የአልጀሪያው ፕሬዚዳንት አብደል አዚዝ ቡተፍሊካ አራተኛው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ከሚያበቃበት ከሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በፊት ሥልጣናቸውን እንደሚለቅቁ ከፕሬዚዳንቱ ቢሮ የወጣው መረጃ አመልክቷል። ‹‹አልጀሪያ ፕሬስ ሰርቪስ›› (Algeria Press Service) የተባለው መንግሥታዊ የዜና ወኪል ባሰራጨው ዘገባ እንዳመለከተው፤ ፕሬዚዳንቱ አራተኛው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ከሚያበቃበት ከሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በፊት ሥልጣናቸውን ይለቅቃሉ፤ በሽግግሩ ወቅት የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን በብቃት ማከናወን የሚያስችሏቸውን ርምጃዎችን ይወስዳሉ።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አልጀሪያውያን ባለፉት ሳምንታት የ82 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ሥልጣናቸውን እንዲለቅቁ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎችን ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ለ20 ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ከሕዝብ ዕይታ ርቀው ቆይተዋል።
በሚቀጥለው ወር መጨረሻ ላይ አራተኛ የሥልጣን ጊዜያቸው ከማለቁ በፊት ለአምስተኛ ዙር በፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ አስታውቀው የነበሩት ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ፤ ከሁለት ሳምንታት በፊት ደግሞ በምርጫው እንደማይወዳደሩና ምርጫው እንደተራዘመ ይፋ አድርገው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን እንደሚለቅቁ ይፋ ቢደረግም የአልጀሪያ ተማሪዎች ግን በዋና ከተማዋ አልጀርስ ጨምሮ በሌሎች በርካታ የአገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች እንዲደረጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
መሐመድ የተባለ የአልጀርስ ተማሪዎች ኅብረት አባል ‹‹የፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ ሥልጣን መልቀቅ ብቻውን በቂ አይደለም። ተቃውሟችንን ማሰማት ካልቀጠልን አልጀርያ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች ጊዜ ጀምሮ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ አገሪቱን መግዛቱን ይቀጥላል። አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ያስፈልጋል›› በማለት ለአልጀዚራ ተናግሯል።
ነዋሪነቷን በአልጀርስ ያደረገችው አመል የተባለች የኮምፒውተር ባለሙያም፤ በመሐመድ ሃሳብ ትስማማለች። ‹‹ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ ከአገዛዙ ሰዎች መካከል አንዱ እንጂ የአገዛዙ ሁሉነገር ባለመሆናቸው የእርሳቸው ከሥልጣን መልቀቅ ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም። ገዢው ቡድን በቡተፍሊካ ሥልጣን መልቀቅ ሊሸውደን እየሞከረ ነው›› ብላለች።
አሚና የተባለች ተማሪ በበኩሏ፤ የፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ለመልቀቅ መወሰን ሙሉ ድል እንዳልሆነ ትናገራለች። ‹‹ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸው የመጀመሪያ እርምጃ እንጂ የመጨረሻ ግብ አይደለም። ሁሉም የአገዛዙ ባለሥልጣናት ከሥልጣን መልቀቅ አለባቸው። አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድ ሆነን አገዛዙን በኅብረት መቃወም አለብን››በማለት ለአልጀዚራ ተናግራለች።
ፕሬዚዳንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ እንዲወስኑ ያስገደዳቸው ምክንያት አልጀሪያውያን የሚያሰሙት ተደጋጋሚ ተቃውሞ ነው ቢባልም ዋነኛው ምክንያት ግን የአገሪቱ ብሔራዊ ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀኔራል አህመድ ጋይድ ሳላህ ፕሬዚዳንቱ አገር ለመምራት ብቁ አይደሉም ብለው ማመናቸውና ሥልጣናቸውን እንዲለቅቁ ግፊት ማድረጋቸው ነው ተብሏል። ይህ የአዛዡ ጫናም በጦሩና በፕሬዚዳንቱ ታማኞች መካከል ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም፤ የአገሪቱ ሕገ- መንግሥታዊ ምክር ቤት በፕሬዚዳንቱ አገር የመምራት እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካና ጠቅላይ ሚኒስትር ኖርዲን ቤዶው እሁድ ዕለት አዲስ መንግሥት ሰይመዋል። አዲሱ መንግሥትም ምርጫ ተካሂዶ ሽግግሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አገሪቱን ይመራል ተብሏል።
ይሁን እንጂ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞችና የተቃውሞ ሰልፍ እያደረጉ የሚገኙ አልጀሪያውያን የፕሬዚዳንቱ ርምጃ በሥልጣን ላይ የሚቆዩበትን ጊዜ ለማራዘም የተሸረበ ሴራ ነው በማለት አጣጥለውታል።
የአልጀዚራው ዘጋቢ ኢምራን ካሃን ከቱኒስ ባሰራጨው ዘገባ፤ የፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ ከሥልጣን መልቀቅ የተቃውሞ ሰልፈኞች ካሰሟቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ቢሆንም፤ አልጀሪያውያን ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ እስከተወገደ ድረስ ችግሩ አይፈታም ብለው በማመናቸው የተቃውሞ ሰልፎች እንደሚቀጥሉ አመልክቷል።
‹‹የአገሪቱን ጦር ጨምሮ በርካታ አካላት ከፕሬዚዳንቱ ጋር ግንኙነት አላቸው። የአገሪቱ መንግሥት የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ለመልቀቅ መወሰን ተቃውሞውን ያረጋጋዋል የሚል እምነት ቢኖረውም በተግባር የሚታየው እውነታ ግን እርምጃው ምንም ለውጥ ማምጣት አይችልም›› በማለት ገልጿል።
በተቃውሞ ሰልፉ ላይ እየተሳተፈ ከሚገኘው ሕዝብ መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች እንደሆኑም ታይቷል። አልጀሪያውያን ወጣቶች በሥራ እድል ማጣት ምክንያት ለአደጋ በሚያጋልጡ ጀልባዎች ጭምር ወደ አውሮፓ ሲሰደዱ ይስተዋላል። የወጣቶቹ ተቃውሞም መነሻው ይኸው ስር የሰደደ የሥራ አጥነት ችግር እንደሆነም ይነገራል።
እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ አልጀሪያን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩትና በአልጀሪያ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛና ጠንካራ ሰው እንደነበሩ የሚነገርላቸው አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ፤ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት እንዲሁም ከሙስናና ከሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ በተነሱባቸው ጠንካራ ተቃውሞዎች ምክንያት ለ20 ዓመታት የቆዩበትን ወንበር ሊለቅቁ ተገድደዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2011
በአንተነህ ቸሬ