ትምህርት እና ጤናን እንደ ሸቀጥ?

ይህንን መጣጥፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳቀርብ የገፋፉኝ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም እኔም በግሌ ይህን መሠል ሁኔታን ተቀብሎ በዝምታ ማለፉን ሕሊናዬ ሊቀበለው አልፈቀደም፡፡ በመሆኑም ለበርካቶች ጭንቀት ድምፅ ሆኖ ማሰማት የዜግነት ግዴታ ነው ብዬ ማመኔም ሌላው ገፊ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

በሀገራችን የተጀመረው የኢኮኖሚያዊ ተሐድሶ ፕሮግራም “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተግባር እየዋለ ይገኛል። ይህም ኢኮኖሚው መነቃቃት እንዲያገኝ ዕድል የሠጠ ሲሆን ውጤቱ በአጭር ጊዜ የሚታይ አይደለም በመሆኑም ወቅቱ ሲደርስ በሂደት የምናየው ይሆናል።

ይህ ጉዳይ በተለያዩ ሀገሮች የተለያዩ ውጤቶች ያሳየበት ባሕሪይ ያለው ቢሆንም ሂደቱ ግን ከበድ ያለ ጫናን የሚያሳድር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። እድገትና ልማትን ለማረጋገጥ መከፈል ያለበት ዋጋ መኖሩንም መቀበል ተፈጥሯዊ ነውና እየጎመዘዘንም ቢሆን በረጅም ጊዜ ግቡ የሚያስገኘውን ተስፋ ስንቅ አድርጎ ችግሩን መቋቋም ይገባል።

ይህን አጠቃላይ የሆነ አስተያየት መግቢያ አድርጌ ለመንደርደር ምክንያት የሚሆነው ከዚህ በታች ከማቀርበው ሃሣብ ጋር ግንኙነት የሌለው ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንዲረዳ በማሰብ ነው።

የሰሞኑ የከተማው ዋነኛ መነጋገሪያ የብዙ ቤተሰቦች ጭንቀት ሆኖ የወጣው ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው 4ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ባፀደቀው፣ “የአዲስ አበባ አስተዳደር የግል ትምህርት አገልግሎት ክፍያ አሠራር ሥርዓት ረቂቅ ደንብ ቁጥር 194/2017 መሠረት፣ በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 1585 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1227 ያህሉ እስከ 65 በመቶ ብቻ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ ይችላሉ” በሚል የተሰራጨው ዜና ነው።

በመሠረቱ የከተማ አስተዳደሩ ይህን ደንብ ለማዘጋጀት ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ሰይሞ እንደፈፀመው የገለፀ ቢሆንም የተካሄደው ጥናት ግን ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ከግምት ያላስገባ፤ ከዚህ በፊት ትምህርት ተቋማቱ ያደረጉትን ጭማሪ ምን ያህል እንደሆነ ታሪካዊ ዳራውን ያልፈተሸ፤ ከሁሉም በላይ ግን ትምህርትና ጤና ለአንድ ማኅበረሰብ ሊቀርብለት የሚገባ የመንግሥት ግዴታ መሆኑን እንዲሁም ይህን መሠል ጉዳዮች እንደ ሌሎች ምርት እና አገልግሎት (ሸቀጦች) ዓይነት ባሕሪይ የሌላቸው እና በነፃ ገበያ የሚዳኙ አለመሆናቸውን የመረዳት ችግር ያለ ይመስላል።

ይህ ጉዳይ በአደጉት የአውሮፓ ሀገራት ጭምር በልዩ ሁኔታ የሚታይ በመሆኑ እንዲያውም እነዚህን ዘርፎች በግል ይዞታነት የማይያዙ የመንግሥት ብቸኛ ኃላፊነት ተደርገው የሚታዩና ጥበቃም የሚደረግላቸው ዘርፎች መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል። ይህን መሠል ጉዳይ ዙሪያ ጥናት ሲካሄድ በባለሙያዎችና የትምህርት ሚኒስትርም ሃሣቡን እንዲሰጥ መጠየቅ የነበረበት ጉዳይ ነው የሚል እምነት በፀሐፊው ዘንድ አለ። (ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የንግድ ቢሮ፣ የፕላንና ልማት ቢሮ እንዲሁም የፍትሕ ቢሮዎች የኮሚቴው አባላት እንደነበሩ የተገለፀ ቢሆንም፡፡)

ይህ ብቻ ሣይሆን ከደርግ ውድቀት ማግስት የግል ትምህርት ቤቶች የማቋቋም ፈቃድ በተሰጠበት ወቅት ጉዳዩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በጥንቃቄ የተፈቀደ ከመሆኑ በተጨማሪ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት የትምህርት ክፍያ ጉዳይ በጥብቅ ቁጥጥርና በሥርዓት ሲመራ እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ መረጃዎችም የሚያሣዩት የክፍያ ጭማሪ በዚህ ደረጃ ሲካሄድ እንዳልነበረ ነው።

