ስለ ልጆቹ በጎ በጎውን ብቻ ካልሆነ በስተቀር ጥፋታቸውንና ድክመታቸውን ለማድመጥ የበርካታ ኢትዮጵያዊያን ወላጆች ጆሮ እጅግም የተከፈተ አይመስልም። “የእኔ ልጅ እኮ…!” እየተባለ አዘውትሮ በወላጆች የሚዘመረው ብቃታቸውና የባህርያቸው ውበትና ድምቀት ነው። ስህተታቸው ይፋ እንዲገለጥና የተገለጠው ስህተትም ሥር ሳይሰድ በባለሙያዎች እገዛና በወዳጆች ምክር እንዲታረም የመፈለጉ መነሳሳት በብዙዎች ዘንድ እጅግም ተመራጭ አይመስልም።
የዚህን መሰሉ ማሕበራዊ ህፀፃችን ዋነኛ ሰበብና ምክንያቱ ለብዙ ምርምር የሚጋብዝ ሳይሆን ያሳደገን ማሕበረሰብ እንዲህ ሆነን ሕይወትን እንድንመራ ቀርጾ ስለሠራን ነው። እንዴታውን እናብራራ፡- “ኑሮና መቃብር ለየብቻ ነው” በሚለው ነባር ባህል ተጠፈንጎ በኖረ ማኅበረሰብ ውስጥ የተፈጠረው የዛሬው ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ “የልጆቹን የችግር ገመና” ገላልጦ ለመፍትሔው ከመድከም ይልቅ፤ “በሩን ዘግቶ ተከድኖ ቢበስል” መምረጡ የኖርንበትና የተለማመድነው “ጥብቅ ኩራታች” ሆኖ እንደተጣበቀን እነሆ ዘመናትን ለመሻገር በቅቷል።
“እህል ከሆነ ይጠፋል፤ ልጅ ከሆነ ይገፋል” ተብሎ እንደተተረተባት እርጉዝ ሴት፤ ዛሬ ዛሬ የሆነውን እንዳልሆነ በመቁጠር “ልጄ/ልጆቼ እኮ…!” እያልን በይሉኝታ ስናሽሞነሙን የኖርነው ችግራችን ከዕለት ወደ እለት ከመቀነስ ይልቅ እየባሰና እየተወሳሰበ ሄዶ ፍሬው ተንዠርግጎ በመገለጡ በአንክርዳድ የተጠመቀውን “ጉሽ” እንደ ማሕበረሰብ እየመረረንም ቢሆን ለመጎጨት ግድ ብሎናል። ይህን መሰሉን የቤታችንን የፈተና ቋጥኝ እንደ ወላጅ በግልጽ እየተወያየን፣ እንደ ሀገር ቅድሚያ ሰጥተን እየመከርን ወደ መፍትሔው መቃረብ እስካልቻልን ድረስ ልጆቻችን በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ እየኖሩ ባእዳን ባለሀገሮች ወደ መሆን ደረጃ እንዳይሸጋገሩ ስጋቱ አስፈሪ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ችግሩም በቀላሉ ላይቀለበስ ይችላል።
ይህ የጋራ “ቁስላችን” ማስረጃና ማረጋገጫ የሚያስፈልገው አይደለም። “በቀይ መብራት” ጭምር እያስጠነቀቀንና እየቀሰቀሰን እንድንነቃ የሚጎተጉተንን የየቤታችንን የልጅ አስተዳደግና የአስተዳደር ተሞክሮን ብቻ መመልከቱ በቂና ከበቂ በላይ ይሆናል። ለአደጋው ክብደት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በግልጽነት ከመወያየት ይልቅ ዛሬም ከጋራ ችግሮቻችን ዐይን አፋርነት ለመላቀቅ ጥረት ያለማድረጋችን ሊታሰብበት ይገባ ይመስለናል። አንዳንዶቹን መሠረታዊ ምክንያቶችና ውጤታቸውን ከታሪክም ከነባራዊ ሁኔታም እየጠቃቀስን ለማሳያነት እናስታውስ።
የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ውድቀታችን፤
