
ከሀገራችን የስኬት ጉዞዎች መሀል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር አንዱ ነው። መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ያለፉትን ስድስት የክረምት ዓመታት ዓለምን ባስደነቀ መልኩ ችግኞችን ተክለናል። ዘንድሮም ብዙዎችን ባሳተፈ መልኩ ሰባተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር 7.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ተደርጓል።
ያለፉት ስድስት የክረምት ዓመታት ተክለን በማጽደቅ ውጤት ያየንበት ነበር። ክረምትን ለልማት በሚል መፈክር በአረንጓዴ ልማት ከራሳችን አልፈን ለብዙዎች የማንቂያ ደወል በመሆን ቀዳሚዎች ሆነናል። አረንጓዴ ልማት ዛፍ ከመትከል ባለፈ በብዙ ሊተረጎም የሚችል ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድነት የቆሙበት፣ ለጋራ ጥቅም በጋራ የተጉበት እንደዚሁም ደግሞ እንደድህነት ያሉ አሳፋሪ ገመናዎቻችን በአንድነት ትግል እንደሚሸነፉ ያሳዩም ጭምር ነበሩ። ህብረብሄራዊነት የታየበት፣ በአንድነት ምንም ማድረግ እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት አጋጣሚ በመሆን ውዳሴ እያገኘ ይገኛል።
‹በመትከል ማንሰራራት› በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የዘንድሮው የተከላ መርሀ ግብር እንደሁልጊዜው ቃላችንን በማክበር ታሪክ የምንሠራበት መሆኑ አያጠያይቅም። በመትከል አጽድቀን ያንሰራራንባቸው ያለፉት ጊዜአቶች ለዛሬ ጉልበት በመሆን ወደፊት እንድንሄድ የሚያደርጉን ናቸው።
አረንጓዴ ዐሻራ ለአረንጓዴ ምድር አሁን ላይ ዓለም አቀፍ መሪ ሃሳብ በመሆን እየተሠራበት ያለ የንቅናቄ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ጽንሰ ሃሳቡ ዓለም አቀፍ ቢሆንም በመሪ ደረጃ ከፊት በመሆን እየመነራው የምንገኘው ደግሞ እኛ ነን። በእጆቻችን ዐሻራ ክረምትን ጠጥተው ለበጋ ተስፋ የሆኑን የዛሬ ችግኝ የነገ ዛፎቻችን ለመጪው ጊዜ የህልውና ዋስትና በመሆን ተወዳዳሪ የላቸውም።
ሀገር የብዙሃን መልክ ናት። እንዲህ ያለው ነቂሰ ውህደት ደግሞ ማረጋገጫ የሚያገኝበት ነው። ስንተክል ኢትዮጵያን እያጸናን፣ ለችግሮቻችን መፍትሄ እየሰጠን፣ የአብሮነት ዐሻራ እያኖርን ነው። ባለፉት የክረምት ዓመታት ውስጥ በሀገራችን መሬት ላይ ዐሻራዎቻችንን አኑረናል።
በአሁኑ ሰአት የዓለም ስጋት ከሆኑ ችግሮች መካከል የዓለም ሙቀት መጨመር በቀዳሚነት ይነሳል። ችግሩ በበርሃማነት እና በአየር መዛባት እንደዚህም ከሌሎች መሰል ችግሮች ጋር ተዳምሮ የብዙዎችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የከተተበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ በመሆን በቀዳሚነት የተቀመጠው ደግሞ አረንጓዴ ዐሻራ ነው። የእኛ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ ትርጉም ያለው ነው። በኢኮኖሚ የፈረጠሙ በርካታ ሀገራት ጉዳዩን አጢነው ለተፈጥሮ ዋጋ እንዲሰጡ ያደረገበትም ነው።
ጥሩ ሥራ ትርፍ አለው። በመትከላችን ሊመጡብን ካሉ በርካታ ስጋቶች ተርፈናል። ለምሳሌ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የደን ሽፋናችን በእጅጉ ጨምሯል። ከግብርና እና ከምግብ ዋስትና አኳያ አመርቂ ውጤት ታይተዋል። በርሃማነትን እና የአየር ንብረት ለውጥን በመቆጣጠር ረገድ ችግኞቻችን አስተዋጽኦ አድርገዋል። የከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋት የዚህ ዐሻራ ውጤቶች በመሆን ይጠቀሳሉ። ከዚህ ባለፈ ደግሞ በርካታ ሀገራት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው ለአየር ንብረት ለውጥ እንዲሠሩ ምክንያት እስከመሆን የደረስንበት አጋጣሚ የሚታወስ ነው።
