የበታችነት ስሜት በፈጠረበት አብሪት በ1967 ዓ.ም መጨረሻ ደደቢት በረሃ የወረደው አሸባሪው ሕወሓት፣ ማንነትና ምንነት ገና ጫካ ሳለ የተነገረና የታወቀ ጉዳይ ነው። ድርጅቱ ስልጣን ከያዘ በኋላም በጠብመንጃ ኃይል እየደፈጠጠ፣ በግፍ የንፁሃንን ሕይወት እየቀጠፈና ለመብታቸው የሚታገሉ ዜጐችን ዘብጢያ እያወረደ እውነተኛ ባህሪውን በገቢር አሳውቋል።
ድርጅቱ በወረራ የተረከበውን በትረ-መንግሥት አስጠብቆ በቆየባቸው አመታትም የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደሰም አቅልጦ፤ እንደብረት ቀጥቅጦ ለመግዛት እንቅፋት ይሆንብኛል ብሎ ያሰበውን ሁሉ ሲለው በዴሞክራሲ ስም እያላገጠ፤ ሲያሰኘው ደግሞ በጦር ኃይል እየደፈጠጠ ሲገዛ ኖሯል።
‹‹እንዳሻዬ አዛዥ ናዛዥ እንዳልሆን ያደርጉኛል›› በሚል ስጋት ከእሱ የተለየ አመለካከትና ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ የተለያዩ ቀለማ ቀለሞችን በመቅባት፣ የፈጠራ ስም በመለጠፍና ሰበብ አስባብ በመፈለግ በቀጥታም ሆነ በረቀቀ መንገድ ሰውሯል:: አስሯል:: ገድሏል:: አስገድሏል::
ቡድኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚፈፅመው የበደልና የግፍ ጽዋ ሞልቶ መፍሰሱን ተከትሎ፤ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በከፈሉት መራራ መስዋትነት ስልጣኑን ሳይወድ በግድ እጁ ተቆልምሞ ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት ከተባረረ እና መቀሌ ከመሸገ ወዲህም የቀደመ እብሪትና የጥፋት ሱሱ ሊላቀቀው አልቻለም::
የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በእርስ ለማናከስ ሌት ተቀን ድንጋይ ሲፈነቅል፣ወደ መቀሌ የሸኘውን ለውጥ ሲያጥላላና ሲቃወም የለውጡ ትሩፋት ለትግራይ ሕዝብ እንዳይረስ እንደ ጎሊያድ መንገድ ሲዘጋም ቆይታል:: የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትእቢት እኔ ካልመራሁ በሚል ፉከራም በአደባባይ ትርኢት ለጦርነት ጠብ መንጃ ሲወለውል ታይቷል::
ይህ ጁንታ ቡድን ይባስ ብሎ መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ እንደሽንፈት በመቁጠር በጦርነት ከበሮ ደላቂ አመራሮቹ ትዕቢት በተለይም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በውድቅት ሌሊት ለሁለት አስርት አመታት ደም እና አጥንታቸውን መስዋዕት አድርገው የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቁ የነበሩ የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተኙበት ከጀርባ በመውጋት የጭካኔ ጥጉን በገሃድ አስመስክሯል::
የጁንታው አባላት ኢ-ሰብአዊ የመሆናቸውን ጥግ በሚያስመሰክር መልኩ የሞቱትንም ወታደሮች ሬሳ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ልብሳቸውን ገፈው እርቃናቸውን ሜዳ ላይ ድርድረው ጨፍረዋል::፡ በሕይወት የተያዙትን ጥይት ላለማባከን በማለት አስተኝተው ሲኖ ትራክ ነድተውባቸዋል::
