ዛሬ የከፋኝን ላወራ ልተነፍስ ነው ብዕሬን ከወረቀት ያገናኘሁት። በጣም ከፍቶኛል ውስጤ የገባውን ኀዘን ጮክ ብዬ አልናገር እሪ ብዬ አልቅሼ አይወጣልኝ ነገር ደረቴ ላይ እየተንቀዋለለ መተንፈሻ አሳጥቶኛል። የወገኔን እርም በልቻለው። የእኔ ሰው ሲያለቅስ አላለቀስኩለትም፤ ደረቱን ሲደቃ አብሬው ለሙሾ አለቆምኩም የእሱ እንባ እኔ ደጅ አልደረሰም በሬን አላንኳኳም ብዬ ይሁን፤ መንጋው ምን ይለኛል ምን ብዬ ከዚህም ከዛም ወገን የእናት የአባቴ ልጅ ሲረግፍ ጎረቤት ዘመድ አዝማዴ ድኳን ጥሎ ሲያነባ እኔ ግን እርሙን በልቼበታለሁ።
የአገሬ ሰው፥ ሰርግ ከቀረበት ሰው ይልቅ ለቅሶ የቀረበትን ነው የሚቀየመው። ሁሉም እኔን ተቀይሞኛል። ለቅሶውን ተበላልተናል። እርም አለብን። ባለአገር ማለት ለቅሶ ደራሽ ነው። እንባ አባሽ የእዝኑን ይዞ ሄዶ እንባ ማደረቂያ የሚያጎርስ ነው። ያለችውን ይዞ ለቅሶ ቤት አምሺ አዳሪው ነው። እኔ ግን ለዛ አልታደልኩም፤ እንደው በቁዘማ መሬቱን ስጭር አድራለሁ፤ ኀዘን ገፍቶ የደፋው አንገቴ የወገኔን ኀዘን መሸከም ያቃተው ጫንቃዬ በራሱ ነፍስ አውቆ አስጎንብሶኛል።
ውስጤ የሚንቀዋለለው ስሜት ወጥቶ ወይ ወርዶ ሰላም የምናገኘው ለቅሶ ስንዳረስ ነው። ምክንያቱም የጋራ ኀዘን ነው አገር የሚፈጥረው። የእገሊት ኀዘን እኔን ተሰምቶኝ የእሷ ኀዘን ውስጥ ገብቼ “ውይ በሞትኩ!” ስንል ነው አገር የሚፈጥረው። “አይ የእገሊት ቀብር ሰርግ ነበር የሚመስለው፤ እድለኛ ናት” የሚባለው ለኀዘንም ዕድል የሚያጠይቀው ኀዘን የጋራ ሆኖ አገር ስለሚሠራ ነው።
በምሽት፥ ለጎረቤት ጩኸት ሮጠን የምንሄደው ነገ እኛ ጋር ሮጠው እንደሚመጡ እርግጠኛ ስንሆን ነው። ከጀርባው ያለ ምልክት ይኼ ነው። ይኼን ባናስብ ተጠቅልለን ነበር የምተኛው። ጎረቤት ሲጮህ … “እነ እከሌ ቤት ችግር አለ” ብለን ያገኘውን ለብሰን አንዳንዱም ላዩ ላይ ብጣሽ ጥሎ እርቃኑን ሮጦ የሚሄደው ለዚህ ነው። ባለአገር መሆን ብድር ማቆየት ነው፤ ነግ በኔ ማለት። ባለአገር ማለት ቅኔው ከባድ ነው። በሰፈሩት ቁና የሚሰፈርበትን ቀን አስቦ የወገኔን በር ያንኳኳው ችግር፤ እገሌ ቤት የገባው ኀዘን እኔ ጋር ይገባል ብሎ አስቦ ነገ ለሚሆነው ዛሬ ተጠንቅቆ መኖር ነው።
ታዲያ የእኔን እርም ሳላወጣ የወገኔን ለቅሶ ሳልደርስ ለተበደለው ካሳ ሳይከፈል ለአዘነው የእዝን ሳይወሰድ ሳልስት አርባ ሙት ዓመት ሳይወጣ፤ ኀዘኑ የውስጥ ረመጥ አድርጎ ያዳፈነውን አንጀቱን እየለበለበ ያሳመመውን ህመም ሳስብ ነው አንገቴን የደፋሁ።
እኔ እንኳን ኖርኩ ባልኩባት በዚህ ዕድሜዬ አገር ታማ ጣር ላይ በሆነችበት፤ የወገኔን እርም በበላሁበት ህመሙን ቁስሉን ማከም በተሳነኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ የአገሬ ህመሟ የወገኔ ኀዘኑ ነው ያስረጀኝ። የአገሬ ቁስሏ ነው ያቆሰለኝ። የበላሁት እርም ያላለቀስኩት ወገንን ፊት ማየት ተስኖኝ ነው ያጎነበስኩ።
ከሁሉ ከሁሉ የቆጨኝ ያች የሞተው ሞቶ የተረፉትን ለዘር ያድርግልኝ ብላ ልጆቿን በጉያዋ ወሽቃ የሰላም ንጋት ይመጣል እያለች ስትጠብቅ የነበረችትን እናት ተስፋ ማስቀጠል ያለመቻሌ ነገር፤ ደርሶ እየጠራ ያለውን የሰላም ውሃ ሲደፈርስ ተው ለማለት ያለመቻሌ ነገር፤ ዳግም በሰቀቀን ነጋ መሸ ነገ ምን ይመጣ ይሆን በሚል በሰለቸ ያፈጀ ሃሳብ ውስጥ ለመኖራቸው ከልካይ አለመሆኔ፤ በቃ ብዬ ሳልከላክልላቸው የመቅረቴ ነገር አንገቴን አስደፍቶኛል።
