ሽብርተኛው ሕወሓት መሠሪውንና የርዕዮተ አለምና የሴራ ፓለቲካ እንዲሁም የፓርቲው ሱስሎቭ ( አይዶሎግ )ን መለስ ዜናዊን ከዛሬ 10 አመት በፊት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም በሞት በብራስልስ ቤልጂየም ካጣ በኋላ ቴክኒካሊ ሞቷል ። ሁል ጊዜ እንደምለው በእድሩ ድክመት ተስካሩም ሙት አመቱም አልወጣለትም እንጂ ። መለስ ከሞተ በኋላ ፓለቲካዊ ቆሌው ተገፏል ። ትቶለት ከሔደው የአለማቀፍ ዲፕሎማሲና የሚዲያ ኔትወርክ ውጭ ፓለቲካዊ ሞተሩ ከነከሰ ሰነባበተ። አዲስ የአገዛዝና የሴራ ሀሳብ ማፍለቅ ተስኖታል። መለስ ባስቀመጠው ቦታ ላይ እዛው ቆሞ ቀርቷል። እዛው እንዳለ አርጧል ።
በሙት መንፈስ እየተደናበረ የአምናና ካች አምና ስልቱንና ስህተቱን እየደገመ ነው። አምና በአማራና በአፋር ክልሎች በማኦ የሕዝባዊ ማዕበል የጦርነት ስልት ወረራ ፈጽሞ ከ300ሺ እስከ 400ሺ ትግራዋይን ለስልጣን ምሱና ለሚያመልከው የጦርነት ጦኦት ገብሯል ። ዘንድሮም በዚህ ቁሞ ቀር ስልቱ ትግራዋይን እየማገደ ነው።
ትግራይን ምድረ በዳና ወጣት አልባ ሊያደርጋት፤ እናቶችንና አባቶችን እንደለመደው ጧሪና ቀባሪ አልባ እያደረጋቸው ነው። የእሱ ልጆችና ሚስቶች ግን ከሀገር በተዘረፈና በሸሸ ሀብት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በአውስትራሊያና በሌሎች ሀገራት የተቀናጣ ህይወት እየመሩ ነው። ከአመት በፊት በአማራና በአፋር ክልሎች የፈጸመው ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ጭካኔም አይረሰም። በ3ኛ ወረራው ቆቦ ላይና አፋር ተመሳሳይ ግፍና ሰቆቃ እየፈጸመ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው ።
ሰሞኑን በየግንባሩ በለኮሰው እሳት ሲለበለብና ሲገረፍ እንደለመደው ሀሰተኛ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም ጀምሯል። የጦር ካምፑና ስንቅና ትጥቅ ማደራጃው ሲመታ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘመን በክረምት ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸው እየታወቀ ትምህርት ቤቶች በአየር ተደበደቡ፤ ተማሪዎች ሞቱ እያለ ጥርሱን የነቀለበትን የውሸት ፍላጻ እያንበለበለ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ይሄን የፈጠራ ወሬውን ያለምንም ማጣራት እንደገደል ማሚቶ ሲያስተጋቡለት ውለዋል። እንደተለመደው ጥምር ኃይሉ ገትሮ አላላውስ ሲለው በፌስ ቡክ ከተሞችን እየተቆጣጠርሁ ነው በማለት በእውር ድንብር የሚደግፉትንና ጋላቢዎችን በውሸት ቀብድ እያጽናና ይገኛል።
የጥምር ኃይሉ ምት እየበረታበት ሲመጣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ሆነው ጥቃት ከፈቱብኝ እያለ እየለፈለፈ ይገኛል። በቀጣይ ከዚህ ከፍ ከፍ ባሉ ሀሰተኛ መረጃዎች ለማደናገር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ። በኬሚካል የጦር መሳሪያ ተጠቃሁ ከሚለው አንስቶ ኩራታችን የሆነውን የአየር መንገዳችንን ስም ለማጠልሸት እንደ አምናውና ካች አምናው እየኳተነ ይገኛል ።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በአልጀሪያ አልጀርስ የሚገኘውን ሳይዳር የተባለውን ግዙፍ የመድሀኒት ፋብሪካ ሲጎበኙ የተነሱትን ፎቶ በኬሚካል የጦር መሳሪያ ጥቃት ሊሰነዝርብኝ ለሚለው መሠሪ ቅጥፈቱ እየተጠቀመበት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ አምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያ እያጓጓዘ ነው የሚለውን የፈጠራ ክሱን ያጀበበትን ፎቶ ዘንድሮም ምንም ሳይቀይር ተጠቅሞበታል። ለዚህ ሀሰተኛ የመረጃ ጦርነቱ ምላሽ ለመስጠት ይረዳን ዘንድ የሕወሓትን ወናፍ አደረጃጀትና አሰላለፍ መለስ ብለን በአለፍ ገደም እንቃኝ ።