ይህንን ተከትሎ መንግሥት ሳይወድ በግድ በክልሉ ሕግን የማስከበር ዘመቻ ውስጥ ገብቷል:: ይሁንና ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሠረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ ወጥቷል:: ‹‹ለውሻ ከሮጡለት፣ ለልጅ ከሳቁለት» እንደሚባለው አሸባሪው ሕወሓት በእርሱ ኃይል የተገኘ ድል በማስመሰል ከተንቤን በረሃ አዋራውን አራግፎ መቀሌ ገብቷል::
ሕፃናት እና የ70 ዓመት አዛውንቶችን ከለላ አድርጎ ዕድሜውን ያራመዘው ቡድን፣ ‹‹ከአማራ ሕዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለን፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን እንወርዳለን›› በሚል በተለይ ኢትዮጵያን የማፍረስ ራዕዩን ለማሳካት በአማራና በአፋር ክልል የለየለት ወረራና ዘረፋን ፈፅሟል::
አሸባሪው ቡድን በአፋር ክልል ያደረሰው ፖለቲካዊ፣ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግፎች እንደተጠበቁ ሆኖ በአማራ ክልል ሕዝብ ላይም ታሪክ ይቅር የማይለው መጠነ ሰፊ ውድመት ፈፅሟል:: እናቶችን፣ እህቶችንና ሕፃናት ልጆችን ከወላጆቻቸው ፊት ደፍሯል:: የነገ ተስፈኛ ወጣቶቻችንን በጅምላ ፈጅቷል::
የዘረፈውን ዘርፎ ወደ ትግራይ ከመውሰድ ባለፈ መውሰድ የማይችለውን በማቃጠል፣ አፋቸው የማይናገሩ ከብቶችን በመግደል ዓለም ላይ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ዘረፋ ፈፅሟል:: አርሶ አደሮች ወዛቸውን ጠብ አድርገው ያለሙትን ሰብል በመዝረፍ በርሃብ አለንጋ አስገርፏል:: የአርሶ አደሮችን ቤት በሞርታር አረር አንድዷል::
ባለሀብቶች ጥረው ግረው የገነቧቸውን ፋብሪካዎች በቻለው አቅም ነቃቅሎ ወስዷል:: አቅሙ ያልፈቀደለትን ሁሉ ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጥ በማሰብ ከጥቅም ውጪ አድርጎ ወደ መጣበት ተመልሷል:: በዚህ ድርጊቱ ለሚሊዮኖች ቀን ጉርስ የሆኑ ፋብሪካዎች በመዘጋታቸው፣ በርካቶች በሥራ አጥነት እና በጥገኝነት እንዲሰቃዩ አድርጓል::
ሕወሓታውያን ፈሪሃ ፈጣሪ እንደሌላቸው በሚያሳብቅ መልኩ ሌላው ቀርቶ የአምልኮ ተቋማቶችን ሳይቀር አውድመዋል:: አቃጥለዋል:: ቤተእምነት መቅደስ ውስጥ ሳይቀር ተፀዳድተዋል:: ቤተ እምነቶችን እንደ ዳንኪራ ቤት በመመልክት መጠጥ ሲጠጡ እና ሲደንሱም ቆይተዋል::
ቡድኑ ዳግም ተቀጥቅጦ ወደ መጣበት መቀሌ ከፈረጠጠ ወዲህም፣ አመራሮቹ ከሕዝብና ከአገር ይልቅ የራስን ምቾት በማስቀደም ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ አያሌ ወጣቶችን አስከፊ ለሆነው ጦርነት መጠቀሚያ ለማድረግ ሲሰናዳ ቆይቷል::
ቡድኑ በተለይ ያን ሁሉ መከራና ግፍ በአማራ ሕዝብ ላይ ፈፅሞ ሲያበቃ ‹‹እኛ ጥላችን ከብልጽግና መንግሥት ጋር እንጂ ከሕዝብ ጋር አይደለም›› በሚል በማር በተለወሰ መርዙን በማቀርሸት ዛሬም እንደትናንቱ ለማሞኘት ሲዳዳውም ተስተውሏል::
