ዛሬም እንደተለመደው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ በሰፈራችን ዋርካ ጥላ ስር ከሚገኘው ድንጋይ ላይ ቆሞ መጮህ ሲጀመር ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች የይልቃል አዲሴን ንግግር ለማዳመጥ ወደ ዋርካው ተመሙ።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ በሰፈራችን ሰዎች መካከል ቆሞ ለበርካታ ጊዜያት በተደጋጋሚ «የዱባ ጥጋብ ያለስንቅ ያዘምታል» እያለ ይጮህ ነበር። የዱባ ጥጋብ ያለስንቅ ያዘምታል የሚለውን አባባል ውስጠ ወይራ መሆኑን የተረዳው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ የዱባ ጥጋብ ያለስንቅ ያዘምታል የሚለውን አባባል በዋርካው ስር ለተሰበሰበው ሰው እንዲያብራራ ይልቃል አዲሴን ጠየቀው።
በዚህ ጊዜ ወፈፌው ይልቃል ንግግሩን እንዲህ ብሎ ጀመረ…..የዱባን ወጥ የበላ ሰው ሆዱ ያለመጠን ስለሚወጣጠር ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ የሚርበው አይመስለውም። ዘመቻ እንደሚሄድ ቢያውቅም እንኳ ስንቅ ቋጥሩልኝ አይልም። ምክንያቱም የዱባ ጥጋብ የሚጎድል ስለማይመስል። ይሄን ምግብ ቀምሰው የማያውቁ ሰዎች ዱባን በቀመሱ ጊዜ በደመነፍስ ያለበቂ ስንቅ ረጅም መንገድ ሊጀምሩ ይችላሉ። በእነኝህ ሰዎች መፍረድ አይቻልም። ነገር ግን የዱባን ባህሪ ጠንቅቀው እወቁ ያለ ስንቅ የሚዘምቱ ግን ይፈረድባቸዋል። ምክንያቱም መጀመሪያውኑ የዱባን ባህሪ ያውቁ ስለነበር።
ሕወሓት አሁን ላይ ዱባን በተደጋጋሚ የሚበላ ነገር ግን ስንቅ የማይቋጥር ዓይነት ሰው ሆኖ በግልጽ እየታየ ነው።
በመጀመሪያው የሕወሓት የትግል ዘመን የምንዋጋው ለራስህ ነፃነት ነው ተብሎ ሲሸወድ አልፈረድንበትም ነበር። ለሃያ ሰባት አመታትም በስሙ ሲነገድ እንዲሁ አልፈረድን ነበር። ሕወሓት ለትግራይ ሁለንተናዊ አጋዥ በሆነው መከላከያ ላይ ሰብአዊነት የጎደለው አሰቃቂ እርምጃ ሲወሰድ አይተው ለምን መከላከያ ይገደላል ብለው በመጠየቅ ፈንታ በመከላከያ መገደል ተደስተው ከበሮ ሲደልቁም አልፈረድንም ነበር። በህግ ማስከበር ዘመቻው ጥልቅ ጉድጓድ የተወረወረውን ወያኔ ከተቀበረበት ጉድጓድ አንስተው ለሁለተኛ ጦርነት ሲመጣም እንዲሁ አልፈረድንም ነበር። አሁን ግን የሕወሓት ደጋፊዎች ከሕወሓት ጋር ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት አውጆ ሊያጠፋን የዱባ ጥጋብ ጠግቦ ሲመጣ ትዕግስታችን ተሟጠጠ።
በነገራችን ላይ የዱባ ጥጋብ የጠገቡ አምባገነኖች በማን አለብኝነት ወረራ በሚፈጽሙ ጊዜ በመጀመሪያዎቹ የጦርነት ሳምንታት አሸናፊዎች የሆኑ ይመስላቸዋል። ወረራ የተፈጸመበት የተቃራኒ ወገንም ወራሪውን ፈጽሞ ሊመክተው የሚችል አይመስላቸውም። ምክንያቱም ጥጋባቸው የዱባ ጥጋብ ነውና። ማንም ሰው ጦርነቱን ማን ያሸንፋል? ገምት ቢባል ግምቱ ጦርነቱን ለጀመረው ኃይል ማድረጉ አይቀሬ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አምባገነኖች ራሳቸውን ለጦርነት ቀድመው ስለሚያዘጋጁ እና በተቃራኒው የሚወረወረው አካል ደግሞ ራሱን ስለማያዘጋጅ እና ስለማያደራጅ ነው። የኋላ ኋላ ግን የተወረረው አካል የተበዳይነት ቁጭት ስለሚያድርበት የወረረውን ኃይል በእርግጠኝነት ማሸነፉ አይቀርም። የዓለም የጦርነት ተሞክሮዎች የሚያሳዩት ይህንን ሃቅ ነው ፡ ለዚህ ደግሞ አያሌ ምሳሌዎች ማሳየት ይቻላል። ለዛሬው የተመረጡ ሦስት ጦርነቶችን በወፍ በረር እንመልከት።
