ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (Strategic Pillars) መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ አቅም እና ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል። ግብይትን የሚያቀላጥፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መስፋፋትና ማደግ በዚህ ሂደት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ከሚኖረው ወሳኝ ሚና አንፃር በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ መሰል የቴክኖሎጂ አሰራሮችን መደገፍ ምጣኔ ሀብታዊ እድገቱን ዘላቂ ለማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥራዎች የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበትና የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማትና ተሳትፎ እያደገ እንዲሄድ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር፣ በኢኖቬሽን ልማት እንዲሁም በምርምር ሥራዎች ላይ የመሪነት ድርሻ እንዲኖረው እንደሚጠበቅ በአዲሱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲም ላይ ተጠቅሷል። ዘርፉ በመሠረተ-ልማት ሥራዎች፣ በሀብት ምደባ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ስለሚኖረው በመንግስት ይተገበሩ በነበሩ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የልማት ሥራዎች ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እያደገ እንዲሄድ እንደሚደረግም ያመላክታል።
በፖሊሲው ላይ እንደተመላከተው፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት ተደራሽ፣ አካታችና ቀልጣፋ የፋይናንስ አቅርቦት አማራጮች ይዘረጋሉ፤ ለሳይንሳዊ ምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ልማትና፣ ለኢኖቬሽን እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ግብይት የሚውሉ ፋውንዴሽኖችና ፈንዶች ይቋቋማሉ፤ኢኖቬተሮችንና ኢንተርፕረነሮችን ለማበረታታት የሚያስችል እንዲሁም ለኢኖቬሽን ልማት ሥራዎች የግሉ ዘርፍ ከመንግስት በቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኝበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል፤የተመራማሪዎች ማበረታቻ ስርዓትም ይተገበራል … በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንቨስተሮች ልዩ ልዩ የታሪፍ፣ የታክስ እና ተዛማጅ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እንዲሰጡ እንዲሁም ለዘርፉ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ተዋናዮች እንዲበረታቱ ይደረጋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ምርትና አገልግሎትን በዘመናዊ አሰራር የሚያቀርቡ ቴክኖሎጂዎች በብዛት ወደ ስራ እየገቡ ይገኛሉ። የዚህ ማሳያ የሆነውና ‹‹ማስዴል›› (MassDel) የተባለ የቴክኖሎጂ ተቋም የጭነት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ አሰራር በይፋ መጀመሩን ሰሞኑን ገልጿል። ‹‹ማስዴል››፣ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ እና አገልግሎቱን የሚፈልጉ ደንበኞችን የሚያገናኝ የሞባይል መተግበሪያ (Application) ሲሆን፣ ከመተግበሪያው በተጨማሪ የድረ-ገጽ (Website) እና የጥሪ ማዕከል (Call Center) አገልግሎቶችን ያካተተ ቴክኖሎጂ ነው።
ቴክኖሎጂው ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፤ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ አገራት የሶፍትዌር ባለሙያዎችን በማሳተፍ የተሰራ ነው። መተግበሪያው በአሁኑ ወቅት በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በቀጣይ ጊዜያት በሌሎች ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራም ይገኛል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ ቴክኖሎጂው ሰሞኑን ይፋ በተደረገበት ስነስርአት ላይ፤ ‹‹ማስዴል›› ቴክኖሎጂ የጭነት አገልግሎትን በማቀላጠፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉ ገልጸዋል። እንደርሳቸው ገለፃ፣ ቴክኖሎጂው ከአዳዲስ የሥራ እድሎች በተጨማሪ ነባር የሥራ እድሎች ዘላቂና መደበኛ እንዲሆኑ በማስቻል ዘላቂ የገቢ እድል ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል። የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂው ዘርፍ ተጠቃሚ እንደትሆን መንግሥት የግሉን ዘርፍና የልማት አጋሮችን በማስተባበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ በመንግሥት ከተወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎች መካከል አንዱ የ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ›› ተነድፎ ወደ ስራ መግባቱ ነው። በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ ከተቀመጡ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ይገኝበታል። የዲጂታል ኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶች ግንባታ፤ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን መገንባትንና ተደራሽ ማድረግን ይጠይቃል።
