አዲስ ዓመትን በአዲስ ልብ ካልተቀበልነው አሮጌ ነው። አዲስ ዓመት አዲስ የሚሆነው እኛ በአስተሳሰብ ስንልቅና አዲስ ስንሆን ብቻ ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ታሪክ አለው፤ ታሪክ ደግሞ በጊዜና በዘመን ውስጥ ያልፋል። የእያንዳንዳችን ታሪክ ከውልደት የሚጀምር በሞት የሚጠናቀቅ የዘመን ሀቅ ነው። ይህ ተፈጥሮአዊ እውነት ደግሞ የሰውን ልጅ ማረፊያ አድርጎ በተቀመጠለት የሥርዓት አውድ ውስጥ እየመጣ የሚሄድ ነው።
ሂያጂውን እየሸኘ… መጪውን እየተቀበለ በማይዛነፍ ፍጹም እውነት ውስጥ የሰውን ልጅ ጉዳይ አድርጎ ይጓዛል። ጊዜ ጌታ ነው፤ ጊዜ ፈራጅ ነው። ጊዜ መጽናናት መሻርም ሁሉንም ነገር ነው። በተፈጥሮ እውነት የጸና..በሚዛናዊነት ምህዋር ውስጥ ሳይንገዳገድ የቆመም ነው።
የጊዜ ጌትነት ግን በራሱ የሚሆን ሳይሆን በሰው ልጅ የማሰብ አቅም የሚወሰን የአእምሮ ነጸብራቅ ነው። የእያንዳንዳችን ትናንት የእያንዳንዳችን ዛሬና ነገ፣ የእያንዳንዳችን ድሮና ዘንድሮ፣ አምናና ካቻምና በዚህ በጊዜና በሰው ልጅ የጋርዮሽ መስተጋብር የተቃኘ ነው። የሰው ልጅ በጊዜ ውስጥ ባለታሪክ ነው። ጊዜ በሰው ልጅ ውስጥ ጉልበታም ነው። የጊዜና የሰው ልጅ ቁርኝት ታሪክን እየደገመ፣ ተፈጥሮን እያጣቀሰ የሚያዘግም ነው። ጊዜ የታሪክ መፈጠሪያ፣ የህልምና ምኞት ካዝና ነው። የምንፈልጋቸው ነገሮች በጊዜ ውስጥ አልፈው የእኛ የሚሆኑ ናቸው።
ካለጊዜ ሰው፣ ካለሰው ጊዜ ምንም ናቸው። ጊዜና የሰው ልጅ እጅና ጓንት፣ መዳፍና አይበሉባ፣ መረብና ዓሣ ናቸው። ሁለት አካል አንድ ገጸ ሰብ፣ ሁለት ገላ አንድ ዓይነት መልክ። በተፈጥሮ እውቀትና ጥበብ ተሰናስለው የተደሩ የዳበሩም እንዲህ ዓይነት። ለዚህም እኮ ነው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ነፍስና ስጋ ፍለጋ የምንዋትተው። ለዚህ እኮ ነው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ከዓምናው የተለየን ለመሆን በአዲስ እቅድና በአዲስ ምኞት የምንሳበው። ለዚህ እኮ ነው ዕድሜአችን የሚያሳስበን፣ ሞታችን የሚያስጨንቀን።
አዲስ ዓመት እንደ ትርጉሙ አዲስ ነው። በውስጡ አንዳች ኃይልና ብርታት አለው። ለሰው ልጅ ሁሉ የሚሆን የመታደስ፣ የመበርታት መንፈስን በውስጡ ይዟል። ብዙዎቻችን ይሄን ኃይል እንፈልገዋለን። በዚህ ኃይል ውስጥ መኖር እንፈልጋለን። ለዚህም ዓመት ጠብቀን የምናቅድ፣ ዓመት ጠብቀን የምንጀምር፣ ዓመት ሲመጣ የምንበረታ በአጠቃላይ ለምንም ነገር አዲስ ዓመት የምንል ብዙዎች ነን። ይገርመኛል የአዲስነት ስሜት የሚያሳድርብን አዲስ ዓመት ሲመጣና ሲቃረብ ነው።