አገር ላይ ሰላም ለማስፈን፤ ጥላቻና ጦርነትን ለማቆም፤ ቂምና ቁርሾ እንዲሽር ማድረጊያ ዋናው መድኃኒት እርስ በእርስ መነጋገር ብቻ ሆኖ ሳለ፤ በባህላችንም ችግሮችን ለመፍታት የምንጠቀመው ሽምግልናን የመሰለ ወግ ከፊታችን ተቀምጦ፤ ምነው ጸብን በእርቅ ለመደምደም ከሽምግልና የበለጠ መፍትሄ አለመኖሩን ዘነጋን?።
ከሰዎች መካከል ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ ታዋቂና አዋቂ ፣ተወዳጅ ፣ አንደበተ ርዕቱእ ፣ አስተዋይ ሰው ተመርጦ አንተም አንቺም ተው ባይ ሽማግሌ የሚሰየምበት ለሰፈር ለጎረቤት ብቻ ሳይሆን ለአገርም የሚያስፈልጋት ወግ ሽምግልና መሆኑን ስለምን ዘነጋነው እያልኩ እጠይቃለሁ።
ምነው በተለያዩ ጊዜያት ሽማግሌዎች ተልከው፤ የሰላም እናቶች የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ አንግበው በጡቶቻቸው ሲለምኑ፣ በእንባ እየተራጩ፣ በጉልበታቸው ጭምር ተንበርክከው ለሽምግልና አደባባይ ሲቆሙ አንገታችንን ሰበር ማድረግ የተሳነን? ምነው የሰው ጥላው፣ የሽማግሌ ግርማው አልከብድ አለን? ሌላው ቢቀር የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በረሃብ እየረገፉ ያሉት ወገኖቻችን ጣር ለምን እኛ ፊት ላይ ምንም ርህራህ እንዳይፈጥር ሆነ?
ምነው ጥይት ከጨረሰው በላይ እኛው በፈጠርነው ችግር ምክንያት በበሽታ፣ የመድኃኒት እጦት፣ በረሃብ የሚጎሳቆልና የሚያልቀው ወገናችንን እርም በላን? ምነው በእኛ ጦረኝነት እንደ ቅጠል በሚረግፈው ወገናችን አስክሬን ላይ የሚፈጸም የመዘባበት ነውረኝነት መፀየፍ ተሳነን? ታዲያ ከዚህ በላይ ህመም፤ ከዚህ በላይ አንገት የሚያስደፋ ነገር ከየት ይመጣ ይሆን?
እኔ ግን ዕድሜዬን ረስቼ በእርጅና አቅም በማጣት እንድጠራወዝ አድርጎኛል። አገሬ ስለ ሰላም ሲል ጎንበስ የሚል፣ ስለ ሕዝቡ ሲል ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው የማጣቷ ነገር፤ አገሬ ጧሪ ደጋፊ ሳይኖራት የነገ ተስፋዋ ብሩሁን ቀን በልጆቿ እየጨለመ፤ ልጅ አልወጣላት ሲል ከመመለከት የተሻገረ ሌሎች አገሮች ከእኛ በሚፈሰው ወንዝ ልማት ሀብታቸውን ሲያሳድጉ እኛ በመነካከስ ላይ ቆመን፤ እርማችንን ስንበላላ የአንዱ ለቀሶ እኛን የማይገደን፣ የአንዱ ቁስል ሌላችንን የማያመን እንደ አገር ማሰብ ቀርቶ እንደ መንደር፤ እሱም ይቅር እንደ ቤተሰብ በሃሳብ መግባባት አቅቶን መደነቋቆርና መደነቋቆል የበዛበት ኑሮ አስልችቶኛል።
በጥቂቶች ፍላጎት ለሚያነባው ሕዝብ፣ በቡድኖች ቅዠት ለሚረግፈው ወገን፣ ለሰላም እንቢተኞች ሲባል ለሚጎሳቆለውና ነገው በአጭር እየተቋጨ ላለው ሕዝቤ ደርሼ እንባውን ያላበስኩለትም፣ ለቅሶውን ያላለቀስኩትም፣ በኀዘኑ ከጎኑ አልቆምኩለትም። እናም የዚህ ወገኔ ኀዘን አስጎንብሶኛል፤ ፊቱን ማየት አሰቅቆኛል። ለዚህም ነው “ይበቃል፣ ይበቃል፤…” ማለቴ። እናም በቃ ስለ ሰላም ሠርተንና ህመማችንን ሽረን የምንቀራረብባትን፤ አንዳችን ለአንዳችን አለኝታ የምንሆንባትን አገር እንፍጠር።
ብስለት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 /2014