መንግሥት እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ከክልሎች የተሰጠ መግለጫ፤
በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በማተኮር በተለይም አሸባሪው ሕወሓት በመንግሥት በኩል የተዘረጋውን የሰላም እጅ በመግፋት ሰሞኑን በአማራ እና አፋር ክልሎች በኩል ጦርነት መክፈቱን አስመልክቶ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ያላቸውን አቋም ገልጸዋል፡፡ ተግባሩንም አውግዘው በአገር ውስጥ ጦርነቱን ቀልብሶ ሰላምን እውን በማድረግ ሂደት ሕዝቦች ሊኖራቸው የሚገባውን ዝግጁነት እንዲሁም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘብና ሊያደርግ የሚገባውን ጉዳይ በመልዕክትነት በማካተት ያወጡት መግለጫ እንደሚከተው ቀርቧል፡፡
- የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤
ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን በተመለከተ ከሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ፤
ከኢትዮጵያ አልፎ በአጠቃላይ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆነው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ በአማራ ክልልና በአፋር ክልሎች ላይ የከፈተውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በፅኑ ያወግዛል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለ27 ዓመታት የአገሪቱን ማእከላዊ ስልጣን ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ ከፈጸማቸው ኢሰብአዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪ በአገሪቱ ሕዝቦች መካከል እርስ በርስ መተማመን እና መተባበር እንዳይኖር የሚያደርግ ጥላቻ በመንዛት የከፋ ስቃይና መከራ ያደረሰ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ቡድኑ የአገሪቱ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ በነበረበት ዘመን የሶማሌ ክልል ሕዝብን ገድሏል፤ አፈናቅሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ተቆጥረው የማያልቁና ለማመን የሚከብዱ ዘግናኝ የጭካኔ ተግባራትን ሁሉ አንድም ሳያስቀር ፈፅሟል፡፡
ከዚህም አልፎ ለርካሽ ፖለቲካና ለስልጣኑ ቀጣይነት ሲል ሴራ በመጎንጎን የሶማሌ ሕዝብ ለዘመናት አብረው ከኖሩት ኢትዮጵያዊ ወንድም እህቶቹ ጋር እንዲጋደልና ደም እንዲቃባ አድርጓል የክልሉን ሀብት በመዝረፍ እና የጥቂት ሰዎች ኪስ ማደለቢያ በማድረግም ክልሉ በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጓል፡፡
ይሔ አሸባሪ ኃይል ባለፈው ግፍና በደሉ ከመፀፀት ይልቅ አሁንም የሶማሌ ክልልን በማተራመስ ሕዝቡ ያገኘውን ሰላምና ነፃነት ለመንጠቅ በአንድ በኩል በክልሉ አዋሳኝ ከሚገኙ ወንድም ሕዝቦች ጋር ሰላም እንዳይኖረው ግጭት በመጥመቅ፣ በሌላ በኩል ከአልሸባብ ጋር ያልተቀደሰ የጥፋት አጋርነት በመፍጠር ክልሉን የማተራመስ እና አገር የማፍረስ ቅዠቱን ለማሳካት እየተራወጠ ይገኛል።
አሸባሪው ሕወሓት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እየተጋለበ በከፈተው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚኖሩ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን ሕይወት አጥፍቷል፤ በእድሜ ልክ ድካም የተከማቸ የሚሊዮኖችን ሀብትና ንብረትም በከንቱ አውድሟል።
የዚህ ባንዳ ቡድን ዋነኛ ሀሳብ ኢትዮጵያን እኔ ወይም የኔ ተላላኪ የሆነ ኃይል ካልመራት አፈርሳታለሁ የሚል ሲሆን ይህን በጤነኛ አእምሮ ሊታሰብ የማይችል ከክፋት ሁሉ የከፋ ሀሳቡን ለማስፈፀምም ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት ምስኪን የደሀ ልጆችን በአደንዛዥ እፅ እያደነዘዘ ወደ እሳት እየማገደ ይገኛል።
ቡድኑ የያዘው እኩይ አላማ ለአገራችን ሁለንተናዊ ሰላም እና ልማት ፀር መሆኑን የሚገነዘበው የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት እና ሕዝብ በምሥራቅ በኩል የሕወሓት አጋሮች በሆኑት እንደ አልሸባብ ባሉ የሽብር ቡድኖች የሚሞከሩ ሙከራዎችን በማክሸፍ እና በመደምሰስ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከማስከበር ባሻገር በሕወሓት ላይ በሚወሰደው እርምጃ እንደሁልጊዜው ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በአፅንኦት እየገለፀ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ያረጋግጣል፡፡
በመጨረሻም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት አቁሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል ተገቢውን ጫና እንዲያሳድር የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም
ጅግጅጋ
- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፤
በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ!
አሸባሪው ሕወሓት የሀገራችን ሕዝቦችን እርስ በርስ በማናከስ አንድነታችንን ለመናድ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም፡፡
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የተሰጠውን ተልዕኮዎችን እየተቀበለ ሀገራችን በብሔር፣ በሃይማኖትና በጎሳ ሲከፋፍል ኖሯል ፡፡
ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበትን አብሮና ተቻችሎ የመኖር ውድ እሴቶቻችን ለመሸርሸር ያልሸረበው ሴራ አልነበረም። ኢፍትሃዊነትን፣ የኢኮኖሚ አሻጥሮችንና በታሪክ ፊት ዘግናኝ የሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ጭምር በዜጎቻችን ላይ ፈጽሟል።
የሀገራዊ አንድነትን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እንደሚጓዝ ግልፅ በማድረግ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ቁጥር አንድ ጠላት መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የንፁሃን ዜጎቻችንን ደም አፍሷል፤ ንብረት አውድሟል፤ የትግራይ ወጣቶችን በእሳት ማግዷል፤ ብዙዎችን አፈናቅሏል። ወትሮም ቢሆን የሠላም አማራጭ የሚያንገሸግሸውና ያለጦርነት ውጪ ውሎ ማደር የማይችለው ይህ ቡድን በሀገራችን መንግሥት በኩል የቀረበውን የሠላም አማራጭ አሻፈረኝ ብሎ ሦስተኛ ዙር ወረራ በአማራና በአፋር ክልሎች በይፋ ጦርነት ከፍቷል።
በዚህም ለሠላም መፍትሄ ዓይኑ የታወረ፣ ጆሮ የተደፈነ መሆኑን አስመስክሯል። ሕወሓት ሕፃናትን ከፊት ለፊት በማሰለፍ የጥይት ቀለብ በማድረግ ሰብዓዊነት ፈጽሞ የማይሰማው በጭካኔ የተሞላ ቡድን መሆኑን በገሃድ አስመስክሯል።
ከግጭትና ጦርነት ውጪ መኖር የማይችለው አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘረጋለትን የሰላም እጅ አሻፈረኝ በማለት በአማራና አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት በፅኑ ያወግዛል፡፡
የክልላችን መንግሥትም የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሌሎች ኢትዮጵያ ወዳድ ወንድሞችና እህቶች ጎን በመሆን አስፈላጊውን ሁሉን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያ መንግሥት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም ግፊት ሊያደርግ ይገባል፡፡
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 22, 2014
ቦንጋ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2014