የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) መሰብሰቢያ አዳራሽ ሊካሄድ በታቀደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ስፖርቱን ለቀጣይ አራት አመታት የሚመሩ ግለሰቦች ለፕሬዚዳንትነትና ለስራ አስፈጻሚነት የሚያደርጉት የምርጫ ፉክክር በጉጉት ይጠበቃል። የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ባለፈው ሳምንት ለፕሬዚዳንትነት የሚፎካከሩ ሶስት የመጨረሻ እጩዎችንና ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የሚወዳደሩ ሃያ ስድስት እጩዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ባለፉት አራት አመታት ፌዴሬሽኑን ሲመሩ የቆዩት አቶ ኢሳያስ ጂራ ከኦሮሚያ ክልል ተወክለው ለፕሬዚዳንትነት የሚፎካከሩ ሲሆን፣ አቶ መላኩ ፈንታ ከአማራ ክልል እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አቶ ቶኩቻ አለማየሁ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እጩ ሆነው መቅረባቸው ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ለፕሬዚዳንትነት የሚፎካከሩ እጩዎች ምርጫውን ቢያሸንፉ የሚሰሯቸውን ስራዎችና እቅዶቻቸውን ከወዲሁ ማስተዋወቅ ጀምረዋል። በምርጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የአማራ ክልል ተወካዩ አቶ መላኩ ፈንታ ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ ምርጫውን ካሸነፉ ለማከናወን ያቀዱትን እቅዶች ማቅረባቸው ይታወሳል። በትናንትናው እለት ደግሞ ሌላኛው ጠንካራ ተፎካካሪ አቶ ኢሳያስ ጅራ በስካይ ላይት ሆቴል ተመሳሳይ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአገልግሎት ዘመናቸውን አጠናቀው ዳግም ለመመረጥ እየተፎካከሩ የሚገኙት አቶ ኢሳያስ፣ ባለፈው የስራ ዘመናቸው ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ያከናወኗቸውን አበይት ተግባራት፣ የስራ ስኬቶች እና ስለነበራቸው የአመራርነት ቆይታ እንዲሁም በቀጣይ አራት ዓመት ቢመረጡ ዋነኛ የስራ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ በመግለጫቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኦሮሚያ ክልልን በመወከል የሚወዳደሩት አቶ ኢሳያስ፣ የፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒው ምስረታ በእሳቸው የአመራርነት ዘመን እውን መሆኑን በማስታወስ፤ ፌዴሬሽኑም የራሱ ህንፃ እንዲኖረው ማስቻላቸውን አስረድተዋል። የኢት ዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሳቸውም በአስተዳደር ዘመናቸው ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል እንደሚጠቀስ አስረድተዋል። አቶ ኢሳያስ አክለውም፤ የተለያዩ የእግር ኳስ ፓይለት ፕሮጀክቶች ጅማሮ፤ የፌዴሬሽኑ ተቀማጭ የባንክ ሂሳብ ማደጉ በስራ ዘመናቸው ካስመዘገቧቸው ስኬቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ አቶ ኢሳያስ ባለፉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሶስት የአመራርነት ዘመናት በጣም የተሻሉ ስራዎች በእሳቸው የአመራርነት ዘመን መከናወናቸውን በመግለጫቸው አብራርተዋል። እንደ አቶ ኢሳያስ ማብራሪያ የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስራ ዘመናቸው ከገጠሟቸው አስቸጋሪ ፈተናዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
አቶ ኢሳያስ በቀጣይም በድጋሚ ከተመረጡ የአሰልጣኞች ስልጠናና የአሰለጣጠን ስርዓቱን ማዘመን ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩበት ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል። የብሄራዊ ቡድን ግንባታም በተመሳሳይ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ እንደሚሆን የጠቆሙ ሲሆን፤ የስፖንሰሮችን አቅም ማሳደግ የፌዴሬሽኑን አቅም መገንባት፤ ፌዴሬሽኑ ከስፖርት መሃበራት ጋር ያለውን ግንኙነት በተሻለ መልኩ በማጠናከር የሴቶች እና የታዳጊዎች እንዲሁም የከፍተኛ ሊግ ውድድሮች የብሮድካስት የስርጭት ሽፋን እንደሚያገኙ ለማድረግ ማቀዳቸውን አብራርተዋል። በዚህም የተሻለ የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።
በተጨማሪነት አቶ ኢሳያስ ምርጫውን በተመለከተ “ግልፀኝነት እና ታማኝነት ይጎለዋል” በሚል ቀድሞ የሚነዛው አሉባልታ መስተካከል እንደሚኖርበት መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል። “በቀጣይ የአራት ዓመት ጉዟችንን ገምግመን ተቋማዊ ለውጥ ላይ እንሰራለን። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ከስፖርቱ ባለፈ ለአገራዊ ምርጫ ምሳሌ እንዲሆን እንፈልጋለን” ያሉት አቶ ኢሳያስ ስለሁለቱ ተፎካካሪያቸውም አስተያየት ሰጥተዋል። “ሁለቱ ተወዳዳሪዎቼ መልካም ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ ይሰሩበት በነበሩበት ኢንደስትሪ ስኬታማ ናቸው። ወደዚህ ስራ መጥተው ውጤት ያመጣሉ ካላችሁኝ ግን ጉባኤተኛው ምላሽ ይስጥበት” ሲሉ ተናግረዋል።
ምርጫውን የሚያስተናግደው ጠቅላላ ጉባኤ ቀደም ሲል ሊካሄድ የታቀደው በጎንደር ከተማ ቢሆንም ከሳምንት በፊት የቦታ ለውጥ ተደርጎበት አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ መወሰኑን ፌዴሬሽኑ ማሳወቁ ይታወሳል። ይህንን በተመለከተ አቶ ኢሳያስ ማብራሪያ ሲሰጡም “ምርጫውን የማስተዳደር ስልጣን ያለው ፌዴሬሽኑ ነው፣ ከጎንደር ወደዚህ ምርጫው ሲመጣ ምክንያት አለው፣ የጉባኤውን ደህንንት መጠበቅ አለብን” ብለዋል።
በመጨረሻም አቶ ኢሳያስ “በምርጫው ከተሸነፍኩ ወደ እግር ኳስ እንደምመለስ እና እንደማልመለስ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው” በማለት ተናግረዋል።
አቶ ኢሳያስ ጅራ በድጋሚ ከተመረጡ የአሰልጣኞች ስልጠናና የአሰለጣጠን ስርዓቱን ለማዘመን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፣