የከሀዲውና የሽብርተኛው ሕወሓት ርዝራዥና ዲያስፓራ ጭፍራ እንደ ቆሰለ አውሬ ደሙን እያዘራ ያገኘውን ለመንከስ መዛከር ከጀመረ አራት አመት አለፈው። ባልጠበቀውና ባላሰበው መንገድ የበላይነት፣ የዘረፋ፣ የአፈና፣ የጥላቻና ሀገር የማፍረስ ፕሮጀክቱ ድንገት የእንቧይ ካብ ስለሆነበት ክፉኛ ተቆጭቷል ። ተንገብግቧል።
አምኖ ለመቀበል ተቸግሯል ። ጣረ ሞት ላይ ቢሆንም በሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ማምሻም እድሜ ነው በሚል ሲፈራገጥ አራት አመት አለፈው። በስሁት ርዕዮት አለምና በፈጠራ ትርክት የካበው የእንቧይ ካብ ተንዷል ። በእውኑም ሆነ በህልሙ ይሆናል ብሎ ባልገመተው የለውጥ ኃይሉና ሕዝባዊ ቁጣው ተናበውና ተመጋግበው ከ50 እስከ 100 አመት አገዛዝ ላይ የመቆየት የቀን ቅዠቱን አስጨንግፈው ጎህ ከቀደደ ቢባጅም አሻፈረኝ እንዳለ ነው ።
ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ የመመስረት ሌላው ቅዠቱ ከንቱ ሆናል። የአደጋ ጊዜ የመውጫ በሩ ከውጭ ተከርችሞበታል። ግራ ተጋብቷል። የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቷል ። ደመ ነፍሳዊ ሆኗል ። አመክንዮና ተጠየቅ ድሮም አልነበረውም አሁንም እንደራቀው ነው። ማመዛዘኛው ይብስ ላሽቋል።
የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም ታሪክ የማይረሳው ፤ ትውልድ ይቅር የማይለው ክህደት እና በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋና የጦር መሳሪያ ዘረፋ የዚህ ደመ ነፍሳዊነት ውጤት ነው ። ከጸሐይ በታች ህወሓትን የሚገዳደር ኃይል የለም። ይህን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎ የሚሞክር መቐሌ መቀበሪያው ትሆናለች። በመከላከያ ላይ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመናል። ከመንግስቱ በላይ እስካፍንጫችን ታጥቀናል። እያለ ሲፎክር፣ ሲያቅራራ፣ ሲፎልልና ሲሸልል እንዳልነበር በዘጠኝ ቀናት እንደ አሸዋ ላይ ሰቀላ ብትንትኑ ወጥቷል ።
ሁልጊዜም ከእያንዳንዱ ውድቀቱና ቀውስ ማግስት በጉያው ተጠባባቂ ደባዎችንና ሸሮችን በጉያው ይዞ የሚዞረው ከሀዲውና እፉኝቱ ሕወሓት/ትህነግ የፕሮፓጋንዳና የሕዝብ ግንኙነት ሌላ አውደ ውጊያ ከፍቷል። በለኮሰው እሳት ተቃጥሎ ዶጋ አመድ ከሆነ በኋላ የተረፈ የውሸትና የፈጠራ ትርክት ፍም አቀጣጥሎ ለጊዜውም ቢሆን ተስፈኞቹን ለማሞቅ ሌት ተቀን እየታተረ ነው። በተወሰነ ደረጃ ድካሙና ልፋቱ መና አለመቅረቱን አምና ታዝበናል ።
ሀሰተኛ መረጃን እንደ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጦር መሳሪያ ያደረገ /ዌፐናይዝ/ያደረገ ድርጅትም ሆነ ሀገር የለም ። በአለማችን እንደ ራሽያው የስለላ ተቋም ኤፍኤስቢ መረጃን እንደ ጦር መሳሪያ የተጠቀመ ወይም የሚጠቀም የለም ቢባልም የትህነግ ርዝራዥና የዲያስፓር ጭፍራ ግን በአይነ ደረቅነት፣ በገገማነትና በገልጃጃነት አሳምሮ ይበልጠዋል። ላለፉት 47 አመታት ርካሽ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሀሰተኛ መረጃን ከክላሹ መሳለመሳ በስፋት ተጠቅሟል። እንደሸሚዝ ከሚቀያይረው ርዕዮት አለም ይልቅ ለሀሰተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም ለፈጠራ ትርክትና የሴራ ፓለቲካ መታመን ይቀናዋል ። በውንብድናውም ሆነ በአገዛዙ ጥሩ አርጎ ያረጋገጠልን ይሄን እኩይ ማንነቱን ነው ።
በሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻውም ሆነ በኋላ ሆን ተብሎ በተዛባና በሀሰተኛ መረጃ የጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳና የማጠልሸት ዘመቻውን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያው እያፈራረቀና እያጃመለ ተያይዞታል። መደበኛውም ሆነ ማህበራዊ ሚዲያው በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ በተጠና ፣ በተቃነጀ፣ በተናበበና በተመጋገበ አግባብ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ይመራል ።ይህ ጸረ የሰው ፍጡር፣ ኢትዮጵያ፣ እውነትና ፍትሕ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ከፍ ሲልም የዲፕሎማሲ ደባና አሻጥር በሀገር ውስጥ በባለ ሁለት ምላሱ ጌታቸው ረዳ ይመራል ።
ምንደኛውና ጥቅሙ በተነካበት እብሪተኛና ማንአህሎተኛ/chauvinist/ የትህነግ ርዝራዥና ጭፍራ ዲያስፓራ ደግሞ ይታገዛል ። ለዚህ እንዲያግዘው ደግሞ “ የትግራይ ወዳጅነት አገናኝ ቢሮ “( Tigray Friendship Liaison Office) በተሰኘ ተቋም አማካኝነት በቀድሞው ዲፕሎማት ወንድሙ አሳምነው እንደሚመራ መስፍን አማን የተባሉ ጸሐፊ በፍት_ሕ መጽሔት፤ 3ኛ አመት፣ ቁ111፣ ታህሳስ እትም ላይ ፤” ከወታደራዊ ሽንፈት ወደ ዲፕሎማሳያዊ ትንቅንቅ “ በሚል ርዕስ ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ ተረድተናል ።
በመንግስታቱ ድርጅት የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በጀኔቭ በመንግስታቱ ድርጅት ሕዝብ ልማት ፈንድ ባልደረባው ዶ/ር ኪዳኔ አብርሃ ከአምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀናጀት የአውሮፓውን የዲፕሎማሲና የአለማቀፍ ሚዲያውን እጅ ለመጠምዘዝ በተደረገው ርብርብ የአንበሳውን ድርሻ ወስደዋል ። ከአትላንቲክ ማዶ በአሜሪካ ያለው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ለአምባሳደር ፍስሐ አስግዶም በአደራ መሰጠቱን እኝሁ ጸሐፊ ጠቁመዋል።
የቀድሞው ታጋይ ሙሉጌታ ገብረህይወት ( ጫልቱ ) ከመለስ ዜናዊ ወዳጅ አሌክስ ዲወል ጋር በመሆን የሕወሓትን ሀሰተኛ መረጃ ያራግባሉ። የኦባማ የብሔራዊ ደህንነት የቀድሞ አማካሪና የአዲሱ የባይደን አስተዳደር ተሿሚ ሱዛን ራይስ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ (ዩኤስኤይድ) የቀድሞ ዳይሬክተር ጌይል ስሚዝ፣ የአሁኗ ዩኤስኤይድ ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር፣ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ፣ የሒውማን ራይትስ ዋች ኃላፊ ኬኔትስ ሮዝ ከእነ የማነ ኪዳኔ ( ጀማይካ )ጋር በመሆን አለማቀፍ ሚዲያውንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ስራ ተጠምደዋል ።