ቀዳሚዎቹ የሀገራችን ሁለት ሙት ሥርዓቶች (ደርግና ኢሕአዴግ) ዘርተውና ኮትኩተው የተንከባከቡት “እርግማን” እነሆ ዛሬ አዝመራው ነጥቶ ፍሬው በየቤታችን ለመዘመር በቅቷል። ግራ ገቡና ኮሚኒስት ነኝ ባዩ የደርግ ሥርዓት የሃይማኖትንና የነባር ሥነ ምግባር ፋይዳን በማጥላላት “ትውልድ የሚያደነዝዙ ኮኬይን ናቸው” በማለት በመርህ ደረጃ ያራመደው ፍልስፍና ብዙው ዜጋ “ለሃይማኖት ጥዩፍ፣ ለፈጣሪ ደንታ ቢስ” እንዲሆን ምክንያት ሆኖ ነበር። አልፎም ተርፎ በመንግሥት ሚዲያም ሳይቀር ይሄው ጥላቻ በግልጽ ይንጸባረቅ እንደነበር የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ ሉሌ(?) (ዮሐንስ ሙሉጌታ በሚል የብዕር ስም) “አጥፍቶ መጥፋት” በሚል ርዕስ ባስነበቡን መጽሐፍ ውስጥ እማኝነታቸውን የሰጡት እንዲህ በማለት ነበር።
“ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ሕዝቡ በመንግሥት ዐይን በማየት ‹ማስታወኪያ ሚኒስቴር› ሲለው ኖሯል። … ፓርቲው (አሠፓ) እና መንግሥቱ በሚከተሉት ርዕዮተ-ዓለም የተነሣ ሚዲያዎቹ በሚያስተላልፏቸው ፕሮግራሞች፣ ዜናና ሀተታ አማካይነት ሃይማኖቶቹን ጎነጥ ሳያደርጉ አያልፉም። ሌላው ቀርቶ በበዓላት ቀናት፤ “እንኳን ደረሳችሁ” ማለት ተለምዶ ነበር። “አደረሳችሁ” ከተባለ በውስጡ አምላክን የሚጠራና የሚያመሰግን መልዕክት ስላለው “ደረሳችሁ” መደበኛ ቋንቋ ወደ መሆን ደርሶ ነበር። አክራሪ ካድሬዎቹም “እንኳን ደረስህ” ሲባባሉም መልሱ “በትግሌ” ሆኖ ነበር” (ገጽ 112-113)።
የደርግ መንግሥት በዋና ዋና የሃይማኖት መሪዎችና በአማንያኑ ላይ ይፈጽም የነበረውን እስከ ግድያ የሚደርስ እጅግ ዘግናኝ ግፍ፣ የአምልኮ ሥፍራዎቻቸውንና የማሕበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማቱን በመውረስ ጭምር የወሰዳቸውን እኩይ እርምጃዎች በተመለከተ ይህ አምደኛ “ኤሎሄ እና ሃሌ ሉያ” በሚል ርዕስ በ1992 ዓ.ም በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ ዝርዝሩን በሚገባ ለማሳየት ሞክሯል።
ፀረ አምላክና ፀረ እምነት የሆነው የደርግ መንግሥት መናድ የጀመረውን የሃይማኖትና የሥነ ምግባር እሴቶች እጅግ በረቀቀ ስልት እንዳያንሰራራ በማድረግ ያጠናከረው በርዕዮተ ዓለም ፍልስፍናው ከደርግ ያልተሻለው “ኮሚኒስት ነኝ” ባዩ የኢህአዴግ ሥርዓት ነበር። የኢህአዴግ ሃይማኖት ጠልነት እንደተጠበቀ ሆኖ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ሥርዓተ ትምህርቱን ቀርጾ የተገበረው ፈሪሃ አምላክ እምነት እንዳይኖርና በጠንካራነት የሚገለጹት ነባር የማሕበራዊ እሴቶች አብረው እንዲከስሙ በማድረግ ጭምር እንደሆነ የግል እማኝነትን ዋቢ በማድረግ አስረግጦ መናገር ይቻላል። የአደባባይ ግልጽ ሌብነት፣ ዘረፋ፣ ሙስና፣ ለመደበኛ ሥራ የሚሰጥ ደካማ ግምት፣ በአቋራጭ ለመክበር