አምባገነኖች በትዕቢት ሲወጠሩ ህሊናቸው ግራ እና ቀኙን፤ ፊት እና የኋላውን ማየት ስለሚያቆም ምድር ላይ ያለ ማንኛውም ኃይል ያለእነርሱ ፈቃድ መኖር እንደማይችል አድርገው ማሰብ ጀምሯል። በእኔ ልክ የተቀደዱ ልብሶችን ልበስ ! ብለው ማስገደድ ይጀምራሉ። ከዜጎቻቸውም አልፈው የጎረቤት አገራትን ሰላም ያውካሉ። ከማወክም አልፈው ወረራ ይፈጽማሉ። ከእነኝህ ዓይነት ሰዎች መካከል ናፖሊዮን ቦናፓርት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ናፖሊዮን ቦና ፓርቲ መላ አውሮፓን መግዛት አለብኝ ብሎ ቆርጦ ተነሳ። የሚችለውንም ያህል ወረረ። በዚህ ጊዜ አውሮፓውያን ናፖሎዮ ቦና ፓርቲን ከፈጣሪ በታች ያለ ፈጣሪያቸው እስኪመስላቸው ድረስ አግዝፈው አዩት። ናፖሊዮን ቦናፓርት በበኩሉ ራሱን ከፈጣሪው ጋር አስተካክሎ ተመለከተ። የትኛውም ምድራዊ ኃይል ሊገዳደረኝ አይችልም ሲል ለራሱ ነገረ። «የዱባ ጥጋብ ያለስንቅ ያዘምታል» ማለት ይህ አይደል !
በድሮ ጊዜ አንዱን ፈላስፋ እንደህ ሲሉ ጠየቁት «ሊያዝኑለት የማያስፈልግ እና የማይገባው ነገር ምንድን ነው?» ፈላስፋውም « የክፉ ሰዎች መሞት !» አለ። ናፖሊዮንም በአውሮፓ የክፉዎች ክፉ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር አውሮፓውያን በሰውየው ግብዝነት ቢያዝኑለትም የሰራቸው የግፍ ሥራዎች ያናድዳቸው ስለነበር ናፖሊዮን በዋተርሉ ጦርነት ሲሸነፍ ያልተደሰተ አልነበረም።
ሌላው አምባገነኖች ቀድመው በመውረራቸው እና በሚጠቀሙት ቅጥ ያጣ ጉልበት አሸናፊ መስለው የታዩበት ጦርነት ደግሞ የአንደኛው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ጦርነቶች ጀርመን እና አጋሮቿ በማን አለብኝነት ጠላቴ ብለው በፈረጇቸው አገራት ላይ ወረራ በመፈጸም ጦርነቱ እንዲፋፋም እርሾ ጨመሩ።
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ኢፔሪያሊስት አገራት የአፍሪካ እና የኤዥያን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት እና በፋብሪካቸው የሚያመርቷቸውን ሸቀጦች ማራገፊያ በማድረግ ገበያቸውን በማጧጧፍ ገቢያቸውን ለማሳደግ አስበው እኔ እበላ እኔ እበላ ሲሉ ተፋጠጡ። ተፋጠውም አልቀሩ ጎራ ለይተው የወታደራዊ ትብብር ቡድን መሠረቱ። ወታደራዊ የትብብር ቡድኖችን ለመመስረት ኦስትሪያ እና ጀርመንን የቀደማቸው አልነበረም። እንግሊዝ እና ፈረንሳይም የራሳቸውን ከእነጀርመን እና መሰል ጠላቶች ራሳቸውን ለመከላከል እና እንዲሁም በአፍሪካ እና በኤዥያ ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የጦርነት ትብብር ማእቀፍ መሠረቱ።
የእነኦስትሪያ እና ጀርመን የጦርነት ትብብር ቡድን በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ የበላይነት የሚዘወረውን የጦርነት ትብብር ቡድንን ለማጥፋት ቋመጡ። ጦርነቱ ተጀመረ። በጀርመን እና ኦስትሪያ የሚመራው ጥምር ጦር ወረራ በፈጸሙባቸው የተቃራኒ አገራት ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ውድመት እና እልቂት ፈጸሙ። በዚህም መጀመሪያ ላይ በእነጀርመን እና ኦስትሪያ የሚመራው የጦርነት ቡድን በእንግሊዝ እና በፈረሳይ የበላይነት የሚዘወረውን የጦር ትብብር ቡድንን በኃይል የደፈቀው መስሎ ነበር። ምክንያቱም በጀርመን እና ኦስትሪያ የሚመራው ጥምር ጦር ቀድመው ስለተዘጋጁ እና ቀድመው ወረራ ስለፈጸሙ ነበር። የኋላ ኋላ ግን ጀርመን እና ኦስትሪያ በፊታውራሪነት የሚመሩት ቡድን አይሆኑ ሆኖ ለመናገር በሚዘገንን መልኩ ለሽንፈት ተዳረገ። ድሮስ የዱባ ጥጋብ ትርፉ ይህ አይደል!