መንግሥት ኢ-ኮሜርስና ተያያዥ ቴክኖሎጂዎች እንዲስፋፉ አስፈላጊ የሆኑትን የሕግ ማዕቀፎችና የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ ለኢ-ኮሜርስ እና ተዛማጅ ስራዎች እውቅና የሚሰጠው የኢ-ትራንዛክሽን አዋጅ፣ ከዲጂታል ክፍያ እና ከሎጂስቲክስ አሰራሮች አንጻር የተዘጋጁ መመሪያዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ እና የኢትራንዛክሽን ደንብ ተጠቃሾች ናቸው ይላሉ።
በ2025 በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢ-ኮሜርስ የሚደረገው ግብይት ሰባት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ይህ የግብይት መጠን በተጠቀሰው ጊዜ በዓለም ላይ ከሚደረገው የችርቻሮ ሽያጭ ውስጥ 24 ነጥብ አምስት በመቶውን የሚሸፍን ይሆናል ብለዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ የሕዝብ ቁጥር፣ በርካታ ወጣት የሠው ኃይልና በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምሩቃን ያላት አገር መሆኗ ለዲጂታል ኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል ሲሉ አመልክተዋል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ፣ አገሪቱ ለዲጂታል ልማት በሰጠችው ትኩረት ምክንያት በዲጂታል በዘርፉ በርካታ የስራ እድሎች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ እድሎች ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀየሩት ቴክኖሎጂዎች ሲስፋፉና የግሉ ዘርፍ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ንግድ ስራ ሲቀይራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፤ ይህን ለማሳካት መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
‹‹ለዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ወሳኝ ከሆኑት ፕላትፎርሞች መካከል የኢ-ኮሜርስ ፕላትፎርሞች ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ የመልዕክት ወይም የጭነት ማድረስ አገልግሎቶች የኢ-ኮሜርስ ስራ የተሳካ እንዲሆን ጉልህ ሚና አላቸው›› ያሉት ወይዘሮ ሁሪያ፣ በ‹‹ማስዴል›› ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ ሁሉም አካላት ቴክኖሎጂውን በብቃትና በኃላፊነት ጥቅም ላይ በማዋል ለአገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሳካት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የ‹‹ማስዴል›› ቴክኖሎጂ ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተዋበ ይላክ፣ ‹‹ማስዴል›› የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ያበለፀጉትና ብዙ አማራጮችን አካትቶ የቀረበ ቴክኖሎጂ እንደሆነ ገልፀዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ቴክኖሎጂው በሞባይል መተግበሪያ ደረጃ የሚቆም አይደለም። የሞባይል መተግበሪያ፣ የድረ ገፅ እና ጥሪ ማዕከል (Call Center) አገልግሎቶችን በማካተት ሁለገብ ሆኖ የመጣ ቴክኖሎጂ ነው። ‹‹ማስዴል›› በተደራጀና በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚመራና የሚተዳደር የቴክኖሎጂ ተቋም በመሆኑ፣ መተግበሪያው በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ላይ የሌሉ የአሰራር መተግበሪያዎችን አካትቶ ይዟል ። ለአብነት ያህል ‹‹ማስዴል›› እቃ አስጫኞች ጨረታ አጫርተው ማስጫን የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል። ይህም ቴክኖሎጂው አሰራሩ ግልጽ በመሆኑ መኪና ያለው ሰው ሁሉ ለመጫረት ያስችለዋል፤ የጭነት አገልግሎት ፈላጊዎቹም ዋጋዎቹን አወዳድረው ዝቅተኛ ዋጋ የሚያገኙበትን እድል ይፈጥርላቸዋል። ጨረታው የጊዜ ገደብ አለው። መወዳደር የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ጭነቱ ከመነሳቱ ቀደም ብለው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ይወዳደሩና ጨረታው ይዘጋል። የጨረታው አገልግሎት ጠያቂዎች ከዋጋም ይሁን ከሌሎች ፍላጎቶቻቸው አንፃር ባለመኪናዎችን ይመርጣሉ፤የተመረጠው ባለመኪና መልዕክት ይደርሰዋል።
