
በኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት ክምችት በስፋት እንዳለባቸው ከሚጠቀሱ ክልሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዱ ነው። ይህም ሆኖ በስፋት እንደሚመረት ከሚነገርለት ወርቅ ባለፈ ሌሎቹ በሚጠበቀው ደረጃ ልማት ላይ እንዳልዋሉ በተደጋጋሚ ይነገራል። የወርቅ ምርትም ቢሆን በዘመናዊ መንገድ ካለመመረቱ ባለፈ፤ በከፍተኛ ደረጃ በኮንትሮባንድ እንደሚንቀሳቀስም የሚሰነዘሩ ትችቶች አሉ። ለመሆኑ ዛሬ በክልሉ ያለው የማዕድን ሀብት ልማት ምን ይመስላል? ስንል በክልሉ ማዕድን ቢሮ የማዕድን ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ዲንቃን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የበርካታ ማዕድናት መገኛ እንደሆነ ቢታወቅም ጥልቅ ጥናት ባለመካሄዱ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች በግልጽ ተንትኖ ለማስቀመጥ አልተቻለም። ይሁንና እስካሁን በተካሄዱ በጣም ጥቂትና ውስን ጥናቶች ውጤት መሠረት በመልማት ላይ የሚገኙ፤ ወደ ልማት በመሸጋገር ላይ ያሉና ያልለሙ፤ ነገር ግን በክልሉ እንደሚገኙ የሚገመቱ ተብለው በሶስት ተለይተዋል።
ከእነዚህ ውስጥ በአግባቡ ተጠንተው የልማት ሥራዎች እየተከናወነባቸው የሚገኙት ወረቅ፤ የከሰል ድንጋይ፤ እምነበረድ /ማርብል/ እና ግራናይት ናቸው። ወርቅ በክልሉ በሶስቱም ዞኖች በሁሉም ወረዳዎች ይገኛል። የድንጋይ ከሰል በክልሉ ከፍተኛ ክምችት እንዳለ የተለያዩ ጥናቶች አመላክተዋል። በተግባር ግን በክልሉ ካማሽ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የማልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ በቅርቡ በአሶሳና መተከል ዞኖች ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ። እምነበረድ በክልሉ በአሶሳ ዞን ቢልዲጊሉ ወረዳ ፤ በካማሽ ዞን ሰዳል ወረዳ በመተከል ዞን ድባጤ፤ ቡለን፤ ጉባ፤ ፓዊ፤ ዳንጉርና ማንዱራ ወረዳዎች በስፋት ይገኛል። በክልሉ የሚገኘው የእምነበረድ ማዕድን ነጭ፤ ግራጫ፤ ሰማያዊ እንዲሁም ሮዝ ቀለም ያለው ነው ይላሉ።
እንደእሳቸው ገለፃ፤ ሌላው የማዕድን ሀብት ግራናይት ነው፡፡ በቅርቡ መመረት የጀመረ ሲሆን፤ በዋናነት በአሶሳና መተከል ዞኖች በከፍተኛ መጠን ግራጫና ሮዝ ቀለም ያለው ግራናይት ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ፈቃድ የወሰዱ አልሚዎች ወደ ሥራ በመግባት ላይ ናቸው። በተጨማሪ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች የሚውል የባዛልት ድንጋይ፤ ጠጠርና አሸዋ በክልሉ ሶስቱም ዞኖች በስፋት እየተመረቱ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ በዘርፉ በርካታ ማህበራትና ግለሰቦች የማምረት ፈቃድ ወስደው፤ ለክልሉና ለአጎራባች ክልሎች ግብዓት በማቅረብ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል አመቲስትን ጨምሮ ሌሎች ማዕድናት በምን ያህል ደረጃ የት አካባቢ እንደሚገኙ የመለየት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ሲሉ የሚናገሩት አቶ አስናቀ፤ ይህ ሥራ ሲጠናቀቅ ለባለሀብቶች ክፍት በማድረግ የልማት ሥራዎች የሚጀመሩ ይሆናል። ዛሬ ላይ በጥቅሉ በክልሉ ያለውን ሁሉን አቀፍ አቅምና ሀብት በማቀናጀትና በመጠቀም ያለውን የማዕድን ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀም እየተሠራ ይገኛል ይላሉ።
