የእኛ ሀገር የስብሰባ ባህል ሁሌም ያስቀኛል። ስብሰባ እንደመውደዳችን መጠን አሁንም ችግራችን አለመቀነሱ ይገርመኛል። የስብሰባ ፍቅራችን ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ስብሰባችን ወደ መፍትሄ አይወስደንም። ከተሰበሰብን በኋላ ስንወጣ ውጊያችችንን እንቀጥላለን።እንደ ስብሰባ ወዳድነታችን እንኳን የእኛን የቀረውን አለም ችግርም መፍታት ይገባን ነበር።ነገር ግን እስካሁን በንግግር የፈታነው ብዙ ነገር የለም።ብዙው ችግራችን አሁንም መፍትሄው እየተፈለገ ያለው በጉልበት ውስጥ ነው።
ስለ ስብሰባ ለማውሳት የፈለግኩት ሰሞኑን ከገጠመኝ ነገር በመነሳት ነው።አንድ ወዳጄ ሰሞኑን ለአንድ ጉዳይ እንደምፈልገው እና አጭር ስብሰባ እንደሚኖረን ነገርኩት። የሰጠኝ መልስ አስገረመኝ። ስንት ይከፈለኛል አለ።እንዲህ አይነት መልስ ሰምቼ ስለማላውቅ ደነገጥኩ። ይህ ወዳጄ ረዘም ላለ ጊዜ በርከት ባሉ የውጭ ሀገራት በስራ የተዘዋወረ በመሆኑ ምናልባትም የእነሱ ተጽእኖ ሊኖርበት እንደሚችል ጠረጠርኩ። ከዚያም ለምን እንደዚህ እንዳለኝ ጠየቅኩት። የእሱ ስራው በቀን ውስጥ በርካታ ስብሰባዎችን ማካሄድ የሚፈልግ ነው። ስለዚህም ስብሰባዎችን የሚለካቸው እና ውጤታማ መሆናቸውን የሚለካው ባለቸው ውጤታማነት እንደሆነ አስረዳኝ። ከእያንዳንዱ ስብሰባም የሆነ አይነት ትርፍ ይዞ መውጣት እንዳለበት እና ይህ ደግሞ አለምአቀፍ ልማድ እንደሆነ ነገረኝ።
የእኛን ስብሰባ መልሼ አስተዋልኩት።ስብሰባችን በአብዛኛው አላማው ምን እንደሆነ አይታወቅም። የብዙው ስብሰባ ግብ ራሱ ስብሰባው መካሄዱ ብቻ ነው። ከስብሰባው ምን ውጤት እንደሚጠበቅ አይታወቅም። እንዲሁ ሰብሳቢው የልቡ እስኪደርስ ድረስ የፈለገውን ያወራል ከዚያ ተሳታፊዎች ደግሞ የመሰላቸውን ይጨምሩበታል፤ በመጨረሻ ስብሰባው በመታከት ያልቃል። ምናልባትም በነዚህ ስብሰባዎች አትራፊ የሚሆነው ለተሳትፎ የሚከፈለው ሆቴል ብቻ ነው።
አንዳንዴ ስብሰባዎቻችን ላይ የምናየው ነገር ከማሳዘን አልፎ ያስቃል። ለምሳሌ አንዳንዱ ተሳታፊ እድል ሲሰጥ ተሻምቶ እድል ይወስድና ከአጀንዳ ውጪ የግል ጉዳዩን ይዘበዝባል። ሌላው ደግሞ ይነሳና የስብሰባው መዘጋጀት በጣም ጠቃሚ እንደሆነ እንዲሁም አቅራቢው ጥሩ አድርጎ እንዳቀረበው፤ መሰል ስብሰባዎች በቀጣይም መዘጋጀት እንዳለባቸው ይዘበዝብና ፍሬ ጉዳዩን ሳያወራ ይጨርሳል። አንዳንዱ ደግሞ ምን አስተያየት መስጠት እንደፈለገ ማሰብ የሚጀምረው ማይክራፎን ከተቀበለ በኋላ ነው። አስቦ ሳይሆን የሚያወራው እያወራ ነው የሚያስበው። ስለዚህም ንግግሩ ፍሬ ጉዳዩም ሆነ መጨረሻው አይታወቅም።
