“የዋህ፤ ጨዋታ የሚወድ ቡድኑን ከልምምድ በኋላ ማዝናናት ከተፈለገ ከፊት የሚቀድመው የለም፤ ኃይለኛ ተቆጪና ለጸብም ቅርብ ነው” ይላሉ በቅርብ የሚያውቁት። በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተጫወተባቸው ክለቦችና በብሔራዊ ቡድን በልምምድ ሜዳ ጭፈራ፣ ጨዋታና ዜማዎች ካሉ እሱ በዚያ አለ ማለት ነው። በቡድን አጋሮቹም ይበልጥ ይወደዳል። ፊቱን አኮሳትሮ ዘቡን ይጠብቃል፤በቁጣ ተከላከዮችን ይመራል፤ሰዓት መግደልና ፍፁም ቅጣት ማዳን የግሉ ነው፤ በአንድ ጨዋታ ከአንድ በላይ ፍጹም ቅጣት ምትና የመለያ ምቶችን ማክሸፍ መለያው ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ(ቦይሴ)።
ሲሳይ የቻን ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎች ወቅት በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ከ31 አመታት በኋላ እኤአ 2013 ላይ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ተከትሎ በእግር ኳሱ ከፍተኛ መነቃቃት ነበር። የዚያ ትውልድ ታሪካዊ ተጫዋቾችና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ከአፍሪካ ዋንጫው ማግስት በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የቻን ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳተፉ። ለዚህ ተሳትፎም የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ከሜዳቸው ውጪ ተፋልመው ማለፋቸው አይዘነጋም። በተለይም በዚያ የመጨረሻ የማጣሪያ ፍልሚያ የዋልያዎቹ ቋሚ ግብ ጠባቂ የነበረው ጀማል ጣሰው ጨዋታው በመለያ ምት እንደሚጠናቀቅ ከአሰልጣኙ ጋር ቀደም ብለው በመግባባት የመለያ ምት የማዳን የተሻለ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ ተቀይሮ እንዲገባ አደረጉ። ሲሳይም አላሳፈራቸውም።
ተቀይሮ ገብቶ ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ዋልያዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቻን ዋንጫ አበቃቸው።
ከዘጠኝ አመታት በኋላ ዋልያዎቹ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመሩ በቀጣይ አመት በአልጄሪያ አዘጋጅነት በሚካሄደው የቻን ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ትናንት ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር የመጨረሻውን የዘጠና ደቂቃ ፍልሚያ ከሜዳቸው ውጪ አድርገዋል። ዋልያዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍቸውን ያረጋገጡት በተመሳሳይ ሩዋንዳን በሜዳዋ ገጥመው ሲሳይ ባንጫ ባዳናቸው ሁለት የመለያ ምቶች ነበር። ዋልያዎቹ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ከሳምንት በፊት አድርገው ካለ ግብ አቻ እንደመለያየታቸው ታሪክ ራሱን ይደግማ የሚል ጉጉት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ፈጥራል። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ሲሳይ ባንጫን እንድናስታውስ ያደረገንም ይህ እውነታ ነው።