የሚደረግ ሩጫ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚታየው ግዴለሽነት ወዘተ. ለሥነ ምግባር መራቆት ግርድፍ ማሳያዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ስለዚህ የዛሬዎቹ አብዛኞቹ ወላጆችም ሆኑ ልጆች በእነዚህ ሁለት ሥርዓቶች ውስጥ ተወልደው ያደጉ ስለሆነ “ሃይማኖታዊ እምነት” የፌዝ ያህል እንዲቀልና ግብረገብ ይሉት እሴት ደብዛው እስኪጠፋ ድረስ የልጆች አስተዳደግና አመራር ዘይቤያችንና የአኗኗራችን መርህ ግለኝነት የተማከለበት “ኬሬዳሽ እና ‹ምንተዳዬ›” ይሉት ዓይነት ሊሆን ግድ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ቀናት በፊት ከመላው ሀገሪቱ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ወጣቱ “ፈሪሃ ፈጣሪ” እንዲያድርበት አጥብቀው የመከሩት ይሄው ሀገራዊ ድቀታችን በእጅጉ ስላሳሰባቸው ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።
ልጆቻችንን ምርኮኛ ያደረገው ቴክኖሎጂ፤
ዓለማችን እንቅልፍ አጥታ በየእለቱ እያበረከተችልን ያለው የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የማሕበራዊ ሚዲያው ጉዳይ ለራሷ ለሰጭዋ ዓለማችን ሳይቀር “ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” እንዲሉ የበረከተ መርገምትነታቸው ውጤት በይፋ መገለጥ ከጀመረ ዓመታት ነጉደዋል። የዘመኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለምድራችን አዳሜና ሔዋኔ የሰው ዘሮች ሕይወትን በማቅለሉ ረገድ ያበረከታቸው አስተዋጽኦዎች በእጅጉ የሚመሰገኑ መሆናቸው በፍጹም የሚካድ አይደለም። የቴክኖሎጂው ትሩፋት ዓለም በጣታችን ውስጥ እንድትገባና አኗኗራችን በብዙ ዘርፍ “የገለባ ያህል እንዲቀል” ማድረጉን ለመካድም ሆነ ለመጠራር በፍጹም አይቻልም።
ችግሩ ከበረከቱ እኩል የመርገምትነቱ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ እየገዘፈ መሄዱ ላይ ነው። በከተማም ይሁን በገጠር በሚገኙት ልጆቻችን ዘንድ ያለ ማሕበራዊ ሚዲያ ተግባቦት ለመኖር እየተቸገሩ ብቻም ሳይሆን ለመኖር ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮቻችን (መብላት፣ መልበስ፣ መጠለል ወዘተ.) እኩል ዋጋው ከፍ ያለ ወደ መሆን ደረጃ ተሸጋግሯል። ግንኙነቱ ለመልካምነት፣ ለበጎነትና ለትምህርት ቢውል ኖሮ ባልከፋ፤ ችግሩ ከዚያም ገዝፎ በሕይወታቸው ላይ የሚፈጽመው ጫናና አሉታዊ ባህርያት መበራከቱ ላይ ነው።
በፌስ ቡክ፣ በዩ ቲዩብ፣ በቲክ ቶክ እና በበርካታ “እድፋም ማሕበራዊ ድረ ገጾች” አማካይነት ሥነ ምግባርንና ማሕበራዊ መስተጋብርን በማንኳሰስና በመዳፈር ለልጆቻችን እየጎረፉ ያሉት በጎ ያልሆኑ መልእክቶችና “አድርጉና ሞክሩት” እየተባሉ ለግብዣ የሚቀርቡላቸው “መርዞች” የስንቶቹን ልጆቻችንን ሕይወት እንዳበላሹና ለአደጋ እንደጋረጡ ለወላጆች ይጠፋል ማለት አይቻልም። ከተፈጥሯዊ ማሕበራዊ ግንኙነት እያራቋቸው፣ ለብቸኝነትና ለድብርት እየዳረጓቸው፣ በአልተፈለጉ “እርኩሰታዊ” ልምምዶች እየዘፈቋቸው እንዳሉ ፍሬያቸው በግልጽ እየተገለጠ ነው።
እርግጥ ነው አብዛኛው የመደበኛ ትምህርቶች አሰጣጥ “ቨርቹዋል” ወደሚሰኘው አተገባበር እየተሸጋገረ እንዳለ የሚካድ አይደለም። የመማሪያና የመርጃ መጻሕፍት፣ የቤት ሥራዎች፣ ለተጨማሪ የዕውቀት ግብዓቶች የሚያግዙ መረጃዎች፣ የምርምር ሥራዎችና ፈተናዎች ወዘተ. ሳይቀሩ በሙሉ የመገኛ ምንጫቸው ቴክኖሎጂው ጎራ ተጠቅልሎ እየገባ መሆኑ አይካድም። ደግመን እንላለን እነዚህ ሁሉ መልካም እድሎች የትምህርቱንና የምርምር ድካምን ስለመቀነሳቸው መካድም ሆነ ለክርክር ማቅረብ በፍጹም የሚቻል አይደለም።
ችግሩ ከእነዚህ መልካም ተግባራቱ ጎን ለጎን የሚጎርፉት ሥነ ምግባር የጎደላቸው መልእክቶችና ተግባራት በልጆቻችን ላይ የሚፈጥሩት ጫና፣ ሥነ ልቦናዊ ቀውስና መጥፎ ልምምዶች እንዴት ሊታረሙ ይችላሉ የሚል ነው። በእጅ ስልካቸው ላይ ተጥደው የሚውሉት ልጆቻችን ብቻም ሳይሆኑ መምህራንና ወላጅ ተብዬዎችም የዚሁ “ዘመን ወለድ” ችግሮች ተጠቂዎች መሆናችን የሚካድ አይደለም። ርእሰ ጉዳዩ በልጆቻችን ላይ ብቻ ስላተኮረ እንጂ ወላጆችንና መምህራንን በሚመለከቱ መሰል ጉዳዮች ላይ ወደፊት በስፋት መመለሳችን አይቀርም።
የሶሻል ሚዲያው በጎ ያልሆነ ተጽእኖ በዛሬዋ ዓለም በወጣቶች ላይ እያሳደረ ያለው ጉዳት እየተነጻጸረ የሚገለጸው “ድምጹን በማጥፋት የማሕበረሰብን በጎ እሴቶች እንደሚያወድም አጥፊ የኒኩሌየር አረር” ነው። በማሕበራዊ መረብ ግንኙነት (chat) ሱስ የተጠመዱ ታዳጊዎችና ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ከቤተሰባዊ ተሳትፎ ርቀው ብቸኝነትንና መገለልን መምረጣቸው የቤታችን ገመና የሸሸገው እውነታ ነው። አላግባብ የሚገድሉትን ጊዜያቸውን እያሰቡና “የሚዘፈቁባቸውን አይረቤ የስሜትና የሥነ ልቦና ማጦች” መለስ ብለው ሲመረምሩም በጸጸት ስለሚቀጡ ለበርካታ የፋይናንስ ቀውስና የጤና ችግሮች እንደሚዳረጉ ጥናቶች በስፋት እያረጋገጡ ነው።
እንቅልፍ ማጣት፣ ድብርት፣ በትምህርት አቀባበል ደካማ መሆን፣ ለሀሰተኛ ዜናዎችና መረጃዎች መጋለጥ፣ የበታችነት ስሜት፣ ለፍቅር ግንኙነት የተሳሳተ ግምትና እምነት ማሳደር፣ በመንፈሳዊ አምልኮ ስም ወደ ተሳሳቱ ልምምዶች መግባት ወዘተ. በመጨረሻም “ራስን በአይረቤነት ፈርጆ” ያልተገቡ እርምጃዎችን እስከ መውሰድ መድረስ በአጥኚዎቹ ውጤት የተረጋገጡ ዋና ዋና ማሳያዎች ናቸው።
