ሰው ብዙ ተፈጥሮ አለው..ከዛኛው አለም ወደዚህኛው አለም ሲመጣ ለራሱና ለሌሎች ታሪክ ሰርቶ እንዲያልፍ ነው:: የሰው ልጅ አቅሙን፣ ሀይሉንና ተፈጥሮውን መጠቀም ከቻለ ታሪክ የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም:: ታሪኮቻችን የተቀመጡት በእኛ የማሰብ አቅምና የማድረግ ሀይል ውስጥ ነው:: ታሪክ መስራት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብርቃችን አይደለም:: በተለያየ ጊዜ አለምን ያስደነቁ፣ ከሰው ልክ አቅም በላይ የሆኑ በርካታ ታሪኮችን ሰርተናል:: አሁንም እየሰራን ነው::
ለአብነት ብንጠቅስ እንኳን የአድዋ የድል ታሪክ አለም የሌለው፣ ለአፍሪካውያን ብርቅ የሆነ የእኔና የእናተ የጋራ ታሪካችን ነው:: በተለያዩ ጊዜ፣ በተለያየ ቦታ አባቶቻችን በአንድነትና በህብረት ታሪክ ሰርተዋል:: ዛሬ ላይ በክብር የምንጠራባቸውን እልፍ የኩራትና የሞገስ ታሪኮችን አስረክበውናል:: የአባቶቹን የጽናት ክንድ የወረሰው ይሄኛው ትውልድ ደግሞ በአባይ ላይ ጀግኖ እንሆ የአባቶቹን ህልምና ምኞት እውን አድርጎታል:: ይሄ ትውልድ እኔና እናተ ነን..ይሄ ትውልድ በመቻል፣ በማድረግ፣ በማሸነፍ የተካነ የአባቶቹ የጽናት ጽንስ የጸነሰው ትውልድ ነው::
ሀገርና መንግስት ከግለሰብ የሚጀምሩ የብዙሀን ስፋት ናቸው:: ሀገር ራዕይ እንዳለው ትውልድ፣ ራዕይ እንዳለው መሪ፣ ራዕይ እንዳለው ዜጋ የሚባርከት የለም:: አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ራዕይ ባላቸው መንግስትና ህዝቦቿ እየተባረከች ነው :: ይሄን እውነት ከሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ውስጥ ሁለቱን መዝዬ ላውጋችሁ:: መነሻዬ በአባይ ላይ ስለጀገኑ እድለኛና ባለ ድል ትውልዶች ነው:: ታላቁን የህዳሴ ግድብ ተንተርሼ ስለዚህ ትውልድ እድልና ድል ላውጋችሁ::
እንደሚታወቀው ይሄ ትውልድ ቁጭት የነቀነቀው፣ የአባቶቹን አደራ ውስጡ አኑሮ እድልና ድልን በመጠበቅ የሚንቀሳቀስትውልድ ነው:: ከስንት አንድ ጊዜ ካልሆነ ብዙ ጊዜ እድልና ድል አንድ ላይ አይመጡም:: ሲመጡ ግን ሌላ ናቸው..ትውልዱን ባለታሪክ፣ ህዝቡን ባለማዕረግ ነው የሚያደርጉት:: እድልና ድል በአንድ ላይ ሲመጡ ተዐምር ነው ። የሚፈጥሩት..ታሪክ ነው :: ይሄኛው በአባይ ላይ የገነነው የእኔና የእናተ ትውልድ እድልና ድል በአንድ ላይ የመጡለት ትውልድ ነው::
በዚህ ትውልድ አብራክ ስር እንደ መብቀል ኩራትና ሰውነት አለ ብዬ አላስብም:: በሁለት ተርባይንና ጀነሬተሮች )ይሄ ትውልድ ታሪክ ከመስራት ባለፈ የአባቶቹን እውነት፣ የያኔውን ትውልድ ምኞት የመለሰ ትውልድ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በሶስተኛው የውሀ ሙሌት ስነስርዐት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ላይ በአባይ ላይ የጀገነውን ይሄኛውን ትውልድ ‹እድለኛና ባለ ድል ትውልድ› ሲሉ ነበር የገለጹት::
አያይዘውም ‹አባይ ሲገደብ እንደማየት፣ ሲፈስ እንደማየት፣ በእጅ እንደመዳሰስ ፣ ኃይል ሲያመነጭ እንደማየት እድለኝነት አለ አልልም:: ይሄ ትውልድ እድለኛና ባለ ድል ትውልድ ነው› ነበር ያሉት:: እውነት ነው የዚህ ትውልድ አንድ አካል ሆኖ በአባይ ላይ እንደመጀገን እድለኝነት አለ አልልም:: የጥንት አባቶቻችን አባይን ገድበው ኃይል የማመንጨት ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው:: ግን እድል አልነበራቸውም:: ግድቡን ገድቦ ኃይል እንዲያመነጭ የሚያደርግ እውቀትና ቴክኖሎጂ፣ የተማረ የሰው ኃይልም አልነበራቸውም:: ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የግድቡን ወጪ የሚሸፍን የፋይናንስ አቅም እልነበራቸውም::