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጋር ለማጣረስ ሲኳትን የነበረው ያለው ሌላው ከሀዲ ዶ/ር መሀሪ ታደለ ነው። በዚያ ሰሞን በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው ስለወሬሳው ትህነግ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የነበረው ማርቲን ፕላውት ፤ የቢቢሲ የአፍሪካ አርታኢ ዊል ሮስ ቢቢሲ አማርኛንና ትግረኛን በትህነግ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በመሙላት እና ኖርዌያዊው ሸተል ትሮንቮል እንደነ ቢቢሲና አልጀዚራ ባሉ አለማቀፍ ሚዲያዎች በመቅረብ ለከሀዲው ትህነግ በመወገን የተዛባና የሐሰት መረጃ በመንዛት ትህነግ አፈር ልሶ እንዲነሳ ሲማስኑ ኖሮዋል ። ዛሬም ለማራገብ በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ ነው ።
የቀድሞው ፓትሪያሪክ የአቡነ ጳውሎስ ልዩ ረዳት ስታሊን ገብረስላሴ (ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ፤ ጆሴፍ ስታሊን በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሶቪየት ዜጎችን የጨፈጨፈ ሰው በላ ገዥ ነው ፤) ፣ አሉላ ሰለሞንና ዳንኤል ብርሀኔና ሌሎች የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ሰዎች ደግሞ የሀገር ቤቱንና የውጭውን የትህነግን የፕሮፓጋንዳ ማሽን መካኒኮች ናቸው። የትግራይ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ነው። ትግራዋይ ሁሉ ትህነግ ነው ሲሉ ካለማፈራቸው ባሻገር በሀገሪቱ ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ጀርባ እጃቸው አለበት።
ከፍ ብየ የጠቃቀስኋቸው የቀድሞ ታጋዮች፣ አምባሳደሮች፣ በአለማቀፍ ተቋማት የሚሰሩ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ አክቲቪስቶች በመማጸኛ ከተማው መሽጎ ከነበረው ከሀዲው የትህነግ ስብስብ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ ካሰማራቸው ጭፍራዎቹ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ የፈጠራ ትርክታቸውን ከመለፈፋቸው ባሻገር የተዛባና ሐሰተኛ መረጃ በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው በመንዛት ሀገራችንን በጦር መፍታት ቢሳናቸው በወሬ ለመፍታት ሌት ተቀን እየተረባረቡ ነው ።
በዋናነት ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH )፣ ትግራይ ፈርስት፣ አይጋ ፎረም፣ ትግራይ ፕሬስ፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ፣ ትግራይ ኦን ላይንና ሰሞኑን ደግሞ እንደአሸን የፈሉ ድረ ገጾችና ዩቲውቦች ሀሰተኛ መረጃውን ሌት ተቀን ያንበለብላሉ። የአጋሮቻቸውን መደበኛና ማህበራዊ ሌሎች ሚዲያዎችን በተውሶ ይጠቀማሉ። ማህበራዊ ሚዲያዎችን አቀናጅቶ የሚጠቀመው በተለምዶ ዲጂታል ወያኔ በመባል የሚታወቀው የከሀዲው ትህነግ ጭፍራ በሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር የፌስ ቡክ፣ የቲዊተር ፣ የቴሌግራም፣ የኢንስታግራምና የዩቲውብ ሀሰተኛ አካውንት በመክፈት እና የአማራና የኦሮሞ ጭምብል በማጥለቅ ጥላቻን፣ ልዩነትን፣ ዘረኝነትንና ልዩነትን የሚያቀነቅኑ የፈጠራ መረጃዎችን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች ያለረፍት ሌት ተቀን ይነዛሉ ።