ዋልያዎቹ ከ31 አመት በኋላ ወደ 2013ቱ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለሱ አዲስ አበባ ላይ ጥምቀት 4 ወሳኙን ድል ከማስመዝገባቸው አስቀድሞ ተጋጣሚያቸው ሱዳን ኦምዱርማን ላይ 5ለ3 ማሸነፏ አይዘነጋም። በዚያ ውዝግቦች በበዙበት ጨዋታም ሲሳይ የዋልያዎቹ የግብ ዘብ ነበረ። በወቅቱ የጨዋታው ዳኛ ዋልያዎቹ ላይ ብዙ በደል ፈጽመዋል። በዚህም ንዴቱን በተለያየ መንገድ ሲገልጽ የነበረው ሲሳይ ነው። ብዙ ግጭቶች ከሜዳ ውጪና ሜዳው ውስጥ ተከስቶ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ነበር ። ሲሳይም በዚህ ነውጥ በበዛበት ጨዋታ በቀይ ካርድ ሰለባ ከሆኑ ተጫዋቾች አንዱ ነበር። በአፍሪካ ዋንጫም በመጨረሻው የናይጄሪያ ጨዋታ የመሰለፈ እድል የተሰጠው ሲሳይ ከሜዳ በቀይ ካርድ ወጥቷል፤ ከገዛ ቡድኑ ተጫዋቾች ጋርም ሲጨቃጨቅ ታይቷል። 2003 የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ የነበረው ሲሳይ በብሄራዊ ቡድን አልተካተተም ነበር።
ከሩዋንዳ ጋር የነበረውን ያን ታሪካዊ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ የዋልያዎቹ ዋና ግብ ጠባቂ የነበረው ጀማል ጣሰው ከሃትሪክ ስፖርት ጋር ባደረገው አንድ ቃለ ምልልስ እንዲህ ሲል ያስታውሰዋል “የእውነት ሰው የሚያደርግህ አጠገብህ ያለው ሰው ነው። አጠገባችን የነበረው ፍቅርና ህብረት ነው ይህን ያመጣው… ከጨዋታው አንድ ቀን በፊት የበረኛ ልምምድ ስንሰራ ሲሳይ ሪጎሬ ሲያድን ጥሩ እንደነበር አይቼው ውስጤ አስቀምጬዋለሁ፣ የጨዋታ ቀን ደረሰ እዚህ 1ለ0 ረታን እዚያ 1ለ0 ተሸነፍንና ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት ልንሄድ ነው እያልኩ ነበር፣ ጨዋታው ሊያልቅ 10 ደቂቃ እንደቀረው ከጀርባዬ የነበረውና ተቀይሮ ሊገባ የተዘጋጀው ብርሃኑ ቦጋለ (ፋዲጋ) ነግሮኝ ነበር።
በዚያ ላይ እርሱ ገብቶ ሳላሀዲን ባርጌቾ ሊወጣ ሲል እኔ ወደቅኩ። ፊዚዮቴራፒስቱ ይስሀቅ ሽፈራው መጥቶ ምንድነው ምን ሆንክ ሲለኝ ሲሳይ ባንጫ እንዲገባ ብዬ ነው ስለው ደነገጠ.. ምንም አለመሆኔን ነግሬው ባሰብኩት መንገድ ሲሳይ ባንጫ ተቀይሮ ገባ። ያኔ ከኔነት ስር ወጥተን የህብረት ጉዞ ላይ ስለነበርን ደስ የሚል ጊዜ እንድናሳልፍ አድርጎናል። ለሀገርህ ስትሰራ ከኔነት ወጥተህ ወደ እኛነት መቀየር የግድ ይላል። ያኔም ሲሳይ ገብቶ አሸንፈን ወጣን። እኔ ገብቼ ሪጎሬ ሳላድን ብንሸነፍኮ ማንም አይጠይቀኝም ግን እርሱ ገብቶ ማሸነፋችን ክሬዲቱን ከፍ አድርጎልኛል ሁሌ ይሄ ቢኖር ደስ ይለኛል። መጀመሪያ ህሊናችን ነው የተደሰተው…. ጥቅሙ በኋላ ይመጣል፣ እኛነት ነግሶ በማሸነፋችን የማልረሳው ገጠመኝ ሆኖልኛል። እግር ኳስ ላይ ከእኔነት ወደ እኛነት የተለወጠ ቡድን ያሸንፋል።”
ሲሳይ በዚያ ወሳኝ ጨዋታ ዋልያዎቹን መለያ ምት በማዳን ብቃቱ ቢታደግም በውድድሩ ከቡድኑ ጋር አልተጓዘም። ከዚያ የቻን ማጣሪያ ጨዋታ በኋላ ዋልያዎቹ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ካላባር አቅንተው ናይጄሪያን ሲገጥሙ በቡድኑ ተጫዋቾች መካከል የነበረው ግጭትና አለመግባባት በቻን ውድድር እንዳላስመረጠው ኋላ ላይ የወጡ መረጃዎች ጠቁመው ነበር።
ሲሳይ ከካላባሩ ጨዋታ በኋላ በብሔራዊ ቡድንም በትልቅ ክለብም ለረጅም ጊዜ ተሰልፎ አልታየም። ዘንድሮ ግን በብሔራዊ ሊግ ለሮቤ ከተማ ተሰልፎ የድል ልምዱንና አቅሙን በመጠቀም ጥሩ ሲንቀሳቀስ ታይቷል። ሮቤ ከተማ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያድግም ሲሳይ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። ከሮቤ ከተማ ጋር ከነበረው ስኬታማ ጉዞ በኋላም ዳግም ለብሔራዊ ቡድን የመሰለፍ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሲሳይ ከደደቢት ጋር በ2005 የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ከመሆኑ በተጨማሪ አንድ ጊዜ የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ለመመረጥ በቅቷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2014