የአዲስ አበባ የሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አይዘዲን ሙስባህ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት የግል ትምህርት ቤቶቹ የዓመታዊ ጭማሪ ጥያቄ ለባለሥልጣኑ እንዳቀረቡና ይህም ከ50% እስከ 263% ጭማሪ እንዲፈቀድላቸው ማመልከታቸውን አውስተው ይህንንም ለማረም ጥናት ያካሄደው ኮሚቴ የደረሰበት ድምዳሜ በተለያዩ ደረጃ ላሉ ትምህርት ቤቶች ማለትም ለቅድመ መደበኛ እስከ 45% ጭማሪ መፈቀዱን፣ ለአንደኛ ደረጃ እስከ 40%፣ ለመካከለኛ ደረጃ 45% እንዲሁም ለሁለተኛ ደረጃ 55% ዋጋ መጨመር ይችላሉ በማለት መግለፃቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

የከተማ አስተዳደሩ ይህን ውሳኔ ሲያሳልፍ ምን ታሳቢ አድርጎ ነው ለሚለው ጥያቄ በግልፅና በዝርዝር የቀረበ ባይሆንም ጠቅለል ባለ መልኩ የዋጋ ግሽበትን (infla­tion) ምክንያት ሆኖ ከትምህርት ቤቶቹ እንደቀረበላቸው የገለፁት ኃላፊው ኮሚቴውም ከዚሁ በመነሳት ፈቃዱን እንደሰጠ መገንዘብ ይቻላል። ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተው (inflation) በዚህ ደረጃ የሚመዘን ነውን? ይህስ ቢሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ትምህርት ቤቶቹ ሲያካሂዱት የነበረው ጭማሪ በዝርዝር ተፈትሾ የተሄደበት ውሳኔ ነውን? የትምህርት ቤቶቹ የሂሣብ መዝገብ (fi­nancial statement) በዝርዝር ታይቶ ያሉበት ቁመና ተጠንቶ የተወሰነ ጉዳይ ነውን?

ለምሣሌ ከሚያቀርቡት ጭማሪ ምን ያህሉ ለመምህራን፣ ምን ያህሉ ለትምህርት ቤቱ ዕድገት ማስፋፊያ በሚል ዝርዝር የፕሮጀክት ጥናት ቀርቦና ተፈትሾ ነው ወደ ውሳኔ የተደረሰው ወይስ በዘፈቀደ በቀረበ አስተያየት ላይ ተመሥርቶ የተሰጠ ውሳኔ? ፀሐፊው የኋለኛው ሚዛን እንደሚደፋ ያምናል።

እንግዲህ ትምህርት እና ጤና በነፃ ገበያ በማይመሩ በአደጉ ሀገሮች ጭምር በልዩ ሁኔታ የሚታዩና የዜጎች መሠረታዊ መብቶች በመሆናቸው ከንግድ እና ከሸቀጥ ምርቶች በእኩል የማይታይ የአገልግሎት ዘርፍ ነው በማለት ማጠቃለል ይቻላል። በመሆኑም “ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” ጋር ደባልቆ አላግባብ ሥራ ላይ የሚውል ከሆነ ችግር ስለሚፈጥር መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እርማት በማድረግ ትክክለኛ አቅጣጫ ማሳየት ይኖርበታል።

ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግና አንባቢያን ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲይዙ የአንድ የግል ትምህርት ቤት የዘጠኝ ዓመታት የክፍያ ዝርዝር በሰንጠረዥ መልክ ቀርቧል።

ከሠንጠረዡ መገንዘብ እንደምንችለው በ2009 አንደኛ ክፍል የነበረ ተማሪ በዓመት 8,800 ብር የትምህርት ቤት ክፍያ ይፈፀም ነበር፤ ለዚሁ አንደኛ ክፍል ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በ2017 የሚፈፀመው ክፍያ ወደ ብር 44,800 አድጎ የምናገኘው ሲሆን በዘጠኝ ዓመት ውስጥ የ36,000 ሺህ ብር እድገት ወይም ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህ ተማሪ ዘጠነኛ ክፍል በሚደርስበት ጊዜ ዓመታዊ ክፍያው ወደ 55,780 አድጎ እናገኘዋለን። ይህ የመጠን እድገት የተከሰተው በ2010፣ በ2011፣ በ2014 እና በ2016 በተካሄደው ጭማሪዎች ምክንያት ነው፡፡ ልዩነቱም ምን ያህል ሥርዓት የሌለው እንደሆነ 55,780-8,800=47,70ዐ መሆኑን እንመለከታለን።

እንግዲህ በ2018 የተማሪዎች ክፍያ ጭማሪ በዚህ ደረጃ እያደገ የመጣውን የክፍያ ተመን በዝርዝር ተፈትሾ የተፈፀመ አለመሆኑን የምንረዳው እንዲህ ብትን አድርገን ስንሠራው ነው፡፡ ሲጀመርስ የጭማሪ ጥያቄ ሊነሳስ ይገባዋልን? በማለት እንድንጠይቅ ያደርገናል። መንግሥትም የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ሕዝቡን ሊታደገው ይገባል።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በበሮባ ቶኪቻው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You