እንደአቶ አስናቀ ገለፃ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የማዕድን ፈቃድ አሰጣጡ በማእከል ደረጃ የሚከናወን በመሆኑ የክልሉን የመወሰን ስልጣን የተጋፋ ነበር። በዚህ የተነሳ ከመሀል ሀገር ብቻ በሚንቀሳቀሱ የባለስልጣናት ቤተሰቦች በበላይነት የተያዘው የክልሉን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የነፈገና ለክልሉ ሕዝብና መንግሥት ምንም ድርሻ የማያበረክት ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና ከለውጡ በኋላ ግን በማእከል ደረጃ በወጡ ፖሊሲዎችና አዋጆች በመመራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል። ይህንን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ሀብት መፍጠር የቻሉና ወደ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች በመግባት ላይ ያሉ የክልሉ ነዋሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።
በማዕድን ዘርፉ በተፈጠረ መነቃቃት አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማነት በመቀየር ላይ ይገኛሉ። እንደ ክልል ወርቅ የማምረት ሥራ የሚከናወነው በሶስት ዓይነት መንገድ ነው፡፡ በባህላዊ፤ በአነስተኛና በከፍተኛ ደረጃ በሚል ተለይተው እየተመዘገቡ ፈቃድ ያወጣሉ። የመሬት እና የሮያሊቲ (ከሰሩት ላይ ለመንግሥት የሚከፍሉትን) ይከፍላሉ። ይህ የሚሰላው ከእያንዳንዱ መኪና የሚለማው እየተገመተ መሆኑን ያስረዳሉ።
የክልሉን የማዕድን ሀብት ልማት ተግዳሮት በተመለከተም የሚናገሩት አቶ አስናቀ፤ ዘመናዊውን መንገድ አለመከተል አንደኛው መሆኑን ያመለክታሉ። ይህም አልሚዎችን ለከፍተኛ ድካም፤ ወጪና አንግልት የሚዳርግ ሲሆን፤ የምርት ብክነት የሚያስከትል ነው። በዚህ ረገድ እስካሁን በክልሉ እየተከናወኑ ያሉት የልማት ሥራዎች በተለይ በወርቅ ልማት ረገድ በስፋት የነበረው አካሄድ በባህላዊ መንገድ ማምረት ነበር። በአሁኑ ወቅት 75 በመቶ የሚደርሱትን ባህላዊ አምራቾች ወደ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ድርጅቶች ለማሸጋገር ተችሏል ይላሉ።
ባህላዊ የሚባሉት የወርቅ ማውጣት ሥራን ሙሉ ለሙሉ በእጃቸው በጉልበት ሲሠሩ የነበሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ ዛሬ ግን እነዚህ ድርጅቶች በከፊል ዘመናዊ በመሆን ክሬሸር፤ ስካቫተርና ሎደር እንዲሁም የተለያዩ የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖችን በመጠቀም በማልማት ላይ የሚገኙ ሆነዋል ይላሉ።
በሌላ በኩል በክልሉ ያለው ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ለአካባቢው ነዋሪና ለሀገር በሚበጅ መልኩ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚኖርበት ጠቁመው፤ ይህንን እውን ለማድረግ በሁለት ጉዳዮች ላይ እንደክልል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው ሙስናን መከላከል ሲሆን፤ ሌላኛው ብክነትን ማስቀረት ነው። ሙስናን በመከላከል ረገድ የመጀመሪያ ትኩረት የሚሰጠው ራሱን አምራቹን በመቆጣጣር ረገድ ለሚከናወኑ ሥራዎች ነው።
በክልሉ በወርቅ ምርት ሂደት የሚሳተፉ አካላት እንደ ድርጅት የሚመዘገቡት አምራችና የወርቅ አቅራቢ በሚል ነው። ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር የሚደረገው ስምምነት ከግብር አሰባሰብ በዘለለ አሠራራቸውንና ሌሎች ጉዳዮችንም የሚያካትት መሆኑን ያስረዳሉ። ወርቅን በተመለከተ አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ የማስረከብ ግዴታ አለባቸው የሚሉት አቶ አስናቀ፤ የሚያገኙትን ገቢ በባንክ በኩል ለተቆጣጣሪ ክፍል እንዲደርስ የሚደረግ ይሆናል ይላሉ። በዚህ መልኩ የማይንቀሳቀስ ድርጅት ሲኖር፤ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ ፈቃድ አስከመንጠቅና ከዘርፉ አስከማስወገድ ብሎም እንደ ጥፋት መጠኑ በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ርምጃ በየደረጃው የሚወሰድ እንደሚሆንም አመላክተዋል።
እንደእሳቸው ገለፃ፤ በሌላ በኩል የቁጥጥር ሥራው ትኩረት የሚያደርገው ደላሎችና በመንግሥት ሠራተኛ አካባቢ በሙስና እና በጥቅማ ጥቅም የመተሳሰር ወንጀል ውስጥ የሚገቡትን ነው። በዚህ ረገድ ቢሮው ጥቆማ ከመቀበል ጀምሮ የማያቋርጥ የክትትል ሥራ የሚያከናውን ሲሆን፤ በጥፋት የሚገኙ አካላት በተመሳሳይ በወንጀል ተጠያቂ የሚደረጉ ይሆናል።
በአጠቃላይ በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት በመቆጣጠር ረገድ ከበፊቱ የተሻለ ውጤት ለመስመዝገብ በርካታ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ይህም ሆኖ በቁጥጥር በኩል እንደ ተግዳሮት ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል በድንበር በኩል አንዳንድ ጊዜም ደግሞ በመሃል ሀገር በኮንትሮባንድ የማስተላለፍ እንቅስቀሴ ይጠቀሳል። ይህንን ተግባር በክልሉ ማዕድን ቢሮ በኩል ብቻ መከታተልም ሆነ መቆጣጠር አይቻልም። በመሆኑም ቢሮው ለዚህ ተግባር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ጨምሮ ከወረዳዎች ጋር በመቀናጀት በመሥራት ላይ ይገኛል ይላሉ።
በዚህ አካሄድ እስካሁን ከሀገር ለማስወጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ሰር ውለው ሕጋዊ ርምጃ የተወሰደባቸው አሉ። ይህ ተግባር ከማዕድን ሀብት ሕገወጥ እንቅስቃሴ በዘለለ የሀገር ጉዳይ በመሆኑ የተጀመሩ ሥራዎች በልዩ ትኩረት ተጠናክረው የሚቀጥሉ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡
እንደአቶ አስናቀ ገለፃ፤ የማዕድን ሀብት ልማት ጉዳይ ሲነሳ የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዳለበት ይታመናል። ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚደረገው የሥራ እድል በመፍጠር ነው። አሁን ባለው አካሄድ በክልሉ በማዕድን ልማት ለመሳተፍ ፈቃድ የሚያወጡ አካላት የመጀመሪያ ሥራቸው የቅኝት ፈቃድ መውሰድ ነው። ይህንን ፈቃድ ተቀብለው ወረዳም ሆነ ቀበሌ ለሥራቸው ሲሄዱ ባሉት አስተዳደሮች አማካይነት ከማህበረሰቡ ጋር እንዲወያዩ ይደረጋል። በዚህ ሂደት ዋና ስምምነት የሚሆነው ለልማት ከተለየው ቦታ ሰላሳ በመቶ የአካባቢው ማህበረሰብ በልማቱ እንዲሳተፍ ማድረግ ነው። ይህንን ተከትሎ በአስተዳደሮች በኩል ነዋሪው እንዲደራጅና ማህበር እንዲያቋቁም ይደረጋል።
በሕጋዊ መንገድ በወረቀትና በማህተም ተረጋግጦ ከወረዳና ከቀበሌ፤ ከውሃ ቢሮ ጭምር ወደ ክልሉ ማዕድን ቢሮ ይላካል። ቢሮም አጠቃላይ ሂደቱን በመፈተሽ እውነተኛ መሆኑ ሲያረጋገጥ ባለሀብቱ ወይም በማዕድን ማውጣት ሥራ የሚሳተፈው ተቋም ሥራውን እንዲቀጥል ይፈቀድለታል። በምንም መልኩ ለልማት ከተለየው ቦታ ሰላሳ በመቶውን ለማህበረሰብ የማይለቅ አካል በማዕድን ልማት ሊሳተፍ አይችልም። ለቀጣይም የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት በየወቅቱ እየተሻሻለና እያደገ መምጣት ስላለበት የሚያገኙትን የሰላሳ በመቶ ድርሻ ለማሳደግ የሚያስችል መመሪያ ለማዘጋጀት በሂደት ላይ እንደሚገኙም ይናገራሉ።
ይሁንና የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ሲታሰብ በቀጥታ ከማዕድን ልማቱ ጋር ብቻ የሚያያዝ አይሆንም። ሆኖም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ እንደ ክልል በማዕድን ዘርፍ ለ4 ሺህ 361 ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ4 ሺህ 303 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ተችሏል። ነገር ግን ከዚህ በተጨማሪ የማዕድን ማውጣት ሥራ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ለሠራተኞች ምግብ ከማብሰል ጀምሮ በቅጥር የሚፈጠሩ የተለያዩ የሥራ እድሎች አሉ። ይህንን ተከትሎ በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር በር ተከፍቷል ለማለት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