አዘጋጆቹስ ቢባል የባሰው አስቂኝ አይደሉ እንዴ። አብዛኞቹ ስብሰባውን የሚያዘጋጁት እቅድ ላይ ስላለ ነው እንጂ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አይደለም።እንዲያው በጀቱ ከሚባክን እንጠቀመው ተብሎ ነው ስብሰባው የሚዘጋጀው። በዚያ ላይ ስብሰባው ላይ የሚታደመው ሰው ከስብሰባው ላይ ምንም ግንኙነት የሌለው ነው። ስለ ስፖርት በሚካሄድ ስብሰባ ላይ የሚጠሩት የሸማቾች አባላት ይሆናሉ። በዚህም የተነሳ ከተሳታፊው ህዝብ አብዛኛው ስብሰባው ስለ ምን እንደሆነ ሳይገባቸው እና የረባ ተሳትፎ ሳያደርጉ እንዲሁ አጨብጭበው አበል ተቀብለው ይሄዳሉ።አንዳንዴ ደግሞ ስብሰባው ላይ የቀረበውን ሃሳብ ብቻ በአድናቆት የሚቀበሉ ሰዎችን ብቻ መርጠው ይጠሩና ስብሰባውን የቤተ ዘመድ ጉባኤ ያደርጉታል።
ዛሬ ላይ አለም ስብሰባ የሚባለውን ነገር በብዙ መልኩ እየቀየረው ነው።ቴክኖሎጂ የሰውን በአካል መገናኘት በጣም ቀንሶታል።ኢሜይል ፤ ቴሌግራም፤ ዙም እና መሰል ቴክኖሎጂዎች ሰዎች ቢሮአቸው ውስጥ ሆነው ስራቸውን እየሰሩ እንዲሰበሰቡ የሚያደርግ ዘመን ላይ ደርሰናል።ስብሰባዎች ላይ የሚጠሩት ሰዎች የሚመለከታቸው ብቻ ሆነዋል።ስብሰባው የሚወያይበት አጀንዳ ተመርጦ የሚደረግበት ሰአትም ተመጥኖ ፤ ግቡም ታውቆ ነው የሚካሄደው።ከሁሉም በላይ የስብሰባ ልማዳቸው የጉልበት ተግባር እንዲቀር አድርጓል ፤ ህዝባቸውም በቋሚነት ለወጥ ውስጥ እንዲኖር አድርጓል።
እኛ ጋር ነገሩ በተቀራኒው ነው። አብዛኞቹ ስብሰባዎች አዲስ አጀንዳ የላቸውም። የዛሬ አመት ያወራንበት አጀንዳ ዘንድሮም አለ። አምና ከስብሰባው በኋላ ያቋቋምነው ኮሚቴ ከሽፎ ዘንድሮም ሌላ ኮሚቴ እናቋቁማለን። አምና ስብሰባው ላይ መካሄዱን አድንቀው አስተያየት የሰጡ ሰዎች ዘንድሮም ስብሰባው መዘጋጀቱ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ። አምና ስብሰባው ላይ ሲያንቀላፉ የነበሩ ሰዎች ዘንድሮም እያንቀላፉ ነው። ከአምናው የተለየ አንድ አዲስ ነገር ቢኖር አምና ለስብሰባ ከወጣው ገንዘብ ዘንድሮ የሚወጣው መብለጡ ብቻ ነው።
የምር የስብሰባ ባህላችን መልሶ መከለስ አለበት። የሆነ ጊዜ እንደውም ህግ ሊወጣለት ነው ሲባል ደስ ብሎኝ ነበር፤ ኋላ ላይ ግን ወሬውም ቀረ። ስብሰባ ግን በአዲስ መልኩ መቃኘት አለበት። ስብሰባዎቻችን በቀናት እና በሰአታት ሳይሆን በደቂቃዎች መለካት አለባቸው። በተሳታፊ ብዛት ሳይሆን በተሳታፊዎች አግባብነት መመዘን አለባቸው። ከወጣበት በጀት እኩል ያስገኘው ግብአት መታየት አለበት። ከተሳታፊ ብዛት ይልቅ የተገኘው ግብአት ዋነኛ ቁምነገር ሊሆን ይገባል።
ከሁሉም በላይ ስብሰባ የህዝብን ችግር በቋሚነት በሰላማዊ መንገድ የመፍታትን ባህል እንድናዳብር ካላገዘ እና ለአበል ብቻ የምንፈልገው ከሆነ፤ ነገር ግን ሁሌም ችግር የምንፈታው በጦርነት ብቻ ከሆነ ችግር ስብሰባዎቻችን ለባህል ለውጥ አልጠቀሙንም ማለት ነው። ስለዚህም ስብሰባዎቻችንን መልሰን መቃኘት አለብን።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም