ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ወደ አቧሬ በሚወስደው መንገድ አለፍ ብሎ በስተቀኝ በኩል ብርቱካናማ ቀለም የተቀባ ባለሶስት ክፍል የብሎኬት ቤት ይታያል። በዙሪያው ካሉ ቤቶች ይልቅ አዲስ መሆኑ ደግሞ በቀላሉ እንዲለይ አድርጎታል። በብሎኬት በተሰራው ቤት ዙሪያ የሚገኙ ከጭቃ የተሰሩና እርጅና የተጫጫናቸው ቤቶች በዚህ አዲስ ቤት የተሸማቀቁ ይመስል ደብዝዘው ይታያሉ።
የዛሬን አያድርገውና ይህ ቤት ከመሰራቱ በፊት በቦታው ላይ ለመፍረስ ቀኑን የሚጠባበቅ ከጭቃ የተሰራ አንድ ክፍል ቤት ነበረበት። ታዲያ ይህ ቤት ፈርሶ ዳግም አዲስ ቤት በቦታው ላይ ይሰራል ብሎ የገመተም ያለመም አንድም ሰው አልነበረም። በዚህ ቤት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በድንገት መገኘት ግን ሁሉንም ነገር ቀይሮታል። ዛሬ በዚህ ቤት ከተስፋ ማጣት ወደ ተስፋ ማግኘት የተሸጋገሩ፤ በእድሜ የገፉ እማሆይ ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ይኖሩበታል።
እማሆይ አዱኛ ከአባታቸው ጉታ ቃዊሶ እና ከእናታቸው ሙሉነሽ ወልደማርያም በደቡብ ኦሮሚያ ከሞያሌ አለፍ ብሎ ዲሎና በሚባል አካባቢ አንደተወለዱ ይናገራሉ። የተወለዱበትን ጊዜ በቅጡ ባያውቁትም ጣልያን ሀገሪቱን በወረረበት ወቅት እንደተወለዱና እድሜያቸውም ሰማኒያ እንደሚገመት በቅርብ ዘመዶቻቸው እንደተነገራቸው ይገልፃሉ።
እናታቸውን በልጅነታቸው ያጡት እማሆይ አዱኛ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ችግር ፈትኗቸዋል። ትምህርትም አልተማሩም። ብዙም ሳይቆዩ ወደ ነገሌ ቦረና ያቀናሉ። እዛም ወታደር አግብተው መኖር ይጀምራሉ። ሁለት ልጆችንም ይወልዳሉ። ባለቤታቸው ወታደር በመሆናቸውና ለግዳጅ በርካታ ቦታዎች ላይ ስለሚንቀሳቀሱ የቤተሰቡ ኃላፊነት በእርሳቸው ጫንቃ ላይ ይወድቃል።
ከነገሌ እስከ ጅማ፣ ከጅማ እስከ አዲስ አበባ የዘለቀው የእማሆይ አዱኛ ህይወት ወትሮውንም በፈተና የተሞላ የነበረ ቢሆንም፤ በተለይ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ወዲህ በፈተና ላይ ፈተና ተደራርቦባቸዋል። እዚህ አዲስ አበባ ከሁለት ልጆቻቸውና ከባለቤታቸው ጋር ከመጡ በኋላ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ጎን ባለው የወታደሮች ካምፕ ውስጥ ሁለት ክፍል መኖሪያ ቤት በአስር ብር ተከራይተው መኖር ይጀምራሉ። የህይወትንም አዲስ የትግል ምእራፍም ይጋፈጣሉ።
ስምንት ልጆችን የወለዱት እማሆይ አዱኛ ለእርሳቸው ከባድ ፈተና የገጠማቸው ባለቤታቸው በነገሌ ጦርነት ከሞቱ በኋላ ነበር። በዚህ ጊዜ የሙት ልጆቻቸውን ለብቻቸው ማሳደግ ለእርሳቸው ከፈተናም በላይ ነበር። የባለቤታቸው 53 ብር የጡረታ ገንዘብ ልጆቻቸውን ለማሳደግም በቂ አልነበረም። በዚህም በካምፑ ውስጥ እየኖሩ ዛሬ አዲሱ ቤታቸው በተገነባበት ቦታ ላይ ሽንኩርትና ጎመን በመዝራት ሸጠዋል። ተከፍሏቸው ውሃ ከቦኖ አመላልሰዋል። ከልጃቸው የክርስትና እናት ባገኙት ሃምሳ ብርም ጉሊት ቡናና ስኳር ነግደዋል። ጠላ ጠምቀውም ሽጠዋል።
አሁን ያሉበትን ቦታ አጥረው ለራሳቸው እንዲያደርጉት አንድ በወታደሮች ካምፕ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሀምሳ አለቃ ምክር ብጤ እንደሰጧቸው የሚያስታውሱት እማሆይ አዱኛ፤ ምክሯን ተቀብልው በዚች ቦታ ላይ ባለሰባት ቆርቆሮ አንድ ክፍል ቤት ለመገንባት ያስባሉ። ወዲያም በካምፑ ይኖሩ የነበሩ ወታደሮች ቦታውን በማጠር ተባብረው ቤቷን ይገነቡላቸዋል። ከካምፑ ለቀው በመውጣትም በዚች አዲስ ጎጆ ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር መኖር ይጀምራሉ።
እማሆይ አዱኛ በዚች አንድ ክፍል ጎጆ ውስጥ ክፉውንም ደጉንም አሳልፈዋል። ልጆቻቸውን ድረዋል፤ ግማሹንም ቀብረዋል። አስር የልጅ ልጆችንም አይተዋል። ጉልበታቸው እስኪደክም ልጆቻቸውን ለማሳደግ ለፍተዋል። ጉልበታቸው እየተዳከመ እስከመጣበት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የባለቤታቸው የጡረታ ገንዘብ ላይ አምስት ብር ተጨምሮላቸው ህይወትን በድህነት ሲገፉ ቆይተዋል። አዲስ አበባ መኖር ከጀመሩም ስልሳ ስምንት ዓመታት እንደዘበት ተቆጥረዋል።
