለመለባቸው ቤተሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አሊ ሃሚድ፤ ልጃቸው ከአምስት ወራት በፊት በጥምር ኃይሉ ለውትድርና እንደተመለመለና ከዚያ ወዲህ ስለልጃቸው ምንም ነገር ሰምተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
በሳዑዲ-ኤምሬቶች ጥምር ኃይል ለውትድርና ተመልምሎ የነበረውና ከጥምር ኃይሉ የጦር ካምፕ አምልጦ ወደ ትውልድ መንደሩ የተመለሰው የ16 ዓመቱ ታዳጊ አህመድ አል-ናቂብ እንደሚናገረው፤ በሳዑዲ አረቢያና በየመን ድንበር ላይ የምትገኘው አል- ቡቃ ለውጊያ የተመለመሉ የመናውያን ሕፃናት የውጊያ ስልጠና የሚወስዱባት ግዛት ናት። ሕፃናቱን የሚመለምሏቸው ሰዎችም ለሕፃናቱ የሚነግሯቸው ለውትድርና ሳይሆን ለሌላ ስራ እንደሚፈለጉ አድርገው ነው።
አልጀዚራ በጉዳዩ ላይ የሳዑዲ አረቢያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለትም በዘገባው ጨምሮ ገልጿል።
ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየመን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩ ወዲህ ከ10ሺህ የሚበልጡ ሰዎች እንደተገደሉና (ከነዚህም መካከል ከ60 በመቶ የሚበልጡት ሰላማዊ ዜጎች እንደሆኑ) ከዚህ የሚበልጡ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰውና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል በድህነት የሚወዳደራት የለም በምትባለው የመን እየተካሄደ የሚገኘው የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከተለው ረሀብና በሽታ የሀገሪቱን ዜጎች ስቃይና መከራ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎባቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በአንተነህ ቸሬ