የመሥራት የመለወጥ ፍላጎታችን የሚነሳሳው መስከረም ሊጠባ ጥቂት ሲቀረው ነው። ህልሞቻችን የሚታወሱን የአበቦቹን ሽታ ተከትለን ነው። ከአሮጌነት የምንወጣው፣ ከድሮነት የምንሸሸው ጳጉሜን ተሻግረን አበባየ ሆይ ሲባል የሚመስለን እልፍ ነን። ሕይወታችን፣ መኖራችን ትርጉም የሚያገኝ የሚመስለን በዚህ ጊዜ ነው። ለአዲስ ሕይወት የምንዘጋጀው ይሄን አዲስ ዘመን ታከን ነው። ሁሉ ነገራችንን ለአዲስ ዓመት አሳልፈን የሰጠን ነን።
ይሄ ስህተት ነው የሰው ልጅ የጊዜ ባሪያ መሆን የለበትም። ዛሬን ለለውጥና ለስኬት መጠቀም ይኖርበታል። የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር ከዛሬ በመጀመር፣ ከአሁን በማቀድ ማሳካት እንችላለን። ብዙዎቻችን ዛሬን አናውቀውም። የአሁንን ኃይል አልተረዳነውም። የቆምንባት ቅጽበት የኃይል የለውጥ መጀመሪያ እንደሆነች ገና አልደረስንበትም። አዲስ ዓመት የምንም ነገር መጀመሪያ እንደሆነ አምነን የተቀበልን ነን። በአዲስ ዓመት ሰሞን ከሞት የምንነቃ፣ ካንቀላፋንበት የምንባንን ብዙ ነን።
በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ለውጥ የለም። በዚህ እምነት ውስጥ ስኬት የለም። ስኬት መነሻውም መድረሻውም አዲስ ዓመት ሳይሆን አዲስ አስተሳሰብ ነው። አዲስ አስተሳሰብ ደግሞ ዛሬን ከመጠቀም አሁንን ከመኖር የሚጀምር ነው። አዲስ ዓመት ሲያልፍ ምኞታችን አብሮ የሚያልፍ ከሆነ፣ አዲስ ዓመት ሲመጣ ምኞታችን ከሞተበት የሚነቃ ከሆነ የአዲስ ዓመትን ትርጉም አልተረዳንውም ማለት ነው። እስኪ ይሄን ለመረዳት የሚያስችለን አንድ ጥያቄ አንስተን እንመልከት።
አዲስ ዓመት ማለት ምን ማለት ነው? በአስተሳሰቡ ላልተቀየረ ማኅበረሰብ አዲስ ዓመት ምኑ ነው? ከመጠበቅና ተስፋ ከማድረግ ላልወጣ ሰውነት አዲስ ዓመት ዋጋው ስንት ነው? ፍቅርን ለማያውቅ ይቅርታን ላልተማረ ልብ ጊዜና ዘመን ምኑ ነው? ለማይሠሩ እጆች፣ ለማያስቡ ጭንቅላቶች አዲስ ዓመትን መጠበቅ ፋይዳው ምንድነው? በብሔር፣ በጎሳ ለሚባላ አገርና ሕዝብ የዘመን መቀየር ፋይዳው ምንድነው? ከወንድሞቹ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ ለሚኖር፣ ተነጋግሮ መግባባት፣ ተወያይቶ መስማማት ላቃተው ፖለቲካና ፖለቲከኛ፣ ትውልድና ዜጋ ዘመንን መሻገር ምንድነው? አምናን እኮ በእልልታና በፌሽታ ተቀብለነው ነበር። ካቻምናን እኮ የደስታና የሰላም ዘመን ብለነው ነበር። ያለፈውን ዓመት ብዙ ልንሠራበት ብዙ ልናተርፍበት አውርተን ነበር።