በአፍሪካ እና በኤዥያ የነበራቸውን ግዛት እና ገበያ ተደራሽነት ለማስፋፋት ቋምጠው የነበሩት የእነጀርመን ቡድን አይደለም ከአፍሪካ እና ከኤዥያ ጥቅም ሊያገኙ ይቅር እና ቀደም ሲል በእነሱ ስር ይተዳደሩ የነበሩ ግዛቶች እና አስተዳደሮች በእንግሊዝና ፈረንሳይ እና ጣሊያን እና ሌሎች አገራት ተቦጫጭቀው ተወሰዱ። ይህ ብቻ አይደለም የተሸነፉት አገራት አሸናፊዎቹ ለጦርነት ያወጡትን የጦርነት ወጪ እንዲከፍሉ ተገደዱ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም የእነጀርመን፣ ጃፓን እና ጣሊያን ወታደራዊ ቡድን ጠግበው እና በትዕቢት ተወጥረው የሚያደርጉትን አጥተው አቅላቸውን ሳቱ። ጥጋባቸው አይሎ ያለመጠን ሆነ። በእጃቸው ሳይሆን በእግራቸው አጨበጨቡ። ሰውን መግደል መዝረፍ መድፈርን እና መሰል ሰይጣናዊ ተግባራትን የዕለት ከዕለት የአስተዳደራዊ ሥራቸው አንዱ አካል እና መገለጫው አደረጉት።
አገራቱ በአውሮፓ፣ ኤዥያ እና በአፍሪካ የሚችሉትን ያህል አገር ወረሩ። የሚችሉትንም ያህል ሰው ገደሉ። የመጨረሻ መጨረሻ ግን የጀርመን፣ ጃፓን እና ጣሊያን የግፍ ሩጫ አሳፋሪ በሆነ ሽንፈት ተደመደመ። በዓለም አቀፉ ፖለቲካ የነበራቸው ተጽዕኖ በዜሮ ተባዛ። እነ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድምጽን በድምጽ የመሻር መብትን ያለማንም ከልካይ ሲወስዱ እነ ጀርመን ደግሞ ለኃያላኑ አገራት እንደ ገና ስጋ ለቅርጫ ቀረቡ። ከሰማይ በታች እንደፈጣሪ በሚፈሩበት ዓለም ተዋረዱ። ክብራቸው በቅኝ ግዛት ከተያዙ አገራት በታች ሆነ።
ሌላው በወፍ በረር እንድናየው ከመረጥኩት የአምባገነኖች ወረራ ደግሞ ሲያድ ባሬ (ዚያድ ባሬ) በኢትዮጵያ ላይ ያካሄደው ወረራ ነው።
ፕሬዚዳንት አብዲራሺድ አሊ ሸርማርኬን በመንፈቅለ-መንግሥት ፈንግሎ ሥልጣን የጨበጠው ሜጀር ጄኔራል ሲያድ ባሬ (ዚያድ ባሬ ) መንበረ ስልጣኑን በያዘ ማግስት ድንበር ማስፋፋትን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ተነሳ። የወሰን ማስፋፋት ፍላጎቱን ጥሙን ለመወጣት መጀመሪያ ላይ ያነጣጠረውም የጥቁሮች መኩሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ነበር። አነጣጥሮም አልቀረ የጥፋት ጥይቱን በኡጋዴን በኩል አሀዱ ብሎ ተኮሰ። በ1966 ዓ.ም ሶማሊያ የአረብ ሊግን መቀላቀሏ የዚያድባሬን የሶማሊያ ልብ በግብዝነት እንዲደነድን አደረገው።
ሜጀር ጄኔራል ሲያድ ባሬ (ዚያድ ባሬ ) ኢትዮጵያን በወረረ የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የሶማሊያ ጦር በሶቪዬት ኅብረት ይደገፍ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ከዩናይትስ ስቴትስ ጋር ወዳጅነት ነበረው። በወቅቱ በቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ የነበሩት ሶቪዬት ኅብረትና አሜሪካም በእንግድነት ተጋብዘው ይሁን በሌላ ምሥራቅ አፍሪካ መግባት ቻሉ። ጦርነቱንም አጧጧፉት።