ከእኔና ከእናተ በፊት ያሉት አባቶቻችን ልክ እንደቀደሙት ሁሉ አባይን ከመገደብ ባለፈ ህልምና ምኞታቸውን እውን የሚያደርጉበት ምንም አጋጣሚ አልነበረም:: አንድ ነገር በተፈለገው መልኩ ውጤት እንዲያመጣ እድልና ድል ግድ ይሉታል:: እድል ወደ ድል የሚወስድ ጎዳና ነው:: በሰዐቱ አባቶቻችን እድላቸውን እንዳይጠቀሙና ወደ ድል እንዳይቀይሩት ሳንካ ተፈጥሮባቸው ነበር::
የግብጽና የአንዳንድ ምዕራባውያን ክፋትና ራስወዳድነት ታክሎበት አባይ ሳይገደብ በምኞት ብቻ እንዲቀር ሆነ:: አባይ ግን አልሞተም በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ በቁጭትና በሀሳብ ነበር:: በዘፈንና በግጥም፣ በፉከራና በቀራርቶ እየተሰደበና እየተገላመጠ፣ እየተናቀና እየተወደሰ መኖሩን ቀጠለ:: አባቶቻችን አርግዘው ሳይወልዱት ለእኛ አደራ ብለውን አለፈ:: እንሆ አባይ ተንከባሎ እድለኛውና ባለድሉ ትውልድ ላይ ደረሰ:: እንሆ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ አባይ ተሞሸረ:: እኛም እልል አልን::
አባይ ጎጆ ወጥቶ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከድህነትና ከኋላቀርነት ሊያወጣ እንሆ ከነግርማ ሞገሱ እየደነፋ ነው:: ተጠናቆ እልል የምንልበት ጊዜ የሁላችንም የዳግም ትንሳኤ ቀን እንደሚሆን አምናለው:: እስከዛው ግን እንደ አይናችን ብሌን፣ እንደ ህልውናችን መሰረት እንጠብቀዋለን። ምክንያቱም አባይ ማለት ከግድብ ባለፈ የአንድነታችን ምስክር፣ ከኃይል ማመንጨት ባለፈ የወንድማማችነታችን ካርታ ነውና::
አፋፍ ላይ ነን..በአባይ ልንስቅ..በአባይ መከራችንን ልንረሳ:: በአባይ የልፋታችንን ልንበላ፣ የአንድነታችንን ውጤት ልናይ:: በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ስራዎች ግንባታ ዘጠና አምስት ከመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ሌሎች ተያያዥ ስራዎች እንዳሉ ሆነው አጠቃላይ አፈፃፀሙ ደግሞ ሰማኒያ ሶስት ከመቶን የዘለለ ሆኖ ተገኝቷል:: በዚህም መሰረት በያዝንው አመት የህዳሴ ግድቡ ካሉት አስራ ሶስት ተርባይኖች በሁለት ዩኒት (በሁለት ተርባይንና ጀነሬተር ) ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር የማድረግ ስራው ተጠናቆ በሁለት መቶ ሰባ አምስት ሜጋ ዋት ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ኃይል ማመንጨት ጀምሯል::
አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ስራ በሁለት አመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን በቀጣይ አመታት ውስጥ አባይ አልቆ ሙሉ በሙሉ ኃይል ወደማመንጨት ሲሸጋገር ከእድገትና ከስልጣኔ ባለፈ ደስታችንን በጋራ የምንቋደስበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም:: እስከዛው የቀሩትን ጥቂት አመታት በተለመደው አንድነትና ፍቅር በተባበረ ክንድ ትንሳኤውን እውን ማድረግ ይጠበቅብናል::