ይህች ደሳሳና ድህነት ጥላውን ያጠላባት ጎጆ ቤት በእማሆይ አዱኛ እሳቤ እንኳንስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርና በአካባቢው ጎረቤት እንኳን ትጎበኛለች የሚል ግምት አልነበረም። ያቺ ቀን ለእማሆይ እጅግ አስደናቂና የማያልቀው ነገር ግን አዲሱ የህይወታቸው ምእራፍ የተጀመረበት መሆኑ ይታወሳቸዋል።
ወቅቱ ክረምት ዓመተ ምህርቱ ደግሞ 2010 ሲሆን፣ የአዲስ ዓመት መቃረቢያ ነበር።
በጊዜው ጋዜጠኞች ደሳሳ ጎጇቸውን ሲወሩ ‹‹ምን ተፈጠረ?›› በሚል በድንጋጤ ውስጥ እንደነበሩ እማሆይ አዱኛ ሁኔታውን ያስታውሳሉ። በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እቤታቸው ሲመጡ የበለጠ ግራ ይጋባሉ።
እማሆይ አዱኛ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሆናቸውን ሰዎች ሲያወሩ ይስሙ እንጂ በፎቶ ወይም በቴሌቪዥን አይተዋቸው አያውቁም። እቤታቸው የመጡ ጊዜም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መሆናቸው ሲነገራቸው በእጅጉ ተገርመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹በእርግጥ እኔን ያውቁኛል?›› ብለው በጠየቋቸው ጊዜም ‹‹አላውቅዎትም›› የሚል መልስ ሲሰጡ በደሳሳዋ ጎጆ ውስጥ ሳቅ ነግሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደሳሳዋ ጎጆ ፈርሳ በአዲስ እንድትሰራ ትእዛዝ ያስተላልፋሉ። እማሆይ አዱኛም ከደስታቸው ብዛት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉት ያጣሉ፤ ቃላትም ያጥራቸዋል። ብቻ ምርቃቱን በላይ በላይ ያዥጎዶጉዱት ጀመር። ልክ እንደርሳቸው ሁሉ በዙሪያቸው ያሉ በደሳሳ ጎጆ ውስጥ የሚኖሩ ጎረቤቶቻቸውም ቤት እንዲሰራላቸው እግረመንገዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠየቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ‹‹ግድ የለም ለእነርሱም ይሰራል›› የሚል መልስ ሰጧቸው። ያቺ ስንት ታሪክ ያሳለፈች የእማሆይ ደሳሳ ጎጆ ብዙም ሳይቆይ ተንዳ በባለሶስት ክፍል የብሎኬት ቤት ተተካች፤ ብዙም ሳትቆይ ሞቀች።
ማጣት እንደማይወዱና ላጣም ሰው ከፍተኛ ሀዘኔታ እንዳላቸው የሚናገሩት እማሆይ አዱኛ፣ ሰው ሲያገኝና ሲሞላለት ደግሞ በእጅጉ እንደሚደሰቱ ይናገራሉ። እርሳቸውም በማግኘትና በማጣት ውስጥ ለዓመታት በድህነት የኖሩ ቢሆንም በዚች ቤት ምክንያት ዳግም አዲስ ተስፋ በማየታቸው እድሜ የሰጣቸውን ፈጣሪያቸውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያመሰግናሉ።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ ቤታቸውን መጎብኘታቸውን ተከትሎ አዲስ ቤት እንዲሰራላቸው በመደረጉ ጎረቤቶቻቸው ደስተኛ በመሆናቸው ‹‹የአብይ እናት›› የሚል ተቀፅላ ስም አውጥተውላቸዋል። እስካሁንም ድረስ በእርሳቸው ደስተኛ የሆኑት ጎረቤቶቻቸው እቤታቸው ድረስ እየመጡ ይጠይቋቸዋል።
እማሆይ አዱኛ አንድም ቀን ቤታቸው ፈርሶ በአዲስ መልክ ይሰራል የሚል እምነት እንዳልነበራቸው በተደጋጋሚ የሚናገሩ ሲሆን፣ ይህ በመሆኑ እራሳቸውን እንደ
እድለኛ ይቆጥራሉ። ቤታቸው ከተሰራ በኋላም የእርሳቸውን ዜና የሰሙ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የእቤታቸውን እቃ ስላሟሉላቸው የበለጠ እድለኛ እንደሆኑ ይናገራሉ። ልክ እንደሌላው ሰው ሁሉ እርሳቸውም የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እለት በእለት ባይከታተሉም ለኢትዮጵያ ሰላም ግን አብዝተው ይመኛሉ፤ ሌት ተቀንም ይፀልያሉ።
የእማሆይ አዱኛ አዲስ ቤት በኩራት ቆሞ ከጎረቤታቸው ቤቶች ይልቅ እኔ እብልጣለሁ እንደሚል የሚያሰብቅ ቢሆንም ከዚህ በፊት ልክ እንደ እርሳቸው ሁሉ ለመፍረስ ጥቂት ቀን በቀራቸው ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ጎረቤቶቻቸው የተሻለ ቤት እንዲያገኙ ይፀልያሉ። ሁሉም ጎረቤቶቻቸው ልክ እንደእርሳቸው በአዲስ ቤት ውስጥ እንዲኖሩም ይመኛሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2011
በአስናቀ ፀጋዬ