2014 እኮ ብዙ ያቀድንበት ብዙ ያሰብንበት ዘመን ነበር፤ ዛሬ ላይ አሮጌ ሆኖ ሲያልፍ ግን መጥፎና ዕድለ ቢስ እንደነበር አወራን፡ ምንም ያላተረፍኩበት ዓመት ነው ስንል ነቀፍነው። አያችሁ የዘመንን እውነት? ዘመን የሚዘወረው በሰው ልጅ አስተሳሰብ ነው። ያለፉት ዓመታቶች ጥሩ ያልነበሩት ዘመኑ ጥሩ ስላልነበር ሳይሆን እኛ ጥሩ ስላልነበርን ነው። እኛ ስላልተቀየርን ዘመኑም አልተቀየረም። የሰው ልጅ ልቡና አእምሮው፣ ሃሳቡና ምኞቱ ካልተቀየረ አዲስ ዓመት ምንም ነው።
ሃሳባችንን ሳናድስ፣ ከድሮነት ሳንወጣ ሰኔና ሐምሌ ገመገም ላይ ቆመን 2014 ለእኔ ጥሩ ጊዜ አልነበረም፣ ለአገራችን መልካም አልነበረም ብንል ልክ አይደለንም። ዘመን በእኛ ስር ነው። አዲስ ዓመት አዲስ የሚሆነው በእኛ አዲስ ልብ ነው። ልቦቻችንን አሳድፈን፣ መንፈሳችንን አስነውረን፣ ፍቅርና ይቅርታን ሳንማር፣ በመነጋገር ሳንግባባ፣ በእርቅ አንድ ሳንሆን ብንቀበለው ያው ነው እንደ ድሮው፤ እኛም ከእርግማን አንወጣም።
ተስፋ ያደረግነው አዲሱ ዓመት ያሰብነውን እንደሚሰጠን ዋስትናችን ምንድነው? የሚመጣው አዲስ ዓመት የምንመኘውን ብልጽግና፣ የምንፈልገውን አንድነት፣ የራቀንን ሰላም እንደሚሰጠን መተማመኛችን ምንድነው? ምንም መተማመኛ የለንም። ልንተማመንበት የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ራሳችን ነን። ራሳችንን ለፍቅር፣ ለይቅርታ፣ ለመነጋገር ዝግጁ ካደረግን እንዳሰብነው አዲስ ዓመት አዲስ ይሆናል።
ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ አዲስ ዓመትን አዲስ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው የሚሆነው። ታሪኮቻችን ውብ የሚሆኑት በእኛ ነው። እኛ ለምንፈልገው ሰላም፣ ለምንፈልገው አንድነት፣ ለምንፈልገው እድገት ዘመን አስተዋጽኦ የለውም። ዘመን ያው እንደትናንቱ ነው። የተፈጥሮን እውነት ጠብቆ መጥቶ የሚሄድ ነው። አትምጣ ብንለውም፣ ና ብንለውም በእኛ ፍቃድ ስር አይደለም። መጥቶ መሄድ ተፈጥሮአዊ ግብሩ ነው።
አዲስ ዓመት ሲመጣም ሆነ ሲሄድ የተለየ ተፈጥሮ የለውም። አዲስም ሆነ አሮጌ የሚሆነው በሰዎች ተጽዕኖ ነው። ቀን ሳንጠብቅ፣ ጊዜ ሳናሰላ፣ አዲስ ዓመት ሳንል የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር አሁን ላይ መፍጠር እንችላለን። ሰላም ከሆነ የምንሻው፣ አንድነት ከሆነ ፍላጎቶቻችን ሰላምና አንድነት በሚያመጡ ሃሳቦች ላይ በማተኮር የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን። ከጊዜ ባርነት መውጣት ይኖርብናል።