አባይ በብዙ ልዩነት ውስጥ አንድነትን የሰጠን ፣ በብዙ መለያየት ውስጥ ያስተቃቀፈን ጽናታችን ነው:: ከአድዋ ቀጥሎ የተከሰተ የትውልድ ክስተት ነው:: ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሱ ምንም ማድረግ እንደሚችሉ ለአለም ያሳዩበት፣ ጠላቶቻችንን አንገት ያስደፋንበት የክብራችን ማህተም ነው:: ከአድዋ ቀጥሎ ትውልድ የሚዘክረው የዚህኛው የእኔና የእናተ ሀቅ ነው:: ኢትዮጵያ የምትጠራበት የዚህኛውና የዚያኛው ትውልድ እልፍ የታሪክ ጌጥ ያላት ቢሆንም:: አባቶቻችንን ስናስብ አድዋን ይሄኛውን ትውልድ ስናስብ ደግሞ የህዳሴ ግድባችንን እናስታውሳለን::
ትውልድ ሁሌም ታሪክ እንደሰራ ነው:: የታሪክ ማብቂያ መለያየት ነው:: ሀገር ትውልድ ብኩን የሚሆኑበት አንድ አጋጣሚ ቢኖር መለያየት..መገፋፋት ነው:: ትውልድ በአንድነት ከቆመ ሁሌም ታሪክ አለው:: ሁሌም ታሪክ መስራት ይችላል:: አድዋም ሆነ አባይ የምንም ሳይሆን የአንድነታችን ሚስጢር ነው:: አሁንም በአንድነት ቆመን እንደ ህዳሴ ግድባችን አይነት ከድህነትና ከኋላቀርነት ከልመናም ሊያወጣን የሚችል የእድልና የድል አሻራችንንእናሳርፍ ::
በአባይ ጉዳይ ላይ የግብጽና የሱዳን የሌሎች ምዕራባውያን ተጽዕኖ ምን ያክል እንደነበር እናውቀዋለን:: በአንድነት መክተን አሸነፍነው እንጂ ተለያይተን ቢሆን ኖሮ አባይን በዚህ ልክ አናየውም ነበር:: ጠላቶቻችን መቼም የእኛን ደስታ፣ የእኛን ሳቅ፣ የእኛን ስኬት ማየት አይፈልጉም:: ከሰው በታች፣ ከሀገር ኋላ ቀርተን ለማኝና ተመጽዋች ሆነን፣ ሲጠሩን አቤት ሲልኩን ወዴት እያልን ታዛዥ ሆነን እንድንኖር ነው የሚፈልጉት:: በተመኘንው ልክ እንድናድግ፣ በምንፈልገው ልክ ቀና እንድንል የአንድነት ክንዳችን በፈጠሩት አባይ ላይም ሆነ በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ልንተባበር ይገባል::
ጠላቶቻችንን የምናሳፍርበት ብቸኛው መንገድ አንድነት ነው:: ኢትዮጵያዊነት አስፈሪና ገናና የሚሆነው በአንድነት ውስጥ ብቻ ነው:: አባይ እንዴት ተገነባ? የአድዋ ድል እንዴት መጣ? ጣሊያንንና ግብጽን፣ እንግሊዝንና ሱማሊያ፣ ሌሎች ወደረኞቻችንን እንዴት ረታን ብለን ስንጠይቅ ስልጣኔ ሳይሆን፣ ዘመናዊነት ሳይሆን፣ እውቀትና ጥበብ ሳይሆን አንድነትን ነው የምናገኘው:: ማሸነፋችን ያለው አንድነታችን ውስጥ ነው::
አብዛኞቹ ታሪኮቻችን፣ አብዛኞቹ እሴቶቻችን በጋራ ሀሳብ፣ በጋራ እምነት፣ በጋራ ፍቅር እውን የሆኑ ናቸው:: በእድለኛና በባለድል ስም አባይን ጨርሰን ሌላ ግድብ፣ ሌላ ታሪክ እንድንሰራ የጽናት ክንዶቻችን ከአብሮነት አይቦዝኑ :: ለሀገር መልፋት ለራስ መልፋት ነው:: ይሄ ትውልድ ዝም ብሎ ባለድል አልሆነም..:: የገባው የሆነ ነገር አለ :: ሰው እውነት ሲገባው ለእውነት ብቻ ነው የሚለፋው:: ሰው ፍቅርና ፍትህ ሲገባው ለፍቅርና ለፍትህ ብቻ ነው የሚኖረው:: መለያየት ምን ያክል ክፉ እንደሆነ ይሄ ትውልድ ገብቶታል :: ከአባቶቹ የወረሰውን የመቻልና የማድረግ ወኔ አባይን እንዲገነባ መንገድ ከፍቶለታል:: ድህነት፣ ኋላ ቀርነት ክብረ ነክ እንደሆነ አውቆታል::
ልክ እንደ ህዳሴ ግድባችን አንዳንድ ታሪኮች ፍቅር ብቻ ነው የሚፈልጉት:: አባይ የመቶ ሀያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የፍቅር፣ የጽናት፣ የተስፋ፣ የህብረት ውጤት ነው:: የብዙ ድሀ ልቦች፣ የበርካታ ምስኪን ነፍሶች የደግነትና የመስጠት ሚስጢር ነው:: እንጂማ ምን ኖሮን፣ ምን ተርፎን አባይን የሚያክል ግዙፍ ፕሮጀክት እንገነባለን? አባይ የቆመው በፍቅር ነው:: አባይ የቆመው በህብረት ነው:: አባይ የቆመው በጽናት ነው::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27 /2014