በተለየ መልኩ ደግሞ ሀገራችን ለጀመረቻቸው ትላልቅ የሜጋ ፕሮጀክቶች የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ወሳኝ ሚና ያለው ሆኖ ውጤቱ እየታየ ነው። የታላቁን ህዳሴ ግድብ ብንወስድ አካባቢው ላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ተግባራዊ በመሆኑ ችግኞቹ ወደዛፍነት ተቀይረው አሁን ላይ አገልግሎት በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
በርሃማነትን በመከላከል፣ ሥነምህዳርን በመጠበቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በማስተካከል፣ የአፈር መሸርሸርን በማስወገድ እንዲሁም ለፍጥረት ተስማሚ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ዛፍ አይነተኛ ሚና ያለው ነው። ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በተለያየ የዓለም ክፍል ብዙ ችግሮችን እንሰማለን። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ቀድመን ተረድተን ከወዲሁ እያደረግነው ያለው እንቅስቃሴ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው።
ዛፍ ሕይወት ነው የምንለው ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ተነስተን ነው። የምንተነፍሰውን አየር የሚያዘጋጁልን እጽዋቶች ናቸው። እነሱ የሉም ማለት የእኛ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል። እኛ ለነሱ እነሱ ለእኛ አስፈላጊ የመሆናችን እውነታ ገና በጨቅላነታችን የተረዳነው እውነታ ቢሆንም ቸልተኝነታችን ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ተገቢ ከመሆኑም በላይ የሁሉም ሃላፊነት ነው።
ከዓለም መጥፊያ ትንበያዎች መሀል የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛው ነው። አሁን ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ካልቻልን ካለፈው ይልቅ መጪው ጊዜ አስፈሪ የሚሆንበት እድል የሰፋ ነው። ትናንት ላይ የተከልናቸው ችግኞች ዛሬ ላይ ዛፍ በመሆን በርካታ ጥቅም እየሰጡን ይገኛሉ። ዓመታት በተቆጠሩ ቁጥር የበለጠ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ሆነው የመገኘታቸው ነገር የታወቀ ነው። ዓለም ዓይኑን ወደ እኛ በማዞር የዓላማችን ተጋሪ በመሆን አካፋና ዶማ መጨበጥ ከጀመረ ዓመታት አልፈዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ከፖለቲካም ሆነ ከሌላ መሰል ሁኔታ ጋር ንክኪ የሌለው ሕይወት የማስቀጠል ጉዳይ ነው። ሁሉም ሰው ለራሱ እና ለሌላው ሲል በጋራ የሚያምጠው የደህንነት ምጥ ነው። ምጡ ሕይወት የሚወልድ፣ ሰላም የሚሰጥ በመሆኑ የጋራ ምጥ ነው።
ይህ ሀገራዊ ዓላማ የአየር ንብረት ለውጥን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የመኖር ዋስትናንም የሚያረጋግጥ በመሆኑ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ዓላማ ያለው ነው።
ተፈጥሮ ቁርጥ እግዜርን አረንጓዴ መልክ ናት። ከመልኩ መልክ ሰጥቶ በአረንጓዴ ቀለም ቀልሟታል። ምድር አረንጓዴ የሆነችው ሕይወት የሚገኝበት ትክክለኛው ማህጸን እሱ ስለሆነ ነው። እግዜር ለሁሉም መልክ ሲሰጥ ‹ምድር ሆይ አንቺ የለምለማት ውብ መልክ ነሽ፣ ሕይወት ባንቺ በኩል ካልሆነ በምንም በኩል ሊያልፍ አይችልም› ሲል እዳ ጭኖባታል። ዛሬ ላይ ዛፍ የምንተክለው በሰው ልጅ የጠፋውን የተፈጥሮ መልክ ለመመለስ ነው። እናም ወደሕይወት ጉዞ ለመጀመር።
ተፈጥሮ በዛፍ በኩል ነው ህልውናችንን የሰጠችን። ስንተክል ትውልድ እየቀረጽን ነው። ስንተክል ዘመን እያበጀን ነው። ስንተክል እዳችንን እየከፈልን ነው። ዛሬ ላይ የምንተክላት እያንዳንዷ ችግኝ ነገ ላይ ሕይወት በመሆን ውለታ ትከፍለናለች። ስለሆነም እንዳለፈው ጊዜ አሁንም ታሪክ መሥራታችንን ለመቀጠል ለሰባተኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ራሳችንን እናሰናዳ።
በዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም