ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተቋጩ ሃሳቦች፣ በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም አገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነስቷቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች አገር ናት።
አገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የቆየ ባህል ቢኖራትም እነዚህን ባህሎች በአግባቡ የመጠቀም ልምዱ ቀስ በቀስ እየጠፋ መጥቷል። ይህ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፣ ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትላንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ይሁንና ከህልውና ባሻገር ስለ መፅናትና መቀጠል እንዲሁም ስለሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ ለእነዚህ ልዩነቶችና አጀንዳዎች መፍትሄ መስጠት የግድ ይላል።
በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ከትናንት ሲንከባለሉ የመጡና በአገር ግንባታ ሂደቱ ላይ የራሳቸውን እክል የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በምክክርና ውይይት ለመፍታት ከፍ ያለ ሥራ ጀምራለች። አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሕግ በማቋቋምና ኮሚሽነሮችን በመሰየም ወደ ሥራ ተገብቷል። ዋናውን የምክክር ሂደት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትም በመከናወን ላይ ናቸው።
አካታች አገራዊ ምክክሩ በሁሉ ረገድ የሰመረ እንዲሆንም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሚናቸው ግዙፍ ነው። የመገናኛ ብዙሃንም ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ እና ሁነትን ከመዘገብ በዘለለ ለምክክሩ ስኬታማነት ከባድና ድርብ ኃላፊነት አለባቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራዊ ምክክር በማድረግ የተሳካላቸው አገራት እንዳሉ ሁሉ ምክክሩ ሳይሳካላቸው የቀሩ አሉ። ለዚህ ደግሞ ሚዲያው እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀስ ነው። ይህ ታሪክ እንዳይደገም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን በሌሎች አገራዊ ጉዳይ ላይ ያሳዩትን ወገንተኝነት በአገራዊ ምክክሩ ላይም መድገም በተለይም ለጉዳዩ ሰፊ ሽፋንና ከመስጠት ጀምሮ ተግባቦት ላይ ጠንካራ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
ከሁሉ በላይ ሙያዊ ነጻነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የአካታች አገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት፣ ታላቅነትና ክስተትነት አምነው በመቀበል ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። ምክክሩ አገራዊ እንደመሆኑ መጠን በተሻለና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ሂደቱን ከመዘገብ፣ መረጃ ከመስጠትና የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ መደላድል ከመፍጠር ጨምሮ የመሪነት ሚናን በመጫወት ይዘታቸውን አገራዊ ጥቅምና ሰላም ላይ ማድረግ የግድ ይላቸዋል።
በምክክር ሂደቱ ላይ የሚነሱ ሃሳቦችን ለማንቋሸሽና ለመግፋት ከሚደረጉ ጥረቶች፤ በጽንፈኝነት የሚወጡ ሃሳቦችን ሌሎች ላይ ከማራገፍ እንዲሁም የአንድን አካል ሃሳብ ባልተገባ መንገድ ከመጠቀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸውም። የራሳቸው አጀንዳ ከመስጠትና አላስፈላጊ ጥብቅና ከመቆም፣ ሃሳብ ከማጠርና አስተሳሰብን ከመገደብ መቆጠብ እንዲሁም ብዝሃነትን የሚቀበሉና ጽንፈኝነትን የማያራግቡ መሆንም አለባቸው።
በእርግጥ መገናኛ ብዙሃኑ የየራሳቸው አላማ፣ አሰራር አቋምና እይታ አላቸው። ይሁንና ደግሞ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ እንደ አገር ማሰብና መስራት የግድ ነው። ይሁንና አሁን ባለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን አደረጃጀትና አሰራር እንደ አንድ ማሰብ አስቸጋሪ የሚሆንበት አግባብ አለ።
በአገራዊ ውይይቱ ላይ መገናኛ ብዙሃኑ በባለቤትነት እንደያዛቸው አካልና ሌላም ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ዘርን፣ አካባቢን፣ ሃይማኖትን ወይም ሌላ ቡድናዊ እሳቤን ተከትሎ የመንጎድ አዝማሚያዎች ሊያስመለክቱ ይችላሉ። ለአብነትም፣ የክልል መገናኛ ብዙሃንን የምክክር አጀንዳዎችን ከሚገኙበት ክልል እሳቤ ጋር ብቻ ማቆራኘት ሊታይባቸው ይችላል።
ይህን ለዚህ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ታዲያ አገራዊ ምክክር በምን አይነት የሚዲያ ሞዴል ሊተገበር ይገባል የሚለው ከወዲሁ ሊጤን ይገባል። መገናኛ ብዙሃኑ የሚመሩበት ዝርዝር መመሪያ ሰነድ መዘጋጀትም ይስፈልጋል። ይህ ሲባል ግን የሚዲያ ነፃነት መጋፋት ማለት አይደለም። ይልቁንም አገራዊ ጥቅሞችን ከግምት ውስጥ ከማስገባት የመነጨ መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም።
በብሔራዊም ሆነ በክልል ደረጃ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ሁነቱን በመዘገብ ሂደት የሙያውን መርህ እና ስነምግባርን ባከበረ መልኩ መስራትና ከተለያየ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትም ሆነ የብሔር ተጽእኖ ራሳቸውን ነፃ ማድረግ አለባቸው።
ከቡድንና አካባቢያዊ ልሳንነት ይልቅ የሁሉም ድምጽ ሆነው፤ የጎጥ ጥቅምን ለማስጠበቅ መሣሪያ ከመሆን መቆጠብ እና አገርን አስቀድመው ስለ አገር ክብርና ከፍታ እያሰቡ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። መገናኛ ብዙሃኑ በነጻነት መስራት የሚችሉበትን አግባብ ለመፍጠርም አዋጆች፣ ህጎችና አደረጃጀታቸው መፈተሽ በተለይም ከፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ተፅእኖ ነጻ የሆነ አደረጃጀት እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከመደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ፈተና ባሻገር የዲጂታል ሚዲያው ለአገራዊ ውይይቱ ከባድ ራስ ምታት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። ምክንያቱ ደግሞ በመደበኛው መገናኛ ብዙሃን መፈፀም የማይቻሉ ተግባራት ለአብነት ሀሰተኛ እንዲሁም ፀብ ቀስቃሽ የሆኑና በጥላቻ የተሞሉ መረጃዎችን በዲጂታል ሚዲያ ሊፈፀሙ ይችላሉና ነው።
በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት የተቀመሩ የፖለቲካ ትርክቶችና የተረጩ መርዞች በአሁን ወቅት ለማኅበራዊ ትሥሥር ገፆች ትልቅ ግብዓት ወደ መሆን አዝማሚያ ሄደዋል። ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ የኢትዮጵያን መልካም የማይፈልጉ አካላት በዲጂታል መንገድም ሆነ በአካላዊ ጦርነት ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
አብነትም ኦሮሞ ሳይሆኑ የኦሮሞ ሥም ገፆችን በመክፈት፤ አማራ ሳይሆኑ የአማራ ሥም የያዘ ገፅ በመክፈት የብሔር ጉዳዮችን አንስቶ በመሳደብና ተቆርቋሪ በመምሰል በሐሰተኛ ገፅ ተጠቅመው ህዝብን ከህዘብ የሚያቃቅሩ አስተውለናል።
በአርቲስቶች፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና በሌሎች ታዋቂ ሰዎች ስም በርካታ ሐሰተኛ የትሥሥር ገፆች ተከፍተው ሲሠሩ ታይቷል። ሐሰተኛ የትሥሥር ገፆች ብቻ ሳይሆኑ ትክክለኛ አካውንቶች ሆነው ጭምር ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን የሚያሰራጩ እንዳሉ እሙን ነው። እንደ መደበኛ በቀላሉ መቆጣጠር የሚቻል አለመሆኑ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያውን ስጋትነት ይበልጥ ያገዝፈዋል።
ይሁንና መደበኛው መገናኛ ብዙሃን ጠንካራ ሆነው መውጣትና እውነተኛ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ አቅምን መፍጠር ከቻሉ በዲጂታል ሚዲያው የሚሠራጨው ሃሰተኛ መረጃ ማዳከም ቀላል ይሆናል። መረጃ የማግኘት መብትን በእጅጉ ቀላልና ቀልጣፍ ማድረግ በተለይም የህዝብን የመገናኛ ብዙሃን መሰረታዊ እውቀት ወይንም ሚዲያ “ሊትሬሲ” ማጎልበት፣ መረጃ በሚመለከት አስተዋይ፣ ጠንቃቃና ፈታሽ እንዲሆኑና በተሳሳተ አረዳድ፤ ያልተፈለገ ተግባር እንዳይፈፅሙ ማንቃት የግድ ይላል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም በአገራዊ ምክክሩ ላይ የሚተላለፉ ዘገባዎችን መሰረት በማድረግ በመገናኛ ብዙሃኑ አሰራር ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል። እንደ ተቋም የመገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ሚዲያዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ፈጥኖ ማዘጋጀትም መተግበር ይጠበቅበታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 /2014