‹‹ማስዴል››፣ የጭነት አገልግሎት ፈላጊዎች የጭነታቸውን እንቅስቃሴ መከታተል የሚችሉበት አሰራርም (Online Tracking Platform) አለው የሚሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ አሽከርካሪዎች ስልካቸው ቢጠፋባቸው፣ ባትሪ ቢዘጋባቸው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ መኪኖች ላይ የጂፒኤስ (GPS) መከታተያ ለማስገጠም እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። ሌላው ‹‹ማስዴል›› የፈጠረው እድል ማንኛውም ማስጫን የሚፈልግ ሰው የሚያስጭነውን ሲያሳውቅ አሽካርካሪዎች ጥያቄውን ተመልክተው የጉዞ ካርታ በመንደፍ ጭነቶቹን ማንሳት የሚችሉበት አሰራር መሆኑን ነው ይላሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ቴክኖሎጂው በተለያዩ አማራጮች አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ነው። ከሞባይል መተግበሪያ በተጨማሪ ደንበኞች በድረ-ገፅ እና በጥሪ ማዕከል (7691) በኩል አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ አማራጮችን አዘጋጅቷል። ‹‹ማስዴል›› ቴክኖሎጂ አሽከርካሪዎች የትኛውን ጭነት ቢያጓጉዙ አዋጭ እንደሚሆንላቸው የሚጠቁም አሰራርም አለው።
‹‹ማስዴል›› ቴክኖሎጂ ከጥቂት ተጠቃሚዎች ብዙ ገንዘብ ማግኘት ሳይሆን ከብዙ ተጠቃሚዎች ብዙ ገንዘብ ማግኘት እንዲቻልና ሁሉም አሸናፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ በመሆኑ አገልግሎት ፈላጊው ማኅበረሰብ በቀላል ዋጋ ሊስተናገድ የሚችልበትን እድል የሚፈጥር ነው።
አቶ ተዋበ እንደሚሉት፣ ‹‹ማስዴል›› አሁን እየተከፈለ ካለው ዋጋ ከ30 እስከ 40 በመቶ በሚቀንስ ዋጋ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ ነው። ይህ ዋጋ አሽከርካሪዎችንና የተሸከርካሪ ባለንብረቶችን የሚጎዳም አይደለም፤ አሽከርካሪዎች በብዛት በመስራት ቀደም ሲል ሲያገኙት ከነበረው ገቢ በእጥፍ የላቀ ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እቃ በዝቅተኛ ዋጋ ከማስጫናቸውም በተጨማሪ ያስጫኑት እቃ ወደሚፈልጉት ቦታ መድረሱን የሚከታተሉበትና የሚያረጋግጡበት አሰራር አለው። የተሸከርካሪ ባለንብረቶችም የተሽከርካሪዎቻቸውን እንቅስቃሴ ለመከታተልና ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል። ቴክኖሎጂው ከአሽከርካሪዎች በተጨማሪ ቴክኖሎጂውን በሚመራውና በሚያስተዳድረው ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰዎችም የሥራ እድል ፈጥሯል።
በቴክሎጂው ለመጠቀም በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺ በላይ መኪናዎች ተመዝግበዋል። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ድርጅቱ ከ30ሺ በላይ መኪናዎችን የመመዝገብ እቅድ አለው። ደርጅቱ በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር በ10ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል። አገልግሎቱ በሚቀጥለው ዓመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭና ግብይት ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል።
የጭነት ገበያው ሁለት ወይም ሦስት አገልግሎት ሰጪ ቴክኖሎጂዎችን ብቻ ሳይሆን በርካታ ተቋማትን የማስተናገድ አቅም ያለው ትልቅ ገበያ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ‹‹ሌሎች ተወዳዳሪ ተቋማትንም እናበረታታለን›› ብለዋል። ‹‹የትኛውም የጭነት መኪና ክፍት ቦታ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ ግብ አለን። ኢትዮጵያ ነዳጅ በውድ ዋጋ የምትገዛ በመሆኗ ያለጭነት የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች እንዳይኖሩ በማድረግ ነዳጅ እንዳይባክን የማድረግ እቅድም ይዘናል። በዚህ ሂደት የተሽከርካሪዎች ምርታማነት ይጨምራል። የዚህ ስራ አጠቃላይ ውጤት ደግሞ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል›› ሲሉ አብራርተዋል።
በአጠቃላይ ‹‹ማስዴል›› ቴክኖሎጂ ለአገልግሎት ፈላጊዎችና አቅራቢዎች ወጪና ጊዜ ቆጣቢ አሰራር ነው። ተሸከርካሪዎች ያለጭነት የሚንቀሳቀሱበትን ጊዜ በመቀነስ የመኪናዎችን ምርታማነት ይጨምራል። ለጭነት ፈላጊው በአቅራቢያው የሚገኝ ተሸከርካሪ የሚመደብ በመሆኑ አላስፈላጊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታ ጥበትን በመቀነስ ለትራፊክ ፍሰቱ ሰላማዊነት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል።
አሁን አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ነው። ብዙ ፍላጎት እየመጣ ያለው ከአዲስ አበባ ውጭ ካሉ አካባቢዎች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተዋበ፣ በቀጣይም አገልግሎቱን በሌሎች ከተሞች ለመጀመር ጥናት እንደተጀመረና ከአጋር ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያም ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ለመንቀሳቀስ እንደታቀደም ገልፀዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 /2014