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እንደሚወርድና በተለይም ከአማራ ሕዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ እያለ ሲናገር ቅንጣት ታክል እፍረት ያልታየበት የሕወሓቱ ጆስፍ ጉብልስ ወይንም የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፣ ጦርነቱን ወደ አማራና አፋር ክልል በማስፋት ለመናገር የሚዘገንን ጥፋት በሕዝብ ላይ ከፈፀመ እንስሳትን ሳይቀር በጥይት ከጨፈጨፈ በኋላ ዛሬ ሳናውቅ ነው የገደልናችሁ የዘርፍናችሁ የማለት ድፍረትን አግኝቶም አይተነዋል::
ሰውየው ከወራት በፊት ‹‹ዝርፊያ መፈፀማችን ትክክል አልነበረም፤ ወደድንም ጠላንም አማራ ወገናችን ነው›› ወዘተ… ንግግር በመቀሌ ላይ ሲያደርግ አድምጠናል:: የዚህ ንግግር አላማ ለአማራ ሕዝብ መቆርቆር አይደለም:: ዶሮን ሲያታልሏት ዓይነት ነው። አፈ ቀላጤው፣ ከቀናት በፊት ደግሞ ‹‹ከምንም ጋር የምናወራርደው ሂሳብ የለንም:: በእኛ በኩል አማራ ክልል ውስጥ ጦርነት ለማድረግ ፍላጎት የለንም›› ሲል ተደምጧል::
የአፈ ቀላጤው ንግግር በተለመደ የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ትናንት በመንበረ ስልጣን እያለ ግንባር ቀደም ጠላቴ የሚል ከምስረታው ጀምሮ በሰነድ በማስደገፍ ማኒፌስቶ ቀርፆ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የአማራም ሕዝብ ሲያሰቃይ መክረሙ ሳያንስ ‹‹ዳግም ወደ ስልጣን እንድንመጣ እርዳኝና እንደቀድሟችን እንሁን›› ዓይነት ነው::
ቡድኑ ጠላቴ ካለው ደርግ ጋር 17 ዓመት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ በነበረበት ወቅት መሰል የትርክት ቴክኒክ ተጠቅሟል:: በወቅቱ ‹‹ጠቤ ከደርግ ጋር ነው›› በሚል የአማራን ሕዝብ እያሞኘ እና እያታለለ ሕዝቡን ደጀን አድርጓል:: የአሁኑም ከዚሁ የተለየ አይደለም::
ቡድኑ እንዳለው ጠቡ ከመንግሥት ከሆነ ለምን ሲባል ሕፃናት፣ አዛውንት እና ነፍሰ ጡር፣ እና መነኩሴ ሳይቀር ይደፍራል፤ ለምን ይገድላል? የሕዝብ መገልገያ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች፣ ባንክ ቤቶችን ስለምን ከጥቅም ውጪ ያደርጋል? ቤተ እምነቶችን ያረክሳል?
‹‹የወጋ ቢረሳም የተወጋ አይረሳም›› እንደሚባለው፣ ሕወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈፀመው ጥፋት መቼም የሚረሳ አይደለም:: እነርሱ ይርሱት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቼም አይረሳውም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም ሲባል ሁሉን ይቅር ቢልም፣ ሕወሓት ግን ያፈሰሰው ደም አስክሮት ዳግም ጦርነት ከፍቷል፡›፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎችና ፋኖዎችም በአሁኑ ወቅትም እብሪተኛውን ቡድኑ በሚገባው ቋንቋ እያናገሩት ይገኛል:: የሽብር ቡድኑ ጋላቢዎቹም አንገት ከመድፋት ውጪ ይይዙት ይጨብጡት ጠፍቷቸዋል::
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችም የማይተካ ሕይወታቸውን ሰጥተው ኢትዮጵያን አሸናፊ፣ ሕዝቦቿንም ቀና ለማድረግ እየተፋለሙና በፈጣን ድል ወደፊት እየገሰገሱ ናቸው። ድልም እንደ ሁልጊዜው የኢትዮጵያ መሆኑ እርግጥ ነው::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2014