ባለፈው አመትና ከዚያ በፊት አመነስቲ ኢንተርናሽናልን፣ ሒውማን ራይትስ ዋችን፣ በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮማሽንን፣ በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ረድኤት ማስተባበሪያ አገናኝን/ዩኤንኦቻ/፣ የባይደንን አስተዳደር፣ አለማቀፍ ሚዲያውን ፣ ወዘተረፈ በማሳሳት ግዳይ ጥለዋል። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን እንድንቀር አድርገዋል። ውሸት እውነትን፣ ጨለማ ብርሀንን ረቷል። በወቅቱ ደካማ የነበረው የኮምንኬሽንና የአለማቀፍ ግንኙነት ስራችን ውድ ዋጋ አስከፍሎናል።
ሉዓላዊነታችን ተደፍሯል። በፈተና ላይ የነበረው ለውጥ ጠልሽቷል። ዙሪያችንን ከበው አሰፍስፈው ሊውጡን ደጅ ቆመው ለሚጠብቁን እንደ ግብጽ ላሉ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶቻችን የልብ ልብ እንዲሰማቸው አድርጓል። እውነት ለመናገር እንደ ሀገር ወዳድ ዜጋ የሆነው ነገር አብግኖኝ ነበር። እንደ ዜጋም ሆነ መንግስት ካለፈው ስህተታችን ተምረንና ተቀናጅተን ይሄን የሀሰተኛ መረጃ ጦርነት መመከት አለብን። ሀቅንና ፍትሕን ይዘን ያዝ ለቀቅ ማድረጉንና መከላከሉን ትተን በሚዲያው የበላይነትን ለመቀዳጀት ሌት ተቀን መስራት ይጠበቅብናል።
የትህነግ ርዝራዦችና ዲያስፓራ ጭፍራዎች ጊዜያዊ የፓለቲካና የአለማቀፍ ግንኙነት ትርፍ እስካገኙ ድረስ ሀገር ስሟ ቢጠፋ ፤ ባፍንጫዋ ብትደፋ ጉዳያቸው አይደለም። በአክሱም ከጺዎን ማሪያም ንግስ ሁለት ቀን በፊት 750 ሶዎች በጅምላ ተጨፈጨፉ ፤ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት ንጹሐንን ገደሉ ፤ አንድ ሴት ለ23 ተደፈረች፤ ወዘተረፈ የሚሉ በሰው ሰራሽ ክህሎት/artificial intelligence / የተቀነባበሩ ፍጹም እውነተኛ የሚመስሉ/deep fake/ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመልቀቅ አለማቀፍ ማህበረሰብን እና ምዕራባውያንን በማደናገር በእንቅርት ላይ ቆረቆር ሆነውብን እንደነበር አንዘነጋውም። የአክሱምን የ” ዘረ ማጥፋት” በቪዲዮ የሚያብራራው ቄስ ሲጣራ አንደኛ ቄስ አለመሆኑ ሁለተኛ በአሜሪካ የሎስአንጀለስ ነዋሪ ሲሆን በቅርብ ወደትግራይ ሄዶ እንደማያውቅ ተረጋግጧል። ለጊዜው የሀሰተኛ መረጃ ውርጅብኝ ዋጋ ቢያስከፍለንም ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል እንዲሉ ቀስ በቀስ እውነቱ እየወጣ ነው ።
ትህነግ ላለፉት 27/30 ተቋማዊና መዋቅራዊ አድርጎ ጊዜውን ጠብቆ እንዲፈነዳ የቀበረው የጎሳ፣ የልዩነት፣ የጥላቻና የመጠራጠር ፈንጅ ሀገሪቱን እየናጣት፤ ሱዳን ሉዓላዊነታችንን ደፍራ መሬታችንን በወረረችበት እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ የተነሳ ግብጽ እንደ ጎን ውጋት ቀስፋ በያዘችን ፈታኝ ስዓት በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ አሜሪካ የጸጥታው ምክር ቤት ባለወር መሆኗን ተጠቅማ ሀገራችንን ሆን ብላ ዜጎቿን በማስራብ መክሰሷ አልበቃ ብሏት የአማራ ልዩ ኃይል ከምዕራብ ትግራይ እንዲወጣ በመጠየቅ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባቷ ይታወሳል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አንተኒ ብሊንከን በየአጋጣሚው የሀገራችንንና የመንግስታችንን ስም ሲያጠለሽ ነበር። ዛሬም ጦርነቱንና ወረራውን የጀመረውን ሕወሓትን እንደማውገዝ፣ ጦርነቱንና ወረራውን እንዲያቆም ጫን ከመፍጠር ይልቅ ሁለቱ ወገኖች በሚል ሾላ በድፍን መግለጫ እያድበሰበሱት ነው ።
እኔም ለሀገሬ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛና አርበኛ ነኝ ! ! !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2014