ይህ በእንዲህ እያለ ከንጉሣዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊው አገዛዝ የተሸጋገረችው ኢትዮጵያ በይፋ ራሷን ማርክሲስት ስትል አወጀች። ወዳጅነቷም ከሶቪዬት ኅብረት ጋር ሆነ። አሜሪካ ደግሞ ድጋፏን ለሶማሊያ አደረገች።
የዚያድ ባሬ መንግሥት ወረራውን አጠናክሮ ወደ መሀል አገር ገሰገሰ። በኢትዮጵያ ላይ እልቆ መሳፍርት የሌለው ጥፋትም አደረሰ። በንፁሃን ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተፈጸባቸው። ወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር ድንበሬ እስከ አዋሽ ነው በማለት ወደ ሐረር ገሰገሰ። ይህን ተከትሎ በለውጥ ውስጥ የነበረው አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ምንስ አዲስ ቢሆን ከአባቶቹ የወረሰውን አገር የማስቀጠል አደራ መወጣት ነበረበት። ይሄኔ ነው በኢትዮጵያ ክተት የታወጀው። የክተት አዋጁን ተከትሎ አያሌ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ታጠቅ የጦር ሰፈር ደረሱ። በአጭር ጊዜ ወታደራዊ ስልጠናቸውን ጨርሰው በግንባር ተገኙ።
ሁለቱ አገራትም ወደ ቀለጠ ጦርነት ገቡ። በወቅቱ የኩባ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፎ ተዋጋ። የሲያድ ባሬ መንግሥት ኩባ የኢትዮጵያውን ጦር ደግፋ እየወጋችኝ ነው ሲል ለዓለም መንግሥት ወቀሳ አቀረበ። ይህንን ወቀሳውን እውነት መሆኑን ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳየትና ለማሳመን በማሰብ በአውደ ውጊያ የሚማረኩ የኩባ ወታደሮች በማስገደድ ለጋዜጠኞች መግለጫ እንዲሰጡ ተደረገ።
ውሎ አድሮ ግን የኢትዮጵያ ጦር ራሱን በሰው ኃይል እና በመሣሪያ አደራጀ። የዚያድ ባሬን ጦርም እያሳደደ ከመሬቱ ይደባልቀው ያዘ። በወረራ ተይዘው የነበሩ በርካታ ግዛቶችም በኢትዮጵያ ጀግኖች ቁጥጥር ስር ዋሉ። የመጨረሻው ውጊያም ካራማራ ላይ ተካሄደ። በወቅቱ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታገዘው የኢትዮጵያ ጦር በሰማይና በምድር ጥቃቱን በማጠናከር የሶማሊያን ጦር ድባቅ መታው ! በወረራ ይዞት በነበረው መሬትም ጠላትን ደቆሰው። እንዳይነሳ አድርጎ አርቆም ቀበረው። የተገፋችው ኢትዮጵያም ጦርነቱን በአሸናፊነት ደመደመች።
በግብዝነት እና በአጉል ትእቢት ተወጥሮ ኢትዮጵያን በወራረ ይዞ የነበረው ሜጀር ጄነራል ሲያድ ባሬ (ዚያድ ባሬን ) ከሽንፈቱ በኋላ ተቀባይነቱ እንደጠዋት ጤዛ ታይቶ ጠፋ። ታላቋ የሚል ቅጥያ የነበራት ሶማሊያም ከካራማራው ጦርነት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት መታመስ ጀመረች። ሲያድ ባሬም 1983 ዓ.ም ከሥልጣን ተወገደ። ከሥልጣን የተባረረው ዚያድባሬ እግሬ አውጭኝ ወደ ናይጄሪያ ሸሸ። እዩኝ እዩኝ ሲል የነበረው ዚያድባሬ ናይጄሪያን አድኝኝ ሲል ተማጸነ። ናይጄሪያም ልመናውን ሰምታ አስተናገደችው። ሕልፈተ ሕይወቱም ለአራት ዓመታት በስደት በቆየባት ናይጄሪያ ሆነ።
ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ለማንሳት ያስፈለገኝ የዱባ ጥጋብ የሚጠግቡ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን ማሳየት ነው። አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን እና የመሰሎቹ ፍጻሜ ምን ሊሆን ይችላል ለሚሉ ሰዎች ማረጋገጫ ይሄው ነው። የዱባ ጥጋብ እውነት የጠገበ ይመስለዋል።
የአህያ ስጋ ከአልጋ ሲሉት ከአመድ ሆነና ነገሩ በ2013 ዓ.ም በሕግ ማስከበር ዘመቻው በትግራይ ክልል የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ልጠግንልህ፣ ሕዝቡ ወደነበረበት ሕይወቱ እስከሚመለስ ስንዴ እየገዛሁ ላብላህ ማለቱ በእነጁንታው ሰፈር እንደሃጢያት ተቆጠረ። መከላከያንም ለሁለተኛ ጊዜ ወጉት። በዚህም ደስታቸው ዳር ስቶ ሲያበላ እና ሲያጣቸው የነበረውን መንግሥት ውለታ መክፈል ሲገባቸው «ወንድ ከሆነ ይግጠመን» በማለት ታበዩ።
ከትግራይ ክልል ወጥተውም የአማራ እና የአፋር ክልልን በግፍ ወረሩ። በግፍ በያዟቸው የአፋር የአማራ ክልሎች የሚገኙ የመሠረተልማቶችን አወደሙ። ሰዎችን ገደሉ ! ደፈሩ! አፈናቀሉ!። የኢትዮጵያ መጥፋት የሚያስደስታቸው ታሪካዊ ጠላቶች በደስታ አቅላቸውን ሳቱ። በተቃራኒው ወረራ የተፈጸመባቸው የኢትዮጵያ ልጆች በከፍተኛ እልህ እና ቁጭት እጅ ለእጅ ተያያዙ። በተባበረ ክንዳቸው የትግሬን ወራሪ ኃይል ቀጠቀጡት። መውጫ መግቢያ አሳጡት። እድለኞች ተርፈው ወደመጡበት ዋሻ ተመለሱ። አብዛኞቹ ግን በወረራ በያዟቸው መሬቶች ተቀበሩ።
አሁንም ከስህተቱ መማር ያልቻለው ወራሪው ቡድን ድፍን የበጋውን ጊዜ በሙሉ ሰላም ነው የምፈለግው፤ ተከብቤአለሁ፤ በርሃብ ላልቅ ነው ፤ ወዘተ እያለ እሪታውን ሲያቀልጠው ከረመ። በዚህም መንግሥት ምን አልባት ሕወሓት እና የጥፋት ፈረሱ በሰራው ስህተት ተጸጽቶ ይሆናል በማለት መድኃኒት፤ የእርዳታ እህል እና ነዳጅ በግፍ ወደ ትግራይ እንዲገባ አደረገ። ይሁን እንጂ ከስህተቱ መማር ያልቻለው የዱባ ጥጋብ የሚጠግበው ሕወሓት የአፋር እና የአማራ ክልሎች ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት ከፈተ ።
ይህ የዱባ ጥጋ እየጠገበ ኢትዮጵያን አላስቆም፤ አላስቀምጥ ያለ ኃይል የኢትዮጵያ ሕዝብ በተባበረ ክንድ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እስካልደመሰሰው ድረስ የኢትዮጵያ እድገት እና «ሰላም ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሁሌም ሲያለቅስ ይኖራል» ዓይነት እንደሚሆን ለመገመት የግድ ነብይ መሆንን አይጠይቅም ። ስለሆነም ይህን የዱባ ጥጋ የጠገበ አገር ጠል ቡድን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ያስፈልጋል። ሁሉም ተሰብሳቢዎች ሀሳቡን የደገፉት በጭብጨባ ነው። ስብሰባውም በዚህ ተጠናቀቀ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 /2014