ሚዛናዊነት የጎደለው የልጆቻችን የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም አሉታዊ ተጽእኖ ሙሉ ለሙሉ ተጠንቶ ተጠናቋል ለማለት ስለማያስደፍር ገና ብዙ ሊተኮርበትና ሊሰራበት እንደሚገባ ይታመናል። “ቴክኖሎጂው የዘመኑ ትሩፋት ስለሆነ ምን ማድረግ ይቻላል?” ከሚለው ከዳተኛነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በልጆቻችን የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ በጊዜ የተወሰነ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ከወላጆች እንደሚጠበቅ የዘርፉ ተመራማሪዎች አጽንኦት ሰጥተው መምከራቸው አልቀረም።
ልጆቻችን “ስማርት ስልክ ግዙልኝ!?” ብለው ሲጠይቁን “ምንገዶኝ! እኔ እንዳደኩት ልጄ ማድግ የለበትም” በሚል የቁጭት ውሳኔ ወላጆች ተገፋፍተው ለችግሩ ምክንያትና ሰበብ እንዳይሆኑ አጥብቀው ቢያስቡበት እንደሚበጅም ተደጋግሞ ይገለጻል። በሀገራችን ዐውድ እንደሚታየው ጡት የሚጠቡ ሕጻናት ሳይቀሩ ሲያለቅሱ ዝም ለማሰኘትና ለማባበል የሚሞከረው የእጅ ስልክን በመስጠት እስከ መሆን ተደርሷል። “በዕንቁላሉ ጊዜ” ያላረምናቸው ልጆቻችን “በበሬ ልክ የሚገመት ጥፋት” ሰርተው ሲጎዱና ማሕበረሰቡን እስከ መጉዳት ሲደርሱ ከመፀፀት ይልቅ ገና ከማለዳው ከጎናቸው ቆመንና እኛም አርአያ ሆነናቸው ወደ “ቀናው መንገድ” ብንመራቸው የተሻለ ይሆናል።
ይህ ዘመን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዘመኑን የሚዋጅ የሥነ ምግባር መገንቢያ የግብረገብ ትምህርት ለልጆቻችን የሚያስፈልግበት ወቅት ነው። የሃይማኖት ተቋማትና “ለሰብዓዊነትና ለበጎነት” ቆመናል የሚሉ ድርጅቶች ይህንን ችግር ልብ ተቀልብ ሆነው ቢያስቡበት ይበጀናል። አየሩ ላይ የናኙት የሀገራችን የሚዲያ ተቋማትም በርብርብ ከወላጆች ባልተናነሰ ድርሻ ችግሩ ላይ ለመዝመት የገዘፈ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊረዱት ይገባል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን “ፈጣሪን ፍሩና ታዘዙ” በማለት ለወጣቶች እንዳስተላለፉት ዓይነት መልእክት ደግሞ ደጋግሞ ከሃይማኖት መሪዎችና ከታላላቆች መስተጋባቱ እጅግ አስፈላጊና ተገቢም ነው።
የኪነ ጥበቡ ሰፈር፣ የትምህርት ሥርዓቱና የተለያዩ ማሕበራዊ መድረኮች (ስፖርት፣ ስካውት፣ ልዩ ልዩ የወጣቶች ተሳትፎ ወዘተ.) ርብርብ በማድረግ ለልጆቻችን ስኬት እንድንዘምር እንጂ ጉዳታቸውን እያየን እንዳናለቅስና እንዳንቆዝም ሊያግዙን ይገባል። ፍሬያማ ድርሻቸውን በመወጣትም የወላጆችን ጭንቀት እንዲጋሩ የትውልዱን አደራ በትከሻቸው ላይ ማስቀመጡ ተገቢና አስፈላጊ መስሎ ታይቶናልና መልእክታችን ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ይድረስልን እንላለን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 /2014