አቶ አስናቀ እንደሚያብራሩት፤ የማዕድን ሥራን በተመለከተ የሚከናወኑ ልማቶች በሙሉ የአካባቢ ጥበቃን ከግምት ያስገቡ ናቸው። እንደ ክልል የማዕድን አዋጅ ደንብና መመሪያዎች ያሉ ሲሆን፤ አንዱ ክፍል የማእድን ልማት ሲከናወን ለአካባቢ ጥበቃ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች የተቀመጡበት ነው። እያንዳንዱ በማእድን ልማት ሥራ ላይ የተሰማራ አካል በፍለጋ ወቅትም ሆነ ማዕድን በሚያወጣበት ወቅት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ አካባቢን በማይበክል መንገድ መሆን ይኖርበታል።
የተቆፈሩ ጉድጓዶችን መልሶ መድፈንና በእጽዋት ወደነበሩበት መመለስ የባለ ሀብቱ ሃላፊነት ነው። በዚህ መልኩ የልማት ሥራውን ከጨረሰ በኋላ በአካባቢው በመሠረተ ልማት ለመሳተፍ ቃል ይገባል የሚሉት አቶ አስናቀ፤ ለምሳሌ ትምህርት ቤት ወይም ሆስፒታል የመገንባት ሥራዎች እንዲያከናውን የሚጠበቅ መሆኑንም ተናግረዋል። በዚህ መሠረት እየሠሩ ያሉ አንዳንድ አልሚዎች ቢኖሩም በገቡት ቃል መሠረት የማይንቀሳቀሱ መኖራቸውን በመጠቆም፤ እነዚህን ወደ ሥርዓት ለማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ይላሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የማእድን ልማት ሲታሰብ ከመሬት ቆፍሮ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የወጣው ሀብት በተገቢውና በሕጋዊ መንገድ ለገበያ እንዲቀርብ ማድረግ አንዱ ነው። በዚህ ረገድ ክልሉ በድንበር አካባቢ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እስከ ቅርብ ጊዜ በስፋት ይከናወን ነበር። በመሆኑም ይህንን ለመከላከል ከክልል ጀምሮ ቀበሌ ድረስ የተዋቀረ ግብረ ሃይል አለ። የገብረ ሃይሉ ዋና ተግባር የኮንትሮባንድ እንቅቃሴዎችን የመከታተል ሥራ ነው። በዚህ ሂደት ሕገ ወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ከተገኙ ግብረ ሃይሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስፈላጊውን ርምጃ ይወስዳል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በክትትል መቆጣጠርም ሆነ ርምጃ መውሰዱ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል በመጠቆም፤ አምራቾች በመደበኛው ገበያ የሚገባቸውን ጥቅም የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲፈጠሩ ይሠራል’ ይላሉ። በየወቅቱ በዚህ ሥራ የሚሳተፉ አካላት ለተደራራቢ ችግሮችና ቅጣቶች ከመጋለጥ ራሳቸውን እንዲቆጥቡ የግንዛቤ ማስጨመጫ ሥራዎች በስፋት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።
ከላይ የተጠቀሱት አበረታች ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ክልሉ ካለው የማእድን ሀብት ብዛትና ከቆዳ ስፋት አኳያ በቂ ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ ቢሮው የበለጠ መደራጀት ይጠበቅበታል ያሉት አቶ አስናቀ፤ አቅምን በማጎልበት ረገድ እንደተቋም ከተሽከርካሪ ጀምሮ በርካታ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውንም ያስረዳሉ። ቢሮው ከሚያገኘው በጀትም ሆነ ሌሎች የገንዘብ ማግኛ አማራጮችን በመጠቀም ራሱን የማደራጀት ሥራዎችን በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
በክልሉ መንግሥት በኩል አሁንም ድረስ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውሰው፤ የሚጠበቀውን ዓላማ ለማሳካት ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ። የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፤ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን መከታተልና በማእድን ማውጫ ቦታዎች አካባቢ ጥበቃን ማረጋገጥ እንደሚሆን አመላክተዋል። ይሁንና ይህ ከፍተኛ በጀትና አቅም እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
በራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም