ከአገር የወጡት ገና በለጋ እድሜያቸው ለትምህርት ነው። መዳረሻቸውን ያደረጉትም ኩባ ሳንዲያጎ ከተማ ነው::ወደኩባ የመሄድ አጋጣሚውን ያገኙት ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በሆኑት በመንግስቱ ኃይለማሪያም የአገዛዝ ዘመን ነው::ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በኩባ ቢማሩና እዛው ቢቆዩም አገራቸው ኢትዮጵያ ለአፍታም ቢሆን ከልባቸው ወጥታ አታውቅም፡፡
እኚህ ሰው፣ ተወልደው ያደጉት ሐረር ነው::በወቅቱ አፋቸውን የፈቱበት ቋንቋ አደሬኛ ሲሆን፣ ሐረር መድረሳ የሚባል የሙስሊም ትምህርት ቤት ገብተው ቁራን መቅራት ጀምረውም ነበር::የደርግ ዘመን መኮንን የነበሩ አባታቸው የሶስተኛው ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆናቸው ከሐረር ወደጭናክሰንና ጅግጅጋ በሚመላለሱበት ወቅት ይዘዋቸው ስለሚሄዱ እንደገና ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው የመማር እድል አግኝተዋል::በሀረር ከተማም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጀመረዋል::
የዛሬው ‹‹የዘመን እንግዳችን›› ዶክተር እመቤት ገዛኸኝ ይባላሉ። የዶክተር እመቤት የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ባለቤትና የሚናሮል ባለድርሻ እንዲሁም መስራች ናቸው::ብቸኝነትን አጥብቀው ይጠላሉ። ከዚህም የተነሳ በርከት ያሉ ሰዎች በዙሪያቸው አይታጡም::በተለይ በቤተሰባቸውና በዙሪያቸው ላሉ የቅርብ ወዳጃቸው ሁሉ ብልሃተኛ፣ አማካሪ እንዲሁም ገበና ሸፋኝም ናቸው::በልጅነት እድሜያቸው አግብተው አራት ልጆች ወልደዋል። በአራስነት ጊዜያቸውን ከስራ ገበታ መራቅ አይሆንላቸውም::የእረፍት ጊዜያቸውን አሳጥረው ወደ ስራቸው ይመለሳሉ። በዚህም አብረዋቸው ለሚሰሩት አርአያ መሆንን ይሻሉ::ዛሬም የስራ ሀላፊነታቸውን የሚወጡት እንደልጅነታቸው ነው::ይህ ንቃት የመልካምነት ስጦታ ነው ብለውም ያስባሉ::
እንግዳችን የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ ሁለቱ ልጆቻቸው ዶክተሮች ናቸው::አንደኛዋ ደግሞ በሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ ያላት ስትሆን፣ አንደኛዋ ደግሞ አርክቴክት ናት:: አዲስ አበባን በቅጡ ያወቋት ከውጭ አገር ተመልሰው ከመጡ በኋላ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለ30 ዓመት ኖረዋል፡፡
ዶክተር እመቤት፣ በተለይ በ1983 እና 1984 ዓ.ም አካባቢ ጃንሜዳ በሚኖሩበት ሰዓት በኤች. አይ.ቪ ምክንያት ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ከ12 በላይ ልጆችን ሰብስበው ከልጆቻቸው ጋር አብረው አሳድገዋል::ያሳደጓቸው ልጆችም በአሁኑ ሰዓት ጥሩ ቦታ ደርሰውላቸዋል::በዚህም ደስተኛ ናቸው::ምንም እንኳን ሁሉንም ልጆቻቸውን ያስተማሩዋቸው ውጭ አገር ቢሆንም ሁሉም ተመልሰው አገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ::የዛሬ እንግዳችን እንዲሆኑ የመፈለጋችን ምክንያትም በበጎ ፈቃደኛ ስራ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆናቸው ሲሆን፣ በተለይ ወጣቶችን ትኩረት አድርገው በሚሰሩት ስራ ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑልን በመፈለግ ነው። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ጭውውት እነሆ ለንባብ ብለናል::
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር እመቤት ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት ደሜ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፤ ምን ለማለት ነው ከሚለው ጭውውታችን እንጀምር?
ዶክተር እመቤት፡- ኢትዮጵያዊነት ደግነት ነው:: ኢትዮጵያዊነት መራራት ነው::ብዙዎች የቅርቡን ክስተት በማየት ኢትዮጵያዊነት ደግነት ሊሆን እንዴት ይቻላል ሊሉ ይችላሉ:: ኢትዮጵያዊነት ግን ደግነት ነው፤ ያለውን መቋደስ ነው:: አንድ የቤተሰብ ኃላፊ የሆነ ሰው በአማካይ 13 ሰዎችን ሊቀልብ ይችላል:: ይህ ቁጥር የልጆቹ ብቻ ላይሆን ይችላል::የእህትና የወንድም ልጅ አሊያም የአክስትና የአጎት ሌላም ሊሆኑ ይችላሉ:: እነዚህን ሁሉ አንድ ሰው ቢኖረውም ባይኖረውም፣ ተበድሮም ይሁን ተለክቶ ያስተዳድራል::ይህ አይነቱ አኗኗር የት አገር ይገኛል ቢባል ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው ብዬ በድፍረት ልናገር እችላለሁ::በሌላው አገር ስትኖሪ በመኖሪያ አፓርትመንት ውስጥ ያለው ጎረቤትሽ ምን እያደረገ ስለመሆኑ የምታውቂው ነገር የለም::አንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብስቦ ሲቀልብና አስጠግቶ ሲያኖር ኖሮት አይደለም፤ የኢትዮጵያዊነት ደም በውስጡ ስላለና እሱ ነገሩ ስለሚያስገድደው ነው::እኔም ይህ አብሮነትና መረዳዳት በደሜ ውስጥ አለ ብዬ አምናለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ሕጻናትን እንዲሚረዱና እንደሚያሳድጉ ሰምቻለሁ፤ ህጻናቱንስ ከየት አምጥተው ነው የሚረዷቸው?
ዶክተር እመቤት፡- ሕጻናትን ከማሳደግ አኳያ ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ ነው:: ድጋፉንም በሁለት አይነት መንገድ ማድረግ ይቻላል:: አንደኛው ለሕጻናቱ ባለቡት ቦታ ድጋፍ ማድረግ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በጉዲፈቻ በመውሰድ ማሳደግ ነው:: ሁለቱም መልካም የሆኑ ስራዎች ናቸው::
ነገር ግን በጉዲፈቻ መልኩ ከሚወሰዱ ሕጻናት መካከል ጤነኛውም እንዳለ ሁሉ ጤናው የተጓደለ ሕጻን አለና እነርሱንም ልክ እንደጤነኞቹ ሁሉ የሚወስዳቸው ሰው እምብዛም አይታይም::ከዚህ አኳያ እኔም ሆንኩ ሌሎቹ ከሜሪጆይ ሕጻናትን ለማሳደግና ለመደገፍም በምንፈልግበት ጊዜ ጤነኛውንም ጤናው የተጓደለውንም ብንወስድ መልካም ነው:: እኔ ያደረኩት ነገር ቢኖር ከማሳድጋቸው 21 ሕጻናት በተጨማሪ የጤና እክል ያለባቸውን አምስት ሕጻናትን መውሰድ ነው::ይህ የራሱ የሆነ መልዕክት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ::ጤነኛ እና ቆንጆ ልጅ ነው ያልነውን መርጠን መውሰዱ ብዙዎች ሊያደርጉት የሚፈልጉት ይሆናል::የጤና እክልም ያለበት ሕጻን የእግዚአብሔር ፍጡር እንደመሆኑ እርዳታችን ሁሉ ከፈጣሪያችን ጋር ሊያቀራርብ የሚችል መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ::
አዲስ ዘመን፡- የሚያሳድጓቸው አምስቱ ሕጻናት ምን አይነት የጤና እክል ያለባቸው ናቸው?
ዶክተር እመቤት፡- ሕጻናቱ በተለምዶ የሚጥል በሽታ፣ የአዕምሮ ዝግመት ያለባቸው የአዕምሮ ሕሙማን ናቸው:: በእርግጥ እነዚህ ወላጅ ያላቸው ቢሆኑም ወላጅ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ በሜሪጆይ እንዲረዱ የተሰጡ ሕጻናት ናቸው:: እነዚህን አምስቱን ከ21 ጋር የቀላቀልኳቸው ለትውልድ ትምህርት ይሆናል በሚል ጭምር ነው::የምንረዳው የጤና እክል ያለበትንም ጭምር እንጂ ጤነኛ የሆነውን ብቻ መርጠን መሆን የለበትም::እነዚያንም ማስታወሱ መልካምነትን ያገዝፋልና ይህ ለሌሎች ትልቅ ትምህርት መሆን የሚችል ነው::
ሰዎችን የምትረጂው፣ የምትወስጂውና የምትደግፊው በማንነታቸው ላይ ተመስርተሸ መሆን የለበትም:: መረዳት ያለባቸው ሰው በመሆናቸው ነው:: በሚጥል በሽታ የሚታመምን ሕጻን ወስዶ ማሳደጉ ዋጋ ያስከፍላል::በዚህ አይነት ሁኔታ ግን ብዙዎች መቸገርን አይመርጡም:: ጤነኛውን ልጅ ወስዶ ማሳደጉ ለታይታ ‹እየረዳሁ ነው› የሚል ስሜት እንዲኖረን ያደርገን ይሆናል::ያንንስ የጤና እክል ያለበትን ማን ያሳድገው? ራስን ከሕሊና ተጠያቂነት ለማሸሽ መሞከሩ መልካም አይሆንም:: እኔ ከሜሪጆይ የጤና እክል ያለባቸውን ሕጻናት ጠይቄ ስወስድ የመጀመሪያዋ ልሆን እችላለሁ::ስለሆነም በተለይ ባለሀብቶች ገንዘብ ኖሮን ለቅንጦት ከምናውለው ይልቅ በእንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ላሉ ድጋፍ ማድረጉ ደስተኞች እንድንሆን ያደርጋል::
አዲስ ዘመን፡- እንደማንኛውም በጎ ፈቃደኛ ሰው የመርዳቱ ፍላጎት ኖሮት የጤና እክል ያለባቸውን መርጠው ለመውሰድ ሲነሳሱ የገጠመዎት ፈተና ይኖር ይሆን?
ዶክተር እመቤት፡– ‹በጎ› የሚለው ቃል በራሱ የቅዱስ መጽሐፍም የቁራንም አካል ነው::ያንን በጎነት ለማድረግ ስትሄጂ ከውስጥ በመነሳሳትና በእምነት ነው ማድረግ ያለብሽ::ስታገዥም ለይስሙላ መሆን የለበትም::ለመደገፍ ስናስብ የጤና እክል ካለበት ይልቅ ጤነኛ ወደ ሆነው ነው መሄድ የምንፈልገው::ወይም ደግሞ በሌላ ቋንቋ እነዚህን እናገልላለን::የጤና እክል ያለባቸውን ሕጻናት መውሰድ ምቾት ይነሳናል፤ አሊያም ተጨማሪ ወጪን ይጠይቃል ስለሚባሉ ልጆቹ የማንም ምርጫ ሳይሆኑ ይታለፋሉ::
ለምሳሌ እኔ በጀት የማደርገው ዓመታዊ ወጪያቸው ላይ ነው::በተለይ የሕክምና ወጪያቸውን እሸፍናለሁ::ምክንያቱም ትልልቅ የጤና ችግር ያለባቸው ናቸው ::ከዚህ ባለፈ ደግሞ የእነርሱን ችግር ለማጣጣም ስል ነው::ምናልባትም የጤና እክል ያለበትን ልጅ የወለደች እናት ልጇን አሳልፋ ለመስጠት የተገደደችው የበኩሏንና የምትችለውን ሁሉ አድርጋ ሊሆን ይችላል::ደግሞም የሚሆነው ይኸው ነው::ይህ ደግሞ የሁሉም ሕመም ሊሆን ይገባልና የየበኩላችንን ማድረግ አለብን እላለሁ::
እኔ በበኩሌ ልጆቹን ከመርዳት ባለፈ አንድ የገባሁት ቃል አለ::ይኸውም እድሜዬ ገፍቶ ምናልባት በሕይወት ካልኖርኩ በሚል በዚህ ጉዳይ ልጆቼን በተለይም ትልቁ ልጄን የጤና እክሉ ያለባቸውን ልጆች ልክ እንደ እኔ ሆኖ የመደገፉን ጉዳይ እንዲያስቀጥል በሚል አስፈርሜዋለሁ:: ይህን ያደረኩት የግድ ልጄ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ትውልድ እንዲቀባበለውም ስላሰብኩ ጭምር ነው:: ልጆቹን ለልጄ አደራ ስል ቀጣይ ትውልድ ውስጥ የምታስቀምጪው አንድ አይነት የመተጋገዝና የመደጋገፍ ባህል እንዲኖርም በማሰብ ነው::
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ እናቶች የጤና እክል ያለበትን ልጃቸውን ከአቅም በላይ ሲሆንባቸው አሳልፈው ለድርጅት ይሰጣሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሲሸሽጓቸው ይስተዋላሉ፤ እርስዎ 26 ልጆችን ይረዳሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አምስቱ የጤና እክል ያለባቸው ናቸውና ለሌሎች ትምህርት ይሆን ዘንድ በዚህ ጉዳይ ምን ማስተላለፍ ይሻሉ?
ዶክተር እመቤት፡- የእኛ የኢትዮጵያውያን ደም እንዳልኩሽ መሰረቱ ደግነት ነው የሚል ጽኑ አቋም አለኝ::አሁን በአጭር ጊዜ የተረሳን የማንነት ጥያቄን ትተን ያለፈ ነገራችንን ስናይ እንደ አገር ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነቷ የሚዘነጋ አይደለም::
ኢትዮጵያዊነት ማለት የእምነት ቤት ማለት ነው::ኢትዮጵያ ማለት በየትኛውም ኃይማኖት ውስጥ ፈጣሪ የሚመሰገንባትና የማይረሳባት አገር እንደማለት ነው::በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም እምነቶች ተከባብረው ይኖሩባታል::የኢትዮጵያውያን ደም ደግና በጎ አድራጊ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት የሚለካው አሁን ጊዜ ባመጣው ከስተት አይደለም::የጥንት አባቶቻችን ወግ አብሮነትንና መተሳሰብን ነው የሚያስተምረን::እኔ በግሌ የእዛ የኢትዮጵያ ደም አካል ነኝ ብዬ አምናለሁ::
እኔን ብትወስጂኝ እናቴ ሙስሊም ናት፤ አባቴ ደግሞ ክርስቲያን ነው::የዚህ ድምር ውጤት ነኝ::በመሆኑም ኢትዮጵያ የመልካምነትን ሕይወት የዘራችልኝ አገር ናት::ኢትዮጵያ ማንነቴን ያደመቀችልኝ አገር ስለሆነች የምኖርባት ደስ ብሎኝ ነው::በጎነት ደግሞ የኢትዮጵያውያን መገለጫ በመሆኑ ለማንም አሳልፈን የማንሰጠው መልካሙ እሴታችን ነው::ይህንንም አጠንክረን ልንይዘው ይገባል::እርግጥ ነው በአሁኑ ወቅት ብዙ ፈተና እና ተግዳሮት የተፈራረቀብን ጊዜ ነው::ብዙም የጎደለብን ነገር አለ::በጉድለታችን ምክንያት የምናጠፋው ጥፋት ኢትዮጵያዊነታችንን አያበላሸውም::እናም እርስ በእርስ እንደጋገፍ ባይ ነኝ::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያን አንዱ ሌላውን እየረዳና እየደገፈ ነው የመጣው፤ ይህ ግን አሁን ላይ ውልክፍክፍ ያለ አይመስልዎትም? እንዴትስ ልናቃናው እንችላለን?
ዶክተር እመቤት፡- አዎ! ኢትዮጵያዊነት በብዙ መልኩ ተዛንፏል::ይሁንና አይታወቃችሁ እንደሆነ እንጂ አሁን አሁን ለውጦች አሉ::ቀላል ምሳሌ ብጠቅስልሽ ‹‹ድንቅ ልጆች›› በሚለው መርሃግብር ላይ አዘጋጁ እሸቱ በሚያቀርባቸው ልጆች እጅግ በጣም ነው የምደነቀው::በተለይ ደግሞ አዕምሯቸው በምን ያህል መጠን እየተቀየረ ያሉ ልጆች እንዳሉ ሳይ በተስፋ እሞላለሁ::ትውልድም እየተቃና ነው ብዬ አስባለሁ::
ድሮ ግብረገብ እንማራለን::በየትኛውም ትምህርት ቤት ቅዱስ መጽሐፍንና ቁራንን የሚከለክል መንግስት የለም::ስለዚህ በትውልድ መካከል ቢያንስ ፈሪሃ እግዚአብሔር አለ::በዚህ እሸቱ በሚያዘጋጀው መርሃግብር ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ማንነታቸውን አሳምረው የሚያውቁ ሕጻናት እንደሆኑ ነው::እሸቱ በልጆች ላይ እየሰራ ያለው ስራ ድንቅ ስራ የሚያስብለው ነው::ትልቅ ውለታም እየዋለልን ነው::አሁን ባለው ሁኔታ ያሉ ልጆች አገራቸውን የሚያደንቁ ሆነው አግኝቼያቸኋለሁ::ልጆች ከጥቂት ዓመት በፊት ሲታዩ የነበረው ከአገራቸው ይልቅ የሌላ አገር አድናቂ ሆነው ነው::ስለዚህ አሁን ትውልድ እየተቃና ነው ብለን ብናስብ መልካም ነው እላለሁ::
በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ዓባይን የመሰለ ግድብ ተገድቧል::በዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ልጆቹ ትልቅ ትምህርት ይማራሉ::በፊትም በሌሎች አገሮች በአይነቁራኛ የምንታየው በጥንካሬያችን ነው::እኔ በግሌ በጣም እሰጋ የነበረው የዓባይ ግድብ ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም በሚለው ላይ ነበር::ያ ሁሉ ተግዳሮት ታልፎ እዚህ መድረስ ተችሏል::ይህ ደግሞ ትውልዱን ቆራጥነትን እና ብርታትን የሚያስተምር ነው::
እኛ አሁን የድሮዋን ጠንካራዋን ኢትዮጵያ ለመመለስ 10 ዓመት እንኳ አይፈጅብንም::ምክንያቱም እየተሰራ ያለው ነገርና እየተሰራበት ያለው ነገር ቀላል አይደለም::የተወላገደውን ማቃናት ደግሞ የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት::
በእኛ አገር ያሉ ወጣቶች አንገታቸውን ደፍተው ሲሄዱ ሳይ በብዙ ያመኛል፤ እንደሌላው አገር ወጣቶች አይደሉም::እጅግ መልካም ስነ ምግባር ያላቸው ናቸው::እንዲያውም ወጣቶች በተቸገሩበት ያህል ልክ አልጎዱንም ብዬ አስባለሁ::አሁን መመለስ የምንችለበት ሰዓት ላይ እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- ወጣቱ የተቃና ይሆን ዘንድ ሕጻናቱ ላይ መስራት ይጠበቃልና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር እመቤት፡- ዋናው ነገር ከቤት ይጀምራል::አንዳንዴ ወላጆች ልጆቻቸውን ‹ውጭ አገር ነው እንጂ ኢትዮጵያማ አትማርም› ሲሉ ይደመጣሉ::‹ቆይ ውጭ አገር እልክሃለሁ› ይሏቸዋል::ቢያንስ እንኳ እዚህ የሌለ ትምህርት ቢሆን ግድ የለም::እንደዚያ ሆኖ እንኳ ‹ልጄ ተምረህ መመለስ አለብህ› ብለው ቢልኳቸው እሰይ የሚያስብል ነበር::ልጆቻቸውን ወደ ውጭ አገር ሲልኳቸው ‹ተምረህ ትመለሳለህ›› ብለው ቢልኳቸው ተምረው ይመለሱ ነበር::
የእኔን ተሞክሮ ብነግርሽ ከኢትዮጵያ የወጣሁት በበቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርም ጊዜ ነበር::በወቅቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ‹‹ተምራችሁ ወደአገራችሁ ትመጣላችሁ›› ብለውን ነው ወደኩባ የላኩን::በውጭ አገር ቆይታችን መቼም ቀን ቢሆን ከአገራችን ውጭ ተመኝተን አናውቅም::ከእኔ ጋር የነበሩ ልጆች ተምረው ወደአገራቸው በመመለሳቸው በአሁኑ ወቅት በጳውሎስ፣ በምኒልክም ሆነ በሁሉም ስፍራ ያሉ በሙያቸው ‹አንቱ› የተባሉ ናቸው::
ምንም እንኳ በውጭ አገር ኩባ የተማርን ብንሆንም በትምህርት ቤታችን ውስጥ የተማርነው ስለኢትዮጵያ መዝሙር እንድንዘምር ተደርገን ነው::የመዝሙሮቹ ግጥሞች ዛሬም ድረስ የማይረሱኝ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር ከመዝሙሩ ግጥም በጥቂቱ ያስታውሱናል?
ዶክተር እመቤት፡- ያውም ከነዜማው ነዋ!
‹‹ጊዜ ቢለያየን ባልኖር አጠገብሽ፣
ቃል ኪዳን አለብኝ ፈጽሞ ላልረሳሽ…››
እያለ የሚቀጥል መዝሙር ነው::ውጭ አገር ሆነን የተማርነው የኩባን አገርና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለን ነው::መንጌ በወቅቱ ሲልከን ‹አማርኛ እንዳትረሱ›› ብሎናል::የሄድነው የተለያየ ባህሪ ያለን ልጆች ነን::የተወሰንን ደግሞ የሙት ልጆች ነን::በወቅቱ እንዘምር የነበረው መዝሙር በውስጣችን የታተመ በመሆኑ ከአገራችን ውጭ ምንም አያስመኘንም ነበር::እኛ በወቅቱ ትምህርት የጨረስን ሰሞን ወደአገራችሁ እንዳትገቡ የሚሉ ነበሩ፤ ነገር ግን ከአገርሽ ውጭ ወዴት ትሄጃለሽ? የተረዳሽው እውነት ቢኖር ተምሮ መመለስን ነው::በሰልፍ ላይ ሁሌም የሚዘመረው መዝሙር በራሱ አገርሽን እንድትናፍቂ የሚያደርግሽ ነው፡፡
እኔ በወቅቱ በጣም ልጅ ነበርኩ::ከአገር የወጣሁት ገና ከአምስተኛ ክፍል ወደ ስድስተኛ ክፍል ተዛውሬ ባለሁበት ጊዜ ነው::ከስድሰተኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርቴን የተማርኩት እዚያው ኩባ ነው::ኩባ ደግሞ የትምህርት አሰጣጡ በጣም ግሩም ነው::አንድ አስተማሪ በትክክል ባያስተምረን አምስት ዓመት ሙሉ ከስራው ሊታገድ ይችላል::ከኩባ በኋላ ለአጫጭር ኮርሶችና ለትምህርትም ጭምር ወደተለያዩ አገሮች የመሄድ እድሉ ነበረኝ::በዚህ ሁሉ አገሮች መካከል ግን መቼም መልሼ የማላገኛት አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን አስተውያለሁ::ኢትዮጵያ በእኔ አስተሳሰብ አቻ ያላገኘኋት አገር ናት::ከአገር ወጥተሸ ልትማሪ ትችያለሽ፤ ነገር ግን ጥለሻት መሄድ አይገባም::አሁን ባለው ትውልድ ላይ ካልተሰራ ችግር ነው::
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በአጼ ኃይለስላሴ የነበረው ትውልድ ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ሲላክ ተመልሶ መጥቶ አገሩን የሚያገለግል እንዲሆን ተመክሮና ተዘክሮ ነው፤ ከዚህ አንጻር የአሁኑ ትውልድ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶክተር እመቤት፡- አዎ! ይህን ነው የምለው:: ለአሁኑ ትውልድ ታላቅነታችንን ካላስተማርንና አደራ ካልሰጠን ትውልዱ አደራውን ለመወጣት አይችልም:: በወላጆችሽና በቅርብ ዘመዶችሽ እንድትሸሺ ከተመከርሽ ትሸሺያለሽ::በጃንሆይ ጊዜ ከአገር ወጥቶ እንዲማር የተደረገ ሁሉ ተምሮ መጣ እንጂ የቀረ የለም ማለት ይቻላል::በደርግ ጊዜ ወጣቱ ላይ ትንሽ አደጋ ደረሰ::በመሆኑም ለሽሽት ምክንያት ሆነ::ኢህአፓን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲፈጠሩ በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚሳቡት ወጣቶች ናቸውና በነበረው ሁኔታ ለሽሽት ምክንያት ሆኗል::እስካሁንም እሱ አይነት ፍርሃት ያለቀቀው አለ፡፡
በዚህ ምድር ላይ የምንፈጠረው አንዴ ነው::ሞትን ፈርተሸ አገር አትለቂም::በአገር መሞት ደግሞ ክብር ነው::ስለዚህ የሚደርሰው የፖለቲካ ተጽዕኖ ጊዜያዊ ነውና አገር ትበልጣለች ባይ ነኝ::ትልቁ ግን የትምህርት ስርዓቱ ነው የተበላሸው ባይ ነኝ፤ ቻይ እንድንሆን አላደረገንም:: ሕይወት የምትደበድብሽ በቦክስ ነው፤ ያንን ጡጫ እንዴት መከላከል እንዳለብን መማር አለብን::ያንን ግን አላስተማሩንም::ከዚህ ውጭ ኢትዮጵያውያን በማንነታችን የምናፍር አይደለንም፤ ምክንያቱም በማንም አገር ቅኝ አልተገዛንም::ከፖለቲካ ረብሻ ሌላ ያባረረን ድህነት ነውና ጠንክረን ልንሰራ ይገባል::ደግሞም በሰው አገር ኢትዮጵያውያን በዝተናልና በቃን::ፈተናን ለመጋፈጥ መዘጋጀት መልካም ነው::ድህነትን ለመዋጋት ብርቱዎች መሆን አለብን::በሰው አገር መኖር ምንም አይነት ነጻነት አይሰጥም::በአገራችን እርስ በእርስ ተረዳድተን ፈተናን መሻገር እንችላለን::በጎነት የሁላችንም ድርሻ ነው እንጂ የአንድ ሰው አይደለም::እኔም እያደረኩ ያለሁት ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ ብዬ ስለማምን ነው::ለዚህም ነው አንቺ በጎ አድርገሻል ስባል ሁሉም ሰው በጎ ነው የሚል መልስ የምስጠው::
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እየተሳተፉ ስለመሆንዎ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አማካይነት ሰምተናል ። የሰሩት በጎ ስራ ለሌላውም አርዓያ ይሆናሉና እስኪ ከአንደበትዎ እንስማው?
ዶክተር እመቤት፡- አሁንም ደግሜ የምነግርሽ ነገር ቢኖር በጎነት የዶክተር እመቤት ስራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሁሉ ስራ ነው::ኢትዮጵያዊነት የሚገለጸው በዚህ ነው::እኔ ሳድግ አዳሪ ቤት በመሆኑ አብሮ መኖርን ተምሬያለሁ::የእኔን ወላጆች ጨምሮ በሁሉም ወላጆች ዘንድ ደግነት ነበር::ስለዚህም ነው ጉዳዩ የእኔ ብቻ ሊሆን የማይችለው፡፡
ቀን በቀን በማያቸው ክስተቶች ውስጥ ልቤን የሚሰብሩ ነገሮች ያጋጥሙኛል::ከታካሚዎች ብጀምርልሽ እንደ ሀኪም መብት ስላለኝ ስለራሳቸው የምጠይቃቸው በጥልቀት ነው::በዚህ ውስጥ ግን ግላዊ የሆኑ ችግሮቻቸውን በድንገት እስማለሁ::ሰምቼም የሁሉም መፍትሔ መሆን ባለመቻሌ በጣም እጨነቃለሁ::ይህ አይነቱ ጉዳይ ግን የእኔ ባህሪ ብቻ ነው ማለት አልችልም፤ ምክንያቱም ብዙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ያለ ነው::
ለምሳሌ እኔ በምሰራበት የጥርስ ሕክምና የጽዳት ሰራተኛ የሆኑት ሁሉ ጤና መኮንን፣ ነርስ ብሎም ሐኪም ሆነዋል:: እንዳጋጣሚ ሆኖ አንዳቸውም ጥለውኝ አልሄዱም፤ ነገር ግን ወደየትኛም ቦታ ቢሄዱም ቅር አልሰኝም፤ ምክንያቱም እዛም ሄደው የሚያገለግሉት ኢትዮጵያውያኑን ነው።
በሌላ በኩል ወጣቶችን በብዙ መልኩ ማገዝ ያስደስተኛል:: በተወሰነ መልኩም ለመርዳት እሞክራለሁ:: ብቻዬን ሆኜ የኢትዮጵያ ወጣት ወደአንድ ቦታ ማድረስ ባልችልም ተደራሽ መሆን ለሚችለው የበኩሌን እሞክራለሁ::እሱ ግን የሚያስደንቅ አይደለም::እንደ እኔ ከሆነ እያንዳንዱ ባለሀብት አንድ ለትውልድ የሚጠቅም ማስታወሻ እየተወ ማለፍ አለበት የሚል እምነት አለኝ::በሌላ በኩል ከመንግስት ጎን በመሆን አገለግላለሁ:: በተለይ በክፍለከተማዬ የሚጠበቅብኝን ሁሉ በማድረግ እየተንቀሳቀስኩ ነው :: ልደታ ወደሚባለው አካባቢ ለወጣቶች ሜዳ እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነዎትና እስኪ ስለእሱ እናንሳ? ምክር ቤት ገብቼ አሳካዋለሁ ብለው ያሰቡትንስ እያሳኩ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር እመቤት፡- በምክር ቤቱ የማሕበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ነኝ::በመሆኑም ማህበራዊ የሆኑ ጉዳዮች በሙሉ ይመለከቱኛል::በዚህ ውስጥ ደግሞ መልካምነትን እንዳስተምርበት እድል ይሰጠኛል::የቋሚ ኮሚቴ ኃላፊዋ ወይዘሮ ዘይነብ ሽኩር በጣም ጠንካራ በመሆናቸው ለሰው ያልተገለጹ ብዙ ነገሮችን እየሰራን ነው፡፡
ሕልሜ ነው ብዬ አስብ የነበረው የዓባይ ግድብ ነው::ይህ ደግሞ ያለምንም ጥርጥር ወደስኬት ማማ የመጣ ጉዳይ ሆኗል::በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቅድመ ንግግሬ የነበረው ሌላው ቢቀር እስኪ ዓባይን እንይ የሚል ነበር::ሌላው ደግሞ እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ጠቀሜታቸው ለህዝብ በመሆናቸው እሱም ላይ እየታየ ያለው ስኬት አስገራሚ ነው::ሕዝቡም ለምርጫ እድል የሰጠን እነዚህን ፕሮጀክቶች እንዲሁም የተማሪዎች የምገባ መርሃግብር ላይ ተደግፈን ባደረግነው ንግግር እንጂ እነሱን መርሃግብሮች ወይም ፕሮጀክቶች እኛ ተመራጮች ሰርተናቸው አይደለም::ምክንያቱም በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ፍቀዱልንና እነዚህንም ፕሮጀክቶች እናስቀጥል ብለን ነው ለህዝቡ ስንናገር የነበረው::
አዲስ ዘመን፡- እንደምክር ቤት ተመራጭነትዎ ወጣቱን ምን መምከር ይሻሉ?
ዶክተር እመቤት፡– ከአንድ መንግስት ቢሮክራሲ መጥፋት አለበት ብዬ አምናለሁ::መማር እየፈለገ ያልተማረ እንዲሁም ተምሮም የተቀመጠ ወጣት አለ::ይህን ጉዳይ ለማስተካከል በመጀመሪያ ከወጣቱ ዘንድ ተነሳሽነቱ መምጣት አለበት::ስራ ሳይንቅ እየሰራ መማር ይችላል::በእርግጥ ደግሞ ወጣቱ አሁን የሚታየው ጭላንጭል የሆነ ነገር አለና ተስፋ የሚቆርጥ አይመስለኝም:: ሌላው ደግሞ የዓባይ ግድብም ሊነጋ ነው፤ ደርሼላችኋለሁ እያለን ነው::ይህን የሚለው ለትውልዱ ነው::ከዚህ ፕሮጀክት ሌሎች ፕሮጀክቶችን መስራት እንማራለንና ለወጣቱ ብዙ ተስፋ አለ::
አገራችን ያልተነካች እንደመሆኗ ብዙ ማዕድናትን የያዘች ናት፤ ይልቁኑ ለዚህ ጉዳይ በዘርፉ ብቁ ለመሆን በትምህርት ዝግጁ ልንሆን ይገባል::እኛ በቅኝ ስላልተገዛን ብዙ ነገራችን ያልተነካካ ነው::ስለዚህም ወጣቱ በዛ ለመሳተፍ ተስፋ በማድረግ አይኑን መክፈት መቻል አለበት::ያሉንን ማዕድናት በአግባቡ መጠቀም እንድንችል በዘርፉ ኮሌጅ መከፈትና መጠናከር አለበት::መማር ያለበት ዶክተር፣ ኢንጂነር ብቻ መሆን የለበትም፤ የአገራችንንም ማዕድን ማውጣት የሚችል ኃይል እንዲኖረን በዘርፉ መማር መልካም ነው::ሁልጊዜ ፈረንጅ መለመን አይገባም::
በአጠቃላይ ትውልዱ አደራ የምለው ጉዳይ በቀጣናውም በአህጉሩም ደረጃ ምንም እንኳ ብዙ ተግዳሮት ቢኖርብንም የቀድሞ የበላይነታችን እናስጠብቅ::ይህ ደግሞ የሚጀምረው ወደእርሻው ፊታችንን በማዞርም ጭምር ነው፤ የተማረ አርሶ አደር መሆን ክብር ነው::የኑሮ ውድነትን ሰርተን ነው መቀየር የምንችለው እንጂ የፈረንጅ እጅ ጠብቀን አንዘልቀውም::ወጣቱ አንድ እንዲያውቀው የምፈልገው ነገር ቢኖር በሌላው ዓለም ላይ ያለው ወጣት ስምንት ሰዓት ብቻ ስለሰራ ሳይሆን ከ12 እስከ 16 ሰዓት በመስራት ነው ኑሮው የተሻሻለው፡፡
ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰራተኛ በጠቅላላ አንድ ስራን ብቻ ሰርቶ ኑሮን ለማሸነፍ መታገልን ማቆም አለበት:: ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት ዝግጁ መሆን አለበት:: በመንግስት ደግሞ ይህ ጉዳይ የተሳለጠ እንዲሆን ቢያንስ የሌሊት የትራንስፖርት አቅርቦትን ማመቻቸትና የሰላሙን ሁኔታ ማስጠበቅ ይኖርበታል::የጨለማውም ጊዜ አብቅቶ ሌሊቱ በብርሃን ሊተካ የግድ ይላል::ምናልባትም ከዚህ በኋላ መብራት በፈረቃ ወደሚለው ጉዳይ እንገባለን ብዬ አላስብም::ይህ ከሆነ ቀን በነርስነት ሙያ ስትሰራ የቆየች ልጅ ማታ ቢያንስ እስከ አራት ሰዓት ሱቅ መሸጥ ትችላለች::ቤታችን ውስጥ እስከ አራት ሰዓት ድረስ ወይ ቡና ስንጠጣ አሊያም በሆነ ባልሆነው ጉድ ጉድ ስንል እንቆያለን::ይህ ካልሆነ በማማረር ኑሯችንንም ሆነ አገራችንን ከፍ ማድረግ አንችልም::ሰው በስራ ሲወጠር አላስፈላጊ የሆኑ የማህበራዊ ትስስር ገጽን በማየት ለነቀፋ ወይም ለምሬት አይዳረግም እላለሁ::
አዲስ ዘመን፡- የሕይወት ተሞክሮዎንና አርዓያነትዎን ለአንባቢዎቻችን ስላጋሩን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር እመቤት፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014