ለምንም ነገር ነገን መጠበቃችን፣ ለምንም ነገር አዲስ ዓመትን መሻታችን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። ሰላም ሊሰጡን የሚችሉ፣ ህልምና ራዕዮቻችንን ልናሳካባቸው የሚችሉ ብዙ ቀናት፣ ብዙ ጊዜዎች አብረውን አሉ። ችግሩ ከአዲስ ዓመት አስተሳሰብ አልወጣንም። ችግሩ ከዛሬ ይልቅ ነገን ተስፋ የምናደርግ መሆናችን ነው። ከቻልን ጊዜ የእኛ ባሪያ እንዲሆን እንቆጣጠረው። ከቻልን እያንዳንዱን ቀናችንን የምንም ነገር አዲስ ዓመታችን አድርገን እንቀበለው።
በጊዜ ባርነት ውስጥ ልዕልና የለም። በመጠበቅ ውስጥ ንግስናና ክብር ምንም ናቸው። ሰው ከትጋት ሲጎድል፣ ከጥረት ሲላላ ለምንም ነገር ጊዜን መጠበቅ ይጀምራል። ጊዜን የመጠበቃችን ምክንያት ስንፍናና አጉል የኑሮ ዘይቤ መልመዳችን ነው። በእውቀትና በእቅድ መኖር ብንጀምር እያንዳንዷ ቀን አዲስ ዓመታችን ትሆን ነበር ወይም ደግሞ ከአዲስ ዓመት በበለጠ ምን ያክል ለለውጥና ለስኬት አስፈላጊ እንደሆነች እንረዳ ነበር። በትጋት ስንሞላ ለምንም ነገር ጊዜ እኛን መጠበቅ ይጀምራል።
በትጋት ስንሞላ ምንም ነገር ከአሁን እንጀምራለን። ጊዜን መጠበቅና በጊዜ መጠበቅ ሁለት የተለያዩ እውነቶች ናቸው። ልክ ለምንም ነገር አዲስ ዓመትን እንደሚጠብቁት እና ለምንም ነገር ዛሬ የተሻለ ቀን ነው ብለው እንደሚያምኑት ሁለት ጉራማይሌ ነፍሶች ዓይነት። ትጉ ነፍሶች የሚፈልጉትን ዘመን ዛሬ ላይ ይፈጥሩታል። ታካች ነፍሶች ደግሞ በመንቀፍ፣ በመሰልቸት፣ በስንፍና፣ በአይሆንልኝም፣ በማመንታት፣ በመወላወል፣ ቆይ ነገ በሚል እሳቤ በመጠበቅ ውስጥ ይቆማሉ።
ብዙ ዛሬዎችን፣ ብዙ አሁኖችን፣ ብዙ ነገዎችን ዘለን አዲስ ዓመትን መጠበቃችን ስንፍናና ስልቹነት ምን ያክል ስር እንደሰደደብን አመላካች ነው። ብልህ ሰው ዛሬን አዲስ ዓመት ማድረግ ይችላል። ጠንካራ ሰው ወደ ነገ ሳይሄድ፣ ወደ ዓምና ሳይሳብ አሁንን ለለውጥና ለስኬት መጠቀም ይቻለዋል። ለተጋ ልብ፣ ለበረታ አእምሮ ሁሌም ስኬት፣ ሁሌም አዲስ ዓመት አለ። ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት አዲስ ዓመት ለእኛ ብሎ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም። መጥቶ እንዲሄድ የተፈጥሮ ግዳጁን እየተወጣ ነው።
እኛ ነን ከተፈጥሮ የራቅነው። እኛ ነን ማስተዋል የጎደለን፤ በጊዜ ሀቅ ውስጥ ቆመን እንኳን መማር አልቻልንም። ለመማር ዝግጁ ብንሆን ጊዜ የሚያስተምረን ብዙ ነበረው። ዓምናን በጉጉት ጠብቀነው የምንፈልገውን ሰላምና አንድነት ካልሰጠን፣ 2014 ለነበሩብን ችግሮች መፍትሄ አድርገነው ቃሉን ከበላ ችግሩ ከጊዜው ሳይሆን ከእኛ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። አዲሱን 2015 በዓምና ልብ ሳይሆን በታደሰና በተቀየረ ልብ ልንቀበለው ይገባል። ያኔ ያለጥርጥር የምንፈልገውን እናገኛለን፤ እንደምኞታችንም ዘመኑ አዲስ መሆን ይጀምራል።
የሚሰማ ጆሮ የሚያስተውል ልብ ቢኖረን ኖሮ የጊዜን ሹክሹክታ እናደምጠው ነበር። ጊዜ ህላዊ ኖሮት መናገር ቢችል ኖሮ … እባካችሁ አትጠብቁኝ እኔ ለሰው ልጅ የሚሆን ምንም የለኝም፣ ለበረቱ እየመጣሁ የምሄድ፣ ለጠንካሮች ሚዛኔን የደፋሁ ነኝ የሚለን ይመስለኛል። በዚህ አያበቃም ‹ከኔ ይልቅ ዛሬና ነገ የላቀ ዋጋ አላቸው። አስራ ሁለት ወራትን አልፋችሁ፣ ሃምሳ ሁለት ሳምንታትን ትታችሁ፣ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናትን ሽራችሁ የምትጠብቁኝ ምናችሁ ሞኝ ነው? ሲል የሚያላግጥብን ይመስለኛል።
መች በዚህ ያበቃና ‹ልቦቻችሁን ሳታድሱ፣ አመለካከታችሁን ሳትቀይሩ ጥሩ ነው መጥፎ ነው እያላችሁ አትሙኝ። እኔ ጥሩና መጥፎ የመሆን ሥልጣን የለኝም። መጥቼ እንድሄድ የታዘዝኩ የተፈጥሮ መንገደኛ ነኝ እናም አትጠብቁኝ በአሁናችሁ ላይ በርትታችሁና ተልቃችሁ ቁሙ› ይለን ነበር። ምኞታችን መልካም ጊዜ ከሆነ እጆቻችንን በሥራ፣ ልቦቻችንን በትጋት እንጥመድ። ምኞታችን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት ከሆነ ደግሞ ለነዚህ የሚሆን ሰውነትን መፍጠር ይኖርብናል።
ካልሠራንበት፣ ካልበረታንበት አዲሱ ዓመትም እንደ አምናና ካቻምና ርባና ቢስ ሆኖ ነው የሚያልፈው። አዲስ ዓመት የዛሬ አብራክ ነው። ብዙ ዛሬዎች ተቆጥረው ነው የምንቦርቅበትን አዲስ ዓመት የሰጡን። ለምንድነው ዛሬአችንን አዲስ ዓመት አድርገን የማንቀበለው? ለምንድነው አዲስ ዓመት ሲመጣ የምናገኘውን ኃይልና ብርታት በቆምንባት ዛሬ ላይ የማንፈጥረው? አትሸወድ፣ አዲስ ዓመት የቀናት ጥርቅም ነው። አትሳቱ አዲስ ዓመት የሳምንታት የወራት ሂደት ነው።
ለመለወጥ ካልተጋን የሚሰጠን አንዳች ነገር የለውም። እኛ እስካልተለወጥን ድረስ የአዲስ ዓመት መምጣት ምንም ነው፤ ቤስቲ ቤስታ የለውም። ጊዜ በተለይም አዲስ ዘመን በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ ዋጋ የሚኖረው የአሁንን ወይም ደግሞ የዛሬን ዋጋ ስናውቅ ብቻ ነው። ዓምና አዲስ ያልነው ዘንድሮ አሮጌ ብለን ሸኝተነዋል። ምንም አላተረፍንበትም። ስለዚህ ከዘመን ቁራኛነት ወጥተን ዛሬን አዲስ ዓመት እናድርግ። በተለወጠ ልብና በተለወጠ ሃሳብ የተለወጠ አገርና ሕዝብ እንፍጠር።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2014